ዶክተር ኢንጂነር አብርሃም
– የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ስራ አስፈፃሚ
ዶክተር ኢንጂነር አብርሃም በላይ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በመከላከያ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ሶስተኛ ዲግሪያቸውን በቡላካ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ፊሊፒንስ በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ሰርተዋል። በተጨማሪም በቻይና የፔኪንግ ዩኒቨርሲቲ በሪሞት ሴንሲንግና ካርቶግራፊ የሙያ መስክ እንዲሁም በጂ.አይ. ኤስ አገራዊ ጋቨርናንስና አርክቴክቸር የምርምር ዘርፍ ትምህርታቸውን በማጠናቀቅ ላይ ናቸው።
ከ1991 ዓ.ም ጀምሮ የኢፌዴሪ የመከላከያ ሰራዊት አባል በመሆን እስከ ሌተናል ኮሎኔል ማዕረግ ደርሰዋል። በመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮሌጅም ሲያስተምሩ የነበረ ሲሆን፣ በተለያዩ ቦታዎች ደግሞ በኃላፊነት አገልግለዋል። በአሁኑ ሰዓት ደግሞ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ስራ አስፈፃሚ በመሆን እያገለገሉ ሲሆን ከተቋሙ ጋር በተያያዘ ከአዲስ ዘመን ጋር ቆይታ አድርገዋል። መልካም ንባብ ይሁንልዎ።
አዲስ ዘመን፡- ተቋሙ በአሁኑ ወቅት በዋናነት ምን ምን ስራዎች ላይ ነው አተኩሮ እየሰራ ያለው?
ዶክተር ኢንጂነር አብረሃም፡- የኤሌክትሪክ ኃይል መሰረተ ልማት ስንል ከማመንጫ ይጀምራል። ከማመንጫ ተነስቶ ከፍተኛ የኃይል ተሸካሚ መስመር አድርጎ ወደ ሰብስቴሽን ይደርሳል።ከሳብስቴሽን በኋላ ደግሞ የስርጭት ስራ ይሰራል።ይህም ማለት ወደየተጠቃሚው የሚደርስበት ስርዓት ማለት ነው።ስለዚህ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በዋናነት የማመንጫውና ከፍተኛ የኃይል መሰረተ ልማቱ እስከ ሳብስቴሽን ያለውን የግንባታ ሂደቱን ስራ ኃላፊነት ወስዶ ነው እየሰራ ያለው።
የማመንጫ ጣቢያዎቻችን በዚህ ጊዜ አብዛኛውን የውሃ ኃይልን መሰረት አድርገው የሚያመነጩ ሃይድሮ የምንላቸው ናቸው። ውስን የንፋስ ኃይል ደግሞ አሉ።እነዚህም አዳማ አንድና ሁለት እንዲሁም አሸጎዳ ሲሆኑ፣ድሮ የተጀመረው አሉቶ ላንጋኖ ደግሞ በእንፋሎት ኃይል የሚሰራ ማመንጫ ነው።ከእነዚህ በተጨማሪ ደግሞ የዲዝል ሃይል ማመንጫዎችም አሉ። እነዚህም በድሬዳዋ፣ በአዋሽ እንዲሁም በቃሊቲ የሚገኙ የዲዝል ማመንጫ ጣቢያዎች ናቸው።በሌላ በኩል ደግሞ ዘንድሮ ወደ ስራ የገባው ቆሼ የኃይል ማመንጫ አለ።በጥቅሉ አሁን ላይ በመስራት ያሉት የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች የምንላቸው እነዚህ ናቸው።
በሂደት ደግሞ እየገነባናቸው ያሉ አብዛኛዎች የኃይድሮ ሲሆኑ፣ እነዚህም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ የኮይሻ፣ የገናሌ ዳዋ ተጠቃሾች ናቸው፤ በንፋስ ኃይሉ በኩል ደግሞ አይሻ የተባለው የንፋስ ኃይል ማመንጫ የፕሮጀክት ስራዎቻችን ናቸው።
በቀጣይ ግን በግል የኃይል ማመንጫ ልማት ስራው የሚሰራው በባለሀብቶች ነው። የግል አልሚዎች በአብዛኛው ወደጨረታ እየገቡ ስላሉ አብዛኛው የሶላር፣ የንፋስ እንዲሁም የውሃ በተጨማሪም የጂኦተርማል ስራዎች በግል ኢንቨስተሮች ይሰራሉ ብለን ነው የምንጠብቀው።
አዲስ ዘመን፡- በግል አልሚዎች በኩል ምን ያህል እንቅስቃሴ ተጀምሯል ማለት ይቻላል?
ዶክተር ኢንጂነር አብረሃም፡- እስካሁን አምስት የውሃ፣መተሃራን ጨምሮ ዘጠኝ የፀሐይ ኃይል ማመንጫዎች በግል አልሚዎች ለማልማት በጨረታ ሒደት ላይ ያሉና ወደጨረታም ሊገቡ የተዘጋጁ ፕሮጀክቶች አሉ። በዋናነት የጨረታው ሂደት የሚከናወነው በገንዘብ ሚኒስቴር ነው።እኛ የምናቀርበው የፕሮጀክት ፍላጎታችንንና ዝርዝሮችን ነው። አሁን ደግሞ በቅርቡ የንፋስንም እንጨምራለን። እነዚህ ሁሉ የማመንጫ ጣቢያዎች በግል ባለሀብቶች የሚለሙ ነው የሚሆኑት።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ታመነጫለች ተብሎ የሚታሰበው የኃይል መጠን ምን ያህል ነው?
ዶክተር ኢንጂነር አብረሃም፡- አሁኑ ያሉት ጣቢያዎች በሙሉ አቅማቸው ቢሰሩ ሊያመነጩ የሚችሉት የኃይል መጠን ወደ አራት ሺ 251 ሜጋ ዋት ነው። ይህን ስል የዲዝሎችን ሳላካትት ነው። በዋናነት የሃይድሮ፣ የጂኦተርማል፣ ከቆሻሻ የሚያመነጨው የቆሼ እና አንደኛ የድሬዳዋ ዲዝል ቢጨመር ከላይ የጠቀስኩትን ቁጥር ነው የሚሰጠን። ይህን ስልሽ ያለን የኃይል ማመንጨት አቅማችንን ለማሳየት ነው።
በመገንባት ላይ ያሉና በቀጣዩ 2012 ዓ.ም ይጠናቀቃሉ ብለን የያዝናቸው ገናሌ ዳዋና የአይሻ ንፋስ ኃይል ማመንጫ ወደስራ ሲገቡ ወደ አራት ሺ 625 ሜጋ ዋት ይደርሳል ተብሎ ይታሰባል።
የግል አልሚዎች ይሰሯቸዋል ብለን ያሰብናቸው ስራዎች በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ይጠናቀቃሉ የሚል ሐሳብ አለንና (ይህን ስል የግል ባለሀብቶቹ በፀሐይም በሃይድሮም ለማመንጨት ወደስራ እየገቡ ያሉትን የሃይድሮው ቢዘገይ በፀሐይ የሚመነጩት ግን ቶሎ ወደሰራ ይገባሉ በሚል ታሳቢ ነው) በፀሐይ የሚመነጩት ወደ አንድ ሺ አንድ መቶ ሜጋ ዋት ነውና በዚህም ተጨማሪ የኃይል ምንጭ ያመነጩልናል ብለን እናስባለን። የውሃው ደግሞ ወደ ሁለት ሺ 71 ሜጋ ዋት ተጨማሪ ኃይል ይኖረናል ብለን ነው የምናስበው።
በመሰራት ላይ ያሉ እንደእነታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና ኮይሻ ሲጨመሩ ወደ ሰባት ሺ 200 ሜጋ ዋት ተጨማሪ የማመንጨት አቅም ይኖራቸዋል። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት በሂደት ላይ ያሉት እነዚህ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- እንደሚታወቀው ትልቁን ኃይል ያመነጫል የሚባለው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ነው፤የዚህ ግድብ መጠናቀቅ ለኢትዮጵያውያኑ ከኃይልም ማመንጨት በላይ ነው፤ ቀደም ሲል ከሜቴክ ጋር በተፈጠረው ችግር ግድቡ ወደኋላ የተጓተተ መስሎም ነበር።አሁን ላይ ሂደቱ ምን ይመስላል?
ዶክተር ኢንጂነር አብረሃም፡- በአሁኑ ሰዓት ሁሉም ኩባንያዎች ወደስራ ገብተዋል።ከሜቴክ ጋር ተያይዘው የነበሩ ስራዎች በሙሉ ወደኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ተዘዋውረው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ደግሞ ለሰብ ኮንትራክተሮች ሰጥቷል።ከመስጠትም በተጨማሪ በህዳሴ ግድቡ ላይ በተግባር ስራ ላይ ነው የሚገኙት።ቀደም ሲልም እንደገለፅነው በመጀመሪያ ኃይል ያመነጫሉ የምንላቸው የዩኒት ዘጠኝና አስር ስራዎች በአሁኑ ሰዓት በፍጥነት እየሄዱና እየተሰሩ ነው። በ2013 መጨረሻ የመጀመሪያው ኃይል ይመነጫል ተብሎም ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን፡- ምን ያህል ሜጋ ዋት፣ መቼ ያመነጫል?
ዶክተር ኢንጂነር አብረሃም፡- ዩኒቶቹ እያንዳንዳቸው 375 ሜጋ ዋት ኃይል ነው የሚያመነጩት። ይሁንና የሚያመነጩት ኃይል ያን ያህል አይሆንም። አንድ የማመንጫ አቅም የሚወሰነው በሚይዘው ውሃና በሚኖረው ከፍታ(ሄድ) ነው እንጂ በሜጋ ዋት ስለጠራነው አይደለም። ዞሮ ዞሮ ሁለቱ ዩኒቶች ኃይል ወደማመንጨቱ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።ይህም ማለት ወደ 2013 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ ማመንጨት ይጀምራሉ።ይህን ለማሳካት የሚያስችሉ ስራዎች ከሰብ ኮንትራክተሮች ጋር እየተሰሩ ይገኛሉ። ኩባንያዎች በስራ ላይ ናቸው።
ዩኒት ዘጠኝና አስር እንዲሁም የቦተም አውትሌት ደግሞ ሙሉ በሙሉ ተነስቶ በአዲስ መልክ ስለሚሰራ የፋብርኬሽን ስራዎች ተጀምረዋል። እነዚህን በማጠናቀቅና የሁለቱን ዩኒቶች ደግሞ የጄኔሬተር ተርባይንና ተተያያዥ ስራውም በመሰራት ላይ ይገኛሉ።ዋና የሚባሉ ዩኒቶች ደግሞ የሚተከሉ ይሆናል። እነዚህ ስራዎች በ2013 ዓ.ም ይጠናቀቃሉ ተብሎ ይታሰባል።
አዲስ ዘመን፡- ግድቡ ሙሉ በሙሉ የሚጠናቀቀው መቼ ነው?
ዶክተር ኢንጂነር አብረሃም፡- በ2015 ዓ.ም የኮንስትራክሽን ስራዎች ሙሉ ለሙሉ ይጠናቀቃሉ።የመጀመሪያው ኃይል ከመነጨ በኋላ ሁለት ዓመት ተጨማሪ የኮንስትራክሽን ስራዎች ይኖራሉ የሚል እቅድ ይዘን ነው እየሰራን ያለነው።
አዲስ ዘመን፡- በግድቡ ላይ የነበረውን የስራ ድርሻ ሜቴክ ትቶ ከወጣ እና ሌሎቹ ኩባንያዎች ከገቡ በኋላ በስራው ሂደት ላይ በግልፅ የታየ ልዩነት ይኖር ይሆን?
ዶክተር ኢንጂነር አብረሃም፡- አዎ! ዋናው ነገር ደግሞ ጤንነቱ የተጠበቀ የግንባታ ስራ መስራቱ ላይ ነው። በአሁኑ ሰዓት የሚያሰጋ ምንም ነገር የለም።ምክንያቱም በዋናነት እየሰሩ ያሉ ኩባንያዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ልምድ ያላቸውና በተግባርም ውጤት ያስገኙ በተጨማም በአገራችን ውስጥም ሌሎችን የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን የገነቡ ኩባያዎች ናቸውና የጥራት ችግሮች ይቀረፋሉ።
ከዚህም በተጨማሪ በአማካሪውም ሆነ በባለቤቱ በኩል ያለው ቁጥጥሩና ክትትሉም ቢሆን በየጊዜው የሚደረግ በመሆኑ በጥንካሬ የሚታይ ነው። ስለዚህም እያንዳንዱ የግድቡ ስራ በጥራት እየተካሄደ ነው። የጥራት ችግር ያለመኖሩን ያህልም የፋይናስ እጥረትም የለብንም። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ ስለሆነ ነው። የፕሮጀክት ማናጅመንት ስርዓቱ ከተስተካከለ ፕሮጀክቱን የሚሰሩ አካላትም በትክክለኛው መንገድ እስከሰሩ ድረስ እንዲሁም የአቅርቦት ችግርም እስካልተፈጠረ ድረስ ፕሮጀክቱ ባቀድነው መንገድ የሚሄድ ነው የሚሆነው።
አዲስ ዘመን፡- ከህዳሴ ግድቡ ጋር ተያይዞ የሶስትዮሹ ግንኙነት ምን ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው?
ዶክተር ኢንጂነር አብረሃም፡- ከሶስትዮሹ ግንኙነት ጋር ተያይዞ ያለውን ጥያቄ መመለስ የሚገባው የውሃ፣ መስኖና ኢንርጂ ሚኒስቴር ነው።
አዲስ ዘመን፡- እንደሚታወቀው በአሁኑ ወቅት የኃይል ፍላጎቱ እየጨመረ የመጣበት ሁኔታ አለና ይህን የኃይል ፍላጎት ለማርካት አማራጭ የኃይል ምንጮችን በተመለከተ ምን ያህል እየተሰራ ነው?
ዶክተር ኢንጂነር አብረሃም፡- በአገሪቱ ያለው የኃይል ፍላጎቱ በስፋት እየጨመረ ነው። እንዲያውም በሚቀጥሉት ዓመታት ደግሞ የኢንዱስትሪው ፍጥነት እያደገ ይሄዳልና የኃይል ፍላጎቱ በጣም በከፍተኛ ሁኔታ እየሰፋ እንደሚሄድ ነው ልምዱ የሚያሳየው። ስለዚህም ይህንን መወጣት የሚቻለው እንዴት ነው ሲባል መንግስት ያስቀመጠው ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት መንግስት ብቻ ኃይል በማመንጨት ፍላጎትን ማርካት ስለማይችል የግል ባለሀብቱም ማልማት ይጠበቅበታል።
የግል ባለሀብቱን ማስገባት የሚያስችሉ ህጋዊ ስርዓቶች፣ ፖሊሲዎች እንዲሁም የአሰራር ስርዓቶች ወጥተዋል። ስለዚህም በእነዚህ የአሰራር ስርዓት መሰረት የግል አልሚዎችን ወደኃይል ዘርፉ ለማስገባት የሚያስችሉ ስራዎች በስፋት እየተሰሩ ነው።
ቀደም ሲል የጠቀስኳቸው በመንግስትና በግል አጋርነት (መግአ)በፀሐይ ብቻ ይሰራሉ ተብለው የሚጠበቁ ፕሮጀክቶች ስምንቱ በጨረታ ላይ ያሉ ሲሆኑ፣አምስት ደግሞ ወደጨረታ በቅርቡ ይገባሉ ተብለው የሚጠበቁ የሃይድሮ አሉ። በቀጣይ ደግሞ በጥናት ላይ ያሉ የንፋስም አሉ።በሂደት ላይ ያለ የመተሃራ የፀሐይ ኃይልም አለ።እነዚህ በግል አልሚዎች ተጠናቀው ወደስራ ከገቡ የኃይል ልማቱ ከመንግስት ጎን ለጎን የሚሰሩ ስራዎች ስለሚታከሉበት ፍላጎቱን ማሟላት ይቻላል። አገሪቱ በውሃም፣በፀሐይም ሆነ በንፋስ እንዲሁም በጂኦተርማል ያላት እምቅ የኃይል ሀብት ከፍተኛ ነው።
ይህ የኃይል አቅም ለአገሪቱ ፍጆታ ብቻ ሳይሆን ለምስራቅ አፍሪካም ሆነ ለቀጣናው አገራት የሚተርፍ ነው። ይህንን ተግባራዊ የምናደርገው የግል ባለሀብቱ ወደስራው ሲገባ ነው።ምክንያቱም መንግስት ሁሌ ብቻውን አልምቶ አይችልምና ነው።በመሆኑም በአሁኑ ሰዓት ይህንን አቅጣጫ ነው በመከተል ላይ የምንገኘው።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይልን ወደ ውጭ አገር በመላክ ላይ ናት? የምትልክ ከሆነ ደግሞ የት የት አገር ነው?
ዶክተር ኢንጂነር አብረሃም፡- የምንልከው የተረፈንን ነው። ምክንያቱም የራስን አሳጥቶ ለሌላው ማድረግ አይቻልምና። ኃይል ማመንጨት እስከቻልን ድረስ የምናመነጨው ኃይል ለአገሪቱ ይውላል፤ትርፍ ሲገኝ ደግሞ ለጂቡቲና ሱዳን ለሽያጭ ይውላል።ጉድለት ካለ ግን ሽያጭ አይኖርም።ባለፈው ዓመት የነበረ አይነት የኃይል እጥረት ሲያጋጥም ለአገሪቱ ፍጆታ ብቻ ነው የሚውለው፤ትርፍ ሲገኝ ግን ለጠቀስኳቸው አገራት እንሸጣለን። የምንሸጠውም ያገኘነውን ያክል ሲሆን፣ይህም እስከ መቶ ሜጋ ዋትና ከዛ በላይም ሊሆን ይችላል። እንደሁኔታው እጥረት ካጋጠመን አገራቱ ሃያ ሜጋ ዋት ብቻ የሚያገኙበት አጋጣሚ አለ። አንዳንዴ ደግሞ 80 አሊያም መቶና ከዛ በላይም ሊሆን ይችላል።
ይህን የምናደርገው የኤሌክትሪክ ኃይሉን አገራችን በጣም የምትፈልገበትና የምትጠቀምበት ዋና ሰዓት የሚባልበትን ጊዜ ሳንነካ ለአገር ውስጥ ፍጆታ ብቻ እንዲውል ነው የምናደርገው። ከዛ ውጭ ባለው ሰዓት ግን የሚመረተው ትርፍ ስለሚሆን ቢሸጥ አገራችን የምትጠቀምበት ይሆናል።
እንደሚታወቀው ዋናው አቅማችን ያለው ከውሃ በምናመነጨው ኃይል ነው።ሌሎቹ እንደ ነፋስና መሰሎች ሲኖሩን ውሃውን መቆጠብ የምንችልበት እድል ይፈጠራልና እየቀላቀልን መስራት ስለሚያስችለን ለመሸጥ ብዙ አማራጭ ይኖረናል።በአሁኑ ሰዓት ግን ውሃ ብቻ በመሆኑ እየተቸገርን ነው።ምክንያቱም ውሃው ከዝናብ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ነው። ሌሎች አማራጮች ሲገኙ ግን ውሃው ዝቅ ባለ ጊዜና ዝቅም እንዳይልም ለመጠቀም የሚያስችሉ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- በአገር ውስጥም እጥረት እንዳለ እየተነገረ ነውና ሽያጩ በአሁኑ ሰዓት አልተቋረጠም?
ዶክተር ኢንጂነር አብረሃም፡- አልተቋረጠም፤ነገር ግን የሱዳንን በተወሰነ መልኩ ቀንሰን ነበር እንጂ ጂቡቲ የተገኘውን ያህል እያገኘች ነበር። በሱዳን በኩል 24 ሰዓት የማግኘት ፍላጎት ስላለ ሰዓቱን ተመሳሳይ እንድናደርግላት ነው የምትፈልገው። እንዲያም ሆኖ በመወያየት እያስተካከልንላት በመሸጥ ላይ እንገኛለን።
አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ በአገሪቱ ባጋጠመው የኃይል እጥረት የተነሳ ተገልጋዩ በተራ እንዲጠቀም ተራ መውጣቱ ይታወቃል፤ለዚህም ምክንያቱ የግቤ ሶስት ግድብ ውሃ ስላጠረው እንደሆነ ነው የተነገረው፤ ይሁንና አንዳንድ አካላት ምክንያቱ ሌላ ነው ይላሉና እዚህ ላይ ምላሽዎ ምንድን ነው?
ዶክተር ኢንጂነር አብረሃም፡- ቀደም ሲል ከገለፅኩልሽ የተለየ ነገር የለም።ስራውን በአግባቡ የሚያውቅ ሰው ሌላ ችግር አለበት ብሎ አያስብም።እንደሚታወቀው ማመንጫዎቻችን ውሃን መሰረት ያደረጉ ናቸው።ስለዚህ ውሃን መሰረት ያደረገ ደግሞ ክረምት የሚገባው ውሃ ከፍተኛ ካልሆነና በበልግም ተጨማሪ ካላገኘ ውሃው ፈሶ ማለቁ አይቀርም።ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት ደግሞ የኃይል የማመንጨት አቅም በሚጠራቀመው የውሃ መጠንና ከፍታ ነው የሚመሰረተው። ከፍታው እየቀነሰ በሄደ ቁጥር የማመንጨት አቅሙ ይወርዳል።
ስለዚህም ጊቤ ላይ ያጋጠመውም ይኸው ነው። በመሆኑም ጊቤ የሚያመነጨው መጠን ቀርቶ አንድ አራተኛ እንኳ ማመንጨት አልቻለም። 1ሺ800 ሜጋ ዋት ያመነጫል ተብሎ የሚታሰበው ጊቤ 200 እና 300 ሜጋ ዋት ብቻ ማመንጨት ከቻለ የለንም ማለት ነው። ስለዚህም ይህ አይነት ነገር ነው ያጋጠመን። በመሆኑም ዋናው መሰረቱ ውሃ ነው።
ከዚህ ሌላ ግን የማይሰሩ ዩኒቶች በየቦታው አሉ። ለምሳሌ አስር ዓመት እንዲሁም አምስት ዓመት የማይሰሩ ዩኒቶች በየቦታው አሉ።በአሁኑ ሰዓት ግን እነዚህ በየቦታው ያሉና የማይሰሩ ዩኒቶች ወደስራው እንዲገቡ እንቅስቃሴ ተጀምሯል።አራት ሺ ያህል ሜጋ ዋት አለን ስንል አራት ሺውም እየሰራ ነው ማለት አይደለም።ሁለት ሺ 500 አካባቢ ነው እየሰራ የነበረው።
የማይሰሩ ዩኒቶችን እንዲሰሩ በማድረግ አሁን ላይ ነው ወደ ሶስት ሺ ሜጋ ዋት እያደረስን ያለነው። ከዚህም በተጨማሪ እያሻሻልናቸው በሙሉ አቅማቸው እንዲሰሩ እያደረግናቸው ነው። ለምሳሌ ተከዜን ብንወስድ ከአራት ዩኒቶች ውስጥ አንዱ ብቻ ነው ሲሰራ የነበረው። የአሸጎዳን ንፋስ ኃይል ማመንጫን ብንወስድ ደግሞ ሙሉ በሙሉ አይሰራም።የግቤ አንድን ብንወስድ የማይሰራ ዩኒት ስንት ዓመት ሙሉ ቆሞ ነው የሚታየው።
አዲስ ዘመን፡- ለምንድን ነው ያሉትን ዩኒቶች በማደስ የኃይል እጥረቱን ለመቅረፍ ያልተሞከረው?
ዶክተር ኢንጂነር አብረሃም፡- ምክንያቱ ሁለት ነገር ነው።አንደኛው የግንዛቤ እጥረት ነው።አዳዲስ ፕሮጀክትን መገንባት እንጂ ነባሮቹ እየተረሱ ስለሆነ ነው። ነገር ግን ቀደም ሲል የነበሩትን በአግባቡ መጠበቅና ከተበላሹም ማደስ ነው እንጂ ሌላ ወጪ የሚያስወጡትን አዳዲሶቹን መጠበቅ በራሱ ስህተት ነው።ይህም የሚያሳየው ለተሰሩ ስራዎች ትኩረት አለመስጠትን ነው።ስለዚህም በአገሪቱ ውስጥ ያሉ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች መቶ በመቶ የሚሰሩ አልነበሩም።
ምክንያቱም ግማሹ ማሽን ተበላሸ የሚል ነው፤ ገሚሱ ደግሞ የጥገና ስራ የሚያስፈለገው ነው፤ግማሹ መለዋወጫ የሚጠብቅና ሌላም ሌላ ችግር ያለበት ሆኖ ነው ያገኘነው። ስለዚህ እንዲህ አይነት የግንዛቤ ማጣት ችግርም ነው ያጋጠመን ማለት ይቻላል። በመሆኑም ነው የኃይል እጥረት የሚያጋጥመው። አሁን ላይ እንደሚታወቀው ደግሞ የአገሪቱ የኃይል ፍላጎት ከጊዜ ወደጊዜ በእጅጉ እየደገ ነው። ስለዚህ አሁን ያሉንን ዩኒቶች ሙሉ በሙሉ እንዲሰሩ ማድረግ ያስፈልጋል።
ሌላውና ሁለተኛው ደግሞ ወደኃይል ማመንጨቱ ይገባሉ ተብለው የታሰቡ ፕሮጀክቶች በሚፈለገው ፈጥነት እየገቡ አልነበረም። ለምሳሌ ገናሌ ዳዋ ወደ ኃይል ማመንጨቱ መግባት የነበረበት ከሶስት ዓመት በፊት ነበር።የህዳሴ ግድቡም ያው እንደሚታወቀው ነው። የፕሮጀክት ማናጅመንት በሰዓቱ ያቀድናቸው ማመንጫ ጣቢያዎች ወደስራ እየገቡ ካላገዙ የኃይል እጥረቱ ይመጣል ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ሰዓት ተገልጋዩን ህብረተሰብን ጨምሮ የኢንዱስትሪ ፓርኮችም ሆኑ የባቡር ጣቢያዎች የኃይል እጥረት እንዳጋጠማቸው ይነገራልና በቀጣይ በኃይል ማጣት የተነሳ ሮሮ እንዳይደመጥ በአጭር ጊዜም ይሁን በረጅም ጊዜ ምን ለማድረግ አስባችኋል? በዚህ ዙሪያ የተፈራረማችኋቸው ስምምነቶችም ካሉ ቢገልፁልን?
ዶክተር ኢንጂነር አብረሃም፡- የኃይል እጥረትና የመሰረተ ልማት እጥረት ይለያያል።የኃይል እጥረት የሚባለው የማመንጨት አቅምን የሚያሳይ ነው። በአገሪቱ ያለው የኃይል ማመንጨት እጥረት አጋጥሞ ፍላጎቱ ካደገ የኃይል እጥረት አለ ይባላል።በየቦታው እየተገነቡ ያሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ቸገረን እያሉ ያሉት የኃይል መሰረተ ልማት ወደራሳቸው ማምጣቱ ላይ ነው እንጂ የኃይል ጉዳይ አይደለም።
ስለዚህ ለመሰረተ ልማቱ ዋናው ግሪድ ተዘርግቷል። ከዋናው ቋት በመውሰድ ወደየኢንዱስትሪዎቻቸው የማድረሱን ሁኔታ በመንግስት እንዲሰራላቸው ነው የሚፈልጉት። በመሰረቱ መሆን ያለበት ግን የትኛውም ግለሰብ ወደራሱ ሌላው ቀርቶ ቆጣሪውንና ገመዱን ሳይቀር እንዲሁም ምሰሶውን ሳይቀር የሚከፍለው ራሱ ነው።
ኢንዱስትሪዎችም ለራሳቸው የሚያስፈልግ ከዋናው ቋት የሚወስዱት የማስተላለፊያ መስመርም መገንባት የሚገባቸው ራሳቸው ናቸው። ይሁንና ከዚህ ቀደም ይህ ግንዛቤ አልነበረም። ሁሉም መንግስትን ብቻ ነበር የሚጠብቀው። እነርሱም መንግስት ይሰራዋል በማለት መንግስት ላይ ሲጭኑ ነው የኖሩት።
በመሆኑም በአሁኑ ሰዓት ይህ አስተሳሰብ መሰበር አለበት።የሲሚንቶ ፋብሪካዎቻችን የራሳቸውን የዘረጉት በራሳቸው ነው።አሁን ምንም አዲስ ነገር የለም።ስለዚህም መንግስት ላይ ጫና መፈጠር የለበትም።መንግስት ሲሉ ደግሞ ኤሌክትሪክ ኃይልን ነው የሚሉት፤ተቋሙ ደግሞ አይደለም ለእነሱ ሌላ ወጪ ሊያወጣ ቀርቶ ለራሱም ቆሞ መሄድ ያልቻለ ነው።
ኢንቨስትመንትን የሚስቡ አካላትም ኢንቨስተሮችን ሲስቡ የሚሏቸው ‹‹እኛ እናስገባላችኋለን ነው።›› ይሁንና ይህ አግባብ አይደለም።እንዲህ አይነት አሰራርም የለም።ፖሊሲያችን ራሱ የሚለው የኃይል መሰረተ ልማቱ በሁሉም አካላት ትብብር የሚሰራ እንደሆነ ነው የሚገልፀው። ለዛም ነው ታሪፉ በጣም ዝቅ ብሎ እንዲከፈል እያደረግን ያለነው። ካልሆነማ እኮ መንግስት ለኃይል መሰረተ ልማት የሚያወጣውን ታሳቢ በማድረግ ታሪፉን ከፍ ማድረግ ነበረበት።
ነገር ግን ኢንቨሰትመንት የሚስቡ የመንግስት ተቋማትም ለኢንቬስተሩ በአግባቡ ካለማስረዳት የተነሳ ጉዳዩን ወደመንግስት የማምጣት አዝማሚያ እየታየባቸው ነው፤ ቢሆንም አሁን ግን ግንዛቤ እየተፈጠረ መጥቷል። ስለዚህ በጥቅሉ ኃይል ስላጠረ ብቻ ሳይሆን በመሰረተ ልማቱ አማካይነት የተመረተው ኃይል ወደሚፈለገው ቦታ ካለመድረሱም የተነሳ የመጣ ጥያቄም ነው ማለት ይቻላል።ይህን ስል ግን የኃይል እጥረት አላጋጠመም ማለት እንዳልሆነና ከዚህ በኋላም እጥረቱ እንዳያጋጥም ከፍተኛ ስራ መሰራት እንዳለብን ወስጄ ነው።
ኃይል ማመንጫዎቻችን በግል ባለሀብትም ይሸፈናሉ ብለን ነው የምናስበው።እንደሚታወቀው መንግስት ባለፉት ሁለት ዓመት በራሱ ኢንቨስት እያደረገ ማመንጫ ጣቢያዎችን አቋቁሟል። ከዚህ በኋላ ኢንቨስት አናደርግም፤ ኢንቨስት ማድረግ ያለበት የግል ባለሀብቱ መሆን አለበት ነው እያልን ያለነው።ባለሀብቱ የማመንጨት ስራውን በአግባቡ በመስራት ወደፊት ማስኬድ ካልቻለ ሌላ አማራጮች መታየት አለባቸው።እሱን ታሳቢ አድርገን ነው ለወደፊቱ የማመንጫ ችግር አይኖረንም የምንለው።
ካልሆነ ግን መንግስት ይዟቸው ያሉ ፕሮጀክቶች ቢጠናቀቁም የኃይል እጥረት ይኖራል ማለት ነው። በቀጣይም ፍላጎቱ እያደገ ስለመሄዱ ምንም ጥያቄ የለውም። ምክንቱም በጣም ከፍተኛ ኃይል ተጠቃሚ ስራዎች እየገቡ ነው ያሉትና። እስከ አንድ ሺ ሜጋ ዋት ኃይል የሚፈልጉ መሰረተ ልማቶች እየመጡ ነው። እንደእነዚህ አይነቶቹ ሲመጡ ደግሞ የከተማውን ብቻ ሳይሆን እንዳለ የአገሪቱን ኃይል በአንዴ የሚወስዱ ናቸውና ፍላጎታቸውን ሊደግፍና ሊያሟላ የሚችል ሌላ አካል ካልመጣ አስቸጋሪ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ እድሉን ልስጥዎ?
ዶክተር ኢንጂነር አብረሃም፡- አብረን እንስራ ነው የምለው፤ የኃይል አጠቃቀማችንን እናስተካክል።ታሪፉ ትንሽ የሆነው ወጪውን መንግስት ስለተሸከመ ነው እንጂ ወጪው ከፍተኛ ነውና እያንዳንዱ ግለሰብም ሆነ የኃይል መሰረተ ልማት ተጠቃሚ ትክክለኛ የሆነ የኃይል አጠቃቀም ስርዓቶችን ቢከተል መልካም ነው የሚል መልዕክት አስተላልፋለሁ። ባለሀብቶች የራሳቸው አስተዋፅዖ እንዲኖራቸው የራሳቸውን የኃይል መሰረተ ልማት በመንግስት የሚቻል ባለመሆኑ በራሳቸው እንዲሰሩም ጥሪ አቀርባለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡኝ ሰፊ ማብረራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ።
ዶክተር ኢንጂነር አብረሃም፡- እኔም አመሰግናለሁ። ለኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉ እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላም አደረሰን ማለት እፈልጋለሁ።
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 5 /2011
አስቴር ኤልያስ