አቶ ሳኒ ረዲ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በኢኮኖሚክስ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በዴቨሎፕመንት ኢኮኖሚክስ ሠርተዋል። ለስምንት ዓመት ያህል በደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደርነትና በግብርና ቢሮ ኃላፊነት፣ የአቅም ግንባታ ቢሮ ኃላፊና የዞን ምክትልና ዋና አስተዳዳሪ በመሆንም አልግለዋል፡፡ ከሁለት ዓመት ተኩል በፊትም ደግሞ በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ልማት ባለስልጣን በሚኒስትር ማዕረግ ዋና ዳይሬክተር ሆነው ሠርተዋል። በአሁኑ ወቅት በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ።
አዲስ ዘመንም በወቅታዊ የሰበል አሰባሰብ እንዲሁም በግብርና ሥራውና የወደፊት እቅድ ዙሪያ ሰፋ ያለ ቃለ ምልልሰን አደርጓል። መልካም ንባብ ይሁንልዎ፡፡
አዲስ ዘመን፡- በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ከግብርናው ዘርፍ ይጠበቅ የነበረው ውጤት አልተገኘምና ምክንያቱ ምንድን ነው?
አቶ ሳኒ፡- ግብርና አገራዊ ኢኮኖሚካል ትራንስፎርሜሽን በማረጋገጥ ሂደት ውሰጥ ትልቅ ተልዕኮ የተሰጠው ሴክተር ነው። የአገሪቱ የኢኮኖሚያዊው ፖሊሲ ሲቀረጽ የህዝብ ብዛቱ ወደ 80 ሚሊየን የሚጠጋ ነበር። ከ85 በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝብም ህይወቱ በግብርና ላይ የተመሰረተ ስለነበርም ነው በእንዲህ መልኩ የተቀረጸው።
ሌላው ከዓመታዊው የአገሪቱ ምርት ከ56 እስከ 60 በመቶውም የግብርና ድርሻ ነበር፤ ከ70 በመቶ በላይም የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ እንደዚያው ግብርናውን መሰረት ያደረገ ነበር፤ ሰፊ ጉልበት፣ አነስተኛ ካፒታል እንዲሁም ቴክኖሎጂ ያለን በመሆኑም እነዚህን አቀናጅቶ የመምራት አቅማችንም ውስን በነበረበት ወቅት ግብርና መር የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ነበረን። ግብርናውንም የያዘ ግብርናና ገጠር ልማት የሚል ፖሊሲም ነበረን፡፡ ይህ ፖሊሲም ግብርናንም ማሳደግ፣ ገጠር ልማቱንም ጎን ለጎን ማስኬድ እንደ ቅድመ ሁኔታ የተቀመጠና ተያይዘው መሄድ ያለባቸው መሆኑን የሚያመለክት ነበር። ተያይዘው ሲሄዱ በተለይም ግብርናው የራሱን ዕድገት እያፋጠነ የሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፉን ይዞ እንዲሄድ ተልዕኮ ተሰጥቶታል።
በግብርና የሚመራ ኢንዱስትሪ ልማት ሲባልም በሂደት ግብርና ድርሻውን ለኢንዱስትሪ እየለቀቀ ኢንዱስትሪው ደግሞ ግብርና ከሚያደግበት ፍጥነት በላይ እያደገ መሄድ አለበት እንደማለት በመሆኑ ግብርና የራሱንም ዕድገት ሳይለቅ ግን ደግሞ ለኢንዱስትሪው ዕድገት አስተዋጽኦ ማበርከት አለበት ማለት ነው።
ከዚህ አኳያ ግብናው በፖሊሲ ደረጃ መላውን ህዝብ በየደረጃው ተጠቃሚና ተሳታፊ የሚያደርግ ዕድገት ማረጋገጥ፣ አገሪቷንም ህዝቧንም ከተመጽዋችነት የሚያላቅቅ ዕድገት ማረጋገጥ፣ ግብርና ዕድገቱን ፈጣንና ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረግ፣ ግብርናው እራሱ በዓለም ገበያ እንዲመራ ማስቻል ተቆጥረው የተሰጡት ኃላፊነቶችም ነበሩ።
እነዚህን ተልዕኮዎች በማሳካት ሂደት ላይ ከሌሎች ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ጋር የሚተሳሰርበትም ግቦች ተቀምጠውለታል፤ አንደኛው በቂ ንጥረ ነገር ይዘት ያለውን ምግብ በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ፣ ሁለተኛው ግብርና ራሱም ሆነ ሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎችን ዕድገት ለማፋጠን የሚያስችል የውጭ ምንዛሪ ማመንጨት፣ ሦስተኛው ለሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች የገበያ ዕድል መፍጠር፣ አራተኛው ጉልበትን በቁጠባ የምንጠቀምበትን ዕድል እየፈጠረ የሰለጠነም ያልሰለጠነም ጉልበት እየተፈጠረ ወደ ኢንዱስትሪውና ወደ አገልግሎት ዘርፉ እንዲሸጋገር ማድረግ ናቸው።
ግብርናን በእነዚህ መለኪያዎች ስንለካው እንግዲህ በየዓመቱ የሚያሳየው ዕድገት አለ። ግን ፈጣን አይደለም፤ ፈጣን አይደለም የምንለው ደግሞ ለማደግ ያለውን ዕድል ስንገመግም ከዚህ በላይ ለማደግ የሚያስችሉት በመሆናቸው ነው።
አዲስ ዘመን፡- ግብርናው ለማደግ ያሉትን ዕድሎች ተጠቅመን ቢሆን ኖሮ ዕድገቱ ፈጣን ይሆን ነበር ማለት ይቻላል?
አቶ ሳኒ፡- የግብርና ፖሊሲያችን አንድ እግር በመሬት ነው የሚለው፤ ይህ ማለት ደግሞ ቴክኖሎጂ ለመግዛት የካፒታል እጥረት አለብን፡፡ ቴክኖሎጂውን እንኳን ብንገዛው የክህሎት ችግር አለ፡፡ በመሆኑም የአርሶ አደሩን ተነሳሽነት ጨምረን ክህሎቱን ተከታታይነት ባለው ሁኔታ እያበቃን ምርታማነቱን ማሳደግ ይገባል፡፡ ጎን ለጎንም ከአካባቢው ምርጥ ዘር የተሻለውን በመጠቀም ቀጥሎ በአነስተኛ ወጪና በመጠነኛ ቴክኒክ ሊፈጸሙ የሚችሉ ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያ እና ኬሚካል እያቀረበን ምርታማነታችንን እያሳደግን ከስር ከስር ደግሞ ቴክኖሎጂ የመጠቀም፣ የመኮረጅና የማላመድም አቅማችንን እያሳደግን መሄድ ግን አንዱ ዕድል ነው።
ከዚህ አንጻር የነበረንን የአርሶ አደሩን እውቀትና ተነሳሽነት እያሻሻልን እንዲሁም በአነስተኛ ገቢና የቴክኒክ እውቀት ሊፈቱ የሚችሉ የቴክኖሊጂ ውጤቶችን አመጥተን እየሠራን እዚህ ደርሰናል፤ ነገር ግን ግብርናው መሠረታዊ መዋቅራዊ ለውጥ አላመጣም። ይህ ደግሞ ዕድገቱንና የማዘመን ሥራውን ጎትቶታል።
አዲስ ዘመን፡- ከግብርናው ዕድገት ባሻገር ማዘመኑ ላይም ብዙ የተሠራ አይመስልም፤ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
አቶ ሳኒ፡- ግብርና መሰረታዊና መዋቅራዊ ለውጥ አመጥቶ አልዘመነም ሲባል ሁሉም አርሶ አደር ለግብርና ሥራው የሚያስፈልጉትን ቴክኖሎጂዎች ተጠቅሟል ወይ የሚለውም አብሮ መነሳት ያለበት ጥያቄ ነው፡፡ ይህንን ስናየው አሁን ላይ 30 እና 40 በመቶ የሚሆነው አርሶ አደር ብቻ ነው ምርጥ ዘርንና ማዳበሪያን በተሟላ ሁኔታ እየተጠቀመ ያለው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ በእጃችን ያለውንም ቴክኖሎጂ ማዳረስ አለመቻላችን ዕድገቱን ጎድቶታል።
ሌላው የጉልበትን ምርታማነት የሚያሻሽሉ እንደ ሜካናይዜሽን ያሉ ቴክኖሎጂዎች ያስፈልጋሉ። ምክንያቱም መሬቱ በወቅቱ ታርሶ ካለማ በተመሳሳይ መንገድ ዘርን በሚገባ ማዳረስ አይቻልም፡፡ ይህ ደግሞ በአንድ ሄክታር ሊኖር የሚችለውን ምርት ማግኘት አያስችልም። ምርት ይባክናል፤ የምርት ጥራትም ይጓደላል። በመሆኑም ምርታማነትን የሚያሳድጉና ጉልበትን የሚቆጥቡ ቴክኖሎጂዎችን ብሎም እንደ ምርጥ ዘር ፣ ማዳበሪያ፣ ኬሚካሎችና ሌሎችንም በተገቢው መንገድ መጠቀም ስላልቻልን አሁንም ግብርናችን ዘምኗል ማለት አንችልም።
አዲስ ዘመን፡- የ2010/11 የምርት ዘመን የመኸር ማሳ ምርት አሰባሰብ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?
አቶ ሳኒ፡- የዘንድሮ የምርት አሰባሰብ ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ከፍተኛ የሆነ ተጽዕኖ ተፈጥሮበታል፡፡ ከመስከረም ወር ጀምሮ በብዙ አካባቢዎች ላይ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እንደሚኖር ከብሔራዊ ሜትሮሎጂ የተገኘውን መረጃ በመያዝ በየትኞቹ አካባቢዎች ችግሩ ሊገዝፍ ይችላል? ጉዳቱንስ እንዴት ልንቀንስ እንችላለን? የሚለውን በማየትና እቅድ በማውጣት ለባለሙያዎች፣ ለባለሀብቶች እንዲሁም ለአርሶ አደሩ ማድረስ በመቻሉ ሥራው በቶሎ እንዲጀመርና ምርቱም እንዲነሳ ተደርጓል።
በተለይም የሜካናይዜሽን አገልግሎት ዕድል ባለባቸው አካባቢዎች ባለሀብቶቹን በማሳመንና ከምን ጊዜውም በላይ አገልግሎቱን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲሰጡ የማድረግ ሥራ ተሠርቷል፡፡ ዝናቡ ከፍ ባለባቸው አካባቢዎችም ተማሪዎች ወላጆቻቸውን ማገዝ ስላለባቸው ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ ተደርጓል። የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና የመከላከያ ሠራዊት አባላትም ድጋፍ እንዲያደርጉ በመሆኑ የዝናቡን ጉዳት ለመቀነስ ተችሏል።
በአሁኑ ወቅትም 7 ነጥብ 8 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ ያለ ምርት ተሰብስቧል። ዘግይተው የዘሩ አካባቢዎች ላይ ያሉ ምርቶችም እየደረሱ በመሆኑ ከስር ከስር የመሰብሰብ ሥራም እየተሠራ ነው። የዝናቡ ስጋትም ሙሉ በሙሉ ስላልተወገደ በሚጥልባቸው አካባቢዎች ያሉ የግብርና ባለሙያዎችም ውሃ ማሳ ላይ እንዳይተኛ በማድረግ የደረሱ ሰብሎችም በፍጥነት እንዲሰበሰቡ እየተሠራ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በአንዳንድ አካባቢዎች ያለው የጸጥታ ሁኔታስ ምርት በመሰብሰብ ሂደቱ ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ እንዴት ይገለጻል?
አቶ ሳኒ፡- በተለይም በምዕራብ የኦሮሚያና የቤንሻንጉል ጉሙዝ አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ መጠነኛ የሆነ ጉዳት ደርሷል። በተለይም በእነዚህ አካባቢዎች ላይ የአገሪቱ 40 በመቶ ያህል የበቆሎ ዘር የሚባዛበት ከመሆኑም አንጻር የአርሶ አደሩ ማሳም ብቻ ሳይሆን ለምርጥ ዘርነት ባለሀብቶች የዘሩት ሰሊጥና በቆሎ ችግር ላይ በመሆኑ ከሁለቱም ክልል የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች፣ ከመከላከያ ሠራዊት የምዕራብ ዕዝ አባላት፣ ከአምራች ባለሀብቱና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ውይይቶች ተደርገዋል።
በዚህ መሰረትም መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ አድርጎ ምርቱ እንዲሰበሰብ የጋራ ኮሚቴ ተቋቁሞ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል። ሠራዊቱም ሥራውን ለመሥራት ተጨማሪ ምን ያህል ኃይል ያስፈልገኛል? የሚለውን እየለየ ሲሆን፣ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥትና የካማሽ ዞን አስተዳደርም የአካባቢው ነዋሪዎች ምርቱን ከሌብነትና ከቃጠሎ በመጠበቅ ላይ ናቸው።
በመሆኑም ይህንን ኃላፊነት እየተወጣ ያለ አርሶ አደር ምርቱን የሚያነሳ የጉልበት ሠራተኛና ተሽከርካሪ ሲገባ ሰብሉ የአገር ሀብት መሆኑን ተገንዝቦ ድጋፍ እንዲያደርግ ከተቻለም በጉልበቱ እንዲሳተፍ የሚያደርግ ኮሚቴ ተደራጅቷል።
በምሥራቅና ምዕራብ ወለጋ ያለውን የበቆሎ ምርጥ ዘር ለማሰባሰብ ባለሀብቶቹን የመደገፍ ሥራ የሚሠራ ኮሚቴ ተደራጅቶ ተሰማርቷል፤ በቤንሻንጉል ጉሙዝ የሚመረተውም በቆሎ በወለጋ በኩል ስለሆነ ወደ መሀል አገር የሚገባው የተዘጉ መንገዶችም ስላሉ ይህንን በማስከፈት የጉልበት ሠራተኞች እንዲገቡ ምርቱም እንዲወጣ የማድረግ ሥራ ተጀምሯል።
በአጠቃላይ ግን የችግሩን ግዝፈት በመረዳት የመንግሥት አካላት፣ የወጣት አደረጃጀቶች ፣የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ምርቱን በወቅቱ ማንሳት ካልተቻለ ለቀጣይ ዓመት የረሀብ አደጋ እንደሚከሰት በመገንዘብ እርቀ ሰላም እያወረዱ ምርቱ እንዲሰበሰብ የማድረግ ሥራውን አጠናክረው መቀጠል አለባቸው።
አዲስ ዘመን፡- አርሶ አደሩ ለምርቱ ተገቢውን ዋጋ አለማግኘቱ ይነሳል ? ብሎም የገበያ ትስስሩ ችግሮች አሉበት፤ በዚህስ ላይ የእርሶ ሃሳብ ምን ይሆን?
አቶ ሳኒ፡- የግብይት ስርዓቱ የተወሳሰበ ፍትሐዊ ያልሆነ ለህገ ወጥ ንግድ የተጋለጠ በመሆኑ የግብርናውን ዕድገት አቀጭጮታል። በግብይት ስርዓቱ አርሶ አደሩ ምርቱን ካመረተ በኋላ እንደ ቡናና ሰሊጥ ያሉ ምርቶችን የአርሶ አደሩ ህብረት ሥራ ማህበራት አሰባስበውና አደራጅተው ለውጭ ገበያም ሆነ ለአገር ውስጥ የሚውለውን ለይተው ያቀርባሉ፤ የመጨረሻው ገዢ የሚከፍለውን ወደ አርሶ አደሩ ለማድረስ እየሞከሩ ነው።
ሆኖም የአርሶ አደሩ የመጨረሻ ምርት ገዢ ዘንድ እስከሚደርስ ድረስ ግን በርካታ ገበያዎችና ባለድርሻ አካለት አሉ፤ በዚህ ምክንያት ደግሞ ምርቱ በመጨረሻ ካወጣው ዋጋ አንጻር አርሶ አደሩ ዘንድ የሚደርሰው በጣም አነስተኛ ነው። በመሆኑም ይህ ሁኔታ መቀየርና አምራቹ በቀጥታ ከተጠቃሚው ወይም በመካከል አንድ አገናኝ ብቻ የሚኖርበት ስርዓት መመቻቸት አለበት፡፡ ይህ ሲሆን ምርቱ በገበያ የሚያወጣው ዋጋ ወደ ዋናው አምራቹ ይደርሳል፡፡ ይህ ደግሞ ምርታማነቱን እንዲያሳድግ ማበረታቻ ይሆነዋል፡፡ ሌላው አምራቹ የተጠቃሚውን ፍላጎት እንዲለይ ዕድል ይሰጠዋል።
ግብርና በገበያ መመራት አለበት፤ አርሶ አደሩ ሰፊውን የዓለም ገበያ እያየ ስለሚያመርት ዕድገቱ ይፋጠናል፤ ለምርቱም የተሻለ ዋጋን ያገኛል፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ የምናመርታቸው ምርቶች ለዓለም ገበያ ተመራጭ ሲሆኑ ነው። ለምሳሌ ቡና፣ ሰሊጥ፣ ሻይ ቅጠል ፣ ቦሎቄ፣ ማሾ እንዲሁም ለኢንዱስትሪ የሚሆነው ጥጥ ባላቸው የገበያ ተፈላጊነት የሚመጥን ሥራን እየሠራን አይደለም።
ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ እነዚህን ሰብሎች ሊሸከም የሚችል መሬትን በጥናት ለይተንና ክላስተር አድርገን በአካባቢው ያሉ አርሶ አደሮች በተመሳሳይ መልኩ እንዲያመርቱ በማድረግ በኩል ችግር በመኖሩ ነው ፤ በመሆኑም ወደ ማምረት ሂደት ስንገባ አካባቢያዊ ስፔሻላይዜሽን ወሳኝነት አለው።
ይህ ሲሆን ደግሞ የአንድ አካባቢ አርሶ አደር ተመሳሳይ ምርትን የሚያመርት በመሆኑ ጉልበትን ሊቆጥቡ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችንም ለማቅረብ ያግዛል፤ በተለይም ሜካናይዜሽን አገልግሎትን የሚያቀርቡ ድርጅቶችን ተቋማትንና ማህበራትን ለማዘጋጀት ይቻላል። ሆኖም ይህንን ሳናደርግ ቆይተናል። ይህም ችግር ሆኖ ኖሯል።
ሌላው የአየር ንብረት ለውጥ የዝናቡን አመጣጥ የቆይታ ጊዜ መጠንና ስርጭት አዛብቶታል። በመሆኑም አሁን ላይ ግብርናው ወደ መስኖ መሸጋገር ያለበት ከመሆኑም በላይ የሚዘንበውንም ዝናብ የሜቲዎሮሎጂን መረጃ ተጠቅሞና ትክክልኛ የመምጫ ጊዜውን ለይቶ ረጅም ጊዜ የሚቆይ ከሆነ ፣ ረጅም ጊዜ የሚቆዩ የሰብል ዘሮችን፣ ቶሎ የሚወጣ ከሆነ ቶሎ የሚደርሱ ዘሮችን፣ መጠኑ አነስተኛ ከሆነም ብዙ ውሃ የማይፈልጉ ዘሮችን፣ መጠኑ ብዙ ከሆነም ብዙ ውሃን የሚወስዱ ስብሎችን በሚያቀርብ ደረጃ ቴክኖሎጂን የማባዛት አቅማችን አልተገነባም።
በጠባብ መሬት ላይ በዓመት አንድ ጊዜ በሚገኝ ምርት የአርሶ አደሩ ህይወቱ ሊቀየር ከድህነትም ሊላቀቅ አይችልም፤ በመሆኑም በዓመት ሁለቴና ሦስት ጊዜ ማምረት መቻል አለበት። ለዚህ የሚሆን ደግሞ የከርሰ ምርድና የገጸ ምድር ውሃ አቅርቦታችን ላቅ ያለ ነው፤ ሆኖም አሁንም በመስኖ የምናመርተው ምርት እጅግ የቀነሰ ነው፡፡ የውሃ አጠቃቀማችንን ግብርናው በሚፈልገው ደረጃ አልገነባነውም።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት በርካታ የገጠሪቱ ክፍል ነዋሪዎች ወደ ከተማ የሚገቡበት ሁኔታ በሰፊው ይታያልና ይህ ከምን የመነጨ ይሆን?
አቶ ሳኒ፡- አሁን ላይ ከገጠር ወደ ከተማ የሚፈልሰው ቁጥር ጨምሯል፤ ግማሹ ለኢንቨሰትመንት ሌላው ደግሞ የተሻለ የሥራ ዕድልን በመፈለግ የሚፈለስ ነው፤ ግብርናው ባለመዘመኑ ምክንያት የሚፈልሰው ሰው ቁጥር ከፍተኛ ነው።
ድሮ አባቶቻችን በሚያርሱበት በሬና ሞፈር አሁን ያለው ወጣት ለማረስ ፍቃደኛ አይደለም፤ ተምሯል፤ በተፈጠረለት ግንዛቤ ልክ ጉልበት ቆጣቢና የተሻለ ቴክኖሎጂን ይፈልጋል፡፡ ይህንን ማቅረብ ባለመቻላችን ግን ወደ ከተማ ሥራ ፍለጋ በመፍለስ ላይ ነው። በመሆኑም ግብርና እያደገ ቢሆንም ባለው አቅምና በሚፈለገው ልክ እያደገ አይደለም፡፡ ስለዚህም ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- ግብርናው በአዝጋሚ ዕድገት ውስጥ ነው ካልን ወደ ፈጣን ዕድገት ሊያመጣው የሚችለው መፍትሔ ምንድን ነው?
አቶ ሳኒ፡- አንድ እግር በመሬት በሚለው ፖሊሲያችን ጀምረን የአርሶ አደሩ የማምረት አቅም እየተገነባ የቴክኖሎጂ ፍላጎትና የአጠቃቀም ሁኔታ እያደገ ቢመጣም፤ ለሁሉም በሚደርስ ሁኔታ እያቀረብን አይደለም፡፡ ይህን ማድረግ ብንችል ምርታማነት ያድጋል፤ የምርት ጥራት ይሻሻላል፤ አርሶ አደሩም በተጓዳኝ በሚሠራቸው ሥራዎች ላይ ጉልበቱን ይጠቀማል።
በመሆኑም ይህንን ሊፈታ የሚችል የሜካናይዜሽን አገልግሎት ያስፈልጋል። ይህንን ለማድረግ ሰትራቴጂ ተቀርጿል፡፡ አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮችም እራሳችሁ ግዙ ብንላቸው ስለማይሆን አገልግሎት የሚሰጡ የግል ድርጅቶችና ህብረት ሥራ ማህበራትን ብድር እያመቻቹ ወደ ዘርፉ እንዲቀላቀሉ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው።
በአሁኑ ወቅትም ከግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ጋር በመተባበር የሜካናይዜሽን አገልግሎቶችን በትግራይ፣ በደቡብ፣ በኦሮሚያና አማራ ላይ 10 ፓይለት የአገልግሎት መስጫ ተቋማት እየተገነቡ ነው። ይህንን ተሞክሮም በመያዝ ወደሌሎች የማስፋት ሥራም ይሠራል። ይህ አነስተኛ ይዞታ ላላቸው አርሶ አደሮች ተመጣጣኝ ክፍያን በማስከፈል የሚጀመር ይሆናል። ይህ መሆን ከቻለ ወጣቶች ግብርና አዋጭ የሥራ መስክ መሆኑን ተገንዝበው በወላጆቻቸው መሬት ላይ አልያም አዳዲስ ትርፍ መሬቶችን በመውሰድ ወደ ሥራው ይገባሉ፡፡ ሌላው የመሬት ለምነትና ምርታማነት ማሻሻል ነው። ለዚህም የሚሆን ጥናት ተደርጎ ተጠናቅቋል።
መስኖም ችግሩን ለመፍታተ አንዱና ዋናው አማራጭ ነው፤ በመሆኑም የመስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከፍተኛ በጀት መድቦ ያሉትን አማራጮች በሙሉ በጥናት ለይቷል። የዝናብ ችግር ባለባቸውም በቶሎ ወደ ልማቱ የመግባት ሥራ እየተሠራ በመሆኑ በቀጣይ በአንድ መሬት ሁለቴና ከዚያ በላይ እያመረትን የምንፈልገውን ምርት በማግኘትና ወደ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ እንሆናለን።
አዲስ ዘመን፡- ከመኸር ምርት አሰባሰብ ቀጥሎ የሚመጣው የአካባቢ ልማት በተለይ የተፋሰስ ሥራ ነውና ከዚህ አንጻርስ ዝግጅቱ ምን ይመስላል?
አቶ ሳኒ፡- ግብርና ዓመቱን ሙሉ የሚሠራ መሆን አለበት፤ አርሶ አደሩ በዓመት አንድ ጊዜ አምርቶ እሷኑ ዓመት ሙሉ የሚመገባት፣ ለሚያስፈልገው ማህበራዊ ወጪም የሚመነዝራት ከሆነ ከድህነት ሊወጣ አይችልም። በመሆኑም የመኸር ሰብል እንደተነሳ በየአካባቢው ባለው የመስኖ ሀብት ላይ ተመሰርቶ ወደ ሥራ ነው የሚሸጋገረው። በዚህም የመሬቱ እርጥበት ሳይሟጠጥ የወንዞችና የሀይቆችም የውሃ መጠን ሳይቀንስ ፈጥኖ ሰብል እያነሱ ወደ ደጋፊ ሰብል ምርቶች እንዲሸጋገሩ እየተሠራም ነው።
በዚህ ዓመት ወደ 3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ከፍተኛ፣ አነስተኛና ጥቃቅን የመስኖ አውታሮች በመታገዝም የተለያዩ የጓሮ አትከልቶችን ለማልማት የምርጥ ዘር ጉድለትንም ለመሙላት የሚያስችል አቅድ ታቅዶ ነው እየተሠራ ያለው። እስከ አሁንም ወደ 500 ሺ ሄክታር መሬት በተለያዩ የአትክልት ዘሮች ተሸፍኗል።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ ቀደም ለሥራ እንዲመች በሚል ግብርና ሚኒስቴር ለሁለት ተከፍሎ ነበር፤ አሁን ደግሞ አንድ ሆኗል፡፡ በተለይም አሁን ላይ ሁለት የነበረውን የሰው ኃይል አንድ አድርጎ በመጠቀም በኩል የታየው ውጤት ምን ይመስላል?
አቶ ሳኒ፡- ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለሁለት ሲከፈል በተለይም የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ዘርፉ የተሻለ ትኩረትና ሀብት ያገኛል በሚል ነበር፡፡ ሀብቱንም የሰው ኃይሉንም ለሁለት ተካፍለን ተንቀሳቀሰናል፤ ሆኖም ሥራው ወደ ታች ሲወርድ በአንድ አርሶ አደርና የቀበሌ መዋቅር ላይ ነው የሚያርፈው፤ ምክንያቱም የእኛ ግብርና ከእንስሳት ሀብት ጋር ተቀናጅቶ የሚሄድ በመሆኑ ይህ ደግሞ ስጋት ሳይሆን ዕድል ነው።
ስለ ቴክኖሎጂ ስናወራ ሰብልና የእንስሳት እርባታ ተነጣጥለው የሚሄዱ አይደሉም፤ እኛም የምንሠራው ሥራ በሁለት ተቋም ላይ ሲሆን፣ አርሶ አደሩ የትኛውን ነው የሚቀበለው። ከጊዜ ብክነት፣ ከሀብት አንጻርም አዋጭ አይደለም፤ በመሆኑም ጥምር ግብርና የምናካሂድ እንደመሆናችን መጠን ግብርናውን ለማዘመን በጣም አስፈላጊ ነው። ውጤቱንም በሂደት የምናየው ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ይኖርዎታል?
አቶ ሳኒ፡- ሁለት ነገር ይኖረኛል፤ አንደኛው አሁን ማሳ ላይ ያለው የመኸር ሰብል (የእህልም ሆነ የምርጥ ዘር ሰብል) ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብና ውርጭ እንደሚኖር ብሔራዊ ሜቲሪዎሎጂ ይፋ አድርጓል፡፡ በመሆኑም በአካባቢው ያሉ አርሶ አደሮች፣ ምሁራን፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ባለሀብቶች ሳይዘናጉ በንቅናቄ መልክ ፈጥኖ ምርት እንዲሰበሰብ አደራ እላለሁ።
ወቅውቱን ባልጠበቀ ዝናብ የምናጣውን ምርት የምናካክስበት የያዝነውንም የምርት ግብ ለማሳካት እንዲቻል በመስኖ ልማት ሥራው ላይ መዘናጋት ሳይኖርና የማሳው እርጥበት ሳይደርቅ ፈጥኖ ወደ ልማቱ መሸጋገር ያስፈልጋል። ሁሉም ሰው ተልዕኮውን ይዞ እንዲረባረብ መልዕክቴን አስተላፋለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- በጣም አመሰግናለሁ።
አቶ ሳኒ፡- እኔም ስለተሰጠኝ ዕድል በጣም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 9/2011
እፀገነት አክሊሉ