ሻጭን ከሸማች ሲያገናኝ የሚውለው ገበያ ሁሌም በግርግር አርፍዶ ያመሻል። ህይወታቸውን በስፍራው የመሰረቱ አንዳንዶችም በየቀኑ ወደዚህ ስፍራ ይመላለሳሉ። ይህ ቦታ ለብዙዎች የእንጀራ መገኛቸው ሆኗል። ሰርተውና ለፍተው በላባቸው የሚያድሩ ሁሉ አመሻሹን የድካማቸውን ያገኙበታል።
ደንበኞችን ለመሳብ የራሳቸውን ስልት የሚጠቀሙ አንዳንድ ነጋዴዎች ዘወትር መልካም ለመሆን ይሞክራሉ። ለሚጠይቋቸው ሁሉ በፈገግታ እየመለሱም በትህትና ያስተናግዳሉ። ሁሌም ቢሆን ‹በእነሱ ዘንድ የደንበኛ ክቡርነት ተጓድሎ አያውቅም። የመጣውን ሁሉ እንደየባህሪው ተቀብለው አግባብተው ይሸኛሉ።
ሸማቾቹም ቢሆኑ በፍላጎትና አቅማቸው ስፍራውን መጎበኘት ለምደዋል። በገበያው የዓመታት ደንበኞችን ማፍራታቸውም በየጊዜው ለሚኖረው ግብይት መንገዱን አቅንቶላቸዋል። እንዲህ አይነቶቹ ያሻቸውን ለማግኘት ገበያውን መዞር አይጠበቅባቸውም። ባለሱቅ ደንበኞቻቸው ዘንድ ሄደው በተለመደው መስተንግዶ የተለመደውን ሸመታ ይከውናሉ።
ሁሉንም እንደየአቅሙ ሲያስተናግድ የኖረወ የአቧሬ ገበያ ሁሌም ቢሆን አጀ ሰፊ ነው። ብዙዎች ያሰቡትን ፈልገው አያጡበትም። ዝቅ ብለው ከሚገዙበት ጉልትና ችርቻሮ ፤ አስመዝነው እስከሚወስዱት ሸቀጣሸቀጥ የሚፈልጉትን አያጡበትም።
ይህ ስፍራ በገዢና ሻጮች ብቻ የተወሰነ አይደለም። በገበያው መኖር ህልውናቸው የቆመ በርካቶች ጭምር ህይወታቸውን ይመሩበታል። ሻይ ቡና ሻጮች፣ ሱቅ በደረቴዎች፣ ልብስ አዟሪዎች፣ ሊስትሮዎችና ሌሎችም አቧሬ ገበያ የእንጀራ ሞሶባቸው ነው።
ደማቁ የገበያ ውሎ ከጫኝና አውራጆቹ ግርግርና ሩጫም ተነጥሎ አያውቅም። በስፍራው ዕቃዎችን እየጫኑ የሚያወርዱ ለፍቶ አዳሪዎች ከመኪኖች ሲጋፉ መዋላቸው ተለምዷል። እነሱ ሁሌም ቢሆን ከሚያወርዷቸው ሚዛን ከባድ ዕቃዎች ላይ አይናቸውን አይነቅሉም። ዕድል በቀናቸው ጊዜም የጉልበታቸውን ዋጋ በድርድር ይቀበላሉ። በስራው ጥርሳቸውን የነቀሉና ዓመታትን የገፉ በርካቶች በዕለት ገቢው ቤተሰቦቻቸውን አሳድረው ልጆቻቸውን ያስተምራሉ። ላባቸውን ጠብ አድርገው ለቤታቸው ይተርፋሉ።
ከነዚህ መሀል የመማር እድሉን ያላገኙ ታዳጊዎች፣ ትምህርት ጀምረው ያቋረጡ ወጣቶችና ሌሎችም አብረው ይውላሉ። እነዚህ ሁሉ ታዲያ ገበያውን በሩጫ ተወዳድረው ማሸነፍ ግድ ይላቸዋል። አንዳንዴ ደግሞ ይህ ሩጫ በ‹‹ይገባኛል›› ሰበብ በጠብና ድብድብ ሊቋጭ ይችላል። እንዲህ በሆነ ጊዜም የሚፈጠሩ አለመግባባቶች በስምምነት የሚታለፍበት አጋጣሚ ይኖራል።
ፍልቅልቁ ደረጀ ጋሻው አይነ ግቡ ታዳጊ ነው። ወላጅ አባቱን በሞት የተነጠቀው ገና ህጻን ሳለ ነበር። በወቅቱ ድንገቴው የአባወራ ሞት ልጆችን ለከፋ ችግር ጥሎ ሚስትን ለመከራ ዳረገ።
የቤቱ ራስ የነበሩት አባወራ ሞት ለመላው ቤተሰብ ፈተና ሆኖ ቀጠለ። በልቶ ለማደር፣ ለብሶ ለመውጣት እጅ ያጠራቸው እናት በትካዜ ውሎ ማደር ልምዳቸው ሆነ። አብሯቸው የኖረው በሽታም ደረስ መለስ እያለ ይፈትናቸው ያዘ።
ደረጀ ከፍ ማለት ሲጀምር ቀለም ይቆጠር ዘንድ ትምህርት ቤት ተላከ። ከጓደኞቹ መስሎ ደብተር መያዙ ግን እንደ እኩዮቹ አላዋለውም። በቂ የሚባል ገቢ ያልነበራቸው እናት ያሻውን ሊሞሉለት አልቻሉም። የዕለት ወጪው፣ ቀለቡ፣ ዩኒፎርሙና ሌላውም አቅምን የሚፈትን ሆነ።
ድህነት ባዘመመው ጎጆ ደረጀንና ታላቅ እህቱን የሚያሳድጉት ወይዘሮ ከበሽታ እየታገሉ ኑሮን ለማሸነፍ ደከሙ። ሲሆንላቸው እየሰሩ፣ ህመሙ ሲጥላቸው ተኝተው እያገገሙ ቀኖችን አሳለፉ።
ለሆድ እንጂ ለስራ ያልደረሱ ልጆች ዕጣ ፈንታ የሚያሳስባቸው እናት ሁሌም ስለነሱ ይጨነቃሉ። የሙት ልጆች መሆናቸውና እንደሌሎች ያለማደራቸውም ከሀዘን ጥሎ ያስለቅሳቸዋል።
ለሚኖሩበት የቀበሌ ቤት የበዛ ኪራይ ያለመጠየቃቸውን ጠቀሜታ ጠንቅቀው ያውቁታል። በቤቱ ውለው የሚያድሩ ነፍሶች በችግር መፈተናቸው ግን ተጨማሪ ህመም ሆኗቸዋል።
ችግርና ጤና ማጣት የሚመላለስባቸው ወይዘሮ አንዳንዴ ከትካዜያቸው አለፍ ብለው የልጆቻቸውን ተስፋ ያስባሉ። ከዛሬ ህይወት ተሻግረውም የነገውን በጎነት ያልማሉ። ልጆቻቸው በወጉ ተምረው ታሪካቸውን እንደሚሽሩ ሲሰማቸው ፊታቸው በደስታ ይፈካል።
ደረጀ በችግር ወድቆ እየተነሳ ስድሰተኛ ክፍል ደረሰ። ይህኔ እናቱ የተስፋቸው ገሚስ ዕቅድ የተሳካ ያህል ተሰማቸው። ነገ በዛሬ ጥረት እንደሚሸነፍ ገምተውም በትንሹ ልጃቸው ተስፋ ጣሉበት።
አንድ ቀን ከመኝታቸው ማልደው የተነሱት የደረጀ እናት ፈጥነው እንደሚመለሱ ተናግረው ከቤት ወጡ። ገና በጠዋቱ መያዝ የጀመራቸው ህመም እየበረታ መሆኑ ተሰምቷቸዋል። ሁሌም ይህ አይነቱን ምልክት የለመዱት ወይዘሮ ለህመሙ ፊት መስጠትን አልፈለጉም። ራሳቸውን እየሸነገሉና ከውስጣቸው እየሞገቱ መንገዳቸውን ቀጠሉ።
ሰዓቱ እየገፋ ምሽቱ እየቀረበ ነው። እስካሁን ግን ‹‹በቶሎ እመለሳለሁ›› ያሉት እናት ብቅ አላሉም። ‹‹እመጣለሁ›› ካሉበት ጊዜ መዘግየታቸውን ያወቁት ደረጀና ታላቅ እህቱ በአይን ረሀብ መዋተት ጀምረዋል። ከአሁን አሁን የእናታቸውን ድምጽ እንደሚሰሙ ገምተውም በጉጉት እየናፈቁ ነው።
ከኮሽታውና ከእግር ኮቴው፣ ከሰዎች ጫጫታና ከሌሎቹ ድምጾች መሀል እናታቸውን ፈልገው ያጡት ልጆች ጭንቀት ጨምሯል። በእነሱ ጨክነው እንደማይቆዩ ስለሚያውቁም የደህንነታቸው ጉዳይ አሳስቧቸዋል።
አመሻሹ ላይ ድንገት በሩን ከፍተው ወደቤት የዘለቁት ጎረቤቶች አይቀሬውን እውነት ከመናገር አልተመለሱም። ገና በማለዳው ከቤት የወጡት ወይዘሮ ከመንገድ ሞተው ስለመገኘታቸው ለልጆቹ አረዱ። ድንገቴውና አስደንጋጩ መርዶም ለቤቱ ሁለተኛው ከባድ ሀዘን ሆኖ የልጆቹን አንገት አስደፋ።
አዲስ ህይወት
አስቀድሞ አባታቸውን በሞት ያጡት ልጆች በእናታቸው ድንገቴ ሞት ቅስማቸው ተሰብሯል። አሁን ተስፋ የሚደርጉት መከታ የለም። የት ናቸሁ ብሎ የሚጠይቅ እናት አባት አጥተዋል። ውሎ አድሮ ግን ለመጪው ህይወታቸው መወሰን እንዳለባቸው ቆረጡ።
ጥቂት ቆይቶ የደረጀ ታላቅ እህት ኑሯቸውን ለመደገፍ አረብ አገር ለመሄድ ያቀደቸው ሙከራ ተሳካ። ከጥቂት ጊዚያት በኋላም አገሯንና ወንድሟን ተሰናብታ ወደቤሩት አቀናች።
አሁን ትንሹ ደረጀ ብቻውን ቀርቷል። እናት አባቱን በሞት፣ ታላቅ እህቱን በስደት ካጣ ወዲህ በእጅጉ ይከፋው ጀምሯል። የሚኖርበት ቤት የቀበሌ መሆኑ ለኪራይ ባይዳርገውም ብቸኝነቱን መቋቋም እያቃተው ነው። ጅምር ትምህርቱን የመቀጠል ዕቅድ በሀሳቡ የለም። ከዚህ በኋላ ኑሮውን ለመቀጠል መስራትና ገንዘብ ማግኘት እንደሚኖርበት አስቧል።
ደረጀ ከቤት መውጣት ሲጀመር ከአካባቢው ልጆች ጋር በፍቅር ተግባባ። አብዛኞቹ ለዕድሜው የቀረቡ ናቸው። ጥቂቶቹ ደግሞ ከእሱ የሚልቁና በእጥፍ የሚበልጡት መሆናቸው ያስታውቃል። እንጀራቸው ጫኝና አውራጅነት የሆነው ልጆች ደረጀን አግባብተው የስራ አጋራቸው ለማድረግ ጊዜ አልፈጀባቸውም።
ደረጀ በዕድሜው ትንሽ መሆኑ ከሌሎች ይለየዋል። ይህን የሚያውቁ ባልንጀሮቹም ‹‹ፈላው›› ሲሉ ይጠሩታል። ፈላው ስራውን ሲጀምር እነሱ በሚሉት ልክ አቅመ ትንሽ አልሆነም። አቧሬ ገበያ መዋል ከጀመረ ወዲህ በጉልበቱ ከሌሎች የሚወዳደር ጠንካራ መሆኑን ማሳየት ጀምሯል።
ፈላውና ጓደኞቹ ሁሌም ወደገበያው ዘልቀው ሽክማቸውን የሚ,ያራግፉ መኪኖችን በሩቁ ይለያሉ። ባለንስር ዓይኖቹ ባልንጀሮች በተለይ ዕድሜ ጠገብ የውይይት ታክሲዎችን ከሌሎች ነጥሎ ለማወቅ በእጅጉ የፈጠኑ ናቸው።
መኪኖቹ በውስጣቸው የሸከፉት ቋጠሮ ከአስጫኝ ነጋዴዎች ባላነሰ ለእነሱም ጭምር ሲሳይ ሆኗል። በሸክሞቹ ልክ የሚያገኙት ክፍያ የዕለት ጉሮሯቸውን ይዘጋል። ለብዙዎቹም የወር ቀለባቸውን ሸፍኖ የጓዳ ቀዳዳቸውን ይድፍናል።
ከትንሹ ደረጀ ጋር ተባብረው የሚሰሩት ሁለቱ ወጣቶች ሁሌም ከሸክሙ የሚገኘውን ገቢ በእኩል ይወስዳሉ። በተለመደው የአሰራር ህግም የሚገኘውን ገቢ አንደኛቸው ይይዛሉ። የዕለቱ ገንዘብ ስብሳቢም ለአገልግሎቱ አስር ብር ታስቦለት ወደ ማምሻው የድርሻቸውን ይካፈላሉ።
በገበያው ያሉ ብዙዎቹ ነጋዴዎች ሶስቱን ልጆች ያውቋቸዋል። ሸቀጣቸውን አውርደው ከሱቅና ከጉልታቸው ሲያደርሱም የሚገባቸውን ሲከፍሏቸው ኖረዋል።
ነሀሴ 8 ቀን 2008 ዓ.ም
ሌሊቱን በሙሉሲዘንብ ያደረው ዝናብ ከነጋም በኋላ የበቃው አይመስልም። እንደማባራት ብሎ ዳግመኛ ሲጀምር ቅዝቃዜን ከወጨፎ አዳምሮ ያገኘውን ሁሉ እያንዘፈዘፈ ያንቀጠቅጣል። ጎርፍና ጭቃው፣ ዳመናና ብልጭታውም የነሐሴን ወር ክብደት ይመሰክራል።
ደረጀ የዛን ቀን ያረፈደው ዝናብ ከሞቀ መኝታው አላስወጣውም። ብርድና ወጨፎውን ባሰበው ጊዜ ተጠቅልሎ መተኛትን መርጦ ከአልጋው አረፈደ። እየቆየ ረሀብ ቢሰማው ግን በድንገት ተነስቶ ወደ ገበያው አቀና።
ስፍራው ሲደርስ በጠዋት ሥራ እንደነበርና ገቢ እንደተገኘ ወሬ ደረሰው። ይህን ሲያውቅ ተኝቶ በማርፈዱ ቁጭት ተሰማው። የከሰዓቱን ስራ ሲያስብ ግን ገንዘብ የመሰብሰቡ ተራ የእሱ ሊሆን እንደሚገባ ወስነ። እንዲህ ከሆነ በስራው ልክ የሚታሰብ ስለሚኖር የተቆጨበትን ገንዘብ እንደሚያካክሰው ገምቶ ፈገግ አለ።
ከቀኑ 7፡00 ሰዓት ከ30
በዚህ ሰዓት አንዳንድ ነጋዴዎች በመኪና ያስጫኑትን ሸቀጥ በገበያው አድርሰው ያራግፋሉ። እንዲህ በሆነ ጊዜም ፈላውን ጨምሮ ሌሎች ጓደኞቹ ከመኪናው ሸክሙን አውርደው የሚገባቸውን ክፍያ ይቀበላሉ። በዕለቱ የሆነውም እንዲሁ ነበር።
ድንገት አንድ ፒክ አፕ መኪና በማዳበሪያዎች የተሞላ ሸቀጥ ይዞ በገበያው መሀል ብቅ አለ። ሌሎች መኪኖችም ጡሩንባ እያሰሙ ደረሱ። ይህን ያስተዋሉት ፈላውና ጓደኞቹ ከመኪናው እኩል እየፈጠኑ የተጫነውን ለማራገፍ ተጣደፉ። መኪናው ሽክሙን አቃሎ እንደጨረሰ ወጣቶቹ የሚገባቸውን ሊቀበሉ ተሰበሰቡ።
በዚህ መሀል ፈላው አስቀድሞ ያሰበውን ዕቅድ አስታወሰ። እሱ በጠዋቱ ስራ ስላልነበረ የአሁኑን ገንዘብ ሰብስቦ የተለመደውን አስር ብር መውሰድ እንዳለበት ለጓደኞቹ አሳወቀ። ከነሱ መሀል ቢኒያም የተባለው ጓደኛቸው የፈላውን ሀሳብ ተቃወመ። ገንዘቡን የመሰብሰብ ተራው የእሱ መሆኑን ተናግሮም በቁጣ አፈጠጠ።
ፈላው የቢኒያምን ውሳኔ ሲሰማ ንዴት ቀደመው። ሀሳቡን ለማስቀየር ያደረገው ሙከራ እንዳልተሳካ ሲያውቅም ለጠብ ተጋበዘ። ሁኔታቸውን ያዩ ባልንጀሮቻቸው ጭቅጭቁን አስቁመው ጠቡን ለማብረድ ከመሀል ገቡ። ይሄኔ ፈላው ቢኒያምን ለብቻው ሊያወራው እንደሚፈልግ ነገረው። ቢኒያም ግን ‹‹ወንድ ልጅ ወሬ አያወራም ዝም በል! ›› ሲል ተሳለቀበት።
በቢኒያም ምላሽ የበሸቀው ፈላው ሳያስበው አንድ ጠንካራ ቡጢ ፊቱ ላይ አሳረፈበት። ቢኒያም ለምላሹ ሲዘጋጅ ግራ አይኑ ላይ ከባድ ህመም ተሰማውና ሰማይና ምድሩ የዞረበት መሰለው። ከግልግሉ በኋላ በንዴት በግኖ እየጮኸ በሩጫ ወደቤቱ ተጣደፈ።
የቢኒያም ቤት ለገበያው ቅርብ ነው። ሲጣደፍ የደረሰው ወጣትም ቤቱ ገብቶ ያሰበውን ለማድረግ ያባከነው ጊዜ አልነበረም። በሹራቡ እጅጌ የሸሸገውን ቢላዋ እንደያዘ ወደገበያው ሲመለስ በአጭር ጊዜ ሆነ።
ከሁለቱ ልጆች ድብድብ በኋላ ወደስራ የተሰማሩት ጓደኛሞቹ ፍራሽ ጭኖ የመጣውን መኪና ከበው ማውረድ ጀምረዋል። ሁሉም ትኩረታቸውን ስራው ላይ አድርገው እየተጣደፉ ነው። በድንገት የቢኒያም ስል ቢላዋ ከፈላው አካል ተሰክቶ ከመሬት ሲዘረር ግን ሁኔታዎች ተለወጡ።
ፈላው ከሆዱ የተሳካውን ቢላዋ ለማውጣትና ቢኒያምን ለመያዝ በደመነፍስ ታገለው። ቢኒያም ይህን ሲያይ ቢላዋውን ከሆዱ አውጥቶ ከደረቱ አሳረፈው። አካባቢው በደም ተበክሎ ጩኽቱ ሲበረክትም ግርግሩን ተጠቅሞ አመለጠ።
ባልንጀሮቹ ክፉኛ የተጎዳውን ፈላውን አንስተውና መኪና ለምነው ሆስፒታል አደረሱ። ያሰቡት አልሆነም። ጓደኛቸው ሆስፒታል ደጃፍ እንደደረሰ ትንፋሹ ተቋረጠ። ቢኒያም ቤት እንደደረሰ የሰራው ሁሉ አስጨነቀው። በአስር ብር መዘዝ በአብሮ አደግ ጓደኛው ላይ ስለት መምዘዙ ከጸጸት ጣለው። ስምንት ሰዓት ሲሆን አላስቻለውም። ስልኩን አንሰቶ ስለጓደኛው ጠየቀ። መሞቱ ተነገረው።
የፖሊስ ምርመራ
የወንጀሉን መፈጸም ሰምቶ ከስፍራው የደረሰው ፖሊስ መረጃ አሰባስቦና አማኞችን ለይቶ ተመለሰ። ድርጊቱን ፈጽሟል የተባለውን ተጠርጣሪ ለመያዝም ተንቀሳቀሰ። ፍለጋውን ከመቀጠሉ በፊት ግን ተጥርጣሪው ሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ ደርሶ እጁን ለህግ እንደሰጠ መረጃ ደረሰው።
አሁን ፖሊስ ተጠርጣሪውን ለክስ የሚያበቃ መረጃን በበቂ ማስረጃዎች ሰንዶ አጠናቋል። ክሱን ለዓቃቤ ህግ አሳልፎም ፍትህ እንዲበየንበት አመቻችቷል። በረዳት ሳጂን ግሩም ታረቀኝ መርማሪነት የተጠናቀቀው ምርመራ በፖሊስ መዝገብ ቁጥር 097/07 በተከፈተ ፋይል ተመዝግቦ ለፍርድ ቤት ውሳኔ ተዘጋጅቷል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጳጉሜ 2/2011
መልካምስራ አፈወርቅ