ከተሜነት ከገጠር ወደ ከተማ ቀመስ ቦታዎች ነዋሪነት በሚደረግ ፍልሰት የሚፈጠር የሕዝብ ቁጥር መለወጥ ወይም በከተሞች አካባቢ የሚኖሩና የተወለዱ ሰዎች ቁጥር ቀስ በቀስ የመጨመር ሂደት የሚከሰት አዲስ የማንነት ለውጥ ሲሆን፤ ከዚህ የስነህዝብ/ዲሞግራፊክ/ ስሪት ጋር ተያይዞ እያንዳንዱ የከተማ ነዋሪ ማኅበረሰብ ከዚህ ለውጥ ጋር የሚጣጣምበትን የሃሳብ ዘይቤ የሚያበጅበት መራሄ ፍኖት ነው።
የባህለ ብዙ ማህበረሰብ አስተምህሮ እንደሚ ሳየው፤ ከተሜነት የራሱ ቀለም አለው። የተለያየ ማኅበረሰባዊ ማንነት ቀልጦ እንደ አዲስ የሚሰራበት የማንነት ማቅለጫ ገንቦ-(Melting Pot) ነው። በመሆኑም ከተሜነት የሰው ልጅ የማደግ፣ የመረዳዳት፣ የመወያየት ሰብዓዊ ግብር መገለጫ ነው ማለት ይቻላል። በአብዛኛው ከተሞች የሚመሰረቱትና የሚያድጉት የተለያየ ማንነት ያላቸው እጅግ በርካታ ሰዎች ለመኖር በሚያደርጉት ትግል በሚፈጠር እንቅስቃሴ እና በአማካይ ውስን ቦታዎች ላይ ለኑሮ መደጎሚያነት በመሥራታቸው ነው። ከተማ ከሌላው የአገር አካባቢ የሚለይበት አንዱ መገለጫው ደግሞ አካታችነቱና ማህበራዊ መስተጋብሩ ነው።
በኢትዮጵያዋ ድሬዳዋ ከተማ አመሰራረቷን ስናይ አዲስ በነበረው የባቡር መስመር ዝርጋታ ጋር በተገናኘ የበርካታ ውጭ ሀገራት ዜጎች መነሀሪያ ነበረችና እንደስልጣኔ መግቢያ መር ትቆጠራለች። ከአገር ውስጥም ቢሆን ከየአራቱም ማዕዘናት የተሻለ ሕይወት በመሻት፤ ጥበብና ዕውቀት ፍለጋ የመጡ፤ ለንግድና ለጥቅም የተሰባሰቡ፤ በተለያየ ደረጃ ባለ በመንግሥታዊና መንግስታዊ ያልሆነ መዋቅር ሚና ያላቸው ዜጎች በርካታ ናቸው። የፈጠሯቸዉ የጋራ ሥልጣኔ ዕሴቶችን ከማስቀጠል ባሻገር ይህንኑ የፍልስፍና አኗኗር የሚመጥን የኢኮኖሚ ብልጽግና ባለቤት መሆንም ይሻሉ።
ማህበረሰቦቿ ሁሌም በከተማው መኖራቸውን እንደመልካም አጋጣሚ ይቆጥሩታል። ሁሉም ማንነታቸውን ረስተው በሚኖሩበት ማኅበረሰብ መስተጋብር ተውጠዋል። በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር፤ ይህ አይነቱ ሁነት በተለይ እንደ ሌሎች የአገሪቷ ከተሞች የብዙዎች ታሪክ አንድ አካል ለመሆን ከሚመነጭ ፍላጎት ብዙ የኢኮኖሚ ጥያቄዎች ሲስተናገዱ ቆይተዋል። የዝግጅት ክፍላችንም ድሬዳዋ የከተማ አስተዳር እንደመሆኗ መጠን ከሌሎች አቻ ከተሞች ጋር በኢኮኖሚዋ ያለችበት ደረጃ ምን ይመስላል? ምንስ ታስቧል? ሲል ተከታዩን ዳስሷል።
በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የፕላንና ኢኮኖሚ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ ተሰማ እንደሚሉት፤ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በተለይ ከቻርተሩ ወዲህ በርካታ ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና የመሰረተ ልማት ሥራዎች እየተሰሩባት የምትገኝ ከተማ ናት። ከተማዋ ራሷን ማስተዳደር ከጀመረችበት ጊዜ እስካሁን ድረስ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑባት ቢሆንም፤ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከሌሎች አቻ ከተሞች አንጻር ስትታይ እድገቷ በሚፈለገው ልክ አይደለም። ይህ ማለት ግን እድገት የለም ማለት ሳይሆን ማህበረሰቡ ከሚፈልገውና መድረስ ከሚገባው አንጻር ሲመዘን አናሳ መሆኑ ነው።
የከተማዋ የኢኮኖሚ ብልጽግና ቀጭጯል የሚሉት ኃላፊው፤ ለዚህም በርካታ ምክንያቶች ሊጠቀሱ እንደሚችሉ አስታውቀዋል። “ከተሞች በኢኮኖሚ እንዲበለጽጉ ሲፈለግ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ ይጠይቃሉ። የፋይናንስ ፍላጎቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣ ነው። ወጭም በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል። የመንገድ፤ የውሀና የቤት ግንባታ መሠረተ ልማቶችን ለማሟላት የፋይናንስ እጥረቱ ከተማዋን እየተገዳደረ ይገኛል” ይላሉ፤ የእድገቱን ተግዳሮት ሲጠቁሙ፤
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ ከማስፈጸም አቅም ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮች ሌላኛው የከተማዋ ኢኮኖሚያዊ እድገት ፈተና ነው። የሚያንስ ቢሆንም የሚገኘውን ፋይናንስ በአግባቡ ሥራ ላይ ከማዋል አንጻር ክፍተቶች አሉ። ፕሮጀክቶች ተጀምረው በተቀመጠላቸው ጊዜ አይጠናቀቁም። ወደ አገልግሎት በመግባት የማህበረሰቡን ችግር በመፍታትና የከተማዋን ተወዳዳሪነት ሊያሳድጉ በሚችሉ ደረጃ ላይ አይደሉም። እነዚህ ምክንያቶች ተደምረው ነው የከተማዋ ኢኮኖሚ በሚፈለገው ደረጃ እንዳይደረስ ያደረጉት። ይህም በማህበረሰቡ ውስጥ ቅሬታ ፈጥሯል።
የከተማዋን ዕድገትና ብልጽግና ከፍ ለማድረግ ጠንካራ የሚባል የትኩረት አቅጣጫ መቀመጡን የሚያወሱት ኃላፊው፤ ድሬዳዋን አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ፤ ማህበረሰቡ የሚፈልገውን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በርካታ ፕሮጀክቶች መነደፋቸውን፤ ከአጠቃላይ የኢኮኖሚ ብልጽግና እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ በፌዴራል መንግስቱ ትብብር ጭምር በመሠረተ ልማትና በማህበራዊ ዕድገት ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታሳቢ መደረጉን፤ በተለይ በመሰረተ ልማት ረገድ ድሬዳዋ በምስራቅ ኢትዮጵያ የንግድ ኢንዱስትሪ አገልግሎት ማዕከል ሆና እንድትወጣ ለማድረግ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም ከጋዜጣው ዝግጅት ክፍል ጋር በነበራቸው ቆይታ ጠቁመዋል።
“የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ችግር ሊቀርፉ ከሚችሉት ውስጥም አንደኛው የኢንዱስትሪ ፓርክ ነው። የኢንዱስትሪ ፓርኩ ግንባታው ተጠናቅቋል። ወደ አገልግሎት እንዲገባም ግፊት እየተደረገ ነው። ማህበረሰቡ ‘ምንም ጠብ ያለልኝ ነገር የለም’ ብሎ የሚያነሳው ቅሬታ ከሚፈታባቸው መንገዶችም አንዱ ይህ የኢንዱስትሪ ፓርክ ነው። ግንባታው በሂደቱም ቢሆን የስራ ዕድልን መፍጠር ችሏል። ከዚህ በተሻለ ደግሞ ወደ አገልግሎት ሲገባ በተለይ ለበርካታ ሰዎች የሥራ ዕድል በመፍጠር የማህበረሰቡን ፍላጎት ከሞላ ጎደል ማሟላት ይቻላል” ብለዋል። ኃላፊው መጻኢውን የከተማዋን ዕድል ሲገልጹ፤
ሁለተኛው አሳታፊ ፕሮጀክት ከመሠረተ ልማት ጋር ተያይዞ የሚነሳው በዚህ ዓመት ተገንብቶ የተጠናቀቀው የድሬዳዋ- ደወሌ- ጂቡቲ የፍጥነት መንገድ ሲሆን፤ ይህ ድሬዳዋን ከጅቡቲ ጋር የሚያገናኝ ፈጣን መንገድ የኢኮኖሚ እድገቱን ከማፋጠን ጋር በተያያዘ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም አስታውቋል።
ኃላፊው አክለውም፤ “ተሰርቶ የተጠናቀቀው የድሬዳዋ ደረቅ ወደብ፤ በከተማዋ ውስጥ የሚካሄዱ አዳዲስ የመንገድ ግንባታዎች፤ የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታዎች ለማህበረሰቡ አገልግሎት ትልቅ ፋይዳ ይኖራቸዋል ተብሎ ይታሰባል። በቂ ባይባልም 358 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታም ስራው በግማሽ ተጠናቅቋል። በዚህ ዓመትም ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃሉ። ከዚህ ቀደም፤ ሥራዎቹ ይከናወኑ የነበረው ከባንክ በሚገኝ ብድርና በቦንድ ግዥ ሲሆን፤ አሁን ላይ በከተማ አስተዳደሩ በጀት አማካኝነት ነው” ብለዋል።
የአገልግሎት አሰጣጥን ሊያሳድጉ የሚችሉ ወደ 700 ሚሊዮን ብር ገደማ በጀት የተመደበላቸው ትላልቅ አዳራሾችና የሲቪክ ማዕከል በግንባታ ላይ ናቸው። በ900 ሚሊየን ብር የተሠራው የድሬዳዋ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክትም እንዲሁ በዚህ ዓመት ተጠናቅቋል። ፍላጎቱ እያደገ ስለመጣ ከተማ አስተዳደሩ ተጨማሪ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን ለመስራት በዝግጅት ላይ ነው። ይህም ከመጠጥ ውሃ ጋር ተያይዞ ይነሱ የነበሩ ቅሬታዎችን ይፈታል ብለው እንደሚያምኑ አቶ ግርማ ገልጸዋል።
መሠረተ ልማቶቹ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ የሚያግዙ በመሆናቸው፤ በተለይ በ2012 ዓ.ም ተወዳዳሪነትን ሊያሳድጉ የሚችሉ ፕሮጀክቶችን ሥራ በማስጀመርና ማህበራዊ አገልግሎትን በማስፋፋት 20 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጠር ጠቁመዋል። ከዚህም ውስጥ 18 ሺህ ዜጎች ቋሚ የስራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ መታቀዱን የተናገሩት ኃላፊው፤ ለዚህ ሥራ የሚያግዙ ቅንጅታዊ አሰራሮች በገጠርም ሆነ በከተማ በተጠናከረ ሁኔታ እየተሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
አዳም ረታ በስንብት ቀለማት መጽሐፉ መግቢያ ላይ “ማንኛዋም ከተማ የሠው ልጅ የሥራ ውጤት ናት (እንስት ብትሆን)። ፈጣሪ እንደ ተራራ፣ እንደ ወንዝ፣ እንደ ሎሚና እንደ ሰላጣ፣ እንደ እግሮቻችን፣ እንደ ጡት ባንዴ አልሰራትም” ይላል። በመሆኑም የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልም ከተማ የሠው ልጅ በዘመናት ሂደት የሚያበጃት የክሱት ግብሩ ውጤት ብቻ ሳትሆን የድብቅ ነፍሱ የሃርነት ንቅናቄ ዓርማ መሆኗን በማስገንዘብ በድሬዳዋ ኢኮኖሚውን ሊያበለጽግ ያለመው ተግባር እውን እንዲሆን፤ የማህበረሰቡም የሕልሙ ማኅተም መድመቂያ ጌጡ የሆነችዋን ከተማ ሁሉን አቀፍ ተጠቃሚ ትሆን ዘንድ፤ የሥራ ፈጠራ አስተሳሰብ ብልጽግናም ይዳብር ዘንድ መልካም ምኞቱን ይገልጻል።
አዲስ ዘመን ጳጉሜ 1/2011
አዲሱ ገረመው