በ2011 ዓ.ም የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ተከትሎ የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚፈታተኑ በርካታ ጉዳዮች ሲከሰቱ ተስተውሏል፡፡ መንግስት የተረጋጋ ኢኮኖሚ በሀገሪቱ እንዲሰፍን ለማድረግም ውስጣዊ ማስተካከያዎችንና ውጫዊ የአቅም ማጎል በቻ ስምምነቶችን ሲያደርግ ቆይቷል። በዚህም መሰረት በበጀት ዓመቱ ከተፈጸሙት አንኳር የኢኮኖሚ ክንውኖች ውስጥ ዋና ዋናዎቹን እንደሚከተለው ለመዳሰስ ተሞክሯል፡፡
የወጪ ንግድ
የሀገሪቱ የውጭ ንግድ በ135 ነጥብ 82 ሚሊዮን ዶላር መቀነሱን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያሳወቀውም በዚሁ ዓመት ነው፡፡ በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት የውጭ ንግድ ዕቅድ አፈጻጸም ካለፈው ተመሳሳይ ዓመት ጋር ሲነጻጸር ከላይ የተጠቀሰውን ልዩነት እንዳሳየ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አሳውቋል፡፡
የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ባስጠናው ጥናት መሰረት የወጭ ንግዱ በጥቂት ነጋዴዎች እጅ መውደቁ ተረጋግጧል፡፡ ለዚህም በርካታ ምክንያቶችና መፍትሄዎችን አስቀምጦ አልፏል፡፡ በሀገሪቱ በወጪ ንግድ በአቅራቢነትና በነጋዴነት የሚሳተፉት ጥቂቶች ብቻ መሆናቸውም የዓመቱ ትልቅ ችግር ተደርጐ ይነሳል፡፡ ይህም የጥቂት ነጋዴዎችን ተጠቃሚነት አጉልቶታል፡፡ ከአምራች እስከ ሸማቹ፣ ከአስመጪው እስከ ተጠቃሚው ድረስ ባለው የህገወጥ ደላሎች ጣልቃ ገብነት የሸቀጦችን ዋጋ በመወሰን ጥቂት ነጋዴዎች እንዲከብሩ ዕድል መፍጠሩ በጥናቱ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲስተዋል ቆይቷል፡፡
ገቢና ኮንትሮባንድ
የገቢዎች ሚኒስቴር በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት 122 ነጥብ 18 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 98 ነጥብ 96 ቢሊየን ብር መሰብሰቡ ተዘግቧል፡፡ በተያያዘም 509 ሚሊየን ብር የሚያወጡ እቃዎችንም በኮንትሮባንድ ሊገቡና ሊወጡ ሲሉ በቁጥጥር ስር ማዋሉም ተሰምቷል፡፡
በመጀመሪያውም ሆነ በሁለተኛው እቅድና ትራንስፎርሜሽን ሊሰሩ የታቀዱ ታላላቅ ፕሮጀክቶች የመንግስትን የአፈጻጸም ችግር ያመላከቱ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ በ2011 በወርሀ ጥቅምት ከእነዚህም ታላላቅ ፕሮጀክቶች ውስጥ አንዱ የሆነው የኦሞ ኩራዝ ቁጥር ሶስት ስኳር ፋብሪካ ተመርቆ ስራ እንዲጀምር ተደርጓል፡፡
በፕሮጀክቶች መዘግየት መንግስት ለ43 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ወጪ መዳረጉም በዚህ ባለቀው ዓመት ከተገለጹ አንኳር የኢኮኖሚ ጉዳዮች አንዱ ነበር፡፡ ባለፉት አሥር ዓመታት በሜጋ ፕሮጀክቶች መዘግየት መንግስት ይህን ያህል ብር ማውጣቱ እንደትልቅ ክስረት ታይቷል፡፡ ከዚህ በኋላ በፕሮጀክቶች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ በታቀደው ጊዜ እንዲጠናቀቁ እንደሚደረግም በ2012 ዓ.ም እቅድ ተይዟል፡፡
የገቢዎች ሚኒስትር ህግ የማስከበር ሥራውን አጠናክሮ በማስቀጠል በታክስ ማጭበርበርና ስወራ የተሰማሩ 135 ድርጅቶችን በመለየት እርምጃ መውሰዱ ይታወሳል በታክስ ማጭበርበርና ስወራም 14 ቢሊየን ብር ገቢ ሳይሆን መቅረቱ ተደርሶበታል፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ በከባድ የሙስና ወንጀል ድርጊት ተጠርጥረው ክስ ከተመሰረተባቸው ተከሳሾች ላይ ያለ አግባብ የተዘረፈ ከ95 ሚሊየን ብር በላይ ወደ መንግስት ካዝና እንዲመለስ ማድረጉም ተዘግቧል፡፡
የኢትዮ ጂቡቲ ምድር ባቡር ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል 54 ሚሊየን ብር ገቢ ማግኘቱን ያሳወቀ ሲሆን ከወር በፊት ገጥሞት በነበረው መጠነኛ አደጋ 10 ሚሊየን የሚገመት ንብረት መክሰሩን ማሳወቁ ይታወሳል፡፡
የኑሮ ውድነት
በ2011 እየተባባሰ የመጣውና ዛሬ ድረስ እልባት ካላገኙ ጉዳዮች አንዱ የኑሮ ውድነት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ገበያ በየጊዜው ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪን እያስተናገደ በመሄዱ በየጊዜው የህዝብ ቅሬታዎች ሲንጸባረቁ ተሰምቷል፡፡ አዲስ ዘመን ጋዜጣ በኑሮ ውድነቱ ምክንያት የተማረሩ ሰዎችን አስተያየት በተደጋጋሚ ሲያስነብብ ከርሟል፡፡ በዓመቱ መጨረሻም የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ባስጠናው ጥናት ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ የዋጋ ጭማሪ እየተደረገ መሆኑን አመላክቷል፡፡ በህገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ እንደተዘጋጀም በዓመቱ መጨረሻ ተመልክቷል፡፡
ኢትዮጵያ በተያዘው ዓመት መጨረሻ በ11 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር የስንዴ ምርት ከውጭ ገበያ በመግዛት ወደ ሀገር ውስጥ እያስገባች እንዳለች ተገልጿል። ስንዴው በተለይም ለተፈናቀሉ ሰዎች እርዳታና ገበያውን ለማረጋጋት የሚውል እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የኤሌክትሪክ ታሪፍ
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አዲስ የታሪፍ ማስተካከያ ያደረገውም በዚሁ በተጠናቀቀው ዓመት ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ለኤሌክትሪክ አገልግሎት ጥቅም ላይ የሚውሉ ግብዓቶች ከ60 እስከ 70 በመቶ በውጭ ምንዛሬ የሚገቡ በመሆኑና ከብር የመግዛት አቅም ጋር ሲነጻጸር አዋጭ ባለመሆኑ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ላለፉት 12 ዓመታት በነበረው ታሪፍ መቀጠሉ አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ አዳጋች ያደርገዋል የሚል ስጋትም ተነስቷል፡፡
ኢኮኖሚያዊ ትስስር
በሌላ በኩል 20ኛው የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በአዲስ አበባ ባደረጉት ስብሰባ የአህጉሪቱን ኢኮኖሚያዊ ትስስርና የህዝቦቿን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አኳያ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚያስፈልግ መክረዋል፡፡ በውይይቱም የአፍሪካን ዕድገትና ሁለንተናዊ ተወዳዳሪነትን የማሳደግ ሃላፊነት የአፍሪካዊያን የራሳቸው መሆኑ የተመከረበት ዓመት ሆኖ ተጠናቋል፡፡
የቡድን 20 አባል ሀገራት በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዲሰማሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ጥሪ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጀርመን በተካሄደው የቡድን 20 አባል ሀገራት ‹‹ኮምፓክት ዊዝ አፍሪካ›› ኢንቨስትመንት ፎረም ላይ ነበር ይህን መልዕክት ያስተላለፉት፡፡
እየተጠናቀቀ ባለው 2011 ዓ.ም ኢትዮጵያና ኤርትራ የየብስ ትራንስፖርት ለመክፈት እንቅስቃሴ ማድረጋቸው ተሰምቷል፡፡ መንገዱ የሁለቱን ሀገር ህዝቦች ከማቀራረብ ባሻገር ከፍተኛ የሆነ ምጣኔ ሀብታዊ ፋይዳ ይኖረዋል ተብሏል፡፡ የኢትዮጵያን ቀጠናዊ ትስስር የገቢና ወጪ ንግድ በማሳለጥ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን እንደሚያሳድግ ተገም ቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ በኢጣሊያ ባደረጉት የስራ ጉብኝትም ከኢጣሊያኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ ጋር በነበራቸው ቆይታ የኢጣሊያን መንግስት ምጽዋንና አዲስ አበባን በባቡር መንገድ ለማስተሳሰር የመጀመሪያውን ጥናት ሙሉ ወጪ ሸፍኖ ለማስጠናት ቃል የገቡበት ዓመት ነው፡፡
አየር መንገዳችን…
በ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ኩራት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያልተጠበቀ አደጋ አስተናግዷል፡፡ ከመነሻው አዲስ አበባ ብዙ ርቀት ሳይበር በአውሮፕላኑ የቴክኖሎጂ ችግር ሳቢያ ወድቆ በመከስከሱ የደንበኞች ሕይወት ተቀጥፏል፡፡ በዚህ ምክንያትም ውዝግብ ተነስቶ በመጨረሻም የቦይንግ ኩባንያ ችግሩ ከራሱ መሆኑን በማመን ይቅርታ የጠየቀበት ዓመትም ነበር፡፡
ስመ ጥሩ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያን ማስፋፊያና የኢትዮጵያ ስካይ ላይት ባለ አምስት ኮከብ ሆቴልን አስመርቋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር አየር መንገዱ ሀገሪቱን ወደ ተሻለ ደረጃ የማሸጋገር ሃላፊነት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ማስፋፊያው 363 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር እንደፈጀና ባለአምስት ኮከብ ደረጃ ሆቴሉም 65 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር እንደወጣበት ተገልጿል፡፡
የግብዓት ግዥ
ለግብዓት ግዢ የሚወጣውን 160 ቢሊየን ብር ለማስቀረት ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢኒስቲትዩት ያሳወቀው በዚህ ባለቀው ዓመት ውስጥ ነው፡፡ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በየጊዜው እየዘመነ መምጣቱን ተከትሎ የግብዓት ግዢው በተመሳሳይ እያሻቀበ ነው፡፡ ወጪውን ለመቀነስ ከዩኒቨርሲቲ የምርምር ማዕከላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑ በዓመቱ ተመልክቷል፡፡
የተፈጥሮ ጋዝ
ኢትዮጵያ ከሦስት ዓመት በኋላ የተፈጥሮ ጋዝ ወደ ውጭ መላክ ልትጀምር የሚያስችላትን እንቅስቃሴ እያደረገች መሆኑም በዓመቱ ከተነገሩ አንኳር የኢኮኖሚ ዜናዎች አንዱ ነበር፡፡ በሶማሌ ክልል የተገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ የሚያለማው የቻይና ኩባንያ ሲሆን ጋዙን ከኢትዮጵያ ወደ ጁቡቲ የሚያጓጉዝ ቱቦ በመዘርጋት ላይ መሆኑም ተስተናግዷል፡፡ ጋዙ በዓመት እስከ አንድ ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር እንደሚያስገኝም አሳውቋል ፡፡
የኦዲት ግኝት
ባለፉት ስምንት ዓመታት በመንግስት ተቋማት የባከነው ገንዘብ 3 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር መሆኑ የተገለፀበት ወቅት ነበር፡፡ ለመንግስት ተመላሽ መሆን ያለበትን የኦዲት ግኝት በተመለከተም ገንዘቡ ተመላሽ እንዲሆን ዋና ኦዲተር ከጠቅላይ አቃቤ ህግ እና ከፓርላማው ጋር በትብብር እንደሚሰራ ተመልክቷል።
የድጎማ ቀመር
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለታዳጊ ክልሎች ይሰጣቸው ከነበረው ድጎማ በነፍስ ወከፍ የሚደርሳቸው መጠን በአንጻራዊነት በዕድገት ደረጃቸውና በህዝብ ብዛታቸው ከፍ ካሉት ክልሎች ጋር ሲነጻጸር ከአስር እጥፍ ወደ አራት እጥፍ መቀነሱ ተገልጿል፡፡ አዲስ የድጎማ ቀመር በቀጣይ ዓመት ሥራ ላይ እንደሚውልም ተገልጿል፡፡
የ2012 ዓ.ም በጀት 386 ነጥብ 95 ቢሊየን ብር ሆኖ መጽደቁም ከአብይ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ነበር፡፡ ከጸደቀው በጀት ውስጥ ለፌዴራል መንግስት መደበኛ ወጪ 109 ነጥብ 46 ቢሊየን ብር ፣ ለካፒታል ወጪ 130 ነጥብ 71 ቢሊየን ብር፣ ለክልሎች ድጋፍ 140 ነጥብ 77 ቢሊየን ብር እንዲሁም ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ስድስት ቢሊየን ብር ሆኖ መደልደሉ ይታወሳል፡፡
የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ
ሀገር በቀል የምጣኔ ሀብት ማሻሻያው የተዛባውን የማክሮ ኢኮኖሚ ለማስተካከል ዜጎችን እኩል ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚረዳ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በዓመቱ ማብቂያ አካባቢ አሳውቀዋል፡፡ የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የሸቀጦች የወጪ ንግድ ደካማ አፈጻጸም፣ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረትና የመንግስት ገቢ የመሰብሰብ ችግር የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው እንዲዳከም ማድረጉን በመግለጽ የማሻሻያ እርምጃዎች ሲወሰዱ እንደነበርም አመላክተዋል፡፡
በአጠቃላይ በዓመቱ ውስጥ እነዚህና ሌሎች ያልተጠቀሱ አበይት ኢኮኖሚያዊ ተግባራት የተፈጸሙ ሲሆን መንግሥት ፈተና የበዛበትን የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማከም ዘርፈ ብዙ ተግባራትን አድርጓል፡፡ በዚህም የሸቀጦች ዋጋ ንረት፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እና መዋቅራዊ ሽግግር የሚዛን የደፉ መሰናክሎች ናቸው። እነዚህን ችግሮች በመፍታት ወደ ተሻለ ደረጃ መሸጋገር እንድትችል የምጣኔ ሀብት ማሻሻያው ተስፋ ተጥሎበታል፡፡
አዲስ ዘመን ነሐሴ 30/2011
ኢያሱ መሰለ