
የአንድን ማህበረሰብ ባህል፣ ወግ፣ ልማድ እንዲሁም ኃይማኖታዊና ባህላዊ ክዋኔዎችን ለማስተዋወቅ ከሚጠቅሙ መንገዶች አንዱ ነው፡፡ የማህበረሰብ ሬዲዮ። እያስገኘ ያለው ፋይዳ ግን ዝቅተኛ መሆኑን በዘርፉ የሚንቀሳቀሱ አካላት ይጠቁማሉ፡፡ ቀጣይነቱ እንደ ሚያሳስባቸውም ነው እነዚህ ወገኖች የሚጠቁሙት።
የኮምቦልቻና አካባቢዋ ማህበረሰብ ሬዲዮ ሥራውን የጀመረው በ 2000 ዓ.ም ነው። ሬዲዮው በተለያዩ ችግሮች ውስጥ የሚገኝ መሆኑን ሥራ አስኪያጇ ወይዘሮ እጅጋየሁ አመሃ ይጠቁማሉ፤ የተቋቋመለትን ዓላማ ከግብ ለማድረስ መቸገሩንም ያመለክታሉ፡፡
ወይዘሮ እጅጋየሁ ሬዲዮ ጣቢያው የማህበረሰቡን ባህል፣ ወግ፣ አኗኗር እንዲሁም ሁለንተናዊ ማህበራዊ ህፀፆችን እየነቀሰ ለማውጣት የተቋቋመ መሆኑን ጠቅሰው፣ አሁን እየገጠሙት ያሉት ችግሮች ቀጣይነቱ ላይ ከፍተኛ ሥጋት ማሳደራቸውን ይጠቁማሉ፡፡
እንደ ሥራ አስኪያጇ ገለፃ፤ ሬዲዮ ጣቢያው ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ በበጎ ፈቃደኛ ጋዜጠኞች ሲሠራ ቆይቷል፡፡ አሁን ሦሰት ሰዎች በቅጥር ቢገኙም ደመወዛቸውን ለመክፈል በጀት የሚገኘው ከተለያዩ ስፖንሰር አድራጊዎች እንዲሁም ማስታወቂያ እንዲነገርላቸው ከሚፈልጉ አካላት መሆኑ ቀጣይነቱ ላይ ሥጋት አሳድሯል።
የተመሰረቱት ማህበረሰቡ ሬዲዮ ያስፈልገዋል በሚል መሆኑን ተናግረው፣ ቋሚ ገቢ ማጣት ሬዲዮ ጣቢያዎቹ ቀጣይነታቸውን እንዳያረጋግጡ እያደረገ ነው ይላሉ፡፡ በዓመት ከመንግሥት የተወሰነ በጀት ማግኘት እንዳልቻሉ ጠቅሰው፣ በዚህም ምክንያት መሣሪያዎች በሚበላሹበት ወቅት እንዲሁም ተወዳዳሪ ሆኖ ባለሙያን ለመቅጠር እንዳልተቻለም ነው ያብራሩት። በዚህም ሳቢያ ሚዲያዎቹ ከፍተኛ ችግር እንዳጋጠማቸው ይናገራሉ።
እነዚህ ሬዲዮ ጣቢያዎች ከሁሉም መገናኛ ብዙኃን በተሻለ መልኩ ታች ያለውን የህብረተሰብ ክፍል የሚደርሱ፣ በሚገባው ቋንቋ መልዕክት የሚያስተላለፉ በአጠቃላይ የመንግሥትን ዕቅድ የሚያስፈጽሙ መሆናቸውን አብራርተው፣ ከበጉ ፈቃደኞች በሚገኘው ገቢ ለሚገዟቸው መሣሪያዎች የሚጠየቁት ቀረጥ ችግር መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ የሚመለከተው አካል ባሉበት ክልል ድጎማን እንዲያገኙ ማደረግ እንዳለበትም ያስገነዝባሉ፡፡
እንደ ሥራ አስኪያጇ ገለፃ፤ ችግሮቹ ከተፈቱና በሁለት እግራቸው እንዲቆሙ ማድረግ ከተቻለ ሬዲዮ ጣቢያዎቹ ማህበረሰቡ ውስጥ በመሆናቸው ለአገር ልማትም፣ ለህዝቦች አንድነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላሉ። በመሆኑም ችግሮቻቸው እንዲፈቱ መንግሥትም ማህበረሰቡም ርብርብ ማድረግ አለባቸው።
የአርጎባ ማህበረሰብ ሬዲዮ ሥራ እስኪያጅ አቶ እስማኤል ቶሃ እንደሚሉት፤ ሬዲዮ ጣቢያው ሥራ የጀመረው ከ2002 ዓ.ም አንስቶ ነው፤ በእነዚህ ጊዜያትም በአርጎቢኛ፣ በአፋርኛና አማርኛ ቋንቋዎች የህዝቡን ባህል፣ አኗኗር የሚያሳዩ እንዲሁም የሚያነሷቸውን የመልካም አስተዳደርና ተዛማጅ ጉዳዮች የሚዳስሱ ፕሮግራሞችን አቅርቧ።
የወረዳው መስተዳደር የሚዲያውን ሠራተኞች ደመወዝና ጥቃቅን ወጪዎች እንደሚሸፍን ጠቅሰው፣ ትልልቅ መሣሪያዎች በሚያስፈልጉበት ወቅት ግን ለተለያዩ ተቋማት የስፖንሰር ጥያቄ በማቅረብ እንዲሟላ ለማድረግ እንደሚሠራም ይናገራሉ፡፡
‹‹ይህ አካሄድ ብዙ የማይጠቅምና ጣቢያውንም ረጅም ርቀት የማያስኬድ ነው›› የሚሉት ሥራ አስኪያጁ፣ ቢያንስ ትልልቅ ዕቃዎችን ለመግዛት የሚያስችል ድጋፍ መገኘት እንደሚኖርበት ያመለክታሉ፡፡ ዕቃዎች በሚገቡበት ወቅትም ከቀረጥ ነፃ መብት ሊኖር እንደሚገባ ነው የጠቆሙት።
«ለማህበረሰቡ ተብለው የተቋቋሙ ሬዲዮ ጣቢያዎች ቀጣይነት ላይ በጣም ችግር አለ፤ በዋነኝነት ሁሉም ማለት በሚቻል መልኩ የበጀት ዕጥረት አለባቸው፤ ሌላው ያላቸውን የተወሰነ መሣሪያም ቢሆን በአግባቡ በሥራ ላይ የሚያውልና ሲበላሹም የሚጠግን ባለሙያ የላቸውም፤ የተማረ የሰው ኃይል ዕጥረት ከፍተኛው ችግር ነው » ሲሉ ችግሮቹን ያብራራሉ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ሙላቱ አለማየሁ የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎች የህብረተሰቡን ባህል ኃይማኖት አብሮ የመኖር እሴቶችን በማሳየት በኩል ሚናቸው ላቅ ያለ መሆኑን ባካሄዱት ጥናት መረዳታቸውን ይናገራሉ።
ህብረተሰቡ ከነዚህ ሬዲዮ ጣቢያዎች ተጠቃሚ እየሆነ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ እያደረገ ያለው ቀጥተኛ ተሳትፎ ግን በጣም ውስን መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ የቦርድ አባላት ተብለው የሚሰየሙት ሰዎችም ባለባቸው የሥራ ኃላፊነት ምክንያት በአንድ ቦታ ተረጋግተው ስለማይቀመጡ መሠራት ያለበት እንዳይሠራ ብሎም ክፍተት እንዲፈጠር እያደረገ መሆኑን ያብራራሉ።
እንደ ዶክተር ሙላቱ ማብራሪያ፤ እነዚህ ሬዲዮዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው የሚመለከታቸው አካላት ከግዥ ጀምሮ እስከ ፖሊሲ ድረስ መታየት ያለባቸውን ነገሮች ማየት ይኖርባቸዋል፡፡ በተቋማት በግለሰቦች እንዲሁም በሌሎች አካላት በቋሚነት ሊደገፉም ይገባል።
በኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን የመገናኛ ብዙኃን ምዝገባና ፍቃድ ዳይሬክተሩ አቶ ሙሉጌታ ሲሳይ እንዳሉት፤ ጣቢያዎቹ የሚቋቋሙት በማህበረሰቡ ነው። በበጀት በኩል ሰፊ ክፍተቶች ይስተዋሉባቸዋል።
ችግሮቻቸውን ለመፍታትም ባለሥልጣኑ ከመመሪያ አንፃር ያለውን እንደሚያይ ጠቅሰው፣ ሌሎች ችግሮችንም ለመፍታት በየደረጃው ያሉ አካላት ተሳትፎ እንዲያደርጉበት እንዲሁም ሚዲያዎቹም ማየት ያለባቸውን ችግሮች እንዲያዩ በማደረግ ቀጣይነታቸውን የማረጋገጥ ሥራ እንደሚሠራም ጠቁመዋል።
የማህበረሰብ ሚዲያዎች በተሟላ ነፃነት ሥራቸውን እያከናወኑ ነው የሚል እምነት የለኝም ያሉት ዳይሬክተሩ፣ በቀጣይ በራሳቸው ኤዲቶሪያል ፖሊሲ እየተመሩ ሥራቸውን ያለማንም ጣልቃ ገብነት እንዲያከናውኑ እንደሚደረግም ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት 49 የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎች ፍቃድ ያወጡ ሲሆን፣ 31ዱ በትክክል ሥራ ላይ እንደሚገኙም መረጃዎች ያሳያሉ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 9/20111
በዕፀገነት አክሊሉ