በምርት ጥራት፣ በመሬት አቅርቦት እንዲሁም የኤሌክትሪክ ኃይልና የውሃ አቅርቦት በፍጥነት ለማግኘት አለመቻልና ለጥሬ ዕቃም ሆነ ለማሽነሪ ግዥ የሚውል የብድርና የውጭ ምንዛሪ እጦት በመሳሰሉ ማነቆዎች የታጠረው የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው ባለፉት ዓመታት ሲጠበቅበት ከነበረው የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት የቻለው ዝቅተኛውን ነው፡፡
ይሁንና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት የዘርፉን ማነቆ በመለየትና መፍትሄዎችን በማስቀመጡ ለውጦች መታየት ጀምረዋል፡፡ 2011 ዓ.ም በጀት ዓመት በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ዘርፍ 240 ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት አቅዶ 63 በመቶ በማሳካት 153 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዶላር ማግኘት ተችላል፡፡ ይህ ቁጥር ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ44 ነጥብ 47 ሚሊዮን ዶላር ጭማሪ ማለትም የ40 ነጥብ 8 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን መረጃዎች ያመላክታሉ፡
ኢንዱስትሪው ያሰበውን እንዳያሳካ እክል ከሆኑበት መሰል ማነቆዎች በተጓዳኝ ዘርፉን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ ረገድ የሚፈለገውን ያህል መጓዝ አለመቻሉም አብሮ ይነሳል፡፡ ይህ ዘርፉን ከቴክኖሎጂ ጋር የማዋሃድ ክፍተትን ለማሻሻልም የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ ይስተዋላል፡፡ ከእነዚህም አንዱ ለዘርፉ እድገት አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ የተለያዩ ዓውደ ርእይዎችን ማካሄድ አንዱ ነው፡፡
የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከህንድ ዓለም አቀፍ ጨርቃ ጨርቅ ማሽነሪ ኤግዚቢሽን ማሕበር ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ የጨርቃ ጨርቅና ማሽነሪ ዓውደ ርዕይ እንደሚካሄድ አስመልክቶ ትናንት መግለጫ ተሰጥቷል፡፡
ዓውደ ርዕይ ‹‹በጨርቃ ጨርቅ ቴክኖሎጂው የበለፀገች አፍሪካ›› በሚል መሪ ሐሳብ በሚሌኒየም አዳራሽ እ.ኤ.አ በ2020 ከየካቲት 14 እስከ 16 እንደሚካሄድና በሁነቱም ከአፍሪካ፣ ከእስያ፣ ከመካከለኛው ምሥራቅና ከአሜሪካ የሚመጡ ከ220 በላይ ኩባንያዎች እንደሚሳተፉበት አዘጋጆቹ አሳውቀዋል፡፡ በአውደ ራእዩ ላይ የቢዝነስ ፣የቴክኒካል ፣ኢንቨስትመንትና በባንክ ኢንስቲትውቶች ሴሚናር እንደሚካሄድም ታውቋል፡፡
ዓውደ ርዕዩን በሚመለከት ማብራሪያ የሰጡት ከህንድ ዓለም አቀፍ ጨርቃ ጨርቅ ማሽነሪ ኤግዚቢሽን ማህበር ኃላፊው ሃሪ ሻንከር፣ ዓውደ ርዕዩ የዘርፉን ምርትና ምርታማነት እንዲሁም ጥራት የሚያሳድጉ አዳዲስ ትክኖሎጂዎችንና አሰራሮችን ተግባራዊ እንዲሆኑ ባለድርሻዎችም በቴክኖሎጂ ረገድ ያሉባቸውን ችግር በመለየት አቅማቸውን እንዲገነቡ፣ ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር እንዲገናኙ በማድረግ ከሁሉ በላይ በዘርፉ ልማት እንቅፋት የሆኑ ተግዳሮቶችን በማቃለል ረገድ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዳለውም አመልክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት መላኩ እዘዘው (ኢንጂነር) በበኩላቸው፤ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ቁልፍ ሲሆን፣ ቴክኖሎጂው ደግሞ ወደ እዚህ ግብ የሚደርስ ዋነኛ መንገድ ስለመሆኑ ይገልፃሉ፡፡
ይህ በሆነበት የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪውን ልማት የሚያግዙ ቴክኖሎጂዎች የሚቀርቡበት ዓውደ ርዕዩ መካሄዱም በኢትዮጵያ ያሉትን የኢንቨስትመንት አማራጮች ለውጭ ባለሃብቶች ከማስተዋወቅና ከቴክኖሎጂ ሽግግር ባሻገር የተለያዩ አገራት ኩባንዎች የሚሳተፉበት እንደመሆኑ የገበያ ትስስር በመፍጠር ረገድ የሚኖረው አስተዋጽኦም ከፍተኛ ስለመሆኑ አፅንኦት ሠጥተውታል፡፡
የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ለማ እንደገለፁትም፣ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው በቴክኖሎጂዎች መደገፉ ለዘርፉ ምርትና ምርታማነት እጅጉን ወሳኝ ነው፡፡
በተለይ በአሁኑ ወቅት በዓለም የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው እጅጉን ከመጎልበቱ በተጓዳኝ ራስን በማጠናከር ተፎካካሪ መሆን በጣም ወሳኝ መሆኑን ያመላከቱት አቶ ሰለሺ፣ የዓለም ገበያን ሰብሮ ለመግባትም ዘርፉን በቴክኖሎጂ በማጎለበት ከዘመናዊነት ጋር መተዋወቅ ግድ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡
በዚህ ረገድ የሚካሄዱ ኤግዚቢሽንና ባዛሮችም የእርስ በርስ የንግድ አጋርነትን ከማሳለጥ በተጓዳኝ ዘርፉን ከቴክኖሎጂ ጋር ይበልጡን ለማዋደድ ፋዳቸው ጉልህ ስለመሆኑ ዳይሬክተሩ ይገልፃሉ። ኢትዮጵያን የአፍሪካ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ ውጥን በተያዘበት በዚህ ወቅት እንዲህ ያለው ዓውደ ርዕይ መምጣቱም ለኢትዮጵያ ትልቅ ዕድል መሆኑን ነው ያብራሩት፡፡
የኢትዮጵያ የሕንድ አምባሳደር አኑራግ ስሪቫስታቫ በበኩላቸው፤ የሁለቱ አገራት ሁለንተናዊ ግንኙነት ረጅም ዓመታትን ማስቆጠሩንና በአክሱም ስልጣኔ በአዱሊስ ወደብ የንግድ አጋርነት አሃዱ ያለውም በቅመማ ቅመምና በጨርቃ ጨርቅ ንግድ መሆኑን ያስምሩበታል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ሁለቱ አገራት በተለያዩ መስኮችም ጠንካራ አጋርነት መፍጠራቸውን ይጠቁማሉ፡፡
በኢንዱስትሪው በተለይም በጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ የሕንድ ባለሀብቶችም ተሳትፎ ከፍተኛ መሆኑን እንዲሁም ከኢትዮጵያ ጠንካራ አጋሮች መካከልም ህንድ በሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን አምባሳደሩ ይገልፃሉ፡፡ አገሪቱ ልዩ ትኩረት በምትሰጠው ለኢንዱስትሪ ዘርፍ መሆኑ ደግም ልዩ እንደሚያደርገው ነው ያስገነዘቡት፡፡
‹‹ህንድ ከዓለም ዋነኛ የጨርቃ ጨርቅ አምራቾች መካከል ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናት፡፡›› ያሉት አምባሳደሩ፣ አውደ ርእዩም አገሪቱ ለጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው ዘርፉ የሰጠችውን ትኩረት እንደሚያግዝና የገበያ ዕድል ይዞ እንደሚመጣም እምነታቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ተካ ገብረእየሱስ እንደሚገልፁትም፣ መንግሥት የኢንዱስትሪውን ዘላቂ እድገት ለማረጋገጥ የተለያዩ የልማት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በመቅረፅ ለተግባራዊነታቸው በትኩሩት እየሰራ ይገኛል፡፡
ለኢንቨስትመንት መስፋፋት ምቹ ከባቢ ሁኔታን በመፍጠር፣ ለልማታዊ ባለሃብቱ የላቀ አገልግሎትና ድጋፍ በመስጠት እና የዘርፉን የሰው ሃብትና የቴክኖሎጂ አቅም ለማሳደግ እንደ ሌሎች ዘርፎች ሁሉ ባለሃብቶችን በአገሪቱ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ላይ መዋእለ ንዋቸውን እንዲያፈሱ የተለያየ ማበረታቻዎችን ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በዘርፉ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች የታክስ እፎይታን ጨምሮ ሌሎችም ማበረታቻዎች እንደሚያደርግላቸውና ለኢንዱስትሪው እድገት ዘርፍ ሁነኛ አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ የመሰረተ ልማትን ተደራሽ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራ እየተከናውኑ ስለመሆኑም ያነሳሉ፡፡
‹‹ቀደም ባሉት ዓመታት በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ያሉ አካላት በርካታ ውጣ ውረዶችን አሳልፈዋል፤ አንዳንዶችም በተለያዩ መሰናክሎች ተጠልፈው ወድቀው ተዘግተዋል፡፡ ›› የሚሉት አቶ ተካ፣ በአሁኑ ወቅት ይህ ታሪክ ሆኖ እንዲቀርና አሁን ዘርፉን አንቀሳቅሶ ምን ችግር አለባቸው የሚለውን በመለየት በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ያስገነዝባሉ፡፡
አሁንም ቢሆን ዘርፉ አልጋ በአልግ አለመሆኑን የሚስማሙበትና ይህ በሆነበት በዘርፉ የተሰማሩ ባለድርሻ አካላትም ባለ በሌለ አቅማቸው ምርትንና ምርታማነት በማሳደግ ወደ ዓለም ገበያው ለመዝለቅ የሞት ሽረት ትግል በማድረግ ላይ መሆናቸውን አቶ ተካ አመልክተዋል፡፡ እነዚህን ትጉህ ባለሀብቶች ተገቢና አስፈላጊ ድጋፍ ማድረግ ቢቻል ደግሞ ከዚህም የተሻለ ስኬት ማስመዝገብ እንደሚቻል አጽንኦት ሰጥተውታል፡፡
ለኢንዱስትሪው ሁለንተናዊ እድገት ዘርፉን ከቴክኖሎጂ ጋር ይበልጥ ማቀራረብ ግድ ስለመሆኑ የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው፣ በአሁኑ ወቅትም ቴክኖሎጂ አማራጭ ሳይሆን ግዴታ ነው፣ በቴክኖሎጂ ያልተደገፈ ቢዝነስ ሀልውናውን ማቆየት አይችልም፤ ወደ ዘመናዊው የቴክኖሎጂ ዓለም መቀላቀልም ለነገ የሚባል አይደለም ነው ያሉት፡፡
የእርስ በርስ የንግድ አጋርነት ከማሳለጥ በተጓዳኝ ዘርፉን ከቴክኖሎጂ ጋር ይበልጡን ለማዋደድ፣ በሌሎች አገራት የጨርቃ ጨርቁን ኢንዱስትሪ የሚያነቃቁ አውደ ርእዮች እንደሚካሄዱ የጠቆሙት አቶ ተካ፣ ከህንድ ዓለም አቀፍ ጨርቃ ጨርቅ ማሽነሪ ኤግዚቢሽን ማህበር ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ የሚካሄደው ጨርቅና ማሽነሪ ዓውደ ርዕይ ፋይዳም ዘርፈ ብዙ ስለመሆኑ ነው ያስረዱት፡፡
በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶችን ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ከዚህ ኤግዚቢሽን መሳተፍ ብቻ ሳይሆን እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው ታሳቢ ማድረግ እንደሚገባውና ለዚህም ከወዲሁ መዘጋጀት እንዳለባቸው አፅንኦት ሰጥተውታል፡፡በዘርፉ የተሰማሩ አካላት ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻም ሳይሆን የዓለም አቀፉን ገበያ ዘልቆ ስለመግባት ማሰብ ግድ እንደሚላቸውም ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡
አዲስ ዘመን ነሐሴ 28/2011
ታምራት ተስፋዬ