
አዲስ አበባ፦ የቀድሞው ማዕከላዊ እስር ቤት ከጳጉሜ 1 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ አራት ቀናት ለጎብኚዎች ክፍት እንደሚሆን የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ አስታወቀ፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ቱኑ ለአዲስ ዘመንጋዜጣ እንደተናገሩት፤ እስር ቤቱ ክፍት የሚሆነው ጳጉሜ 5 ቀን 2011 ዓ.ም የሚከበረውን የፍትህ ቀን ምክንያት በማድረግ ነው፡፡ እስር ቤቱ በብዙዎች ዘንድ አስፈሪ ገጽታ ያለው፤ የብዙ ሰው ህይወት የጠፋበትና አካል የጎደለበት ከመሆኑ አንጻር ሁሉም ሊያየውና ሊጎበኘው የሚያስፈልግ በመሆኑ መርሀ ግብሩ እንዲዘጋጅ ተደርጓል፡፡
እንደ አቶ ዝናቡ ገለጻ በእስር ቤቱ ታስረው የነበሩ “እዚህ ነበርኩ እኮ “ብለው በታሪክነቱ እንዲያስታውሱት፤ ሌላውም የህብረተሰብ ክፍል የድርጊቱን አስከፊነት በመረዳት ዳግም እንዳይፈጸም፣ለማውገዝና ታሪካዊ ቃል ለመግባት ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡ ችግሩን የፈጸሙ አካላትም በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ መልዕክት ያስተላልፋል ፡፡
በአገራችን እና በፍትህ ሥርዓቱ የነፈሰውን መልካም የለውጥ አየር አድናቆት እየቸረንና ለለውጡ ቀጣይነት ማነቆ የሆኑ ተግዳሮቶችን እየተዋጋን የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ አለብን ያሉት አቶ ዝናቡ፣ የህዝብና የመንግሥት አመኔታ የተቸረው የፍትህ ተቋም ለመገንባት በአገሪቱ አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በማድረግ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት፣ የሰላም፣ የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ሥርዓት ግንባታ ለማጎልበት ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ዘንድሮ በአገር አቀፍ ደረጃ “ለሕግ ተገዥ ነኝ” በሚል መሪ ቃል በልዩ ልዩ ዝግጅቶች በድምቀት የሚከበረው የፍትህ ቀን፤ ለዘመናት ማዕከላዊ እስር ቤት ሲባል በቃል የሚሰማው ወጣቱ ትውልድ አውቆትና እስር ቤቱ በሰው ልጆች ህይወት ላይ ያደርስ የነበረውን ክፋት ተረድቶት በታሪክ አጋጣሚ ዳግም እንዳይፈፀም ሊያደርግ እንደሚገባና ዜጎች የከፈሉትን ዋጋ ለማሰብ እንደሚያግዝ አብራርተዋል፡፡
በአራቱ ቀናቶች በወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ላይ እጃቸውን ዘርግተው ግፍ ያደረሱ ግለሰቦችን በድርጊታቸው በማውገዝ በማዕከላዊ እስር ቤት ኤግዚቪሽን ተዘጋጅቶ በህዝብ እንደሚጎበኝም ነው የተናገሩት፡፡
በመጨረሻም ለፍትህ ሥርዓት መሻሻልና ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ ህብረተሰቡም ተሳትፎውን በማጠናከር የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ ዳር ማድረስ እንደሚገባ በመጠቆም፤ ከጳጉሜ አራት በኋላም ባሉት ጊዜያት የተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎችና ማረሚያ ቤቶች በህዝብ እንደሚጎበኙ አቶ ዝናቡ አስታውቀዋል፡፡
ከ40 ዓመታት በላይ ዜጎች ሲታሰሩበት፤ ሲሰቃዩበትና እስከ ህይወት ማጣት ዋጋ ሲከፍሉበት የቆየው ማዕከላዊ እስር ቤት ለውጡን ምክንያት በማድረግ በመንግሥት ውሳኔ እንዲዘጋና ወደ ሙዚየምነት እንዲቀየር መወሰኑ ይታወሳል፡፡
አዲስ ዘመን ነሃሴ 29/2011
እፀገነትአክሊሉ