“… ሁሉም ልጆች ምሳ ሊበሉ ቁጭ ሲሉ እሱ ግን ቀደም ብሎ ይወጣና ወደ መጫወቻ ሜዳ ይሄዳል:: መምህሯ ለምንድነው ምሳህን የማትበላው?” ስትለው “አላየሽኝም እንጂ በልቻለሁ”ይላታል:: አንድ ቀን ሁሉም ተማሪዎች ለሰልፍ ስነስርዓት ሲወጡ መምህሯ የልጁን የምሳ ዕቃ ከፍታ ተመለከተች:: ባዶ ዕቃ ነው የያዘው:: ይህንን የተመለከተች መምህር ለትምህርት ቤቱ ባለቤት አሳወቀች::
በሁኔታው ውስጧ የተነካው የትምህርት ቤቱ ባለቤት ታዲያ እንዴት ልጅ ምግብ ሳይመገብ ይማራል ብላ ወገቧን ታጥቃ ችግረኛ ልጆችን ለመመገብ መስራትን አንድ ብላ ጀመረች :: በእዚህና በሌሎችም በርከታ ስራዎቿ አርዓያ ትሆነን ዘንድ ለዛሬ “የህይወት እንዲህ ናት” አምዳችን እንግዳ አድርገናታል፤
-የ ኢትዮጵያ ስኩል ሚል ኢንሺየቲቭ መስራቿን ወይዘሮ ፍሬዓለም ሺባባውን::
ከውልደት እስከ ዕድገት
ወይዘሮ ፍሬዓለም ሽባባው ይህችን አለም የተቀላቀለችው ነሐሴ 6 ቀን 1970 ዓ.ም በመዲናችን አዲስ አበባ ነው∷ ይሁን እንጂ ዕድገቷ በዚችው ከተማ አልቀጠለም∷ የህይወት ውጣ ውረድ ብዙ ነውና ወላጆቿ አካባቢ ቀይረው ወደ አማራ ክልል ቻግኒ በመሄዳቸው የእሷም ዕድገት በእዛው ሆነ∷
ትምህርቷንም እስከ ዘጠነኛ ክፍል በቻግኒ መከታተሏን ትናገራለች∷ ቀጥላም ባህርዳር ትምህርት ቤት እስከ 12ኛ ክፍል ተምራ ጨረሰች∷ “ትምህርት የጨረስኩት በ17 ዓመቴ ነው∷ ከዛ ወደ አሜሪካ ሀገር ሄድኩ ∷ አሜሪካ ለሰባት አመት ቆይቼ የቢዝነስ አድሚንስትሬሽን ማኔጅመንት ትምህርት ተከታተልኩ∷ ሆኖም ሳላጠናቅቅ ከሰባት ዓመት ቆይታ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ መጣሁ ∷
ወደዚህ የመጣሁት በፍላጎቴ ነበር∷ በሀገሬ ውስጥ መኖር በጣም ደስ ይለኛል ∷ ችግርን ማየት ብዙ ትምህርት ስለሚሰጠኝ ህብረተሰቡ የሚጋፈጣቸውን ችግሮች ምንጫቸው ምንድነው? መፍትሄውስ? የሚል ከልጅነቴ ጀምሮ ጥያቄ ነበረኝ∷ ይሄንን ማጥናት ማወቅ መፍትሄም መፈለግ እንዳለብኝ አስብ ነበር∷
እዚህ ከመጣሁ በኋላ ተመልሼ ትምህርት ቤት ገብቼ ነው ሁለት ዲግሪ የሰራሁት∷ ደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ገብቼ በሂውማንና ሶሻል ስተዲስ የመጀመሪያ ዲግሪ߹ በዲቨሎፕመንት ስተዲስ ኦነርስ ሁለተኛ ዲግሪ ሰራሁ∷ እነዚህ ትምህርቶች በራሴ ፍላጎት የተማርኳቸው ናቸው ∷ ቢዝነስ ትምህርት ለመማር ስገባ ግን በቤተሰብ ፍላጎት ነበር∷ እናቴ የወለደችው ስምንት ሴቶች እና ሁለት ወንዶች ናቸው∷
ሁልጊዜ እንደ አባትሽ የንግድ ፈጠራ እና ችሎታ ይታይብሻል፤ በባህሪም ሆነ በሌላውም እሱን ትመስያለሽ ይሉኛል∷ ስለዚህ ትምህርቱንም እንድማር የተደረገው በቤተሰብ ውይይት ነበር∷ በእርግጥ ስራ ፈጣሪነቱ ለእኔ ብዙም አይከብድም፤ ነገር ግን ራሴን ሳየው ብዙውን የማዘነብለው ወደ ማህበረሰብ ሳይንስ ነው ∷
እኔ ውስጥ ያለው ፍላጎት የማህበረሰብ ግንባታ ስለሆነ ማህበረሰቡን ምን ያህል እንደሚጠቅም ሂሳብ ሰርቼ ነው ተመልሼ ትምህርት ቤት የገባሁት∷ በምፈልገው የሙያ ዘርፍ በመማሬም በጥሩ ፍጥነት ߹ በከፍተኛ ውጤት ደስ ብሎኝ ዲግሪዬን አገኘሁ∷ እነዚህ ትምህርቶች አሁን ለምሰራው ስራ በጣም ጠቅመውኛል ∷ እኔ የታዳጊ ሀገሮችን ችግር ነው ያጠናሁት∷ ይሄ በጣም ትልቅ ድጋፍ አድርጎልኛል∷ በሀገሬም ያለው ችግር ቀላል እንዳልሆነና ወገብን ጠበቅ ማድረግ የሚጠይቅ መሆኑን ተረድቻለሁ∷ ይሄንን ጥናት እየሰራሁ በባህር ዳር 16 ዓመት ቆይቻለሁ” ትላለች∷ አሁን ኑሮዋ አዲስ አበባ ነው∷
የልጅ ግዴታው
ቤተሰብ ማገዝ የልጆች ግዴታ ነው∷ ቤተሰቦቻችን የወለዱንና ያሳደጉን ናቸው∷ የእነሱ ስራ ችግር ሲገጥመው ማገዝ ይኖርብናል∷ እኔ ከአሜሪካ ሲመጣ ቤተሰቦቼን በጉልበት ስራ ሳይቀር አግዝ ነበር∷ አባቴ ትልቅ ሆቴል ባህርዳር ላይ ለመገንባት ቦታ ተረክቦ ገና እየታረሰ ነበር የመጣሁት∷ ምንም ስራ አልተጀመረም∷ ስለዚህ ቦታውን ተረክቤ እኔ እሰራዋለሁ ብዬ ገባሁ∷ ቦታው ትንሽ አስቸጋሪ ነበር∷ የሚገነባው ደግሞ ለአካባቢው ትልቅ ኮንስትራከሽን ነው ∷
ብዙም መሰረተ ልማት የለም፤ ከባንክ ጋር የነበረውን ችግር ከባድ ነበር ፤ አልረሳውም ∷ ስራው ቶሎ ቶሎ በፍጥነት ማለቅ የነበረበት አያልቅም ∷ እኔ ደግሞ በውጪ ቆይቼ ወደ ስራው ስለገባሁ በጣም ከባድ ነበር ∷ የአሜሪካውያና የእኛ ሀገር የስራ ባህልና በጣም የተለያየ ነው∷ ሆኖም በብዙ ትግል ሆቴሉ ተጠናቆ ስራ መጀመሩ ለእኔ ትልቅ እርካታ ነበር ∷
የስራ መጀመሪያ
ኢትዮጵያን የምናገኛት ባደግንበት ቤት ውስጥ ብቻ አይደለም∷ ብዙ ቦታ አለች∷ ከአንድ ቦታ ወጥተን ወደ ሌላ ቦታ ስንሄድም ኢትዮጵያ አለች∷ ብዙ ህዝብ ߹ ባህል ߹ አመለካከት የያዘች አገር ናት∷ በቋንቋ ߹ በባህል߹ በሀይማኖት የተለያየን ብንሆንም በአኗኗራችን߹ ለችግር መፍትሄ ባለመስጠታችን እና እንግዳ አቀባበላችን ደግሞ አንድ ያደርገናል∷ ሁሉንም አንድ የሚያደርግ ደግሞ የጋራ ጠላት አለ ፤ይሄ ደህነት ነው ∷
ይሄም በጣም ያስገርመኛል ∷ ስለዚህ ልጆቻችንን የምናሳድግበት መንገድ መፈተሽ አለበት የሚለው ነው ድምዳሜ ላይ ያደረሰኝ∷ ምናልባት የልጅ አያያዛችን አንድ አይነት ሆኖ ነወይ ወደ አንድ አይነት ደህነት ውስጥ ያለነው? የሚል ምርምር መሳይ ነገር መፈለግ ጀመርኩ∷
ባህርዳር ከተማ ላይ ባህርዳር አካዳሚ የሚባል ትምህርት ቤት ከፈትኩ∷ ትምህርት ቤቱ አሁን 18 ዓመቱ ነው∷ በግሌ የጀመርኩት የመጀመሪያ ስራዬ ነው ∷ ስራ ሲጀምር 50 ተማሪ ነበር የተቀበልነው∷ ከዛ በየዓመቱ ቁጥሩ እያደገ ሄዶ አሁን ከሶስት ሺ በላይ ተማሪዎችን ይዟል∷ ከ300 በላይ ዜጎች የስራ ዕድል ከፍቷል∷ ምናልባትም በክልሉ ካሉ ከግል ትምህርት ቤቶች ትልቁ ሊሆን ይችላል ∷
ተማሪዎቹም በከፍተኛ ውጤት በየዓመቱ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ይገባሉ ∷ ለእኔ ያ ትምህርት ቤት ማህበረሰቡን የማውቅበት ቤተ ሙከራዬ ነው ማለት ይቻላል∷ ልጆች በቤት ውስጥ የሚያድጉበትን߹ የሚያዙበትን߹ በቤተሰብ ߹በመምህራኑ ፤ በመምህራን ስልጠና በኩል ያለውን ክፍተትና የትምህርት ስርዓቱ በተጨባጭ ችግራችንን የማይፈታ መሆኑን ያየሁበት ነበር ትላለች∷
ወይዘሮ ፍሬዓለም ለበርካታ ችግረኛ ህፃናት ነፃ የትምህርት ዕድል ትሰጣለች ∷ ይሄ ደግሞ በየቤቱ ያለውን ችግር እንድታውቅ በር ከፍቶላታል∷ በተለይ ትላለች በተለይ እሷ ነፃ የትምህርት ዕድል የሰጠችው አንድ ተማሪ ባዶ የምሳ ዕቃ ይዞ እየመጣ ተማሪ ምሳ ሲመገብ እሱ በመጫወቻ ቦታ በባዶ ሆዱ እንደሚያሳልፍ መስማቷ የማህበረሰቡ ችግር ምንድነው ማህበረሰቡን በምን ላግዝ የሚለውን ህልሟን የሚፈታላት ቀን ሆኗል∷
“ በተለያዩ የማህበራዊ ስራዎች ላይ እሳተፋለሁ∷ በነጋዴ ሴቶች ߹ በሌሎች የአቅም ግንባታ ስራዎች በመሳሰሉት ሁሉ እሳተፋለሁ∷ ራሴንም በስራ የወጠርኩት እንዴት አድርገን ነው ከችግር የምንወጣው የሚለው ለማወቅ ስለምፈልግ ነው∷ እሱን በመጠየቅ ሂደት ውስጥ ስለነበርኩ ምንም ነገር አይደክመኝም ∷ ሁልጊዜም ፍለጋ ላይ ነኝ ∷ አሁን ብዙ ነገር አውቄያለሁ ∷ ያወቀኩት ነገር ግን እኛ የምንፈልገው ነገር ቀላል አለመሆኑን ነው∷ ፍላጎታችን ከባድ ነው፤ አንዳንድ ጊዜ ታዲያ አቅምና ፍላጎት አይመጠጣንም∷ አቅሙ ከየት እንደሚመጣ አይታወቅም∷ ”
የድህነት ቀለበት
ልጅ መጀመሪያ ከተጎዳ ከድህነት አይወጣም∷ እሱም የሚወልደው ልጅ በድህነት ይቀጥላል∷ ከዛ ቀጥሎ የሚወልደውም ተመሳሳይ ይሆናል∷ ስለዚህ በትውልድ መካከል የድህነት ቀለበት ይቀጥላል ∷ አሁን በዚህ የድህነት ቀለበት ውስጥ ያለው ህዝባችን ብዙ ነው∷ ይሄንን አዙሪት እንዴት ሰብረን ነው አንድ ትውልድ እንኳን ማዳን የምንችለው? ይሄንን ለማድረግ ስራው የሚጀመረው ከልጆች ነው የሚል ጠንከራ አቋም አላት∷
ብዙ ጊዜ በእኛ ሀገር ትኩረት የሚሰጠው ለትላልቁ ሰው ነው∷ ለልጅ ትኩረት አይሰጠውም፤ ይሄ ነው ሀገሪቱን ከድህነት ውስጥ አላስወጣት ያለው∷ ብዙ የበጀት ድልድሎችን ከፓርላማ ሲወጡ እመለከታለሁ∷ አብዛኛው ለጸጥታ߹ ለደህንነት ߹ ለመከላከያ߹ ለእስር ቤቶች ለመሳሰሉት (ለወንጀል መከላከል) የሚመደብ በጀት ነው∷ ለህጻናት ተብሎ ከሚወጣው በጀት ጋር ምንም ግንኙነት የለውም∷ ልጆቻችን ሲራቡ ምግብ የምትሰጥ ሀገር አይደለችም ∷
ነገር ግን አድገው ራሳቸውን መቻል ሲያቅታቸው ወደ ወንጀልና ስርቆት ሲሄዱ በእስር ቤት የምትቀብል ሀገር ናት∷ የማህበረሰብ ሳይንስ ሂሳብ እዚህ ላይ ያስፈልገናል∷ እኔ የማየው ጉዳቱን ነው ∷ ለእስር ቤት ߹ለወንጀል መከላከል የሚወጣውን ትልቅ ገንዘብ ልጆች ምግብ እንዲያገኙ߹ ከትምህርት ቤት እንዳይወጡ ቢደረግ ߹ ትምህርት ቤቶችን በደንብ ብንይዝ እና ልጆችን በስርዓት ብናስተምራቸው ነገ የሚፈጠረውን ወንጀል በብዙ እጥፍ መቀነስ እንችላለን ∷ ህብረተሰቡም እፎይ ብሎ ይኖራል∷ የማህበረሰብ ሂሳብ ሲሰላ የቱ ጋር ቢሰራ ነው ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት የሚቻለው የሚለውን ይመልስልናል∷
ሁሉም ሀገር ተሞክሮ አለው∷ ተሞክሮውን ማየት ይገባል∷ ባደጉ እና ባላደጉ ሀገራት ያለው ልዩነት የመንገድ እና የህንፃ አይደለም፤ የልጅ አያያዝ ልዩነት ነው ∷ እኔ ለመዝናናትም ይሁን ለማንኛውም ጉዳይ ውጪ ሀገር ስሄድ መጀመሪያ የምመለከተው ትምህርት ቤታቸውንና የልጆች አያያዛቸውን ነው∷ ህንድ߹ ኬንያ߹ደቡብ አፍሪካ߹ ብራዚል … ሌሎችም ቦታ ሄጄ ትምህርት ቤቱን አይቻለሁ∷ ከዚህ በመነሳት መንቃት አለብን የምለው በልጆች አያያዝ ላይ ነው∷
ይሄንን ችግር ለመከላከል ከአራት ዓመት በፊት ኢትዮጵያ ስኩል ሚል ኢንሺየቲቭን መሰረትኩ∷ መጀመሪያ ሊያስጨንቀን የሚገባው የልጆች ጉዳይ ነው∷ ጤናቸው እንዳይጓደል߹ የስነልቡና ችግር እንዳይገጥማቸው߹ እንዳይጠቁ ከፍተኛ ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል∷ ለልጆች የደህንነት ጉዳይ ወሳኝ ነው߹ ሁለተኛ ንጽህና ነው∷ ስለ ትምህርት የምናወራው የሚሰጣቸውን የቤት ስራ ክትትል እና ከቤተሰብ ጋር ያለው ግንኙነት ቀጣዩ ነው∷
ልጆችን የምናሳድገው ከቤተስብ ጋር በጋራ ነው∷ ስለዚህ የሚተላለፈው መልዕክት ተመሳሳይ መሆን አለበት∷ ይሄ የሚመጣው በኋላ ነው∷ መጀመሪያ ግን ልጆች በምግብ እንዳይጎዱ ማድረግ ነው∷ ብዙ ልጆች በባዶ ሆዳቸው የሚማሩ መኖራቸውን ዳታ ሰብስቤ ስመለከት በጣም ትልቅ ሀገር አቀፍ ችግር ሆኖ አገኘሁት∷
ከትምህርት ሚኒስቴር ያገኘሁት መረጃ ከትምህርት ገበታቸው የሚያቋርጡት አብዛኛዎቹ አራተኛ ክፍል ሳይደርሱ ነው ይላል∷ ይሄ ሁሉ ልጅ እያቋረጠ አይደለም ሀገር የምታድገው ∷ ያላቋረጡትም ቢሆኑ በደንብ እየተማሩ አይደለም∷ በጣም ጥቂት ልጆች ናቸው በተለያየ ድጋፍ በጥሩ ሁኔታ ተምረው ለቁም ነገር የሚበቁት∷ አንዳንዱም አጋጣሚ ነው∷
አብዛኛው ልጅ ግን በከባድ ችግር ውስጥ የሚያልፍ ማንም የማይደርስለት߹ መሄጃም የሌለው ነው∷ ለልጆቻቸው እያካፈሉ ጦም የሚያድሩ እናቶችም ቁጥር ቀላል አይደሉም∷ ለእኔ ይሄ ትልቅ ችግር ሆኖ ታየኝ∷ ልጆቹን ከድህነት እናውጣና የአንድ ትውልድ ታሪክ እናድርገው∷ የትምህርት߹ የደህንነት߹ የስልጠና ጉዳይ ልጆቹን መመገብ ስንችልና ፋታ ስናገኝ የምንሰራቸው ናቸው∷
የምገባ ፕሮግራም ለልጆች
በየክልሉ ሄድኩ ፤ብዙ ቦታዎችን ጎበኘሁ∷ የክልል መንግስታትን በማነጋገርና ጥናት በማቅረብ ምግብ ለሁሉም ልጅ የሚቀርብበት ሀገራዊ ስርዓት ያስፈልጋል የሚል ክርክርና ሙግት ይዥ ተነሳሁ∷ ይሄንን ሀሳብ በወቅቱ አንዳንዶች ሲቀበሉት ሌሎች ግን አልተቀበሉትም ∷ ያልተቀበሉበት ምክንያት ህፃናቱ በጣም ብዙ ናቸው፤ ይሄንን ሁሉ ልጅ የምንመግብበት ገንዘብ የለም የሚል ነበር∷
እኔ ደግሞ ሀብት አለን፤ ሀብታችንን በደንብ ስለማንጠቀምበት ነው የሚል ነበር መከራከራዬ∷ ሀብት የለንም ብለን የምናልፈውም ጉዳይ ሳይሆን ግዴታ ነው∷ እንደምንም ብለን የምንሰራው መሆን አለበት∷ ይሄንን ቁጭ ብለን መምከርና መነጋገር አለብን∷ ይሄ የአስራ አምስት ዓመት ስራ ይጠብቀናል∷ ስለዚሀ መጀመሪያ ፖለቲከኞቹን߹ ህግ አውጪዎች߹ ሚኒስትሮች እውቀት ያላቸው በሚሰሩት ስራ በመሆኑ የስነምግብ ሳይንስ እውቀት እንዲኖራቸው ነው ያደረግነው ∷
ምግብ በማጣት አእምሮቸው ߹ አካላቸው እየተጎዳ ስራ መስራት የማይችል ህብረተሰብ እየተፈጠረ ነው ∷ ስለዚህ ኢትዮጵያ ምግብን በደንብ መያዝ አለባት∷ ግብርና ተልዕኮውን ማስተካከል አለበት∷ ምግብ ለህፃናት ነፃ ለህብረተሰቡ ርካሽ መሆን አለበት∷ ዜጎች ከገቢያቸው በጣም ትንሹን ብቻ ማውጣት አለባቸው ተብሎ በፖሊሲ ገደብ ሊቀመጥለት ይገባል∷
ይሄንን ካደረግን ነው በአምራቾቹ ላይ ኢንቨስት የምናደርገው∷ የምናበረታታው∷ በሀገራችን ማበረታቻ የሚሰጠው ለኤክስፖርተር ብቻ ነው ∷ ልጆቻችን ምግብ ሳይመገቡ ስለምግብ ߹ስለ ወተትና ስጋ ኤክስፖርት እናወራለን∷ ይሄ ለእኔ ነውር ነው∷ መጀመሪያ እንደ ሀገር ህዝቧን መቀለብ አለባት∷ ልጆቻችን በሚፈልጉት አይነትና መጠን ወተት߹ ስጋ߹ እንቁላል … መመገባቸውን ካረጋገጥን በኋላ ነው ስለ ኤክስፖርት ማውራት የሚያስልገው∷ አሁን ባለው ሁኔታ ከፈረሱ ጋሪው ቀደመ አይነት ሁኔታ ይታየኛል ∷
የሰቆጣ ፕሮግራም
የኢትዮጵያ ስኩል ሚል ኢንሺየቲቭ ዓላማ የትምህርት ቤትን የምገባ ፕሮግራም አጀንዳ ማድረግ ነው∷ ትምህርት ቤት ውስጥ ምግብ መመገብ መብት እንዲሆን ߹ፕሮግራሙ የችግረኛ ፕሮግራም ተደርጎ ሳይሆን የሁሉም ተማሪ ጉዳይ እንዲሆን ማድረግ ነው∷ የትምህርት ቤት ምገባ የድሆች ሳይሆን የዜጎች ፕሮግራም ነው∷ ይሄ አሁን ሀገራዊ አጀንዳ ሆኗል∷
ስራውን ስንጀምር በአምስት ክልሎች ሞዴል ትምህርት ቤቶችን መርጠን ለአንድ ትምህርት ቤት 10 የወተት ላሞች ሰጥተን እያሳየን ነበር∷ ይሄንን ፕሮግራም 25 ትምህርት ቤቶች ላይ ተግብረነዋል ∷ ፕሮግራሙን በጀመርንባቸው ቦታዎች ለአንድ አመት አለማምደን ነው የምንወጣው∷ በዚሁ መሰረት አሁን ተቋቁመዋል∷ 35 ሊትር ወተት ለማህበረሰቡ ያቀርባሉ∷ ሌላውን ለተማሪዎቻቸው ይጠቀማሉ∷ በዚህ መልኩ ብዙዎቹ ውጤታማ ሆነዋል∷
አንዳንዶቹ በአስተዳደር ችግር ገጥሟቸዋል∷ ሆኖም የፕሮግራሙ አተገባበር በደንበ ከተያዘ ውጤታማ ነው∷ ይሄ ህጻናትን በሙሉ ወተት ማጠጣት የሚያስችል ሞዴል ነው∷ ላሞች ሊረቡ በማይችሉበት ቦታዎች ላይ ደግሞ የምግብ ማቀነባበሪያ ሰርተናል∷ ሰቆጣ ላይ የምግብ ማቀናባበሪያ ተክለን አልሚ ምግብ እየተዘጋጀ ልጆቹ ጠዋት ጠዋት ይመገባሉ ∷ አልሚ ምግቡ ብዙ ምግብ የበሉ ያክል ይጠቅማል∷ ለዚህ የሚሆን የአሰራር ማንዋል አዘጋጅተን ጉዳዩ ለሚመለከተው ሁሉ ሰጥተናል∷
ሰሞኑን ብዙ የክልል መንግስታት እስከ ስምንተኛ ክፍል የምግብ ፕሮግራም እንዲያቀርቡ መመሪያ ደርሷቸዋል∷ አዲስ አበባም ለ300ሺ ልጆች ምግብ እንደሚያቀርብ ߹ ኦሮሚያና አማራ በተመሳሳይ እንደሚያካሂዱ ሰምቻለሁ∷ ይሄ ለእኔ ትልቅ ግብ ነው∷ በአራት አመት ውስጥ እዚህ ደረጃ ይደርሳል ብዬ አስቤ አልነበረም∷ አሁን ውጤቱን ሳየው ስራዬም እዚህ ደረጃ በመድረሱም በጣም ደስ ብሎኛል∷ በቀጣይም ፕሮግራሙ እንዳይበላሽ߹ በትክክል ህብረተሰቡም ባለቤት ሆኖ እንዲያግዝ አብረን እንሰራለን∷
ጓደኝነት
ፍሬ የደሆች ጓደኛ ናት ይባላል እውነት ነው? (ሳቅ… በሳቅ) እኔ የሁሉም ጓደኛ ነኝ ∷ ሰውን በሰውነቱ ነው የማየው፤ የሰዎች ደረጃና ማንነት እንዳላያቸው አያደርገኝም∷ ምንም ቢሆኑ ሰውን የማይበት መነጽር ሰው በቃ ሰው ነው የሚል ነው∷ ቁጭ ብዬ አዳምጣለሁ፤ ጊዜ ሰጥቼ አብሬ አሳልፋለሁ፤ ያላቸውም ሆነ የሌላቸው ነገር ከእኔ ጋር ግንኙነት የለውም∷ እኔና እነሱ ሰው በመሆናችን አንድ ነን ∷ ስለዚህ ብዙ ጓደኞች አሉኝ ∷
“ላስብበት”
ወይዘሮ ፍሬዓለም የመጀመሪያዋ የሆነ አንድ መጽሀፍ ጽፋ እነሆ ለንባብ ብላናለች∷ የመጽሀፏ ርዕስ ደግሞ “ላስብበት” ይላል∷ ምን ይሆን የምታስብበት ስል ጥያቄ አነሳሁላት∷ ላስብበት የሚለው ቃል ለህጻናት ፈጥኜ የምሰጠው መልስ ነው አለች∷ ብዙ ጊዜ ህጻናት ድንገት የሚጠይቁት ከባድ ጥያቄ ነው∷ መልስ እንኳን ቢሰጣቸው ከዛ ሲሉ ይቀጥላሉ∷ ስለዚህ ወዲያው መልስ መስጠት አይቻልም∷
ስለዚህ መጽሀፍ አገላብጬ߹ ሰዎችን ጠይቄ ߹በራሴም ተመራምሬ መልሰ መመለስ ስላለብኝ ወዲያው ስጠየቅ ግን ‹‹ላስብበት›› የሚል ፈጣን መላሽ እሰጣቸዋለሁ∷ ልጆች ለጥያቄያቸው ተገቢውን ምላሽ ማግኘት አለባቸው∷ ለምሳሌ አንድ ልጅ ከአባይና ከኢትዮጵያ ቀድሞ የተፈጠረው ማን ነው? ብሎ ጠየቀኝ ይሄን እኔም አስቤው አላውቅም ∷ በጣም ገራሚና አስደንጋጭ ነው∷ ስለዚህ ትክክለኛውን መልስ ማግኘት አለበት∷ እነሱ ሲጠይቁኝ እኔ የምመልስበት መንገድ እነሱንም ይቀርጻል∷ ለዚህ ደግሞ የዝግጅት ጊዜ ያስፈልጋል∷ ስለዚህ ላስብበት እላለሁ∷
የመዝናኛ አውድ
በጣም አድርጌ የምወደው ጥበብ ቲያትር ነው∷ ጊዜ ካገኘሁ እንኳን የማየው ፊልም ሳይሆን ቲያትር ነው∷ ሌላው መዝናኛዬ ከልጆቼ ጋር ማሳለፍ ነው∷ ልጆቼ ትንንሽ ሆነው ረጅሙን ጊዜ የማሳልፈው ከእነሱ ጋር ነበር ∷ ሌላው በጣም የምዝናናበት የቤት ውስጥ ስራ ነው፤ ምናልባት ያልተለመደ ይሆናል∷ እኔ ግን በቤት ውስጥ ምግብ ማብሰል߹ ማጽዳት߹ ልጆችን መንከባከብ በጣም የምዝናናበት ስራ ነው∷ እቤት ጓደኛ መጥራትና መጋበዝ ߹በራሴ ምግብ ማዘጋጀት ከልጆች ጋር መዋል አዘወትራለሁ∷ ቅዳሜ ደግሞ ሁልጊዜም ከልጆቼ ጋር ቋሚ ፕሮግራም አለን ∷ ከቁርስ በኋላ ውሏችን በመረጥነው ቤተ መጽሀፍት መጽሐፍ ስናነብና መጽሃፍ ስናገላብጥ ማሳለፍ ነው∷ የወደዱትን መጽሀፍ ደግሞ ገዝተን እንመለሳለን∷ ይሄ ልጆቼ በጣም የሚወዱት አሁን ድረስ የሚያስታውሱት ፕሮግራማችን ነው∷
የልጅ አስተዳደግ
ሶስት ልጆች አሉኝ∷ ለልጆች ጊዜ መስጠት በጣም አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ∷ አንዱም በህጻናት ላይ እንድሰራ ያደረገኝ ይሄ ከልጆቼ ጋር ማሳለፍ መሆኑ ይገባኛል∷ ከሰራሁት ስራ ሁሉ አሁን በጣም የሚያስደስተኝ ልጆቼን ለማሳደግና ለመንከባከብ የሰራሁት ስራ ነው ∷
አሁን ሁለቱ ልጆች ዩኒቨርሲቲ ገብተዋል፤ ትንሿ ልጄ 12ኛ ክፍል ናት∷ የሚኖሩትም ውጪ ነው∷ አሁን ልጆቼ አድገዋል፤ አስፈላጊውን መስመር ይዘዋል∷ ይጎዱብኝ ይሆን የሚል ስጋት ውስጥም አልገባም፤ ምክንያቱም ከመሰረታቸው በደንብ ቀርጬ አሳድጌያቸዋለሁ እነሱ ከእኔ ምንም አይፈልጉም፤ በልጅነታቸው መስራት የሚገባኝን ሰርቻለሁ∷ ቤተሰብ ለልጆች ሰፊ ጊዜ ሰጥቶ ማድረግ ያለበትን አድርጎ በኋላ መልቀቅ ነው ያለበት∷ ብዙ ቤተሰቦችን ግን መጀመሪያ ልጆችን አይዙም፤ ካደጉ በኋላ ለመያዝ ይሞክራሉ∷ ይሄ የተጣመመ ዛፍ ለማቃናት እንደሞመከር ይሆናል ∷
ትዝብት
ኢትዮጵያን ሳስብ በየክልሉ ስንቀሳቀስ ያየኋቸውን ልጆች ነው የማስታውሰው ∷ እነሱን ሳይ ብዙ ነገር ያሳዝነኛል∷ ከአንዱ ጉዳት ወደ ሌላ ጉዳት እየሄደ ያለ ህብረተሰብ ነው∷ በእርጋታ የተቀመጠ ህብረተሰብ ነገሩን እንኳን የማያውቅ ነው∷ ይሄን ሳስብ አዝናለሁ∷
ብዙ በሀገሪቷ ውስጥ ያሉ ሰዎች ወደ ማስተዋል የሚመጡ ቢሆን ጥሩ ነው∷ ነገን ጥሩ ለማድረግ ዛሬን ጥሩ ማድረግ ይገባል ∷ ነገ ጥሩ የሚሆነው ዛሬ ልጆች ላይ መስራት ስንችል ነው የሚል እምነት አለኝ ∷ ነገ አላመለጠንም፤ ነገ ዛሬ በእጃችን ያሉ ልጆች ናቸው∷ የታላቅነት߹ የሀብት߹ የታሪክ ߹የስልጣን … ፉክክር ይታየኛል∷ ጥላቻ እንቅፋት ሊሆንብን አይገባም∷ በዓለም ላይ ብዙ ነገር ተቀይሯል∷ ስለዚህ በልጆች ላይ መስራት ቅድሚያ የሚሰጠው መሆን አለበት∷ ጥላቻን߹ ቂምን …አናውርስ∷
የወደፊቱ እሳቤ
ብዙዎች መጽሐፉን አድንቀውታል፤ ፃፊ እያሉ ያበረታቱኝም አሉ∷ እኔም በቀጣይነት አንድ አጠር ያለ መፅሀፍ በኢኮኖሚ ዘርፍ እፅፋለሁ ብዬ አስቤያለሁ∷ እዚህ ሀገር ገና ምንም ነገር አልተሰራም ማለት ይቻላል∷ በመጀመሪያ በልጆች ላይ የምሰራውን ስራ አጠናክሬ እቀጥላለሁ∷ የሁሉም ነገር መሰረት የዛሬ ልጆች ናቸው የሚል ጠንካራ አቋም አለኝ∷ ሌላው በኢኮኖሚው ላይ ማገዝ እንዳለብኝ ይሰማኛል∷
ሁሉም ዜጋ በልቶ የሚያድርባት ሀገር እንድትሆን እፈልጋለሁ∷ እዚህ ሀገር የሚኖር ሰው ይሄንን ነገር እፈልጋለሁ ብሎ ሁለት ጊዜ ባያስብ ደስ ይለኛል ∷ ምን እበላለሁ? እንዲህ አይነት ትምህርት ቤት መማር እፈልጋለሁ፤ እዚህ ደረጃ መድረስ አለብኝ ብሎ ሁለት ጊዜ ማሰብ አይገባውም ∷ ለዚህ የሚሆን ነገር ተመቻችቶ መሆን የሚፈልጉትን ሁሉ መሆን አለባቸው∷ ኢትዮጵያ ልጆቻችን ህልማቸውን የሚኖሩባት ሀገር መሆን አለባት∷ ለዚህ ደግሞ መስራት ያለብኝን ሁሉ እሰራለሁ∷
ከእንግዳችን ጋር ካደረግነው ውይይት ያቀረብነው ህይወትን በጭልፋ እንዲሉ ነው∷ ቦታ ገድቦን በዚሁ አበቃን∷ ሰላም!
አዲስ ዘመን ነሐሴ 26/ 2011
አልማዝ አያሌው