የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት በአሁኑ ወቅት ካለው ጥራትና ደረጃ አንጻር ሲመዘን፣ በዘርፉ የተሰማሩት አገልግሎት ሰጪ ማህበራት/ተቋማት የያዙት ሽፋን በቂ ያለመሆኑ፤ የማያስተማምንና ምቾት የሌለው፤ ለጥንቃቄ የማይመች፤ ደኅንነቱ የማያስተማምንና ጊዜን የሚያባክን መሆኑ ይነገራል፡፡ በዘርፈ ብዙ ችግሮች የተወጠረውን ይህን የአገልግሎት ዘርፍ ከማዘመን ጀምሮ ለማስፋትም የተሻለ አገልግሎት ማሳየት እንደሚኖርበት ይመከራል፡፡
በኢኮኖሚ የበለጸጉ አገሮች ልምድ እንደሚ ጠቁመው፤ ለኢኮኖሚው መመንደግ እንደምክንያት ከሚጠቀሱት ውስጥ ዋነኛው ለትራንስፖርት አገልግሎት የሰጡት/የሚሰጡት ትኩረት ከፍተኛ መሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም፤ ደረጃ በደረጃ የተመቻቸ የትራንስፖርት አገልግሎት ለተገልጋዮች ሲሰጡ ይስተዋላል፡፡
በኢትዮጵያ የትራንስፖርትን ችግር ለማቃለል የመንግሥት ኃላፊነት ብቻ ነው ተብሎ እንደማይታመን የተረዱት አካላትም በዘርፉ ያለውን ችግር ለማቃለል በቂ ባይባልም ኩባንያዎችን በማቋቋም ተወዳዳሪ ለመሆን እንቅስቃሴ ጀምረዋል፡፡
በዚህም ዘመናዊ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ወደ ሥራ የገቡ ጥቂት በረዥም ርቀት የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች መፈጠራቸውና ወደ ሥራ መግባታቸው የሚታወቅ ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ ኦዳ የተቀናጀ የትራንስፖርት አገልግሎት አንዱ ነው፡፡
አቶ እሸቱ ዘለቀ የኦዳ ኢንተግሬትድ ትራንስፖርት ሼር ካምፓኒ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ ኦዳን ለማቋቋም እንቅስቃሴው የተጀመረው ከሦስት ዓመታት በፊት ነው፡፡ የኩባንያው መመስረት ዋና ዓላማ በክልልም ሆነ በአገሪቷ ከማህበረሰብ ጥያቄዎች አንዱ የሆነውን ትልቅ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ነው፡፡ ይህንን ጥያቄም በተደራጀ መልኩ ለመፍታት ሲባል ተቋሙ ተመስርቷል፡፡ እንዲህ ያሉትን አገራዊ የሆኑ የሰዎች ጥያቄዎች በፖለቲካ እሳቤ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚና በተለያዩ መንገዶችም መልስ በመስጠት የማህበረሰቡን ቁልፍ ችግር መመለስ እንዲቻል ጭምር ነው የተቋሙ ምስረታ ያስፈለገው፤
እንደ አቶ እሸቱ ማብራሪያ፤ መሰል ተግባራትን ማከናወን የሚችሉ ውስን ኩንባያዎች በአገሪቷ ተቋቁመዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥም አንዱ ኦዳ ኢንተግሬትድ ትራንስፖርት ሼር ካምፓኒ ነው፡፡ የኦዳ ኩባንያ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል፤ የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራና ተጨማሪ የኢኮኖሚ ጥያቄዎችን መሠረት ባደረገ የኢኮኖሚ አብዮት እንቅስቃሴ ውስጥ ይገኛል፡፡ ኩባንያው ስሙ “ኢንተግሬትድ ትራንስፖርት” ይባል እንጂ፤ በውስጡ በርካታ ተግባራትን ማከናወን የሚያስችለውን ማዕቀፍ ይዟል፡፡ ብዙ ቢዝነሶችን ያቀፈ በመሆኑ አስፈላጊ ከሆነ ወደ ፊት የስም ለውጥ በማድረግ በተለያዩ ሴክተሮች ውስጥ ተሳታፊ የመሆን ዕድሉን ያሰፋል፡፡ ኩባንያው ሥራ የጀመረባቸው በዋናነት ሁለት ቢዝነሶች ናቸው፡፡ በእርግጥ በህግ እንዲሰራ የተፈቀደለት ብዙ ሴክተሮች ናቸው፡፡ ግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ሪል ስቴትና ሌሎች አገልግሎቶች ላይ ተሰማርቶ ይሠራል፡፡ ብዙ ትልልቅ ኩባንያዎችንም አቋቁሞ መስራት ይችላል፡፡
የኦዳ ኩባንያ ለጊዜው የማህበረሰቡ አንገብጋቢ ችግር በሆነው የትራንስፖርትና የኢነርጂ አቅርቦት ላይ በመሰማራት ሥራ መጀመሩን የሚገልጹት ሥራ አስኪያጁ፤ በተለይ በአሁኑ ወቅት በአገሪቷ ከፍተኛ የትራንስፖርት ችግር ስላለ ኩባንያው ወደዚህ አገልግሎት መግባቱ የማህበረሰቡን የኢኮኖሚ ችግር ከማረጋጋት አንጻር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ይጠቁማሉ፡፡ የተቋሙ ዋና ሥራ ከሆኑት ሁለት አገልግሎቶች ውስጥ አንዱን ማለትም፤ በአሁን ወቅት ሰፊ የትራንስፖርት አገልግሎት በቅርብ ጊዜ ውስጥ እንደሚጀምር፤ ከነዳጅ አቅርቦት ጋር በተያያዘም በቂ የሆነ የተደራሽነት አገልግሎት ችግርን ለመቅረፍ እንደሚሰራ፤ ሌሎች አገልግሎቶችም በጥናት ላይ ተመስርተው እንደሚከናወኑ አስታውቀዋል፡፡
“በትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍ ጥራት ያላቸውን አውቶቡሶች በጥሩ ዋጋ እንግዛ በሚል ውሳኔ ላይ ከተደረሰ በኋላ፤ ከምስራቁ ዓለም የሚመጡ አንዳንድ ምርቶች በተወሰነ መልኩ የጥራት ችግር ስለሚገጥማቸው ከአውሮፓ ገበያ 50 አውቶቡሶችን ገዝተናል፡፡ ምስራቅ አፍሪካን ማገናኘት አለባቸው ተብሎ ሲታሰብም በጥንካሬያቸውና በዘመናዊነታቸው ላይ ትኩረት ተደርጎ ነው” ይላሉ ሥራ አስኪያጁ የግዥ ሂደቱን መነሻ ሲያብራሩ፤
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ የግዥ ሂደቱን በተመለከተ በርከት ያሉ የገበያ ጥናቶች ተደርገዋል፡፡ ጥራት ያለው ዕቃ ለማግኘት በሚደረግ ሂደት ውስጥም ፈተናዎች ነበሩ፡፡ ነገር ግን፤ በመጨረሻ የስዊድን ኩባንያ የሆነው ቮልቮ አሸናፊ በመሆን ጥራት ያላቸው አውቶቡሶች እንዲገዙ ተደርጓል፡፡
ግዥው ሲከናወን እያንዳንዳቸው ስምንት ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎባቸዋል፡፡ ለአጠቃላይ ግዥውም 400 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል፡፡ በአሁን ወቅት በሙከራ ደረጃ ከ50ዎቹ አውቶቡሶች ውስጥ አራቱ ብቻ በድሬዳዋ፤ በነቀምት፣ በሻሸመኔና በሀዋሳ መስመሮች አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው፡፡ ሙሉ አገልግሎቱም በቅርቡ መሰጠት ይጀምራል፡፡ ኩባንያው ምንም እንኳን ለጊዜው በ50 አውቶቡሶች ሥራ ለመስራት ያስብ እንጂ፤ ወደፊት እስከ 300 የሚደርሱ አውቶቡሶችን በመግዛት ከአገር ውስጥ አገልግሎት በተጨማሪ ከምስራቅ አፍሪካ ጋር የሚያስተሳስር ሲሆን፤ ከፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ጋር በመነጋገር እንደ አስመራ፣ ጅቡቲ፣ ጁባ፣ ሙምባሳና ካርቱም የመሳሰሉትን መዳረሻ ስፍራዎች ከኢትዮጵያ ጋር በየብስ ትራንስፖርት ለማስተሳሰር አቅዷል፡፡ ይህም በሶስት ዓመታት ውስጥ እውን ይሆናል፡፡ የሰው ሀይል ቁጥር ከማሳደግና ጥራት ያለው ባለሙያ ከመቅጠር ጀምሮ ሥራውን ሙሉ ለሙሉ ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚያስችል አዳዲስ የአሰራር ስርዓት ተዘርግቷል፡፡
አቶ እሸቱ በአሁኑ ወቅት ለአገሪቷ የህዝብ ቁጥር የሚመጥን የትራንስፖርት አገልግሎት እንደሌለ በመግለጽ፤ የኦዳ የተቀናጀ ትራንስፖርት አገልግሎት ህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ክፍያ አማራጭ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያገኝና በየጊዜው የሚጨመረውን አግባብ ያልሆነ ክፍያ በመተው በህጋዊ መንገድ መጓዝ እንዲችል ያደርገዋል፡፡ በተጨማሪ፤ ሌሎችም ወደዚህ አገልግሎት ውስጥ እንዲገቡ ያነቃቃል ብለዋል፡፡ የትራንስፖርት አማራጭ መብዛቱ ሰዎች እንደልባቸው ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው ለሚያከናውኑት ማሕበራዊ ህይወት ስኬታማነት ረጂ መሆኑን፤ አገሪቷም በዚህ ዘርፍ የምታገኘውን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እንደሚያሳድግም ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያን ከተቀሩት የምስራቅ አፍሪካ አገራት ጋር በየብስ ትራንስፖርት ማስተሳሰሩ፤ በአየር ትራንስፖርት የመሳፈር አቅም የሌላቸውንና በየብስ ትራንስፖርት መጓጓዝ የሚፈልጉትን ተጠቃሚ ለማድረግ፤ እንዲሁም በርካታ የቱሪስት ፍሰት እንዲኖርና የቱሪዝሙን ዘርፍ ለማሳደግ እንደሚረዳ ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል፡፡ ተቋሙ ይህንን ሲያከናወን ቢዝነሱን ከመስራት ጎን ለጎን ለሌሎች መሰል ኩባንያዎች ምሳሌ ለመሆን፤ በሌሎች አገራት የሚስተዋለውን የትራንስፖርት ስርዓት ተሞክሮ በአገር ውስጥ እንዲለመድ በማድረግ፣ በዘርፉ ያለውን ችግር በመቅረፍ ህዝቡ ያለእንግልት የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያገኝ ለማድረግም ሚናው ቀላል እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡
ሥራ አስኪያጁ እንዳሉት፤ ተቋሙ እየጀመረ ባለው የትራንስፖርት አገልግሎትም እስካሁን ሹፌሮችንና ኦፊሰሮችን ጨምሮ 200 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ እድል ፈጥሯል፡፡ እያንዳንዱ አገልግሎት ሰጪ አውቶቡስ ወዴት እየተንቀሳቀሰ እንዳለ፤ በምን ያህል ፍጥነት እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ፤ ንብረት እንዳይጎዳ በአጠቃላይ ሁኔታውን የሚዳስስ “ግሎባል ፖዚሽኒንግ ሲስተም፤ ጂፒኤስ” የሚገጠምለት ሲሆን፣ ይህ አሰራር በተለይም በአገሪቱ በየጊዜው እየበዛ የመጣውን የትራፊክ አደጋ ከመቀነስ አኳያ ያለው ትልቅ ሚና ተሞክሮ ሊወሰድበት ይገባል፡፡
ወደ ምስራቅ አፍሪካ ጉዞ ለማድረግ ትልቅ ፈተና እንደሚገጥመው ስጋታቸውን የሚገልጹት አቶ እሸቱ፤ በተለይ ጎረቤት አገር ከሆነችው ኬንያና ሌሎች የአውሮፓ አገሮች ልምድ በመቅሰም አገልግሎቱን እውን ማድረግ እንደሚቻልም ነው የተናገሩት፤ ከሞሮኮ ተነስቶ ወደ እንግሊዝ፤ ስፔን፤ ጀርመንና ፈረንሳይ የሚጓዘውን የ100 ዓመት እድሜ ያስቆጠረውን የትራንስፖርት አገልግሎት የሰጠ ተቋምም ለኩባንያው ትልቅ ተምሳሌት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
አቶ እሸቱ “አፍሪካ በተፈጥሮ ሀብት ከማንም በላይ ናት፡፡ ሀብቱን የመጠቀም አቅም ላይ ግን በርካታ ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡ ኦዳ ኩባያንም በዚህ ረገድ ከትራንስፖርት አገልግሎቱ ጎን ለጎን በማዕድን ስራዎች ላይ በመሰማራት ጉልህ ሚና የሚጫወት ይሆናል” ሲሉ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በማሰማራት የትራንስፖርት ችግር ለማቃለል አውቶቡሶችን ከማቅረብ ባሻገር ኩባንያው በሌላ ሴክተር ላይ የሚኖረውን ተሳትፎም ጠቁመዋል፡፡
አዲስ ዘመን ነሀሴ 24/2011
አዲሱ ገረመው