
አዲስ አበባ።- የኢትዮጵያ የባህር ትራንስ ፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በሞጆ ደረቅ ወደብና ተርሚናል የማስፋፊያ ሥራ ምክንያት የልማት ተነሺ ለሆኑ አባወራዎች እና እማወራዎች የኑሮ ማሻሻያ ስልጠና እየሰጠ መሆኑ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አሸብር ኖታ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ በሰጡት መረጃ፤ በሞጆ ደረቅ ወደብና ተርሚናል የማስፋፊያ ሥራ ምክንያት 59 የልማት ተነሺዎች መኖራቸውን ገልጸው፤ ምንም እንኳን እነዚህ አባወራዎች እና እማወራዎች ከቦታው ሲነሱ ተገቢ ካሳ የተከፈላቸው ቢሆንም መልሶ ለማቋቋምና ኑሯቸውን ለማሻሻል ድርጅቱ ከዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ለ34ቱ ተነሺዎች ሥልጠና እየሰጣቸው መሆኑን አስታውቀዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ ሥልጠናው በአርሶ አደሮቹ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ ሲሆን፤ በኑሮ ማሻሻያ ሥራዎች ለሚሠማሩ አርሶ አደሮች ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊት የተለያዩ የስጋ ከብቶች የማደለብ፣ የወተት ላሞች፣ የዶሮ እርባታ ዘዴና አያያዝ፣ የእንስሳት መኖ አዘገጃጀትና የጤና አጠባበቅ ላይ በጥናት የተደገፈ ሥልጠና እየተሰጣቸው ይገኛል።
ከሥልጠናው በኋላም ሰልጣኞች በፈለጉት የሥራ መስክ መሠረት አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶች ይሟሉላቸዋል። በስልጠናው ላይ መሳተፍ የማይችሉ አቅመ ደካሞችም የካሳውን ክፍያ በአግባቡ እንዲጠቀሙበት ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እየተሰራ ነው። በቀጣይ ለ53 የአርሶ አደር ልጆች ሥልጠና በመስጠት በሚሰራው የፕሮጀክት ማስፋፊያ ሥራ ውስጥ ተካትተው የሥራ ዕድል ይፈጠርላቸዋል።
የሞጆ ደረቅ ወደ ማስፋፊያው ሥራ ሲጀምር ነባሩን ጨምሮ በአጠቃላይ በ188 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፍ ሲሆን፤ ይህም አሁን ያለውን የኮንቴነር ተርሚናል አገልግሎት ወደ ኮንቴነር ማዕከልነት መቀየር ያስችለዋል። ከኢንዱስትሪ ፓርኩ ጋር የተሳለጠ ግንኙነትም ይኖረዋል።
አዲስ ዘመን ነሃሴ 24/2011
አዲሱ ገረመው