ኢትዮጵያ የማዕድን ዘርፉ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ከመደገፍ ባለፈ ለዜጎች የሥራ እድል መፍጠር እንዲችል ለይታ በመስራት ላይ ትገኛለች። የዘርፉ የእድገትና የለውጥ ማጠንጠኛ ተደርጎም ተወስዷል። ይህን ጉዳይ በመምዘዝ የሚተነትነው የአለም ባንክና አጋሮቹ፣ አለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን፣ የካናዳ የውጭ ንግድና ልማት ተቋም፣ የአውስትራሊያ መንግስት እና የእንግሊዝ አለም አቀፍ ልማት በቅንጅት ያስጠኑት ጥናት ነው። የተጠቃለለው የጥናት ሪፖርት እንዳመላከተው ሀገሪቱ በዘርፉ እምቅ ሃብት አላት።
ይህ ምቹ ሁኔታ ደግሞ በርካታ ሥራ ፈላጊ አካላትን ሥራ ማስያዝ የሚያስችል መሆኑ ተመላክቷል። ኢትዮጵያ ከወርቅ በተጨማሪ ለኢንዱስትሪ ግብዓት በሚውሉ ማዕድናት በተፈጥሮ የታደለች ነች። የሲሚንቶ ምርት ጥሬ ግብዓቶችና የማዕዘን ድንጋዮች በአነስተኛ ኢንዱስትሪዎች ይመረታሉ። ሌሎች የኢንዱስትሪ ማዕድናት ደግሞ በጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት በልማዳዊ አሰራር ይመረታሉ።
ዘርፉን ሊያበረታታ የሚችለው ሌላው ተጠቃሹ ደግሞ የፖታሽ ክምችት(ኦላና ፓታሽ ) ነው። እነዚህን አካባቢዎች በተደራጀና በሠለጠነ የሰው ሀይል ማልማት ከተቻለ ለበርካታ ሚሊዮን ዜጎች የሥራ እድል ይፈጥራል በተጨማሪም የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እንደሚታደግ እምነት ተጥሎበታል ሲል ሪፖርቱ ያብራራል።
ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ ዓመታት ለሥራ አጥ ዜጎች ሥራ ማስያዝ የሞት ሽረት ጉዳይ አድርጋ መያዟን የሥራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን በማቋቋም ጭምር አቋሟን አሳውቃለች። በዚህም ከ3 ሚሊዮን ዜጎች በላይ በ2012 በጀት ዓመት ሥራ እንዲይዙ ይደረጋል ብሏል። በተጨማሪም ዘርፎቹን ለይቶ በማስቀመጥ በመንግስትና በግል ባለሃብቱ ቅንጅታዊ ተሳትፎ የሥራ እድል ምንጭ ይሆናሉ በሚል እምነት ከጣለባቸው መካከል የማዕድን ዘርፉ ተጠቃሽ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ዘርፉ የ2011 ዓ.ም ጨምሮ ባለፉት ተከታታይ አመታት እያስመዘገበ የመጣው አፈጻጸም አበረታች አይደለም።
ከችግሮቹ ባልተላቀቀበት ሁኔታ የኢኮኖሚውን ዘርፍ በማነቃቃትና ሀገራዊ ለውጡ መሰረት እንዲይዝ በማድረግ ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል እንዲፈጥር መታጨቱ ዘርፉ ያሉበትን ችግሮች በምን መልኩ ተወጥቶ ነው ለዚህ ስኬት የሚበቃው? ምን ምቹ ሁኔታዎችስ ተፈጥረዋል? በሚሉት ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የሚመለከታቸው አካላት የሰጡት ምላሽ እንዲህ ተጠናቅሯል።
የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በዋናነት ከዘርፉ በሁለት መንገድ በሚገኙ ገቢዎች ተጠቃሚ ይሆናል በማለት ሃሳባቸውን የጀመሩት በማዕድንና ነዳጅ ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር የእቅድ ዝግጅት፣ክትትልና ግምገማ ዳይሬክተር አቶ ገረመው ነጋሳ፤ ማዕድናትን ወደ ውጭ ሀገር በመላክ በሚገኘው የውጭ ምንዛሪና በሀገር ውስጥ ደግሞ ፈቃድ ከመስጠት፣ከማደስ፣ ከማምረት( ከሎያሊቲ) እና ከነዳጅ ድፍድፍ ዘይት(ፒትሮሊየም) ደግሞ ተጨማሪ ኩባንያዎች ውል ሲፈራረሙ የሚገኙት ገቢዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከጊዜ ወደ ጊዜ ለሚስተዋለው የአፈጻጸም ማነስ ምክንያቱ ደግሞ በወርቅ ምርት ላይ ብቻ መንጠልጠላችን እና በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ ግጭቶች በወለዷቸው ችግሮች ነበር ያሉት አቶ ገረመው ከካናዳ መንግስት በተገኘ የፕሮጀክት ድጋፍ አማካኝነት ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር የሚያስችል ሰፊ ሥራ ተሰርቷል ባይ ናቸው።
ከዚህ ቀደም ኦፓል፣ኢመራልድና ሳፋየር የመሳሰሉት ውድ የጌጣጌጥ ማዕድናት በተገቢው እየተመረቱ አልነበረም ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በፕሮጀክቱ ድጋፍ ማዕድናቱ ከመሬት ሳይበላሹ መመረት እንዲችሉ፣ እሴት በሚጨምር መንገድ እንዴት መዘጋጀት እንዳለባቸው፣የተሻለ የገበያ አማራጭ እንዴት ማግኘት እንደሚቻል ለአምራቾችና ለሚመለከታቸው አካላት ሥልጠና ተሰጥቶ ወደ ሥራ ተገብቷል ይላሉ።
በመሆኑም ባለፉት ጊዜያት ያጣነውን የተሻለ ገቢና ሰፊ ሥራ እድል አሁን ማግኘት የምንችልበት ወቅት ነው። ቻይናና ሕንድ ከኢትዮጵያና ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጥሬ ማዕድናትን በመግዛት እሴት ጨምረው በማቅረብ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ዜጎቻቸው የሥራ እድል መፍጠር ችለዋል። ከፍተኛ የሀብት ምንጭ እንዲያገኙ አድርጓቸዋል። ሀገራችንም ይሄን ማድረግ የምትችልባቸው ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል ነው ያሉት አቶ ገረመው።
የሚኒስቴሩ የ2011 ዓ.ም በጀት አመት አፈጻጸም እንደሚያሣየው 4 ነጥብ 95 ቢሊዮን አዲስ የኢንቨስትመንት መጠን አስመዝግቧል። አምስት የምርትና 19 የምርመራ ፈቃዶች እንደሆኑ የተገለጸ ሲሆን የወርቅ ማዕድን፣የዕብነበረድ፣የብረት፣የከበሩ የጌጣጌጥና ሌሎች ማዕድናት ፍለጋ ኢንቨስት የተደረገው ካፒታልም አንድ ነጥብ 124 ቢሊዮን ነው።
ከዚህ በተጨማሪም 11 ነባር የነዳጅ ፍለጋና ልማት ሥራዎች ስምምነት ተፈጽሞ ለፍለጋው ከአንድ ነጥብ 96 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገ ሲሆን በአጠቃላይም 3 ነጥብ 088 ቢሊዮን ብር በሥራ ላይ መዋሉ ተጠቅሷል። ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ቢሆንም ለ2012 የሥራ እድል ለመፍጠር የሚያግዝ መሆኑም ተመላክቷል።
በሌላ በኩል በመላው ሀገሪቱ ያጋጠሙት አጠቃላይ የጸጥታ ችግሮች ለአልሚ ባለሃብቶች ከፍተኛ ፈተና ነበር ያሉት በሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ሞገስ ስብሃት ባለሀብቶቹ ከባለድርሻ አካላት ማግኘት ያለባቸውን አገልግሎቶች እንዳያገኙ በማድረግና ለኮንትሮባንድ ንግድ በማጋለጥ ለአፈጻጸሙ ማነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበራቸው ገልጸዋል።
በተጨማሪም የሚድሮክ ወርቅ አምራች ኩባንያ በአካባቢ ብክለት ችግር በጊዜያዊነት ሥራ እንዲያቆም በመደረጉ እና የአካባቢና የጤና ብክለት ችግር በዓለም አቀፍ ስታንዳርድ እንዲጠና ለማድረግ ረጅም ጊዜ በመውሰዱ፤ ኢዛና ወርቅ ኩባንያ ኬሚካልና ሌሎች ግብዓቶች ከውጭ ለማስገባት ተገቢውን የውጭ ምንዛሪ ድጋፍ ከብሔራዊ ባንክ ባለማግኘቱ ምክንያት የሚጠበቀውን ያህል ወርቅ ማምረት ባለመቻሉ፤ በሁሉም ወርቅ አምራች ክልሎች የኮንትሮባንድና ህገ ወጥ ንግድ መስፋፋትና ዘርፉን ትኩረት በመስጠት መምራት ባለመቻሉ፣ በተለያዩ ድንበር አካባቢዎች ህጋዊና ህጋዊ ያልሆኑ ሸቀጣ ሸቀጦችን መገበያያ/ በጥቁር ገበያ ሂሳብ/ ወርቅን መጠቀማቸው፤የቅንጅት ሥራዎች በተጠናከረ መንገድ ባለመፈጸማቸው፤ በሀገሪቱ ተከስቶ በነበረው የጸጥታ ችግር አምራቹ በተረጋጋ መንፈስ ማምረት አለመቻሉ ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።
እንደ አቶ ሞገስ ገለጻ የተለዩትን ችግሮች በመቅረፍ ሰፊ የሥራ እድል መፍጠር ይቻላል። ከመቼውም በላቀ ሁኔታ መንግስትም ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው። በመሆኑም ለዘርፉ ከተቀመጡት የትኩረት አቅጣጫዎች አንጻር የሚጠበቁት ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ፋይዳዎች በ2012 በጀት ዓመት መገኘት ይችላሉ ባይ ናቸው።
አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን መሳብና ነባር ፕሮጀክቶችን በማጎልበት ወደ ውጪ የሚላኩ ማዕድናትን በአይነት፣በጥራትና በመጠን በማሳደግ የምንዛሪ ግኝትና የሥራ እድል ፈጠራን ማሳደግ የቀጣይ የትኩረት መስኮች እንደሆኑ ተናግረዋል።
በ2012 ዓ.ም ሰፊ የሥራ እድል ይፈጠራል። ኢኮኖሚውን የሚያነቃቃ ገቢም ይገኛል። ለዚህም አምስት ፕሮግራሞች ተነድፈው ቁልፍ የአፈጻጸም አመላካቾች ተቀምጠውላቸዋል ያሉት አቶ ሞገስ በቀጣይ ለሥራ እድል ከተለዩት መካከልም የዘርፉን የማስፈጸም አቅም በእውቀትና በቴክኖሎጂ አጎልብቶ የማዕድንና ነዳጅ ፍለጋና ጥናትን በማጠናከር የከበሩና ብረት ነክ ማዕድናት፣ የኢንዱስትሪ ማዕድናት፣ የግብርና ግብአት ማዕድናት፣ የግንባታ እና የጌጥ/ ማጋጊያጫ ማዕድናት፣ የጌጣጌጥ (ቀለማማ ድንጋዮች) ማዕድናት፣ የአለኝታ ቦታዎች የሚለዩ ሲሆን የተፈጥሮ ጋዝና ነዳጅ ፍለጋና የባዮፊዩል (አማራጭ ነዳጅ) ጥናቶች ይከናወናሉ።
በኩባንያዎች የሚከናወኑ የምርመራ ፕሮጀክቶችን ከተጠሪ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ይሰራሉ። በዚህም የሥነምድር መረጃ ሽፋንና ጥራትን አሳድጎ ኢንቨስትመንትን በስፋት ለመሳብ የሚያስችል ሁኔታ ይፈጠራል። በማዕድንና ነዳጅ ዘርፍ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት በሰፊው በማስተዋወቅ ኢንቨስትመንትን በከፍተኛ ደረጃ የመሳብ ሥራ የሚከናወን ሲሆን የማዕድናት አለኝታዎችን የማስተዋወቅ ሥራም ይሰራል ተብሏል።
የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችና ኢንተርፕራይዞች በማዕድን ዘርፍ በግልም ሆነ በሽርክና እንዲሠሩ በሰፊው በማስተዋወቅ አዳዲስ ኢንተርፕራይዞች እንዲፈጠሩ ይደረጋል። በአጠቃላይ ከዚህ በታች በተጠቀሱት ተግባራትም ለ500 ሽህ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር ያስችላል ብለዋል አቶ ሞገስ ስብሃት።
የማዕድናት የውጭ ምርት አቅርቦትና ግብይት ጋር ተያይዞ ሰፊ የሥራ እድል የሚፈጠር ሲሆን ወርቅ በኩባንያዎች፣ በባሕላዊ፣ በአነስተኛ እና በኢንተርፕራይዞች፤ ታንታለም በባህላዊ አምራቾች፣ ከኢንዱስትሪ ማዕድናት በኩባንያዎች ጨው፣ ሶዳ አሽ፣ ድንጋይ ከሰል እና ከጌጣጌጥ ማዕድናት ኦፓል፣ ኤመራልድ፣ ሳፋየር፣ኳርትዝ፣ክሪስቶጰሬዝ፣ ጋርኔት፣ ቶርማሊን፣ አጌት፣አሜቲስት፣ አኳማሪን፣ አማዞናይት፣ ሩቢ (ኮሮንደም)፣ ሞርጋናይት፣ አምበር፣ ማንጋኔዝ ፣ ክሮማይት፣ ቤሪል እና ሲልካ ሳንድ በሰፊው እንዲመረቱ ተለይተዋል። ከእነዚህ ማዕድናት ሽያጭም 265 ነጥብ 82 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢም ይገኛል።
በአጠቃላይ በ2011 ዓ.ም በማዕድን ዘርፉ የተስተዋሉት ችግሮች ብዙ ዋጋ ያስከፈሉ ብቻ ሳይሆኑ አገር ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ገቢ ሳታገኝም ቀርታለች። ይሁን እንጂ ዘርፉ ካሉበት ተግዳሮቶች ተላቆ ሰፊ የስራ እድል ለመፍጠር እንዲችል ትኩረት አግኝቷል። በመሆኑም በ2012 ውጤታማ ስራ እንዲሰራ በተቋሙ የተያዘውን እቅድ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ በማድረግ የዘርፉን እድል ማለምለም ይቻላል።
አዲስ ዘመን ነሀሴ 23/2011
መሐመድ ሁሴን