ባርኔጣ፣ ኮፍያና ቆብ ሁሉም ለእራስ መከለያ ለተመሳሳይ ጥቅም የሚውል ቢሆንም የቆብ አገልግሎት ከባርኔጣና ከኮፍያ ይለያል፡፡ ቆብ መነኮሳት የሚያደርጉት ሲሆን፣ ባርኔጣና ኮፍያ ሁሉም ሰው የሚገለገልበት ነው፡፡ ባርኔጣ ወይም ኮፍያን በአብዛኛው የሚጠቀሙት ወንዶች ቢሆኑም ሴቶችም ያጌጡበታል፡፡ ለምን ይጠቀማሉ? የሚል ጥያቄ ቢቀርብ ደግሞ ምላሹ ለፀሐይ መከላከያ፣ ለማጌጫና ፀጉር የሌላቸው ደግሞ ጭንቅላታቸውን ለመሸፈን የሚውል ነው የሚሆነው፡፡
ባርኔጣና ኮፍያ ጥቅማቸው አንድ ቢሆንም አንዱን ለመለየት የፈለኩት የዛሬው የፈጠራ ባለሙያ አብዛኛው ሰው አዘውትሮ በሚጠቀመው ኮፍያ ላይ ስለሥራው የፈጠራ ሥራ ላስነብባችሁ ስለፈለኩ ነው፡፡ የፈጠራ ባለሙያው ከፊት ለፊቱ ረዘም ባለው ኮፍያ ላይ ድንቅ የፈጠራ ሥራ በመሥራት ኮፍያን ከተለመደው መጠቀሚያነት ባለፈ ለሌላ አገልግሎትም እንዲውል ማድረግ ችሏል፡፡
የፈጠራ ባለሙያው ተማሪ ደረሰ ቱጫ ይባላል፡፡ በደቡብ ክልል ሀዋሳ ከተማ በሚገኘው ታቦር መሰናዶ ትምህርት ቤት የ11ኛ ክፍል ተማሪ ነው፡፡ ከመደበኛ ትምህርቱ ጎን ለጎን የትምህርት ክፍለ ጊዜውን በማይነካ ተሰጥኦውን በመጠቀም የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡
የፈጠራ ሥራው መከላከያ ሠራዊቱንም ተደራሽ ያደረገ ነው፡፡ ለተንቀሳቃሽ ስልክም እንዲሁ እንዲያገለግል ተደርጎ ነው የተሠራው፡፡ የሠራዊት አባላት ለመገናኛ የሚጠቀሙበት በእጃቸው ይዘው የሚንቀሳቀሱት መገናኛ መሣሪያ በውጊያ ላይ ወይንም በእጅ ለመያዝ በማይመች ሁኔታ ውስጥ ሲሆኑ በኪሳቸው ውስጥ አድርገው በቀላሉ ለመገናኘት የሚያስችል ፈጠራ ነው፡፡
የሠራዊት አባላቱ በማይመች ሁኔታ ውስጥ ሲሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ መገናኛውን ሁልጊዜም በእጅ መያዝ አይጠበቅባቸውም፡፡ በኪሳቸው ውስጥ በማድረግ መረጃ ለመለዋወጥ ያስችላቸዋል፡፡ በተመሳሳይ ለተንቀሳቃሽ ስልክ ጥቅም ላይ የሚውለው ይህ ፈጠራ የብዙ ሰዎች ስጋት የሆነውን የተንቀሳቃሽ ስልክ ስርቆት ለማስቀረት ይረዳል፡፡ ሰዎች ስልካቸውን ከኪሳቸው ሳያወጡ ባደረጉት ኮፍያ በመታገዝ የስልክ መልዕክታቸውን መለዋወጥ ይችላሉ፡፡
«በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ» እንዲሉ በአናት ላይ የሚደረገው ኮፍያ በተገጠመለት የኤሌክትሪክ ኃይል መሰብሰቢያ አማካኝነት የስልክና የመገናኛ መገልገያዎችን ጥቅም እንዲሰጡ በማድረግ ከስርቆት ስጋት ነፃና ለአጠቃቀም ምቹ በመሆኑ ፈጠራው ያስደንቃል፡፡ በእጅ ባለ ነገር ችግር መፍታት ማለት እንዲህ ነው፡፡
በኮፍያው ላይ የተሠራው ፈጠራ ጥቅም ላይ የሚውለው በኮፍያው ፊት ለፊት ላይ በተገ ጠመው የኃይል መሰብሰቢያ አማካኝነት ነው፡፡ የተሰበሰበው ኃይል ወደኤሌክትሪክ ኃይል እንዲቀየር ያደርጋል፡፡ በአንድ ጊዜም 3ነጥብ 7ቮልት ኃይል የመሰብሰብ አቅም አለው፡፡ በዚህ አማካኝነት የስልክ ግንኙነቱ ይደረጋል፡፡ የሚሰ በሰበው ኃይል በሁለት መንገድ ሲሆን፤አንዱ በቀጥታ ከፀሐይ ኃይል፤ ሌላው ደግሞ ኮፍያውን ከሚጠቀመው ሰው በሚወጣ ሙቀት ነው፡፡
ኮፍያው ወልቆ በቤት ውስጥ እንዲቀመጥ ካልተደረገ በስተቀር የኃይል መቋረጥ አያጋጥምም፡፡ ወልቆ ሲቀመጥም የተጠራ ቀመው ኃይል እስኪያልቅ ይሠራል፡፡ የስልክ ግንኙነቱንም ያለ ጆሮ ማዳመጫና በጆሮ ማዳመጫ መጠቀም እንደ ሚቻል ነው ተማሪ ደረሰ የገለጸው፡፡ ያለጆሮ ማዳመጫ በሚሞሪ አማካኝነት ድምጹን በመስማት መጠቀምም እንደሚቻል ተናግሯል፡፡
ተማሪ ደረሰ ከቫዝሊን ማስቀመጫ እቃዎች፣ ከባትሪ፣ ለሶላር ከሚውሉና ሌሎችም ጥቅም ላይ ውለው የተጣሉ ቁሳቁሶችን በመጠቀም ነው ፈጠራውን የሠራው፡፡ ተማሪ ደረሰ ፈጠራውን ለመሥራት አንድ ዓመት ጊዜ ወስዶበታል፡፡ ዲዛይን ሲያወጣ፣ ከምን እንደሚሠራ እንዲሁም የገበያ አዋጭነቱን ሲያጠና ነው ይህን ያህል ጊዜ የወሰደበት፡፡ የሠራውን የፈጠራ ሥራ በራሱና አንዳንድ የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚዎችም እንደተጠቀሙበት ማረጋገጡን ይናገራል፡፡
ተማሪ ደረሰ ከዚህ ቀደም የመሬት መንቀጥ ቀጥ መከሰቱን ቀድሞ የሚያሳውቅ በፀሐይ ኃይል የሚሰራ ጫማ ሠርቷል፡፡ አንድ ሰው በፎቅ ላይ ሆኖ የመሬት መንቀጥቀጥ ቢያጋጥም ቀድሞ መረጃውን በማግኘት ቶሎ እንዲያመልጥ ምልክት ይሰጠዋል፡፡ በዚህ መልኩ ከአደጋ ሊተርፍ ይችላል፡፡
ተማሪ ደረሰ እንዲህ ፈጠራ የታከለበት ቴክኖሎጂን ለመሥራት በትምህርት ቤቱና በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር በአውደ ርዕይ ዝግጅት ላይ በመጋበዝ ከሚደረግለት አንዳንድ ድጋፍና ማበረታቻ በተጨማሪ ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር የሚሠራው በሳይንስ፣ ቴክኖሎጅ፣ኢንጂነሪንግና ሂሳብ ላይ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን የሚያግዝ ‹‹ስቲም ሲነርጂ››የተባለ ድርጅት በሥልጠና፣ በውድድሮችና ኤግዚቢሽኖች ላይ እንዲሳተፍ እገዛ እንደሚያደርግለት ይገልጻል፡፡
ተማሪ ደረሰ የፈጠራ ክህሎቱን በማሳደግ እራሱንና ሀገርን ለመጥቀም ከፍተኛ ፍላጎት አለው፡፡ፍላጎቱን ለማሳካትም በትምህርቱ ጠንክሮ እየተማረ መሆኑን ይናገራል፡፡ ለተሻለ ትምህርትም በግሉ የውጭ የትምህርት ዕድል በመሞከር ላይ ይገኛል፡፡
እንደተማሪ ደረሰ የፈጠራ ክህሎት ያላቸውንና በሀገር ደረጃም ለሳይንስና ቴክኖሎጅ የተሰጠውን ትኩረት በተለያየ መልኩ በማገዝ ላይ የሚገኘውን «ስቲም ሲነርጂ» የተባለው ተቋም በኢትዮጵያ ተወካይ የሆኑትን አቶ ጌታቸው ገዛኸኝን አነጋግረናል፡፡ ስለድርጅቱ ስያሜ እንደገለጹት ሳይንስ፣ ቴክኖሎጅ፣ ኢንጂነሪንግና ሂሳብን በአንድ ላይ አጣምሮ በመያዙ ነው ስያሜው የተሰጠው፡፡
ድርጅቱ በሳይንስ ዘርፍ የተለያየ ክህሎት ያላቸውን ወጣቶችና ተማሪዎች ክህሎታ ቸውን የሚያዳብር ሥልጠና በመስጠት፣ ለሥራ የሚያስፈልጋቸውን ግብአት በማገዝና የተለያየ ድጋፍ በማድረግ እንዲሁም በኤግዚቢሽንና በውድድር ላይ የሚሳተፉበትን ቅድመ ሁኔታ በማመቻቸት በማገዝ ላይ ይገኛል፡፡ በቅርቡ የተከበረውን የዓለም ሳይንስ ቀንን ምክንያት በማድረግም በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጅ ሚኒስቴር በተዘጋጀው ኤግዚቢሽን ላይ እንዲሳተፉ በማመቻቸት ሥራዎቻቸውን እንዲያሳዩና እርስ በርስም ተሞክሮ እንዲለዋወጡ በማድረግ እንዳገዛቸው አመልክተዋል፡፡ ዋናው የባህሪ ለውጥ ማምጣትና ክህሎት መፍጠር እንደሆነም አመልክተዋል፡፡
እርሳቸው እንዳሉት ድርጅቱ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጅ፣ ኢንጂነሪንግና ሂሳብ ትምህርት መደበኛ ትምህርቱን እያገዘ ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንዲያስችልና የሀገሪቷን የ70/30 የትምህርት ፖሊሲ ለማጠናከር ከ8ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ሥራውን የጀመረ ሲሆን፣ በዋናነትም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር የሚሠራ ነው፡፡ የመጀመሪያ ማዕከሉንም በቢሾፍቱ ነው ያቋቋመው፡፡ በሂደት በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች በማስፋፋት ማዕከሎቹ ወደ 22 ከፍ ብለዋል፡፡ ሥራዎች የሚከናወኑት በቤተሙከራና ፕሮጀክቶችን በማገዝ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
ድርጅቱ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር የሚሠራው ከአንደኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ የሚገኙ ተማሪዎችን ማዕከል አድርጎ ቢሆንም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር አብሮ መሥራት የፈለገው በምርምር ሥራና በማህበረሰብ አገልግሎት ህብረተሰቡን ስለሚደርሱ በእነርሱ አማካኝነት በቀላሉ ለመሥራት እንዲያስችለው እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ በተጨማሪም የትምህርት ተቋማቱ የሚደረገውን ድጋፍ ማገዝ የሚችል የሰው ኃይልና የተጀመሩ የፕሮጀክት ሥራዎችን የማስቀጠል አቅም ስላላቸው እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
አቶ ጌታቸው እንዳሉት «ስቲም ሲነርጂ» ዋና መሥሪያ ቤቱ በአሜሪካን ቦስተን ሲሆን፤ በተለያዩ ሀገሮች ቢሮዎች ቢኖሩትም በስፋት በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኘው ግን በኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡
ለምለም መንግሥቱ