አዲስ ዘመን፡- መንግሥት ኢኮኖሚውን ሪፎርም ማድረግን በተመለከተ እስከ አሁን ለሪፎርሙ መደላድል ሲሠራ መቆየቱም ይነገራል። ከዚህ በኋላ በኢኮኖሚ ሪፎርም ላይ በትኩረት እንደሚሠራ እየገለፀ ነው። ሪፎርሙ በዋናነት ምን ምን ተግባሮች የሚከናወኑበት ነው?
ኮሚሽነር አበበ፡- በአሁኑ ወቅት እንደሚታወቀው በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራው ማክሮ ኢኮኖሚክ ኮሚቴ ሰፊ የሆነ የኢኮኖሚ ሪፎርም አጀንዳ በመንደፍ ለማስፈፀም በየጊዜው እየተገናኘ እየሠራ ነው። የሪፎርሙ አጀንዳ ፕራይቬታይዜሽን እና ሊብራላይዜሽን እንደሚያስፈልጋቸው በታመነባቸው የተለያዩ ዘርፎች ላይ ጥናት ተካሂዷል። ጥናቱ ወደ ሥራ ማስገባት፣ የግል ዘርፉን ማበረታት፣ የሀገሪቱን የበጀት እጥረት ማስተካከል፣ የገቢ ምንጭን ማስፋት፣ የውጭ ንግድን ማበረታታት፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረትን መፍታት፣ የግል ዘርፉ ከቢዝነስ ከባቢ ሁኔታ ጋር ተያይዞ የሚገጥመውን የተለያዩ ተግዳሮቶች እና ማነቆዎች መፍታት እና ለሀገሪቱ ዜጎች በቂና አስተማማኝ የሥራ ዕድል መፍጠርን የሚያካትት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ በኋላ ኢንቨስትመንቱ ወይም የኢኮኖሚ ልማቱ የሚለካው በሚያስገኘው የሥራ ዕድል መጠን ነው እየተባለ ነው፤ ይህ ማለት ምን ማለት ነው?
ኮሚሽነር አበበ፡- እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ የወጣት ሀገር ናት። በዓለም ባንክ ጥናት መሰረት በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ በሥራ ሊሰማሩ የሚችሉ ዜጎች ከሀገሪቱ ጠቅላላ ህዝብ ቁጥር ወደ 60 በመቶ ገደማ የሚሆን ሲሆን፣ በየዓመቱ በሁለት ሚሊዮን እያደገ ይገኛል። በመሆኑም በፍጥነት እየጨመረ የሚገኘውን የሠራተኛ ቁጥር ከኢንዱስትሪያላዜሽን፣ ኢንቨስትመንት ፍሰት እና ኢኮኖሚ ልማት ጋር በማጣመር ለሥራ ፈላጊዎች በቂና አስተማማኝ የሥራ ዕድል መፍጠር ከመቼውም በላይ የመንግሥት መሰረታዊ የፖሊሲ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሀገሪቷ የብሔራዊ ህልውና መለኪያ እንዲሆን ያደርገዋል።
አዲስ ዘመን፡- መንግሥት በተያዘው የበጀት ዓመት ለሦስት ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር በያዘው እቅድ መሰረት የኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ሚና ምን ያህል ይሆናል ብለው ያምናሉ?
ኮሚሽነር አበበ፡- መንግሥት የግል ዘርፉ ከቢዝነስ ከባቢ ሁኔታ ጋር ተያይዞ የሚገጥሙትን የተለያዩ ተግዳሮቶችና ማነቆዎች በተለይም ከትራንስፖርት፣ የሀገሪቷን የውጭ ምንዛሬ መጨመር፣ የመሰረተ ልማት አቅርቦት እና በፌዴራል እና በክልል የሚገኙ የተለያዩ የመንግሥት ተቋማት አሠራር ቀላል ተገማች ግልጽ አለመሆን ጋር ተያይዘው የሚነሱትን በመለየት የመፍትሄ ሃሳቦችን ወደ ሥራ የማስገባት ሥራ በስፋት ጀምሯል። ይህም የግል ዘርፉን በማበረታታት እና ጥራት ያለው የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ወደ ሀገሪቷ በመሳብ ለሀገሪቷ ለሥራ ፈላጊ ዜጎች ጥራት ያለው፣ በቂ፣ አስተማማኝ እና ዘላቂ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ይረዳል፤ ዘላቂ የሆነ ከፍተኛ የሆነ የእውቀት እና የክህሎት ሽግግርን እንዲኖር ያደረጋል።
አዲስ ዘመን፡- የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ እና ወደ ፓርኮቹ የሚገቡ የውጭ ባለሀብቶች እየጨመሩ መምጣታቸው ይታወቃል። ከኢንቨስትመንቱ የሚገኘው ጥቅምስ እየጨመረ ነው?
ኮሚሽነር አበበ፡- በአሁኑ ወቅት ሰባት የግል ኢንዱስትሪ ፓርክ አልሚዎች እና አስራ አንድ የመንግሥት ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ተጠናቀው እና የማመረቻ ሼዶች ሙሉ በሙሉ በባለሀብቶች ተይዘው ወደ ምርት በመግባታቸው ምክንያት ለሀገሪቷ ከፍተኛ የሆነ ጥቅሞችን እያስገኙ ነው። ይህም ከ70 ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች (ወደ 80 በመቶ ሴቶች) ጥራት ያለው፣ ዘላቂ እና አመርቂ የሥራ ዕድልን መፍጠር፣ የዕውቀት ክህሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማረጋገጥ፤ የውጭ አገር ባለሀብቶች ከሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ጋር የበለጠ በግብዓት አቅርቦት ትስስሮሽን በመፍጠር እና በሀገር ውስጥ የሚመረተውን ምርት በመጨመር እና ለሀገር ውስጥ ገበያ እና የውጭ አገር ንግድን በማበረታታት የውጭ ምንዛሬን እጥረትን ከመቅረፍ አኳያ ያለው አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ ነው።
አዲስ ዘመን፡- አገሪቱ በቀጣይም የኢንዱስትሪ ፓርኮቹን ወደ 30 የማሳደግ ዕቅድ እንዳላት መረጃዎች ይጠቅሳሉ። በሥራ ላይ ያሉት ፓርኮች ያስገኙት ፋይዳ ተገምግሞ ነው ወደ ግንባታው የሚገባው? የት አካባቢስ ነው የሚገነቡት? በእዚህ ምን ያህል ሠራተኞችን ለማቀፍስ ታቅዷል?
ኮሚሽነር አበበ፡- መንግሥት ከዚህ በኋላ ለኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ምቹ የሆነ የለማ መሬትን ለግል አልሚዎች እንደሚያስተላልፍ እንጂ መንግሥት በራሱ ወጪ ፓርኮችን እንደማያለማ አቅጣጫ ተቀምጧል። ከዚህም ጋር ተያይዞ መንግሥት የአዋጪነት እና የሥነ-ምህዳር ጥናት አካሂዶ ከለያቸው ስፍራዎች መካከል አሶሳ፣ ሠመራ እና አይሻ ይገኙበታል። በዕቅድ ላይ ያሉት ኢንዱስትሪ ፓርኮች ሙሉ በሙሉ ተገንበተውና ለምተው ወደ ምርታማነት ሲሸጋገሩ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ ተብሎ ይገመታል።
አዲስ ዘመን፡- የውጭም ይሁኑ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች የተለያዩ የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎችን እንዲጠቀሙ ምቹ ሁኔታ ቢፈጠርላቸውም ኢንቨስትመንቱን ወደፊት ሊያራምዱ እንዳልቻሉ ይገለፃል። በዚህ የተነሳም የሀገር ሀብት መባከኑም ይታወቃል።
ይህ ችግር እንዳይደገም ወደ ፓርኮች የሚገቡ ባለሀብቶች የሚመለመለበት መንገድ እንዴት እየተሠራበት ነው?
ኮሚሽነር አበበ፡- የውጭም ይሁኑ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ኢንቨስመንታቸውን በሚፈለገው የጥራት እና የብቃት መጠን ለማስኬድ አለመቻልን ለማስተካከል ይሠራል። በዚህም አንደኛ በተመረጡ ሴክተሮች፣ በቂ አቅም እና ጥራት ያለው ኢንቨስትመንትን
መሳብ፣ ሁለተኛ ደግሞ የገቡትንም በማቆየት የተሳለጠ የድሕረ ኢንቨስትመንት ድጋፍ አገልግሎት በመዘረጋት እና የሚገጥሟቸውን ዋና ዋና ተግዳሮቶች ማለትም የመሠረተ ልማት አቅርቦት መጓደል፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የፀጥታና አለመረጋጋት ችግሮች እና የመሳሰሉትን በመፍታት ተወዳዳሪ ማድረግ ሲሆን፣ ሦስተኛው ደግሞ ጥራት ያለው ምርት፣ የሥራ ዕድል እና በቂ የሆነ የእውቀት እና ክህሎት ሽግግር በባለሀብቶች እንዲከናወን ጥብቅ የቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋት ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- የኢንዱስትሪ ፓርኮች መገንባት ቀደም ሲል ያጋጥም የነበረው የመሰረተ ልማትና የቦታ ጥያቄ ችግር እንዲፈታ ማስቻሉ ይነገራል። ይሁንና በአሁኑ ወቅት ደግሞ ኢንቨስትመንቱ በተለይ በኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት ክፉኛ እየተፈነ ነው ይባላልና ይህን ችግር እንዴት ለመፍታት ታስቧል?
ኮሚሽነር አበበ፡- መንግሥት የኃይል አቅርቦት ችግርን በበቂ መልኩ ለመፍታት ከሁለት በኢነርጂ እና በመሠረተ ልማት ዘርፍ እውቅና ካላቸው ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል። የመጀመሪያው በኢነርጂ እና በመሠረተ ልማት ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ስመ ጥር ከሆነው ሴመንስ (SIEMENS) ከተባለው የአውሮፓ ኩባንያ ጋር የተደረገው ስምምነት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በባለፈው ቤልት ኤንድ ሮድ ፎረም (Belt and Road Forum) ላይ ስቴት ገሪድ (State Grid) ከተባለው ግዙፍ የቻይና ኩባንያ ጋር የተደረገው ስምምነት ነው።
እነዚህ ሁለት ስምምነቶች በሀገሪቷ እና በኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ እየታየ ያለውን የኃይል አቅርቦት እጥረት እልባት የሚሰጡ ይሆናሉ። በአሁኑ ወቅትም ስምምነቶቹን ወደ ሥራ ለማስገባት ከሚመለከታቸው የተለያዩ የመንግሥት ባለድርሻ አካላት ቡድን ተዋቅሮ አብረን እየሠራን እንገኛለን። ከዚህም በተጨማሪ ሌሎች የኃይል አቅርቦት ምንጮች እንደ ፀሐይ፣ ንፋስ በመሳሰሉት በመጠቀም ሃይል ለማመንጨት ከሚችሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ስምምነት ላይ መድረስ ተችሏል።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መዳረሻ እየሆነች ትገኛለች። ለእዚህ አንዱ ምክንያት ደግሞ የኤሌክትሪክ አቅርቦት በርካሽ የሚገኝባት መሆኗ ነው። ሀገሪቱ በኤሌክትሪክ ታሪፍ ላይ ያደረገችው ጭማሪ በተፈላጊነቷ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አያሳርፍምን?
ኮሚሽነር አበበ፡- ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በአለፉት አስርት ዓመታት ውስጥ በአራት እጥፍ አድጓል።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የንግድና የልማት ጉባዔ (የUNCTAD) የ2018/2019 እ.ኤ.አ የኢንቨስትመንት ፍሰት ሪፖርት እንደሚያመለክተው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከፍተኛ የሆነ የኢንቨስትመንት ፍሰት መዳረሻ ከሆኑት አምስት አገራት መካከል ትመደባለች። ለዚህም ውጤት ሀገሪቷ በዝቀተኛ ዋጋ የምታቀርበው የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ጉልህ ሚና ይጫወታል።
መንግሥት የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ዋጋ ተመን ላይ ከአስር ዓመታት በላይ ምንም አይነት ማሻሻያ ሳይደረግ ቆይቷል። አሁን ተግባራዊ የተደረገው የዋጋ መሻሻያ ባለሀብቶችን በማይጎዳ መልኩ እንዲተገበር በማሰብ ጭማሬው በሚቀጥሉት አራት ዓመት ውስጥ (በዓመት እየተከፋፈለ) ቀስ በቀስ ወደ ሥራ እንዲገባ ተደርጓል። የመጨረሻው ዓመት የኤሌክትሪክ ሃይል ተመንም ኢትዮጵያን ዝቅተኛ የኤሌክትሪክ ዋጋ ተመን አላቸው ከሚባሉት አገራት ተርታ የሚያወጣት አይሆንም፤ በመሆኑም በሀገሪቷ የኢንቨስትመንት ፍሰት መዳረሻነትም ሆነ ተወዳዳሪነቷ ላይ ሊያሳድር የሚችለው አሉታዊ ተጽኖው የጎላ አይሆንም።
አዲስ ዘመን፡- አገራችን ንግድና ኢንቨስትመንት ቶሎ ከማይጀመርባቸው አገሮች በሚል ከተፈረጀችበት ለመውጣት መንግሥት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ነው። ይህን ተከትሎም ለውጦች እየተመዘገቡ መሆናቸው ይገለፃል። ይህ እርምጃ በኢንቨስትመንቱ ላይ ምን ያህል ለውጥ ያመጣል ብለው ያምናሉ?
ኮሚሽነር አበበ፡- በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ ዕድገት እና ሥራ የመፍጠር አቅም እጅግ የተገደበ፣ የወጣቶች የሥራ ፈጠራ ተነሳሽነት አነስተኛ የሚባል ነው። ለዚህም ውድድርን የሚገድቡ፣ ለጊዜ ብክነትና የገንዘብ ወጪ የሚዳርጉ፤ እንዲሁም ተገማችነት የሌላቸው እና ጊዜ ያለፈባቸው የመንግሥት ተቋማዊ አሠራሮች እና የሕግ ማዕቀፎች በዋነኝነት እንደምክንያትነት ይጠቀሳሉ። የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ የግሉን ዘርፍ ከማበረታታት ይልቅ ማነቆ ሆኖ እንደቆየ የማይካድ እውነታ ነው።
በመሆኑም ባለፈው ታህሳስ ወር በተደረገው የቢዝነስ እና ኢንቨስትመንት ከባቢ ሁኔታን የማሻሻል ውይይት ላይ መንግሥት ለግል ዘርፉ ማነቆ የሆኑትን አሠራሮች ለማዘመን እና ኢትዮጵያ ንግድና ኢንቨስትመንት ቶሎ መጀመር መቻል በ/doing business/ ላይ ያላትን ደረጃ ለማሻሻል በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ መሪነት፤ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስተባባሪነት፤ 10 የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ያካተተ የስትሪንግ ኮሚቴ ወይም ቡድን ተቋቁሟል። በዚህም መሠረት ባለፉት ወራት ማሻሻያዎች ተደርገዋል። እነዚህም በዋነኛነት እና በጥቅል ሲታዩ የግል ቢዝነስን በመክፈት፣ በማስተዳደር እና በመዝጋት ወቅት ያሉትን የመንግሥት አሠራሮች ቀላል፣ የተቀላጠፈ፣ ተገማች እና ዘመናዊ እንዲሆኑ ማድረግ የሚያስችሉ ናቸው። የኢንቨስትመንት ፍሰት እና የግል ዘርፉን ተወዳዳሪነትና ሥራ የመፍጠር አቅም ከመጨመር ባሻገር ወጣቶች አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን የመሞከር እና ችግሮችን የመውሰድ ተነሳሽነታቸው የመጨመር፣ ግብርን ግዴታ ለመወጣት የሚተጋ ዜጋ ለመፍጠር እና ሙስናን ጨምሮ ብልሹ አሠራሮችን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ አስተዋጽኦ ያመጣሉ ተብሎ ይገመታል።
በሥራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ሕግ ማዕቀፍ (የኢንቨስትመንት አዋጅ ቁጥር 769/2004 እና የኢንቨስትመንት ደንብ ቁጥር 270/2005 (እንደተሻሻሉ)) በአተገባበር ላይ ኢትዮጵያ ለኢንቨስተሮች ክፍትም ሆነ ምቹ እንዳልሆነች የሚያሳይ ሁኔታ ነበረው። በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ባለው የኢንቨስትመንት ሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያ በአገሪቱ የግል ዘርፉን ተሳትፎ ለማሳደግ እየተካሄዱ ካሉ ለውጦች ጋር እንዲናበብ ከማድረግ ባሻገር የአገር ውስጥ እና የውጭ ባለሀብቶች ሊሳተፉ የሚችሉባቸውን ዘርፎች በመከለስ የማስፋት ሥራ ተሠርቷል።
በሥራ ላይ የቆየው የኢንቨስትመንት ሕግ ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የተፈቀዱትን ዘርፎች በግልጽ በመዘርዝር የተቀሩትን በሙሉ ለተሳትፎ የሚከለክል የአቀራረብ ስልት (positive list approach) የሚከተል ነው። የሕግ ማሻሻያው ይህን አሠራር በመቀየር ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የተከለከሉትን ዘርፎች ብቻ በግልጽ በመዘርዘር የተቀሩትን ዘርፎች ሙሉ በሙሉ ለውጭ አገር ኢንቨስትመንት የሚከፍት (negative list approach) አሠራርን ዘርግቷል። በተጨማሪም የተጠቃለለ የሕግ ሰነድ በመጠቀም ማለትም በተለያዩ ሕጎች የወጡትን በመሰብሰብ የኢንቨስትመንት አስተዳደር እና ቁጥጥር ሥርዓቱን ግልጽ፣ ተገማች፣ የተሟላ፣ ቀልጣፋ እና ዘመናዊ ማድረግ የሚያስችል ነው፤ የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎችን ወጥ እና ውጤታማ በሆነ መልኩ በማስተዳደር፣ በተቋማት መካከል ቅንጅትን በመፍጠር የኢንቨስትመንት ማነቆ ለሆኑ ጉዳዮች በአፋጣኝ መልኩ መፍትሔ ለመስጠት በማስቻል እና ግልፅ እና ውጤታማ በሆነ መልኩ የባለሀብቶች ቅሬታ የሚስተናገድበት ሥርዓት የሚዘረጋበትም ነው። በእነዚህ ሥራዎችም ወደ ሀገሪቱ የሚመጡ ኢንቨስተሮችንም ሆነ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን የመደገፍ ተግባር ይከናወናል።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ምላሽ አመሰግናለሁ።
ኮሚሽነር አበበ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ነሀሴ 21/2011
አስቴር ኤልያስ