ሀረሪዎች ከቤት አሰራር ጀምረው ለየት የሚያደርጋቸው ብዙ ባህሎች አላቸው። የቤት አሰራራቸውን ደብሪ ጋር እያሉ ይጠሩታል። አሰራሩ ጣሪያው ከእንጨትና አርማታ ሲሆን ይህ የሆነበት ምክንያትም በሙቀት ጊዜ ቅዝቃዜ፣ በቅዝቃዜ ጊዜ ደግሞ ሙቀትን እንዲፈጥርላቸው ነው። ግርግዳው ደግሞ ከድንጋይ ውጤቶች የተሰራ ነው። ውስጡ ብዙ ለየት ያሉ ቁሶችንም ሆነ ለአገልግሎት የሚውሉ የቤት ውስጥ ገጽታዎችን ይይዛል።
እኛም ዛሬ ከውጪው አንስተን ውስጥ ድረስ በመዝለቅ ባህሉን በስፋት የሚያስቃኘውን ሙዚዬም ልናስጎበኛችሁ ወደድን። ሙዚዬሙ ብዙ ሀረሪዎችን የሚገልጥ ነገሮችን ይዟል። ለዛሬው የመረጥነው በሀረሪዎች ዘንድ ሁሉም ቤት ሊታዩ የሚችሉትን ብቻ ሲሆን፤ እነርሱም አምስቱ መደቦችና ምሳሌነታቸው። እንዲሁም በእነርሱ ዙሪያ ስለሚከወኑ ተግባራት ነው።
የሙዚየሙ በሩም ሆነ መስኮቱ የክልሉ ሴቶቹ ለሰርግና ለበዓላት እጅና እግሮቻቸውን እንደሚያስውቡት ንቅሳት ዓይነት በሚያምሩ ቀለማት ጥበብ ተውበዋል። በተለይም በጋብቻ ጊዜ እንስቶች የተለያየ ቅርጽ ያለው ንቅሳት እግርና እጃቸውን ይሸልማሉ። ይህ ልምዳቸው ይሆናል ሙዚዬሙም ላይ እንዲሰፍር ያደረገው። ይህንን እዩኝ እዩኝ የሚለውን የውጪ ገጽታ አጠናቀን ወደ ውስጥ ስንገባ ደግሞ ሌላ ነገር እንመለከታለን። በአንድ አይነት ቀለም የተዋበ ቢሆንም በልዩ ልዩ ቁሳቁሶች ላይ መገኘቱ ውበቱን በበርና መስኮቱ ላይ ከተመለከትነው የላቀ አድርጎታል። በተለያዩ ክፍሎች ውስጥ የሚታየው ውበት አትውጡ የሚያሰኝ ነው። በውስጥ ስለሚገኙት አስደናቂና ውብ ነገሮች የሐረሪ ክልል ባህል ማዕከል ሰራተኛና የሙዚዬሙ አስጎብኚ የሆኑት ወይዘሮ ሩቅያ መሀመድ እንዲህ ሲሉ አስረድተውናል።
እርሳቸው እንደገለጹት፤ ሙዚዬሙ ከአምስት መቶ ዓመት በላይ እድሜን ያስቆጠረ ነው። በሀረሪዎች ዘንድ የቤት አሰራር ባህልን የተከተለ ነው። በተለይ በሁሉም የእስልምና ሀይማኖት ተከታዮች ዘንድ አምስቱ መደቦች (የሰዎች መቀመጫ) በሁሉም ቤት ያገኛሉ። እነዚህ አምስት መደቦች በእድሜ ደረጃ፣ በእውቀት (ባላቸው የትምህርት ሁኔታ) እና በጾታ ልዩነት የሚሰሩ ናቸው። መደቦቹ በስፋትና በመጠናቸው ይለያያሉ።ከአንደኛው መደብ ብንጀምር «አሚር ነደባ» ይባላል። አሚር ማለት ንጉስ ማለት ነው። ስለሆነም ንጉሱ የሚቀመጥባት መደብ ነው። ቀደም ባሉት ጊዜያት ማለትም ከአምስት መቶ ዓመት በፊት ሀረሪዎች በአሚር ወይም በንጉስ ይተዳደሩ ስለነበር ይሄ ለእርሱ መቀመጫነት እንዲሆን አድርገው ይሰሩታል። ይሁንና የመንግስቱ ሥርዓት በመለወጡ መደቡን የሚቀመጥበት የቤቱ አባወራ ነው።
ሁለተኛው መደብ ደግሞ «ጊዲር ነደባ» እየተባለ ይጠራል። ይህ መደብ ሸሆች፣ ኡለማዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ ለአገር ሰላም የሚሰሩና ፍትህ የሚሰጡ ታላላቅ ሰዎች የሚቀመጡበት ነው። ለተለያየ አገልግሎት በቤት ውስጥም ሲሄዱ ከእነርሱ ውጪ እንዲቀመጥበት አይፈቀድም። በሰርግና በለቅሶ ጊዜም ቢሆን እነዚሁ አባቶች ቁርዓን ይቀሩበታል ።
ሶስተኛው መደብ «ጉቲ ነደባ» የምትባለው ስትሆን፤ የዚህች መደብ ዋና አገልግሎት ወጣት ወንዶች የሚቀመጡባት ነች። ይህ የሚሆነው ለሁለት ምክንያቶች እንደሆነ ወይዘሮ ሩቅያ ይናገራሉ። የመጀመሪያው ትልልቆቹን በቅርብ ሆነው እንዲያገለግሉና እንዲታዘዙ ለማድረግ ነው። በሸርዓ ህግ ሴቶች በዚያ አካባቢ እንዲጠጉ አይፈቀድም። ስለዚህም ወንድ ወጣቶች በዚያ መደብ ላይ እንዲቀመጡ ይደረግና ትልልቆቹን የሀይማኖትና ሌሎች አባቶችን ያስተናግዳሉ።
ሌላው ደግሞ እጮኛ የሚፈልጉ ወንዶች በዚያ ቦታ እንዲቀመጡ ይፈቀድላቸዋል። ምክንያቱም በዚያ ቦታ የሚቀመጥ ወንድ ከፊት ለፊቱ የተሰቀለውን በባህሉ አጠራር «ወንጠፍ መውረጃ» የሚባለውን የሴቷ እናት ልጅ አለኝ ጠይቁ ምልክት ይመለከታል። ከዚያ በቦታው ላይ ምንጣፍ ካለ ቤተሰቡን ለመጠየቅ ሽማግሌዎችን ይልካሉ።
«ወንጠፍ መውረጃ» ማለት ምን ማለት ነው ካላችሁ ወይዘሮ ሩቅያ እንዳሉን፤ አንዲት እናት ምን ያህል ለትዳር የደረሰች ሴት ልጅ እንዳላት የምታሳውቅበት ነው። ይህንን የምታስቀምጠውም ግርግዳ ላይ በእንጨት ተመትቶ በተደረደረ የራሱ ቦታ ላይ ነው። እናም ይህንን ወንዶች ካዩ በኋላ ጥያቄው አልቆ ሰርግ ከተደገሰ ምንጣፉን የመጀመሪያ የሰርጉ ከቤተሰቡ የተበረከተ ልዩ ስጦታ አድርጋ ለልጇ ትሰጠዋለች።
በሀረሪ ባህል ዘንድ ይህንን ምንጣፍ እዚያ ያስቀመጠች እናት ለተጠየቀችው ሁሉ መልካም ምላሽ የመስጠት ግዴታ አለባት። ምክንያቱም በቦታው ላይ ማስታወቂያ ስለሰራች። ሆኖም አግቢዋ ግን ካልተስማማች አይሆንም። ይልቁንም የምታገባውን ሰው ለማየት በተሰራላት «ቁጢቀላ» እየተባለ በሚጠራ ፎቅ ላይ ሆና ምርጫዋ መሆኑንና አለመሆኑን በወንድሟ አማካኝነት ትናገራለች። አይነውሃው ያላማራት ከሆነ እንደማትፈልገው፤ ከተስማማች ደግሞ እሽታዋን ትገልጻለች።
የሀረሪ እናቶች ለሴቷ ይህንን አይነት ማስታወቂያ ሲሰሩ ለወንዱም እንዲሁ «ሀማት ሞት» የሚባል ሰፌድ ከፊት ለፊት በተደረደሩ እንጨቶች ላይ ይሰቅላሉ። ሀማት ሞት ማለት የአማች ሰፌድ ማለት ሲሆን፤ ይህ የሚደረገው ወንዱ መስፋት ስለማይችል እርሱን ለመሸፈን ሲባል እንደሆነ ወይዘሮ ሩቅያ ነግረውናል። እናም ሀረሪዎች ስንት ወንድ፣ ስንት ሴት ልጅ ለትዳር እንደደረሰ ለመንገር ይህንን አይነት ዘዴ ይጠቀማሉ።
ወደ መደባችን ስንመለስና በአራተኛ ደረጃ የምናነሳው «ገብትሔር ነደባ» የሚባለውን መደብ ነው። ከቤቱ በር ጀርባ የሚሰራና ከሦስቱ መደቦች ራቅ ያለ ነው። «ሲትሪ» ወይም የተከለለ ቦታም ነው። ምክንያቱም በእምነቱ ዘንድ ወንድና ሴት ተቀላቅሎ መቀመጥ ክልክል ነው። በዚህ መደብ ላይ የሚቀመጡት ደግሞ እናቶች ብቻ ናቸው። በእርግጥ ቤት ውስጥ ከሆነና ቤተሰብ ከሆኑ ይህ የሚፈቀድበት ሁኔታ አለ። እንግዶች ባሉበት ወቅት ይሄ እድል አይሰጥም። እንደባህሉና ህጉ መሆን ይጠበቅባቸዋል።
የመጨረሻዋና አምስተኛዋ መደብ « ጢፍ ነደባ» እየተባለች የምትጠራው ስትሆን፤ ትንሽ ሆና ጥግ ላይ የምትሰራ ነች። ይህቺ መደብ አገልግሎቷ ለአቅመአዳም ወይም ለአቅመሄዋን ያልደረሱ ልጆች የሚቀመጡባት ነች። በሀረሪዎች ዘንድ ትንንሽ ልጆችም የራሳቸው መደብ ያላቸውና ቦታ የሚሰጣቸው ለመሆናቸው ይህ ምስክር ነው። ታዲያ እነዚህ መደቦች በየትኛው የቤቱ ክፍል ውስጥ ይገኛሉ? ካላችሁ መልሱ እንዲህ ነው።
ትልቁ ቤት ማለትም በበር ሲገባ ፊት ለፊት ላይ የሚታየው አራት መደቦች የሚታዩበት ቤት ነው። ይህ ክፍል «ጌረዋክርተት» እየተባለ ይጠራል። በዚሁ ክፍል ደግሞ ከለል ብሎ የሚታየው መደብ የእናቶች መቀመጫው ገብትሔር ነደባ ይገኛል። ስለዚህም በአንድ ቤት ውስጥ አምስቱም መደቦች ይታያሉ። ነገር ግን ሌሎች ክፍሎችም ይህንን የትልቁን ቤት አገልግሎት የሚያሰፉም አሉ። ከእነዚህ መካከል አንዱ «ቁጢቀላ» እየተባለ የሚጠራው ፎቅ ሲሆን፤ የምትታጨዋ እንስት ባለቤቷን የምታይበትና ውሳኔ የምታስተላልፍበት ክፍል ነው።
ሌላው ክፍል ደግሞ በጋብቻ ጊዜ የሙሽራ ቤት ወይም ጫጉላ ቤት የሚሆን ሲሆን፤ ከጋብቻ በኋላ ደግሞ ለልጅ ቤት የሚያገለግል ተደርጎ ይሰራል። ይህ ክፍል «ክርቴት» በመባል ይጠራል። በዚህ ቤት ላላገቡ ወንዶች ማስጠንቀቂያ የሚሆን አለንጋ የሚቀመጥበትም ነው።
ሀረሪዎች ቤት ሲገነቡ ተግባራዊ የሚያደርጓቸው በርካታ ነገሮች አላቸው። ከእነዚህ መካከል ደግሞ ከላይ የጠቀስናቸው አምስቱ መደቦች ዋነኞቹ ናቸው። በሌላ በኩል ሞታቸውን ወይም አንድ ሰው ዘላለማዊ አለመሆኑን ሁልጊዜ እንዲያስብ ለማድረግም ከበሩ ፊት ለፊት ጉድጓድ መሰል የመቃብር ውክልና ያለው ይሰራሉ። ይህ ደግሞ በሀረሪዎች ዘንድ ለሰዎች በጎ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ነጋሪ፤ ከማንም ጋር ተጣልቶ እቤቱ ቢመጣ ቁጣውን አብራጅ ነው። ይቅርታ መጠያየቅ እንዳለበትም ማሳሰቢያ የሚሰጥበት እንደሆነ ይታመናል።
ሁሉም የሙስሊም እምነት ተከታይ ፈጣሪውን የሚያከብርና የሚፈራ ለማድረግ የሚያግዝና ሞትን እያሰበ መልካም ነገሮችን እንዲያደርግ ሀይል የሚሰጥ እንደሆነም ወይዘሮ ሩቅያ አጫውተውናል። ይህ ጉድጓድ «ለሀዲ» እያሉ የሚጠሩት ሲሆን፤ ቁርዓን ማስቀመጫ ነው። ባህሉ ሁሉን በእኩል የሚያይ፤ ቦታ የሚሰጥና ሞትን የሚያስብ በመሆኑ እንኑርበት እያልን ሀሳባችንን ቋጨን። ሰላም!
አዲስ ዘመን ነሀሴ 19/2011
ጽጌረዳ ጫንያለው