ለጋስ ሰው ማለት ከተረፈው የሰጠ ሳይሆን ካለው ላይ ያካፈለ ነው። ነገ ማንና የት እንደሆንክ አታውቅምና ሁሌም ያንተን እርዳታ ለሚፈልጉ ሰዎች እጅህን ፈጽሞ አትከልክላቸው። ህይወት በመደጋገፍ የተሞላች ናትና ወንድምህን ለመርዳት ወደኋላ አትበል።» የሚለው ሀሳብ መመሪያቸው ነው። ዓለም በብዙ ጥሩ ሰዎች የተሞላች ባትሆንም ይህንን ሀሳብ በተግባር የሚያውሉ አንዳንዶች ግን አይታጡም። ከእነዚህ መካከል የዛሬ «የህይወት እንዲህ ናት» አምድ እንግዳችን ወይዘሮ ዮርዳኖስ አስመላሽ አንዷ ናቸው።
ዛሬ ሰዎችን ከውድቀታቸው ለማንሳት ብዙዎች ይፈራሉ። ከዚያ ይልቅ የውሻ ቡችላ ገዝተው ማሳደግን ይመርጣሉ። በዚህም ክፋት በርትቶ ችግረኛ ሰውን የሚፈልገው እንኳን ጠፋ። ግን ደጎች አለመጥፋታቸውን የሚያሳዩን ጥቂቶች አሉንና እነርሱን ያብዛልን ከማለት ውጪ ምን ይባላል? እነዚህ ሰዎች በየጎዳናው የወደቁ ምስኪኖችንም በአይናቸው አይተው ልባቸው ውስጥ ያስቀምጡና ለመርዳት ይነሳሉ። ስለዚህም ለሌሎች አርአያ የሚሆን ነገር አላቸውና እኛም ተሞክሯቸውን ለማቅረብ ወደናል።
ውልደቷ አሰብ ሰቂር አካባቢ ነው። በ1968 ዓ.ም እንደተወለደች በትክክል ያረጋገጠችው ቤተሰቦቿ ጋብቻ ሲፈጽሙ ቀለበታቸው ላይ ካጻፉት ዓመተ ምህረት በመነሳት መሆኑን ትናገራለች። ለአባትና እናቷ የመጀመሪያ ልጅ በመሆኗ ደግሞ እንደብርቅ ነው የምትታየው። ቤታቸው በደስታ የሞላው በእርሷ አማካኝነት ነው። ልጅ ደስታ፣ ተስፋ ሰጪ ነው ይባል የለ። ስለዚህም ቤቱን በደስታ ሞላሽው፣ አወድሽው ለማለት ስለፈለጉ ከሽቶ መአዛ ጋር አመሳስለው ስሟን ናርዶስ አሉት።
አሰብ ሳለች ከቤት ባትወጣም ከእናትና አባቷ ጋር እየተጫወተችና በቤት ውስጥ የተለያዩ ሥራዎችን በመስራት ታሳልፍ ነበር። የቤት ውስጥ ሙያ በሚገባም ለምዳለች። በዚያ ላይ ቤተሰቦቿን ሱቅ ውስጥ በመጠበቅም ታግዝ ነበር። በእርግጥ አንድም ቀን ሸጣ አታውቅም። ይሁንና እናቷ ቤት ምግብ ስትሰራ ከፍ ያለ ወንበር ላይ ታስቀምጣትና ሰው ሲመጣ ትናገራለች።
የናርዶስ ወላጆች ሀብት አላቸው የተባሉ ነጋዴ ናቸው። ስለዚህም እርሷም ሁልጊዜ ነጋዴ መሆንን ታልማለች። ሁሉ ነገሯን ከንግድ ጋር ማስተሳሰርም ይመቻታል። ይሁንና ከቤት ወጥታ እንድትጫወትም ሆነ የፈለጋትን ነገር እንድታደርግ ስለማይፈቀድላት በቤት ውስጥ ነበር ይህንን ምኞቷን ለማሳካት የምትጥረው። መጫወት ስትፈልግ እንኳን ከቤተሰብ ውጪ አትችልም። ቤት ውስጥ ሁሉ ነገር ተሟልቶላት ጨዋታ ፍለጋ ውጪ እንዳታማትር ትደረጋለች። ይህ ደግሞ ጭምት ሆና እንድታድግ አድርጓታል።
ከቤት መውጣት ሲያምራት አባቷ በሳይክል ይዟት ሽርሽር ይሄዳል። ከዚያ መልስ በቤት ውስጥ ትቀመጣለች። ከጓደኞቿ ጋር መጫወት ስትፈልግ ደግሞ እነርሱ እንዲመጡ ይደረጋሉ እንጂ እርሷ አትሄድም። ለጥናት ብቻ ነው የሚፈቀድላት። ለያውም በመኪና ተወስዳ በመኪና ትመለሳለች። ስለዚህም በጣም ውጪውንና ጨዋታን ናፍቃ ነው ያደገችው። በተለይም አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ ይህ ሁሉ ነገር እንደበረታባት ታስታውሳለች።
ናርዶስን በቤት ውስጥ የምትረዳት ሴት በጣሙን ትወዳት ነበር። በመንከባከብም ሆነ የተለያዩ ሥራዎችን በማስለመድ ታግዛታለች። ስለዚህ ከእናቷ ቀጥሎ የምትወደው እርሷን ነው። ይህ ደግሞ ስሟን እስከማስቀየር አድርሷት እንደነበር ታስታውሳለች። ቤተሰብም በሁለቱ መካከል መግባትን አይፈልግምና ዝምድናቸው እንዲቀርብ ሲሉ ናርዶስ የሚለውን መጠሪያዋን ዮርዳኖስ ብላ የሰየመችውን ስም ተቀበሉ። ዛሬ የምትጠራበት ስምም በእርሷ የተሰየመ ሆነ።
ዮርዳኖስ በባህሪዋ ብዙ ነገሮችን በዝምታ የምታሳልፍ ልጅ ስትሆን፤ እርቧት እንኳን ምግብ ስጡኝ አትልም። ሁሉን ነገር በራሳቸው እስኪያደርጉላት የምትጠብቅ ነች። በዚህ ደግሞ አንድ ቀን የተከሰተው ነገር የምትወዳትን ሴት ጨምሮ አስቆጥቶ ነበር። ይኸውም መኪና ላይ አሳፍረው ወደ ትምህርት ቤት ሊወስዷት ሲሉ ጫማዋ ተቀዶ መታየቱ ነው። «ለምን ጫማሽ እንዳለቀ አትናገሪም» ሲሉ ዮርዳኖስን ከተቆጧት በኋላ «አንቺስ የተቀደደ ጫማ ለምን አደረግሽላት» በሚል ተናደው ተወዳጇን ረዳታቸውን ጮኸውባት እንደነበር አትረሳውም።
እንደማንኛውም ልጅ ቦርቃና ተጫውታ አለማደጓ የሚያስቆጫት ልጅ ዮርዳኖስ፤ በዛሬ ህይወቷ ላይ ከሰው ጋር ለመግባባት ብዙ ዋጋ እንዳስከፈላት ትናገራለች። «ይህ የሆነው ቤተሰቦቼ ስለማይወዱኝ አይደለም። ትምህርት ላይ ትኩረት እንዳደርግና በጨዋታ ብዛት የማይፈለግ ነገር ውስጥ እንዳልገባ በማሰባቸው ነው። ጓደኛ ያበላሻታል ብለው ስለሚያምኑም ወጣ ብዬ እንዳልጫወት ገድበውኛል። በዚያ ላይ በቤት ውስጥ ሁሉን አይነት መጫወቻ ስላሟሉልኝ የጨዋታ ጥማቷን ታረካለች ብለው ያምናሉ። ስለዚህ ለእኔ ብለው በመሆኑ አልፈርድባቸውም» ትላለች።
ትምህርት
የመጀመሪያ ትምህርት ቤቷ ቤቷ ነበር። አባቷ የተማሩ ስለነበሩ በሚገባ ያስጠኗታል፤ በዚህም ፊደላትንና ቁጥሮችን መለየት ችላለች። በአባቷ ካገኘችው ትምህርት በኋላ ቤተሰቦቿ ወደ አስመራ ተጉዘው መኖር በመጀመራቸው አሰብን ለቃ አስመራ ውስጥ «ካንቦኒ» በተባለ የካቶሊኮች ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን መከታተል ጀመረች። እስከ ስድስተኛ ክፍልም ተማረች። ከስድስተኛ ክፍል በኋላ ግን መንግስት ትምህርት ቤቱን በመውረሱ ወደ ሌላ ትምህርት ቤት ተዛወረች። እድገት የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን ተቀላቀለች።
ከ12ኛ ክፍል በኋላ ትምህርቷን መቀጠል የምትፈልገው ውጪ አገር በመሆኑ እድሜዋ ለመውጣት ስለማይፈቅድላት በአዲስ አበባ የተለያዩ እውቀት ሊያስጨብጡ የሚችሉ ስልጠናዎችን መውሰድ ጀመረች። በተለይም እንደ ኮምፒውተርና ቋንቋ ትምህርት አይነት ላይ በስፋት ትሰለጥን ነበር። ከዚያ በአካል ገዘፍ ስለምትል 18 ዓመት ባይሞላትም ሞልቷታል በሚል ትምህርትን ፍለጋ ባህር ማዶ ተሻገረች።
እንግሊዝ አገር «ኪንግስተን» ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በባዮኬሚስትሪ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ለመማር ተመዝግባ ዓመት ከመንፈቅ ሲሆናት መማሯን አቆመች። ምክንያቱም በእንግሊዝ አገር ሦስት ዓመት መቆየት ያልቻለ ሰው በእድሉ ተጠቃሚ መሆን አይችልም ። ስለዚህም የእርሷ አማራጭ ወደ አገሯ መመለስ ቢሆንም ወገቧን ታጠቅ ብላ በዚያው ለመቆየት ትምህርቱን አቁማ ሥራ መስራት ጀመረች። በሰው አገር ላይ ሆኖ ከቤተሰብ በሚላክ ገንዘብ ብቻ መኖር ያዳግታልና በገንዘብ ያዥነት ተቀጥራ በመስራት ሦስት ዓመታትን አሳለፈች።
እንደተባለው ከሦስት ዓመት ቆይታ በኋላ በጀቱ ስለተፈቀደላት ሙያውን ከሥራዋ ጋር እንዲዋሃድ ለማድረግ ወደ ቢዝነስ ማኔጅመንት ቀይራ ከሰኞ እስከ አርብ በ«ሄንደን» ዩኒቨርሲቲ እየተመላለሰች መማሯን ቀጠለች። ዓርብ ከሰዓት እና ቅዳሜን ሙሉ ቀን እየሰራች በሳምንት 50 ፓውንዷን በመቀበል የትምህርት ወጪዋን እየሸፈነችም ሳትቸገር የመጀመሪያ ዲግሪዋን አጠናቀቀች። ከዚያ በኋላ ግን ትምህርቱን አልቀጠለችም። ቀጥታ ሥራዋ ላይ ማተኮር በመፈለጓ ወደ ሥራ ገባች።
የባህር ማዶ ቆይታ
«ኩክ ሴቭ ሱፐርማርኬት» በብዙ ውጣውረድ ውስጥ አልፌ ብገባበትም ትምህርቴን እንድማር አግዞኛል። ከማንም በላይ እንጂ ከማንም በታች እንዳይደለሁም እንድረዳ አስችሎኛል። በተለይ የልጅነት ዝምታዬን የሰበርኩበትና ጥሩ መሪ እንድሆን ያደረገኝ የሥራ ቦታ ነው» የምትለው ባለታሪኳ፤ ገንዘብ ተቀባይ ለመሆን በቤት ውስጥ አለቃ ብቻ ሳይሆን በአጋር ሰራተኛም ትልቅ ፈተና ነበረበት። ሁሉም ተቆጣጣሪ የሚኮንበትና በተለይም በቀለም ምርጫ የሚታመንበት ነው። ስለዚህ ይህንን ሁሉ ውጣውረድ ማለፍ ግድ እንደሆነና እርሷም ጫናውን ታግላ በማሸነፍ ለዚህ እንደበቃች ትናገራለች።
«ገንዘብ ተቀባይ መሆን በራሱ ልምድንና መግባባትን የሚጠይቅ ነው። አለቆችም ቢሆኑ ይህንን ባህሪ አይወዱትም። ሰነፍና የማይሰራ አድርገው ይፈርጃሉ። በተለይም ተግባብቶ ገንዘብ ማምጣት ካልተቻለ ለሥራው ምቹ አይደሉም ተብሎ ለመቀጠር አዳጋች ነው።» የምትለው እንግዳችን፤ ድክመትን ማየት ለመለወጥ መሰረት ይሆናል ባይ ነች። ምክንያቱም ዝምታዋን ለመስበር አንድ ዓመት ከስምንት ወር ጥራለች። በዚያ ላይ ሌሎች ደንበኛ ከሌለ በቋሚነት ከተሰጣቸው ሥራ ውጪ አይሰሩም። እርሷ ግን በእነርሱ ድክመት ገብታ ገንዘብ የማታገኝበትን የጽዳት ሥራ ሳይቀር ትሰራ ነበር። ይህ ደግሞ ደረጃዋ በአንድ ጊዜ ከፍ እንዲል አድርጎታል።
«ኢትዮጵያዊያን በየትኛውም ቦታ ቢሄዱ ላመኑበት ነገር የሚሞቱ፣ የሚታገሉና አላማቸውን ከግብ የሚያደርሱ ናቸው። ለዚህም እኔ ራሴ ምስክር ነኝ። በገንዘብ ተቀባይነት ብቀጠርም ኃላፊ፣ የዲፓርትመንቱ ሱፐር ቫይዘር በመጨረሻ ማናጀር ሆኜ እስከመስራት ደርሻለሁ። ከዚያም አልፌ በራሴ ድርጅት ከፍቼ እየሰራሁ እገኛለሁ። ለዚህ መሰረቱ ደግሞ ፈተናን ማለፍ እንደምንችል የወረስነው ባህል ስላለ ነው» ትላለች።
የወይዘሮ ዮርዳኖስ ጥንካሬ በዚህ ብቻ አያበ ቃም። በባህር ማዶ ሳለች በአምስት ሱፐርማርኬቶች ውስጥ ተዘዋውራ ስትሰራ ተጋጭታ አታውቅም። ከማንኛውም የሥራ ቦታዋ ስትለቅ በጸባይና በመግባባት እንደነበር ትናገራለች። ይህ ብርታቷ ወደ ልጅነት ህልሟ እንደመለሳትም ትገልጻለች። «ቸርች ሚሽን ሶሳይቲ» የሚባል ድርጅት ውስጥ ገብታ ዓመታትን በሥራ ስታሳልፍ የሰዎች እርዳታን ተመለከተች።
የእርሷም ጸሎት ታወሳት። እናም ቦታው ላይ እየሰራች ያካበተችውን ብር ይዛ ከባንክ ተበድራ ጨመረችበትና ቤት ሰርታ ኪራዩን እየተጠቀመች የድርጅቷን የስራ ፈቃድ አወጣች። ከዚያ የምትሰራበትን ድርጅት ትታ አስመጪና ላኪ የሚያደርግ የቤተሰብ ድርጅት መስርታ ነበርና ከዚያ የምታገኘውን ገቢ ከጓደኞቿ መዋጮ ጋር በማድረግ ህልሟን ለማሳካት ወደ አገሯ ተመለሰች።
“ፒዩር ኢን ዘ ሞሪሚንግ” የተባለ በጎ አድራጎት ድርጅት አቋቁሟ ዘጠኝ ዓመት ሙሉ መኖሪያዋን አዲስ አበባ አድርጋ ችግረኞችን ማገዟን ቀጠለች። ለመሆኑ እንዴት ለበጎ አድራጉት ተግባራት ተነሳች? ካልን መልሱ ብዙ ነው። ሆኖም ሁለቱ ነገሮች ግን በዋናነት ይጠቀሳሉ። የመጀመሪያው የህጻኗ ልመና ሲሆን፤ ሁለተኛው ዘወትር በየመንገዱ የምታያቸው ችግረኛ ሰዎች ናቸው።
ዘወትር ከእንግሊዝ አገር ስትመጣ ከበራቸው ፈንጠር ብላ የምትቀመጠው የሦስት ልጆች እናት ጉዳይ ልቧን ይሰብራታል። እንስቲቱ ልጆቿ ራቅ ብለው እንዲጫወቱ ታደርግና ትለምናለች። እነርሱ ሲመጡ ደግሞ ዝም ብላ ቁጭ ትላለች። አንድ ቀን ይህንን ለምን እንደምታደርግ ጠየቀች። ምክንያቱም ለማገዝ ነውና የመጣችው በእርሷ መጀመርን ፈልጋለች።
ስትለምን የነበረችው እንስት ባሏ ጥሏት በመሄዱና ልጆቿን ለማሳደግ በመቸገሯ በዚህ ሥራ እንደተሰማራች ታስረዳታለች። ልጆቿን የሚያሳድግላት ካገኘች ልመናውን እንደምታቆምም ትገልጻለች። ለማገዝ የመጣችውም ዮርዳኖስም ይህን ሀሳቧን አድምጣ የእርሷን ልጆች የሥራዋ መጀመሪያ አድርጋ ወደ በጎ አድራጎት ስራ እንደገባች አጫውታናለች።
ሆድ ያባባ ልመና
ልጅ እያለች ነበር ይህ ሀሳብ በአዕምሮዋ መሰረት የጣለው። በተለይም ከግቢ እንዳትወጣ ተደርጋ ማደጓ የውጪውን ሁኔታ እንዳታውቅና ብዙ ችግረኛ እንዳለ እንዳትረዳ ቢያደርጋትም በየቤቱ ተዘዋውረው የሚለምኑ ሰዎች በተደጋጋሚ ወደ ቤታቸው መምጣታቸው ግን ሁልጊዜ ጥያቄ ይፈጥርባት ነበር። እናም ይህ ህልም በተግባር እንዲተረጎምና ለእነዚህ ሰዎች እንድትደርስ ዘወትር ጸሎት ታደርግ ነበር። በተለይም አንድ ቀን የገጠማት ይበልጥ እንድታለቅስና አምላኳን እንድትማጸን አስገድዷታል።
ነገሩ እንዲህ ነው። የአራት ዓመት ህጻን ስትሆን፤ በር እያንኳኳች ነበር። በሩን ከፍታ የተቀበለቻት ደግሞ የትናንቷ ናርዶስ የዛሬዋ ዮርዳኖስ ነች። የልጅቷ አጠያየቅ ልቧን ሰብሮታል። «ትንሽ ቁራሽ እንጀራ ለምሳዬ» የሚለው። ምክንያቱም እርሷ በተንደላቀቀ ግቢ ውስጥ ያደገች ነችና ህጻናት እንዲህ የሚለምኑ አይመስላትም። እናም በቀጥታ በሩን ገርበብ አድርጋ ወደ አሳዳጊዋ አቀናች። የህጻኗን ሁኔታም እርሷም በእንባ ጭምር አስረዳች።
ሁኔታዋ ያሳሰባት አሳዳጊዋ «አይዞሽ ብዙ የተረፈ እንጀራ ስላለ ይህንን እንሰጣታለን» አለችና በትሪ ሙሉ እንጀራ ወጥ ተደርጎበት ሰጠቻት። ደስ እያላትም ልትመግባት ወደ ህጻኗ አመራች። ዮርዳኖስ ይዛው የመጣችው እንጀራና ትሪ አይደለም በህጻኗ አቅም ለራሷ ለዮርዳኖስም ከብዷት ነበር። ስለዚህም ልጅቷ ይህንን ስታይ ራቅ ብላ በር እያንኳኳች የምትለምነውን እናቷን ጠራች። እናትም መጥታ ተቀብላ መርቃ ሄደችና ራቅ ብላ በመቀመጥ እርሷ ሳትመገብ ልጆቿን ማጉረስ ጀመረች።
ይህ ደግሞ ይበልጥ ዮርዳኖስን አሳዘናት። ለ10ደቂቃ ያህል ቆማ ተመልክታም ሀዘኗ ስለበረታባት በሩን ዘግታ በመግባት በረንዳ ላይ ሆና ማልቀስ ጀመረች። ሲበቃትም ገብታ መጸለይዋን ተያያዘችው። ለእነዚህ ሰዎች እንድደርስ እርዳኝ በማለትም ተማጸነች።
«አምላክ የለመኑትን አይረሳም። እኛ ግን እንዘነጋና ዛሬ ምን አይነት መኪናና ጌጣጌጥ ወይም ሌላ ነገር እንግዛ ብለን እንጨነቃለን። እኔ ለ17 ዓመት እንግሊዝ አገር ስሰራ እነርሱን አስታውሼ አላውቅም።» የምትለው ባለታሪኳ፤ ቀደም ሲል ትምህርቷን ጨርሳ ውጪ ሄዳ በዚያ ሙያ ሰርታ ተለውጣ በመጀመሪያ ገላቸውን ማጠብ ከዚያ ሆዳቸውን መሙላትን የተመኘችና የጸለየች ቢሆንም ይህንን ዘንግታ መቆየቷ እንዳስቆጫት ትናገራለች። ሆኖም በዚያው ባለመቅረቷ ደግሞ አምላኳን ታመሰግናለች።
በገንዘብ ብቻ ሳይሆን በሙያቸውና በአቅማቸው የተለያዩ የበጎ አድራጎት ሥራ ለመስራት ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱትን ሰዎች ያጋጠመኝ ጸሎቴን እንዳረሳ ሊያደርገኝ ስለፈለገና ለችግረኞች እንድደርስ በማሰቡ ነው የምትለው እንግዳችን፤ በሰፈራቸው ተቀምጠው ልጆቻቸውን እየመገቡ እነርሱ ጦማቸውን የሚያድሩት እናቶች ጉዳይ ላይ ገብቶ ተገን መሆን ከምንም በላይ ያስደስታል። ችግር ቢኖርም ያለን ማካፈል ደግሞ የበለጠ በረከት እንደሚቸርም ትናገራለች። ይህ ደግሞ ለ72 ልጆች እንድትደርስ አድርጓታል።
ሥራው ሲጀመር መረጃዎችሽ ጠፍቷል እስከመባልና ከዚያም አልፎ በየቀኑ እስከመመላለስ እንዳደረሳት የምትናገረው ዮርዳኖስ፤ የሥራ ፈቃድ ለማውጣት ዓመት እንደፈጀባትና በዚህም በእንግሊዝ አገር ቅርስ ይሆነኛል ያለችውን ሳይቀር እንዳሸጣት፤ ለራስሽ ነው ጥቅሙ ተብላም እንደተከሰሰችበትም አጫውታናለች። ግን ይህም ቢሆን አልቆጨኝም ትላለች። ምክንያቱም ያለመችውና የጸለየችውን ለማሳካት ሰርታለች። በችግር ውስጥ አልፋም ድርጅቱን በሁለት እግሩ አቁማዋለች። በዚህ ደስተኛ መሆኗን ትናገራለች።
የሃምሳ ሳንቲም ክስ
ድርጅቱ ሲመሰረት የሚሰበሰበውን ገንዘብ በቀጥታ ለሚመለከተው አካል ማድረስ ዋና አላማዋ ነው። በዚህም 98 በመቶ የሚሆነው ለተረጂዎቹ ስታሰጥ ሁለት በመቶውን ብቻ ለሥራ ማስኬጃ ትጠቀማለች። ግን ይህ ታማኝነቷ ለምን ያሰኛቸው ሰዎች እንደነበሩ ትናገራለች። በተለይ የማትረሳው የሃምሳ ሳንቲሟን ክስ ነው። «ሃምሳ ሳንቲም ለምን ሰጠችኝ። በሀምሳ ሳንቲም ለልጄ ምን ላደርግለት እችላለሁ? ሌላውን ራሷ እየበላችው ነው» የሚለው ጥያቄ ዛሬ ድረስ ያስቃታል። ነገሩ የሆነበት ምክንያት እንዲህ ነው ትላለችም።
ሥራውን ስትጀምር ገንዘቡን ለአሳዳጊዎች በቀጥታ ትሰጥ ነበር። ግን ለምን እንደሚያውሉት አይታወቅም። ልጆቹንም የሚፈለገውን ያ ህ ል አይመግቧቸውም። በተጨማሪ ተረጂ የ ሆ ኑ ልጆችን በልመና አሰማርተዋቸው ይገኛሉ። ስለዚህ ይህ ቆሞ አስፈላጊው ነ ገ ር ተገዝቶ እንዲቀርብላቸው ተወሰነ። በዚህም ሁሉ ነገር ተገዝቶ ብር ከተረፈ ለባለቤቱ ይመለሳል። እናም አንድ ቀን ለተረጅዋ ልጅ የመጣው ገንዘብ ብዙ ነገር እንዲገዛላት አስችሎ ነበር። ይሁንና ካላት ውስጥ ሃምሳ ሳንቲም ተረፈ። ይህ ደግሞ ከማንም ገንዘብ ጋር እንዲቀላቀል አትፈልግምና እናቲቱ እንድትወስድ አስጠራቻት።
በወቅቱ ሃምሳ ሳንቲም ዋጋ ነበረውና የጎደላትን ትሞላበታለች ብላ እንደነበር የምትገልጸው ዮርዳኖስ፤ የእናትየዋ ምልከታ የተሳሳተ በመሆኑ አልተቀየመችም። ምክንያቱም በጎ ለማድረግ ብለው አንዳንድ ልጅን የሚረዱላት ጓደኞቿ የሰጡትን በተግባር እንዲያዩ ትፈልጋለች። በዚህም ከስህተቷ ተምራ በምትወስደው እርምጃ የተቃና ነገር አምጥታለች። ይኸውም ቀደም ሲል ሀ ም ሳ ሳንቲም በመስጠቷ የመጣባትን ክስ ለማስቀረት ዛሬ ምንም ያህል ቢተርፍ ለተረጂ ቤተሰቦች አትሰጥም።
ይልቁንም ተ ረ ጂ ልጆቹ የቀጣይ ህይወታቸውን ያስተካክሉበት ዘንድ የቁጠባ ደብተር ከፍታ ትቆጥብላቸዋለች። አሁንም በተደጋጋሚ ቢከሷትና ድንገተኛ ግምገማ እያደረጉ ቢፈትኗትም እንደማትወድቅና ነጻ እንደምትሆን ስለምታምን «ስህተቶቼን አርምበታለሁ እንጂ አልወድቅበትም» በማለት ይህንን ድርጊታቸውን እንደማት ጠላው ትናገራለች። «በክሱ ይበልጥ ብርታትና ድርጅቴን አጠነክርበታለሁም» ባ ይ ባይ ነች።
« «ከቤተሰብ ተለይተው የሚያድጉ ልጆች አ ባ ት እናት እንደሌላቸው ያስባሉ። ችግረኛ መሆናቸውንም እያስታወሱ ያድጋሉ።» የምትለው እንግዳችን፤ ድርጅቱ ልጆቹን ባሉበት እንዲያግዝና ከስድስት ወር እስከ 1 8 ዓመት ያሉ ልጆችን እንዲደግፍ የሆነው ይህንን ስሜታቸውን ለመጠበቅ እንደሆነ ትናገራለች።
አገሯን በተለያየ መልኩ ለመደገፍ 12 ፕሮጀክቶችን የቀረጸች ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ አንዱን ብቻ ተግባራዊ በማድረጓ ከዚህ በላይ እዚህ መቆየት እንደሌለባት ያመነችው ዮርዳኖስ፤ እነዚህን ፕሮጀክቶች ለማሳካትና ከ72 በላይ ልጆችን ለማሳደግ ስትል ተመልሳ ከሳምንት በኋላ እንግሊዝ አገር እንደምትሄድ ትናገራለች። «የእኔ ስኬት በዚህ ብቻ አያበቃምና ሌሎችንም መስራት እፈልጋለሁ። እኔ ባልፍ እንኳን የእኔን አላማ የሚደግፉ ብዙዎች አሉና ያስቀጥሉልኛልም» ትላለች።
ቤተሰብ
ዮርዳኖስ እናትና አባቷ በፍቅርና በደስታ የኖሩና ፍቅራቸው የሚያስቀና በመሆኑ እርሷም እንደነርሱ መሆንን ሁልጊዜ ትፈልግ ነበር። ይሁንና «ይህ ለእኔ አልተፈቀደም» ትላለች። ብዙ ጊዜ ሞክራም በፍቅር ህይወቷ የተሳካላት መሆን እንዳልቻለች ትናገራለች። ነገር ግን እግዚአብሔርን በአንድ ነገር እንደምታመሰግነው ትገልጻለች። ቢያንስ ለአይኗ ማረፊያ የምትሆናትን ልጅ ስለሰጣትና የምታግዛቸው ልጆች የእኔ ቤተሰብና ልጆች ናቸው ብላ እንድታምን አድርጓታልና። ስለዚህም በቤተሰብ ህይወቷ ደስተኛ እንደሆነች አውግታናለች።
መልዕክት
«የሚታዩትን ችግሮች የነገራችን ማዕከል አናድርግ፤ ነገር ግን የምንለውን ሆነን መገኘትን፣ ያየነውን ሰርተን ማሳየትን መለያ ምልክታችን እናድርግ» የምትለው ባለታሪኳ፤ የሰው አገር መቼም ከሰው አገርነቱ አይቀርም። ስለዚህ በሰው አገር ለመስራት እንጂ ለመኖር አገርን መምረጥ ቅድሚያ ማድረግ እንደሚገባ ትናገራለች። ሰርተን ለአገራችን ልማትና ብልጽግና እንጂ ሌላ አገር ለመለወጥም መታተር የለብንም ትላለች። ሁልጊዜ መትጋት በአገር ኩራት መሆን አለበት። የተማርንበትን ሙያ አገራችን ላይ መተግበር የመጀመሪያ መሆን ይኖርበታል። ከዚያ ባለፈ ቅን ልብ ኖሮን ለሰዎች መኖርን መልመድ ያስፈልገናል ትላለች።
መስጠት ልዩ ጸጋ ነው። ግን ለሚገባው መሆን አለበት፣ በሰጡት ነገር ለውጥ መምጣቱን መከታተልና ውጤቱን መለካትም ይገባል። ለዚህም ተረጂ ልጆቹ በአስተሳሰባቸው የተለወጡ መሆናቸውን ተመልክቻለሁና ከእኔ ተማሩም ትላለች።
እስካሁን በድርጅቱ እየረዳች በቆየችበት ጊዜ ውስጥ ሦስት ልጆች ዩኒቨርሲቲ ገብተው ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ናቸው። አንዷ 11ኛ ክፍል ደርሳለች። ይሁንና ይህቺ ልጅ አሁን የእርሷን እገዛ አትፈልግም። ምክንያቱም እርሷ «እስካሁን ስላገዥኝ አመሰግናለሁ። እህቶቼ ደርሰው እያገዙን ነው።
በዚያ ላይ እራሴም ብሆን ሳንቡሳ እየሰራሁ እማራለሁ። ከዚህ በፊት እኔ እንደነበርኩት ያሉ ልጆች ብዙ ናቸውና ለእነርሱ ድረሽላቸው» ብላታለች። ዮርዳኖስም እንዲህ ቅን ልቦች ያላቸውን ልጆች እናገኛለንና በጎነታችንን እናጠንክር ስትል ትመክራለች። እኛም ቅን ልቦች ቅን ሰው ይፈጥራሉና ቅንነታችንን እንጨምር መልዕክታችን እናድርግና ለዛሬ በዚህ እናብቃ። ሰላም!
አዲስ ዘመን ነሐሴ 19 / 2011
ጽጌረዳ ጫንያለው