ገበሬው አባወራ በከፋ ሀዘን ውስጥ ከርመዋል። ሁሌም ብቻቸውን ሲሆኑ ይተክዛሉ፡ የሚያዋያቸው ወዳጅ ዘመድ ሲያገኙ ደግሞ የልባቸውን እያወጉ፡ የትናንቱን ከዛሬው ያነሳሉ። የትዳር አጋራቸው በሞት ከተለየቻቸው ቀናት ተቆጥረዋል። ሚስታቸውን አፈር አልብሰው ከተመለሱ ወዲህ በለቅሶ ውለው ያድራሉ። ዘወትር የሙት ልጆቻቸው ዕጣ ፈንታና የጎጇቸው መቀዝቀዝ ያሳስባቸዋል። በእሳቸው ትከሻ ብቻ የሚስታቸውን ሸክም ደርቦ መኖር እየከበዳቸው ነው።
አንድ ቀን አባወራው መንገድ ውለው ከቤት ተመለሱ። አረፍ ከማለታቸው ግን ከወደ ውጭ የሰሙት ድንገቴ ጩኸት አስደንብሮ አስነሳቸው። ከልጆቻቸው መሀል አንደኛዋ ከጓሮ እየተጫወተች መሆኑን ያውቃሉ። ሌሎቹም ቢሆኑ ከአካባቢው አልራቁም። ጉዳዩ ግን ይህ አልሆነም። ትንሽዋ ልጃቸው ወርቅነሽ በስተጓሮ በኩል በእባብ ተነድፋ ወድቃ ነበር።
አባወራው ይህን ሲያውቁ አምርረው አለቀሱ። የሚስታቸው ሀዘን ሳይበቃ ይህ ክፉ ገጠመኝ መከሰቱም ልባቸውን ሰበረወ። የዛን ቀን ጎረቤቱ ተሰባስቦና ወዳጅ ዘመድ ተጠራርቶ የባህል መድሀኒቱን እያሻሸ መፍትሄውን ሲሻ ቆየ። ሌሊቱን ግን የወርቅነሽ ህመም የከፋ ሆኖ አደረ።
ሲነጋ አባት ልጃቸውን ይዘው ከቤት ወጡ። አሁን የትንሽዋን ልጅ ህይወት የማትረፍ ሩጫ ላይ ናቸው። በሚኖሩበት የገጠር አካባቢ በቂ ህክምና ይሉት የለም። ልጅቷ ውላ ካደረች ደግሞ ህይወቷ ሊያልፍ ይችላል። ይህን ሲያስቡ ጊዜ አላጠፉም። ማልደው ገስግሰው ልጃቸውን አዲስ አበባ ካለ አንድ ሆስፒታል አደረሱ።
አዲስ አበባ ቅርብ የሚሉት ዘመድ አላቸው። እሳቸው ለሰውየው አጎት ናቸውና በክፉና ደግ አጋጣሚዎች ሁሉ ሲያገኙት ቆይተዋል። አሁንም ቢሆን ይህ ሰው ጉዳዩን ካወቀ ጀምሮ ከጎናቸው አልራቀም። ሲያዝኑ እያዘነ፣ ሲያለቅሱ እያባበለ አጋር ሆኗቸዋል።
ከቀናት በኋላ ልጅቷ አገግማ ዓይኖችዋን ገለጠች። ይህኔ አባት በደስታ እያነቡ ፈጣሪያቸውን አመሰገኑ። የአጎቱን ደስታና የህጻኗን ደህንነት ያስተዋለው ሰውም ስሜታቸውን ተጋርቶ አብሯቸው አነባ። መልሰው ወደ ገጠር መሄዳቸውን ሲያውቅ ግን ስለልጅቷ ሀሳብ ገባው።
አጎት እንግድነታቸውን ጨርሰው ወደ ሀገራቸው ለመሄድ ሲዘጋጁ እሱ በውስጡ ስለሚመላለሰው ጉዳይ አንስቶ አዋያቸው። ልጅቷን ገጠር ከሚመልሷት እሱ ዘንድ እየተማረች እንደ ልጁ ቢያሳድጋት እንደሚወድ ነገራቸው። አጎት ይህን ሲሰሙ ውስጣቸው ተረበሸ። ፈጥነው ለውሳኔ ቢቸገሩ ዝምታን መርጠው ቆዩ። አለፍ ብለው ግን የነገውን የተስፋ ህይወት አሰቡት። ተምራ የመለወጧን ጉዳይ ሲያልሙት ደግሞ ገጻቸው በፈገግታ በራ። ይህኔ ልጃቸው ከተማ የመቅረቷ መልካምነት አመዘነባቸው። እናም ወሰኑ። የአስር አመቷን የሙት ልጅ በአደራ አስረክበው ወደ አገር ቤት ብቻቸውን ሊመለሱ ተስማሙ።
ኑሮ በአጎት ቤት
አሁን ትንሽዋ ወርቅነሽ ኑሮን በአዲስ አበባ ጀምራለች። ህይወቷ ካደገችበት የገጠር ልማድ የተለየ መሆኑም አሰደስቷታል። የቀድሞ ልብሷ በከተሜ ልብስ ከተቀየረ ወዲህ ቤት ካሉ እኩዮችዋ ጋር ተመሳስላለች። ህመም የከረመበት አካሏ ማገገም ሲጀምር ደግሞ ደስተኛ መሆንዋ በፊቷ መነበብ ያዘ።
‹‹አጎቴ›› እያለች የምትጠራው አሳዳጊዋ ቃሉን ማጠፍ አልፈለገም። በአዲስ አመት ትምህርት ቤት አስመዝግቦ ቀለም ሊያስቆጥራት ወሰነ። ወርቅነሽ ይህን ስታውቅ ይበልጥ ደስታዋ ጨመረ። የነገውን መልካምነት አስባም እንደልጅነቷ ዘለለች፣ ቦረቀች።
በወርቅነሽ አጎት ቤት ከእሷ ዕድሜ የሚበልጡና የሚያንሱ ልጆች አብረዋት ይኖራሉ። ሁሉም ልክ እንደስዋ ትምህርት ቤት ገብተዋል። የመጀመሪያው ልጅ ኤልያስ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ነው። እንደታላቅነቱ ታናናሾቹን ትምህርት ቤት አድርሶ የመመለስ ሀላፊነቱ ተጥሎበታል። ወርቅነሽ የእነሱን ያህል ዕድል ባታገኝም እንደቤተሰብ አባልነቷ ያሻቸውን ያደርጉላታል።
የቤቱ ልጆች የራሳቸው መኝታ ክፍል አላቸው። ወርቅነሽ ደግሞ ከአልጋቸው ስር አንጥፋ ጎንዋን ታሳርፋለች። ጠዋት ተነስተው ትምህርት ቤት ሲሄዱም የበሉበትን አንስታ የአቅሟን ትከውናለች። አንዳንዴ ደግሞ የቆሸሹ ልብሶችን የማጠብና ሌሎች ስራዎችን የመፈጸም ግዴታው አለባት።
አጎቷ አደራውን ተቀብሎ ትምህርት ቤት ካስገባት ወዲህ የአባቷን መጠሪያ በራሱ ስም ቀይሯል። እንዲህ መሆኑም ወርቅነሽ እንደልጅ አንድትታይና ባይተዋርናት እንዳይሰማት አድርጓል። አልፎ አልፎ አባቷንና እህት ወንድሞቿን መናፈቋ አልቀረም። ከቤተሰቡ ፈጥና መቀላቀሏና ልጅነቷ ግን ሁሉን ያስረሳታል።
ወርቅነሽ ብልህ ልጅ ናት። አንዴ ያየቸውን በቶሎ አትረሳም። ሰዎችን ለመግባባትና ጨዋታ ለመጀመርም የሚያህላት የለም። አንዳንዴ ግን ደርሳ የምትከፋበት ጉዳይ አይጠፋም። በተለይ ደግሞ የቤቱ ትልቅ ልጅ ኤልያስ ሰበብ እየፈለገ ሲጣላት መዋሉ ሆድ ያስብሳታል።
ወርቅነሸ ከሌሎቹ የአጎቷ ልጆች ጋር ሶስት አመታትን በፍቅር ኖራለች። ኤልያስ ግን ሁሌም ምክንያት እየፈለገ ይተናኮላታል። ከእነሱ አልጋ ስር ፍራሽ አንጥፋ ስትተኛም ዕንቅልፍ እኪወስዳት ጠብቆ የለበሰችውን ይገፋታል። ብርድ ልብሱን ከላይዋ አንስቶም በሀፍረት አስክትሸማቀቅ ያሳፍራታል። ጉዳዩ እየባሰ ምርር ባላት ጊዜ ወርቅነሽ ለአጎቷ ሚስት እየተናገረች ታስወቅሰዋለች። እሱ ግን የእናቱ ምክርና ተግሳጽ ከአንድ ቀን በላይ አያዘልቀውም።
ኤልያስ ድርጊቱን እያሰለሰ ይደጋግመዋል። ልጅቷ ለእናቱ እንዳትነግርበትም እየተለማመጠ ይሸነግላታል። በሌሎች ዘንድ ጨዋና ዝምተኛ ለመምሰል የሚያደርገው ሙከራ ተሳክቶለታል። ይህ ዘዴውም ቤተሰቡ ዳግም እንዳይጠረጥረው አድርጓል። የወርቅነሽ የልጅ ልብም የሚሆነውን ሁሉ አየተወ ይዘናጋል።
ታህሳስ 14 ቀን 2005 ዓም
በዚህ ቀን ማለዳ ሁሉም የቤተሰብ አባል ወደተለመደው ስፍራ ተሰማርቷል። ሁሌም ቢሆን የቤቱ አባወራና ሚስታቸው ከቤት ሲወጡ እግራቸውን ተከትላ በር የምትዘጋው ወርቅነሽ ናት። ረፈድ ሲል ደግሞ ወደ ትምህርት ቤት የሚሄዱት ልጆች ከግቢው ይወጣሉ። የታናናሾቹን እጅ ይዞ ትምህርት ቤት የሚያደርሳቸው ኤልያስም በዚህ ሰአት ግዴታ ውን ሊወጣ ዝግጁ ይሆናል።
ገና በማለዳው ከዕንቅልፏ የነቃችው ወርቅነሽ እንደወትሮው ሁሉ ቁርስ የተበላበትን አነሳስታ ለቀሪ ስራዎች ደፋ ቀናውን ጀምራለች። ድንገት ግን ከወደ ውጭ የሰማችው ድምጽ ትኩረቷን ሳበው። ጆሮዋን ጣል አድርጋም አቅጣጫውን ለየች። ኮቴው የአጎቷ ልጅ የኤልያስ መሆኑን ስታውቅ ግን ተመልሳ ወደ ጓዳ ገባች።
ኤልያስ ልጆቹን ትምህርት ቤት አድርሶ እየተመለሰ ነበር። እንዳያት በሩን ከፍቶ ወዳለችበት ዘለቀ። በእጁ አንድ የጂንስ ሱሪ ይዟል የአባቱ ነው። ወርቅነሽ ጉዳዩ ስለገባት ቀና ብላ አስተዋለቸው። ከወትሮው የተለየ ገጽታ ያየችበት መሰላት። ኤልያስ የሱሪውን ኪሶች ፈትሾና አገላብጦ ሲጨርስ እንድታጥብለት ትዕዛዝ ሰጣት። ወርቅነሽ ሌሎች ስራዎች እንደሚጠብቋት ታውቃለች። የእሱን ትዕዛዝ ግን ‹‹እምቢኝ›› ማለት አይቻላትም።
ኤልያስ ትዕዛዙን ከሰጣት በኋላ የለበሰውን ቀይሮ እጀ ጉርድ ካናቴራና ቁምጣ ለበሰ። ጫማውንም በፍጥነት ለወጠ። ወርቅነሽ ሱሪውን ተቀብላ ወደ ማጠቢያው ስታመራ ካለበት ቆሞ አሻግሮ ተመለከታት እሷ ገጽታው ከቀድሞው ፈገግ ያለ ቢመስላት ልትለማመጠው ሞከረች። ባልጠነከሩ ቀጫጫ እጆቿ ጂንሱን እያሸችና ሳሙና እየመታችም ዝምታውን በንግግር ሰበረች።
ወርቅነሽ የአጎቷን ልጅ አለባበስ አስተውላ ጨዋታውን ከግርምታዋ ጀመረች። እጁን በዚህ መልኩ አጋልጦ አይታ አታውቅምና በሁኔታው ስለመደነቋ አልሸሸገችውም። ደጋግማ ስታየው ደግሞ አንድ ምስል ውል አለባት። በምታየው መልኩ አልፋም አጎቷን አስታወሰች። ሳሎን ከተቀመጠው አልበም ውስጥ አባቱ በልጅነቱ እንደሱ ሆኖ ፎቶግራፍ ስለመነሳቱ ነግራውም ፎቶው አልበም ውስጥ እንደሚገኝ ጠቆመችው።
ኤልያስ የወርቅነሽ ጨዋታ ተመችቶታል። ያጠበችውን ካሰጣች በኋላም ‹‹አየሁት›› ካለችው ስፍራ ፈልጋ ፎቶውን እንድታሳየው ጠይቋታል። ይህን ስትሰማ ተደሰተች። ፎቶውን ልታሳየውም ተነሳች። እሱም ፎቶግራፉን አይቶ ለማረጋገጥ ከኋላዋ ተከተላት።
ወርቅነሽ ከሳሎኑ እንደገባች አልበሙን መፈለግ ጀመረች። ቀድሞ ከነበረበት ቦታ አላገኘችውም። ቆም ብላ ስታስብ ከብፌው ላይ ሊኖር እንደሚችል ገመተች። ብፌው ከእሷ ቁመት በላይ በመሆኑ አትደርስበትም። ከሳሎኑ ወንበሮች አንዱ ላይ ወጥታ ለማውረድ ተንጠራራች። አልበሙ ከእጇ እንደገባም ገጾቹን አንድ በአንድ እያገላበጠች ፍለጋዋን ያዘች። ፎቶው ግን አልነበረም።
ኤልያስ አጋጣሚውን እንዴት እንደሚጠቀ ምበት ያስባል። ሁሌም ቢሆን ወርቅነሽ ዘመዱ መስላው አታውቅም። ባያት ቁጥር ስሜቱ እየተለወጠ ሲቸገር ቆይቷል። ህጻን ልጅ መሆኗና በአባቱ ስም መጠራቷ ያሰበውን ከማድረግ እንደማይመልሰው ለራሱ ነግሮታል። ይህ ቀን ደግሞ ዛሬ ሊሆን ግድ ነው።
ኤልያስ በሁኔታዋ ተገርሞ ያስተዋላት ጀምሯል። አሁን ለእሱ የፎቶግራፉ ጉዳይ አያሳስበውም። በተለየ ትኩረት ፍለጋ ላይ መሆኗ ደግሞ የሁኔታውን መለወጥ እንድታየው አላስቻላትም። የእሱ ዓይኖች ግን ተጠቅልሎ ከተቀመጠ ድፍን ሶፍት ላይ አነጣጥረዋል። የሶፍቱን እሽግ ፈታና በእጆቹ ላይ መጠቅለል ጀመረ። ‹‹አዎ! ትንሽዋ ወፍ›› ዛሬ መጠመድ አለባት።
ወርቅነሽ ፎቶውን ፈልጋ በማጣቷ ወንበሩን ከቦታው መልሳ ወደጓዳው አመራች። ድንገት ግን በሶፍት የተጠቀለለው የኤልያስ እጅ በአፏ ላይ አርፎ ትንፋሽ አሳጣት። የአቅሟን ያህል እየታገለች ልታስለቅቀው ሞከረች። አልቻለችም። ግጥም አድርገው የያዟት እጆች አቅምና ትንፋሽ ሲያሳጧት ራሰዋን ስታ ተዘረረች።
ኤልያስ ያልጠበቀው በመከሰቱ ተደናግጧል። እንዲህ በቀላሉ አቅም የምታጣ አልመሰለውም። አሁን ሁኔታውን ለማስተካከል መረጋጋት ይኖርበታል። ከወደቀችበት አንስቶ ከልብስ ማጠቢያው ገንዳ ውሀ እያፈሰሰ ሊያነቃት ሞከረ። ቅዝቃዜው ሲሰማት አይኖቿን ገለጠች። ፊት ለፊት ስታየው ግን ሁኔታውን አስታወሰች። ድርጊቱን ተቃውማም መጮህና ማልቀስ ጀመረች።
ኤልያስ ሁኔታዋን ሲመለከት ምንም እንዳልተፈጠረ ለማስመሰል ሞከረ። እያባበላትም ሳሎን ከሶፋው ላይ እንድታርፍ ደግፎ ወሰዳት። ወርቅነሽ የለበሰቸው ቱታ በውሀ መራሱን አይታ ራሷን ዳሰሰች። በድንጋጤ እንደራደችም ከሳሎኑ ደርሳ ከሶፋው ተቀመጠች። ወዲያው ግን ሰውነቷ ዝሎ አቅሟ ሲክዳት ተሰማት።
የልጅቷን መዳከም ያስተዋለው ኤልያስ ከሳሎኑ ትቷት ወደ መኝታ ክፍሉ አመራ። ቆይቶ ሲመለስ የተለወጠ ነገር የለም። አሁንም ወርቅነሽ ከነድካሟ ናት። ኤልያስ መልሶ ማሰብ ጀምሯል። ያሻውን ለማድረግ ከዛሬ የተሻለ ቀን እንደማይኖር አውቋል። በድካም ዝላ የወደቀችውን ልጅ እያየ ቀረባት። ወዲያውም የለበሰችውን ቱታ ለማውለቅ መታገል ጀመረ።
ወርቅነሽ ኤልያስ በጉልበት እየታገላት መሆኑን ስታውቅ በድንጋጤ ለመነሳት ታገለች። ወዲያው ግን በፈርጣማ እጆቹ ተገፍትራ ወደቀች። ሰውነቷን እየነካካ እየሳመና እየታገለ ሊያባብላት ሞከረ እንዳሰበው ሆኖ በቀላሉ አልተሸነፈችም። እየታገለችና አየጮኸች ስትበረታበት አፏን አፍኖ አስጨነቃት። ሰውነቷን እንዳሻው አድርጎም የፍላጎቱን ፈጸመ።
ከድርጊቱ በኋላ ልጅቷ እያለቀሰችና እየጮኸች ያደረገውን ሁሉ ለአባቱ እንደምትናገር አሳወቀቸው። ይህኔ ንዴቱ ግሎ አይኑን አፈጠጠ። እንዳለችው የምታደርግ ከሆነም ፈጽሞ እንደማይለቃት እየማለና እየዛተ አስጠነቀቃት። ይህን ብሎ ዞር ከማለቱ ዓይኑ በአንድ ቦታ ላይ አተኮረ።
ከበሩ ጥግ የተቀመጠውን ረጅም ቢላዋ እንደዋዛ ሊያልፈው አልፈለገም። ከነበረበት አንስቶ በወርቅነሽ አንገት ላይ አሳረፈው። መላ አካሏን አልፎ በልብሶቿ መውረድ የጀመረውን ትኩስ ደም ሲመለከት ጠጋ ብሎ ትንፋሽዋን አደመጠ። ህይወቷ እንዳለፈ ሲገባው ደም የነካውን ቢላዋ በልብሶቿ ጠራርጎ ስለቱን ካገኘበት መለሰ። ለማፈን የተጠቀመበትን ሶፍት በመስኮት ወረወረና ደም የነካውን እጁን ታጥቦ ልብሶቿን ሰበሰበ።
በሩን የኋሊት ዘግቶት ሲወጣ ዞር ብሎ አላየም። አዕምሮውን ለቀጣይ ዕቅድ እያዘጋጀው በመሆኑም ጊዜ ማጥፋት አላሻውም። ደም የነካውን ልብስ እንደያዘ አጥሩን ዘሎ ወጣ። የያዘውን ገደል ጨምሮ ሲመለስም ከውጭ በኩል ቆሞ በሩን ማንኳኳት ያዘ። ደጋግሞ የወርቅነሽን ስም እየጠራም በሩን እንድትከፍትለት ጠየቀ። የእጆቹ ምት አየጨመረ ሲሄድ ከውስጥ ያለ ሰው እንዳልሰማው ምልክት ሆነለት። ለሚያዩት ሁሉ የተናደደ ለመምሰልም ሙከራው ተሳካለት።
አሁን ኤልያስ ደጋግሞ ያንኳኳው በር ባለመከፈቱ ዘሎ መግባት እንደሚኖርበት አውቋል። ‹‹ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ›› የሆነውን ዕቅድ ለራሱ እንዳሳለፈም እግሮቹን በብረት በሩ ላይ አሳርፎ ወደ ውስጥ ዘለለ።
ድንገቴው ጥሪ
የቤቱ አባወራ ከልጃቸው በመጣው የስልክ ጥሪ የደረሳቸው መልዕክት በእጅጉ አስደንጧቸዋል። ኤልያስ አጥሩን ዘሎ ሲገባ ያጋጠመውንና የነገራቸውን እውነት ለማመን ተቸግረዋል። በስፍራው ሲደርሱ ትንሽዋ ወርቅነሽ በቢላዋ ታርዳና ልብሶቿ ተገፎ እርቃኗን ባይዋት ጊዜም ‹‹ህግ ይፍረደኝ›› ሲሊ ለፖሊስ ‹‹አቤት›› አሉ።
የፖሊስ ምርመራ
ፖሊስ የደረሰውን ጥቆማ ተከትሎ ዮሴፍ ጥምቀተ ባህር ልዩ ቦታው ‹‹ሸገር›› ከተባለ ሰፈር ደርሷል። በግቢው ገብቶ ወደሳሎኑ ሲያልፍም በሚያሳዝን ሁኔታ የተገደለችውን ህጻን አስከሬን አግኝቶ ቴክኒካዊ መረጃዎችን ከአካባቢው ማስረጃዎች ጋር አዳምሯል። በወቅቱ ከነበሩት ማሳያዎች መሀል እንደ ኤልያስ ለወንጀሉ ጥርጣሬ የቀረበ ሰው ያላገኘው ፖሊስ ለተጨማሪ ጥያቄዎች እንደሚፈልገው አሳውቆ ወደማረፊያ ቤት ወሰደው።
አሁን ፖሊስ ምርመራውን ማካሄድ ጀምሯል። በምክትል ሳጂን መንግስቱ ታደሰ የወንጀል መርማሪነት የተጀመረው ሂደት በአግባቡ እየተከወነ ነው። በመዝገብ ቁጥር 484/05 የተከፈተው ፋይልም አስፈላጊ የሚባሉ መረጃዎች ሁሉ ይመዘገቡበታል።
ከፖሊስ የቀረበለትን ጥያቄ ያለምንም ችግር ሲመልስ የቆየው ኤልያስ ወንጀሉን እንዳልፈጸመ ለማስረዳት ሞከረ። ሙከራው ሁሉ እንደማያዋጣው ሲገባው ግን እውነታውን ተናግሮ ድርጊቱን ስለመፈጸሙ አምኖ በፊርማው አረጋገጠ። ፖሊስ በቂ የሚባል ማስረጃና መረጃ በእጁ ከገባ በኋላ ተከሳሹን ለፍርድ ለማቅረብ የሚያስችለውን ሰነድ ወደ ዓቃቤ ህግ አሳለፈ።
አዲስ ዘመን ነሐሴ 18 ቀን 2011
መልካምስራ አፈወርቅ