የዘመናዊ ኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ (አርት) ሊቅ ናቸው፡፡እኝህ ሊቅ ለረጅም ዓመታት በተለያዩ የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች በዘመናዊ አርት(ስዕል) በመምህርነት አገልግለዋል፡፡እውቁ ሊቅ ፕሮፊሰር አቻምየለህ ደበላ በ1941 ዓ.ም አዲስ አበባ መርካቶ አካባቢ የተወለዱ ሲሆን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኪነ ጥበብ ትምህርት ቤት (አርት ስኩል) እውቅ ሰዓሊያን በሆኑት እስክንድር በጎሲያን፣ ዓለም ፈለገሰላም፣ገብረክርስቶስ ደስታ፣ሀንሰን ብሃ ባሉ መምህራን ተምረዋል፡፡
ብርሃኑ ዘሪሁን፣ጳውሎስ ኞኞና ሌሎች ታዋቂ ጋዜጠኞች ለሚ ጽፏቸው ጽሁፎች የካርቱን ስዕሎችን ይሰሩ ነበር፡፡ እንዲሁም ፕሮፌሰር አቻም የለህ በናይጄሪያ አህመዱ ቢሎ ዩኒቨርሲቲም በግራፊክና ፕሪንቲንግ አርት ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡በአሜሪካን አገር በሞርጋን ዩኒቨርሲቲና በሜሪላንድ ኮሌጅ ኦፍ አርት ኢንስቲትዩት በዲጂታል አርትና በሙዚየም አስተዳደር ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ይዘዋል፡ ፡በዚሁ አገር የሶስተኛ ዲግሪያቸውን በመያዝም አሜሪካ በሚገኙ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በመምህርነት ለረጅም ዓመታት አገልግለዋል፡፡የስዕል ሥራዎቻቸውንም በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚዘጋጁ የተለያዩ የስዕል ኤግዚቢሽኖች ላይ በማቅረብ ሥራዎቻቸውንና አገራቸውን አስተዋውቀዋል፡፡
ከሙያቸው ጎን ለጎንም ፕሮፌሰር አቻምየለህ ደበላ ትልቁ የኢትዮጵያ አንድነት ኃይሎች ስብስብ የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሽንጎ) የሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ አባላት ሆነው ሰርተዋል፡፡መድህን ተብሎ የሚጠራውና በአሜሪካን አገር እየተንቀሳቀሰ በሚገኘው የፖለቲካ ፓርቲ አመራርም ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ግሎባል አሊያንስ ተብሎ በሚጠራው ግብረ ሰናይ ድርጅትም የቦርድ አመራር ሆነው እየሰሩ ነው፡፡እኝህ እውቅ ምሁር በስዕል ሥራዎቻቸው፣ቱሪዝምን በማስተዋወቅ፣የፖለቲካ ተሳትፏቸውና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ቃለ መጠይቅ አድርገንላቸዋል፡፡እነሆ፡-
አዲስ ዘመን፡- ፕሮፌሰር ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ለምን ጉዳይ ነው ?
ፕሮፌሰር አቻምየለህ፡- እኔ ከረጅም ዓመታት የውጭ አገራት ቆይታ በኋላ ነው ወደ ኢትዮጵያ የመጣሁት። የመጣሁበት ዋና ጉዳይ መንግሥት ዲያስፖራው በሙያው አገሩን መደገፍና መሳተፍ እንዳለበት ያስተላለፈውን ጥሪ ተከትዬ ነው። እኔም ከልጅነቴ ጀምሮ ባዳበርኩት የኪነ ጥበብ(ስዕልና የሙዚየም አስተዳደር) ሙያ ያለኝን እውቀት ለማካፈል ነው በራሴ ተነሳሽነት ወደ አገሬ የተመለስኩት።
አዲስ ዘመን፡- ሰዓሊ የሆኑት መርጠው ወይስ ስለተማሩት ብቻ ነው?
ፕሮፌሰር አቻምየለህ፡- የስዕል ፍቅር ያደረብኝ ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ ነው። ለትምህርት ቤት ጓደኞቼ የስዕልና የዲዛይን የቤት ሥራ ሲኖር እኔ ነበርኩ የምሰራላቸው ። ስዕል በሰራሁላቸው ቁጥር ከትምህርት ቤታችን ጀርባ ሙልሙል ዳቦ ከሚሰሩት እማማ አደሽ ሙልሙል ዳቦ ይገዙና አብረን እንበላ ነበር ። የስምንተኛ ክፍል ሚኒስትሪ ፈተና ከወሰድኩ በኋላ መግቢያ ፈተናውን ጥሩ ውጤት አምጥቼ አርት ስኩል ( ኪነጥበብ) ትምህርት ቤት ገባሁ።
አምስት ዓመታት የስዕል ትምህርትን ከተማርኩ በኋላ ዲፕሎማ ያዝኩ። የኪነ ጥበብን (አርትስኩልን) የመሰረቱት ፈለገሰላም ናቸው። አቶ ገብረክርስቶስ ደስታ አስተምረውኛል። አሸናፊ ከበደ ያሬድን የሙዚቃ ትምህርት ቤት ያቋቋሙ ናቸው። እሳቸውም አስተምረውኛል። በአፍሪካ ሁሉ የታወቀ ትምህርት ቤት ነበር። ትምህርቴን ከጓደኞቼ ጋር ከጨረስኩ በኋላ የተወሰነው ተመራቂ በአስተማሪነት በየጠቅላይ ግዛቱ ተመደበ። ሥራ ፈልጎም የተቀጠረ አለ። እኔም ደግሞ ሥራ ፈልጌ ቱሪስት ድርጅት ተቀጠርኩ። እናም መርጨ የገባሁበትና የምወደው ሙያ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በምን ሙያ ዘርፍ ነው ቱሪዝም የተቀጠሩት?
ፕሮፌሰር አቻምየለህ፡-በስዕል ሙያ ነው። አገርን የሚያስተዋውቁ ግራፊኮችንና ስዕሎችን እሰራ ነበር። በዚያን ጊዜ አቶ ሀብተስላሴ ታፈሰ የቱሪዝም ሚኒስትር ነበሩ። ቱሪዝም ድርጅትን ያቋቋሙ እሳቸው ናቸው። ሁሌም እዚያ በር ላይ ያዩኝ ስለነበር አንተ ደግሞ መቼ ነው ዘበኝነት የቀጠርኩህ አሉኝ። አልተቀጠርኩም ገና ሊቀጥሩኝ ነው የመጣው ስላቸው ይዘውኝ ወደ ቢሮቸው ወሰዱኝ። በዚያን ጊዜ አንድ ሚኒስትር ቢሮ መግባት ታአምር ነበር። ቢሮቸው አስቀምጠውኝ ሥራቸውን ከሰሩ በኋላ ምን ትሰራለህ ብለው ጠየቁኝ? ሰዓሊ ነኝ ስላቸው ዲፕሎማው የታለ ሲሉኝ ገና አልተሰጠኝም ብዬ ባዶ እጄን ዘርግቼ አሳየኋቸው ።
ገርሟቸው በድርጅቱ ውስጥ የአርትና ፋብሪኬሽን ክፍልን የምትመራውን ጅን ኩን የምትባል እግሊዛዊትን ጠሯት። ስትመጣም እኔን እያሳዩ ይህ ወጣት ልጅ ሰዓሊ ነው። ሥራ ስጭውና ጥሩ የሚሰራ ከሆነ ይቀጠር የማይችል ከሆነ ደግሞ አባሪው ብለው መመሪያ ሰጧት። እሷም አንድ ጠረጴዛና ወንበር ሰጥታኝ የምሰራውን በዝርዝር አስረዳችኝ። ሥራም ሰጥታኝ እኔም በምትፈልገው መልኩ አሳምሪ ሰርቼ ሰጠኋት። ከዚያም በሚኒስቴሩ የሥራ ባልደረባ ሆኜ ተቀጠርኩ።
በወሩ መጨረሻ ላይ 300ብር ደመወዝ ተሰጠኝ። 300 ብር አይቼም አላውቅም። እናም የተሰጠኝ አዳዲስ ብር ነው እየፈነደኩ ብሩን ይዥ ወደ ቤቴ ሄድኩ። ብሩን ለእናቴ ሰጠኋት። በ1960 ዓ.ም 300 ብር በጣም ብዙ ነው ። እናቴም ደንግጣ ወድቆ ነው ያገኘኸው ወይስ ባንክ ዘረፍክ አለችኝ። እኔም ሥራ ተቀጥሬ ያገኘሁት መሆኑን አስረዳኋት። ይህን ምክንያት በማድረግም በብሩ የሚገዛው ተገዝቶ መለስተኛ ድግስ ተደገሰ። በአካባቢው ሰውም ተመረኩ። እናቴም በጣም ደስ አላት።
አዲስ ዘመን፡-ቱሪዝምን ለማስተዋወቅ ምን ምን ትሰራላችሁ?
ፕሮፌሰር አቻምየለህ፡-ሁለት ዓመታት ያህል ቱሪዝም ሚኒስትር የህትመትና ስርጭት ሥራ ክፍል ምክትል ኃላፊም ሆኜ ሰርቻለሁ። አገርን ለማስተዋወቅ ብዙ ነገሮች እንሰራ ነበር። የዋና ዋና ከተሞች የሚታወቁበትን መገለጫ ጭምር በማካተት ስዕሎችን እንስላለን። ለምሳሌ የአዲስ አበባ ከተማ ፣የጎንደር፣የባህርዳር፣ የጅማና የሌሎች ከተሞችን ስዕልና ግራፊክስ እንሰራ ነበር ። ብዙ ጊዜ ቱሪስቶች የምንሰራውን ፖስተር ይገዙት ነበር።
በኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚሸጥ ደግሞ አንበሳ ምስል ያለበት በወርቅ ቅብ ሼሚዝ ላይ የሚደረግ ጌጥ እንሰራለን። እኛ ዲዛይኑንና ስዕሉን እንሰራለን አቶ ሀብተስላሴ ጣሊያን ወይም ጃፓን አገር ሄደው አሳትመው ይመጡ ነበር። የመጫወቻ ካርታም ሰርቻለሁ። በዚህ የመጫወቻ ካርታ ላይ ያሉት ምስሎች የኢትዮጵያን የተለያዩ ባህሎች አልባሳትን የሚያንጸባርቁ፣የአርበኝነትን ተጋድሎ የሚያሳዩና የንጉሶች ምስልን ያረፈበት ነው። ለምሳሌ ወለድ የሚለው ላይ አርበኞች ከነ ልብሳቸው ንጉስ የሚበላውን ካርታ ደግሞ አጼ ቴዎድሮስን፣ አጼ ዮሐንስንና አጼ ምኒልክን፣አድርጌ ካርታ አሳትሚያለሁ።
አጼ ኃይለስላሴን በካርታው ውስጥ አላካተትኩም። ካርታውን አቶ ሀብተስላሴ ለአጼ ኃይለስላሴ ወስደው አሳዩአቸው። ጃንሆይም እኛ የታለንበት አሏቸው። አቶ ኃብተስላሴም እሳቸውን ለምን አላከተትካቸውም ሲሉ ጠየቁኝ ?እኔም በህይወት ያሉትን በህይወት ከሌሉት ጋር መደባለቅ ክብር ማሳጣት ነው ብዬ
ነው አልኳቸው። የተለያዩ ፖስተሮችንም እሰራለሁ። ለምሳሌ ሰርቲን መንዝ ኦፍ ሰን ሻይን የሚለውን ግራፊክሱንና ዲዛይኑን የሰራሁት እኔ ነኝ። ብዙ ፖስተሮችን ሰርቻለሁ። የተለያዩ ብሄረሰቦችን አለባበስ፣ ባህላዊ ዕቃዎችን፣ገቢያዎችን ለምሳሌ የሀረር ገበያ ስዕልን ከሰረኋቸው ስዕሎች አንዱ ነው። የዛሬ 49 ዓመት በፊት የሰራኋቸው ሥራዎች የቱሪዝም ድርጅት ቦሌ በሚገኘው የስጦታ ዕቃዎች መሸጫ ውስጥ ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን፡-የትምህርት ጉዞዎት የት ነበር ያበቃው?
ፕሮፌሰር አቻምየለህ፡-የቱሪስት ድርጅት ሥራዬን እየሰራው ትምህርት መቀጠል አለብኝ በሚል ነጻ የትምህርት ዕድል ሳፈላልግ ነበር። የዚያን ጊዜ ወጣቶች ለትምህርት አውሮፓና አሜሪካ መሄድ ነበር ፍላጎታችን። ሆኖም በእነዚህ አገራት የትምህርት ዕድል ላገኝ አልቻልኩም። አፍሪካ ኢንስቲትዩት የሚል ተቋም አዲስ አበባ ውስጥ ነበር። ይህ ተቋም ከትምህርት ሚኒስትር ጋር በመተባበር አፍሪካውያን ተማሪዎች በአፍሪካ ውስጥ በሚል የመጀመሪያ ዲግሪ የትምህርት ዕድል ይሰጡ ነበር። እኔም በዚህ ዕድል ናይጄሪያ የትምህርት ዕድል አገኘሁ።
አርማዶቢሎ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪዬን በግራፊክና በፕሪንቲግ ያዝኩ። በዩኒቨርሲቲው 13 ኢትዮጵያውያን የትምህርት ዕድል ያገኘን ብንሆንም አርት ስኩል የገባሁት እኔ ብቻ ነበርኩ። ናይጀሪያ የተማርኩት ከ29 የአፍሪካ አገሮች ከመጡ ተማሪዎች ጋር ነው። ከተለያዩ አፍሪካ አገሮች ጓደኞቼ ጋር እረፍት ሲኖረን ወደ ቶጎ ሎሜ፣ ላይቤሪያና ሌሎች የምዕራብና የሰሜን አፍሪካ አገሮች መጎብኘት ችያለሁ። ሮዲዥያ(ዝምባቢዌ) ጃን ሆይ በአፍሪካ ነጻነት ላይ ጠንከር ያለ አቋም ስለነበራቸውና ይናገሩ ስለነበሩ አላስገባ ብለው ከለከሉኝ። ስዕል ሸጬ በማገኘው ገንዘብ በጭነት መኪና እየተንጠለጠልኩና ከሰውና ከእንስሳት ጋር አብሬ እጓዝ ነበር።
በዚህ መልኩ ብዙ የአፍሪካ አገሮች ሄጃለሁ። መኪናው ላይ ሆኜ ስዕል እየሳልኩ ነበር የምጓዘው። ገንዘብ ለማግኘት ሳይሆን እውቀት ለማግኘትና ፍላጎቴን ለማሟላት ነው የምንሰራው። ይህ ለእኔ አዲስ አይደለም። አገር ቤት እያለሁም ትምህርት ሲዘጋ አብረውን ከሚማሩ የክፍለ አገር ልጆች ጋር አብሬያቸው ገጠር እሄዳለሁ። ወለጋ፣ ጅማ፣ ጎጃምና አጋሮ ሄጃለሁ። በሄድኩበት ሁሉ እናቶች እንደ ልጃቸው አድርገው ነው የሚንከባከቡኝ። ይህም ኢትዮጵያዊ ስሜቴን እንዲጠናከር አድርጎልኛል። ለስዕል ሥራዬ ጠቅሞኛል። በየቦታው ያሉ የቋንቋ፣የባህል ልዩነቶችንና አንድነቶች እንድረዳ አድርጎኛል።
ሁለተኛ ዲግሪ ለመያዝ ፍላጎት ስለነበረኝ በናይጀሪያ የስዕል ኤግዚቢሽን አሳይቼና የተለያዩ ስዓሎችን ሽጬ ባገኘሁት ገንዘብ ወደ እንግሊዝ አገር ሄድኩ። ከናይጀሪያ ቀጥታ ወደ እንግሊዝ አገር ነው የሄድኩት። ለንደን ውስጥ ሀይድ ፓርክ የሚባል ቦታ እሁድና ቅዳሜ ለመዝናናትና ለመጎብኘት ብዙ ሰው ይመጣል። የሚመጡ ሰዎችን ስዕል ወዲያውኑ እየሰራሁ ገንዘብ አገኝ ነበር።
700 ፓውንድ አጠራቀምኩ። በኋላ ዓለም አቀፍ የተማሪዎች ማህበር ከእነሱ ጋር ወደ አሜሪካ ሄድኩ። ወደ አሜሪካ ስሄድ ቪዛ አልነበረኝም፤ ዝም ብዬ ነው የሄድኩት። ብዙ ኢትዮጵያውያን በእኔ መልኩ የሄዱ አሉ። ኒዮርክ ዩኒቨርሲቲ ለመማር አመለከትኩ። ሆኖም አልተሳካም። የነበረኝም ገንዘብ እየተመናመነ በመምጣቱ ብዙ ኢትዮጵያውያን ወደ አሉበት ዋሽግተን ዲሲ አቀናሁ። በዋሽንግተን ጎዳና ስንቀሳቀስ እንደ አጋጣሚ ጓደኛዬን አገኘሁት። በአጠገቡ ሳልፍ አቻምየለህ ብሎ ተጠመጠመብኝ። ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ ምን እየሰራህ ነው ብዬ ስጠይቀው ሚዙሪ ዩኒቨርሲቲ ነው የምሰራው አለኝ።
ከዚያም ቤቱ ወስዶኝ ሰሀን የማጠብ ሥራ አስገባኝ። የተወሰነ ጊዜ ሰሀን ማጠብ ሥራ ስሰራ ቆይቼ አካባቢውን እየለመድኩ ስሄድ ሌላ ሥራ መፈለግ ጀመርኩ። እንደ አጋጣሚ ቦልቴሞር ስቴት የሚባል ዩኒቨርሲቲ የአርት ክፍል ዳይሬክተሩ ናይጀሪያ እያለሁ ኤግዚቢሽን ሳሳይ ተዋውቀን ነበር። የሥራ ማመልከቻ ወደ ዩኒቨርሲቲው ሳስገባ ተቀበሉኝና እዚያው ዩኒቨርሲቲ በሙዚየም አስተዳደር ሁለተኛ (የማስተርስ) ዲግሪዬን ሰራሁ።
ከተማው ውስጥ እየተላመድኩ ከሄድኩ በኋላ ከማስተማሩ ጎን ለጎንም የስዕል ሥራዎችን ለመጀመሪያው በሰሜን አሜሪካ ዘመናዊ የስዕል ኤግዚቢሽን አዘጋጅቻለሁ። የሙዚየሙ ሥራ ብዙ ሥራ ስለነበር ስዕል የመስሪያ ጊዜ አላገኘሁም። ሜሪላንድ ኢንስቲትዩት ኮሌጅ ኦፍ አርት ሌላ ሁለተኛ ዲግሪ በአርት ያዝኩ። በዚሁ ማስተማር ጀመርኩ። ከዚያ ኦሀዮ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ይዥ ሄጀ እኔ ራሴ የትምህር ዕድሉ ተጠቃሚ ሆንኩ። በዲጂታል አርት ሶስተኛ ዲግሪ (ፒኤችዲ) አገኘሁ።
እያስተማርኩ ነው የተማርኩት። የኖርዝ ኮራላይና ዩኒቨርሲቲ ዲን ዩኒቨርሲቲውን ስትጎበኝ እያስተማርኩ ነበር። ኃላፊውን ጠይቃ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የኮምፒዩተር ግራፊክ መምህር ስላልነበራቸው ከ1991 ጀምሮ እስካሁን ድረስ እያስተማርኩ ነው። በአሜሪካ አገር በሚገኙ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ብዙ ተማሪዎችን አስተምሬ አስመርቄያለሁ።
እዚያ አገር የምታስተምረው ስለህ በተግባር እያሳየህ ነው እንጂ ማነብነብ ብቻ አይደለም። ስለ ጥቁር አሜሪካ ኪነጥበብ ዕድገት፣ስለ ግራፊክስ፣ስለ አፍሪካ ኪነ ጥበብ ታሪክ፣ስለ ዘመናዊ የአፍሪካ ኪነ ጥበብ፣ አስተምሬያለሁ። አሁንም እያስተማርኩ ነው። የተወለድኩት በ1941 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ መርካቶ አካባቢ ነው። የኔታ አስገድግድ የቄስ ትምህርት ቤት ገብቼ እስከ ዳዊት ድረስ ተምሬያለሁ። ከዚያም በወሰን ሰገድ ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርቴን ተከታትያለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ከማስተማርና ስዕል ሥራዎች ጎን ለጎን ማህበራዊ ኃላፊነትዎን ለመወጣት የሚሰሯቸው ሥራዎች ይኖሩ ይሆን?
ፕሮፌሰር አቻምየለህ፡-በሰሜን አሜሪካ የምንኖር ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች የምንሰራቸው ሥራዎች አሉ። ለምሳሌ በግሎባል አሊያንስ ፎር ኢትዮጵያንስ የሚል ድርጅት አለ። ከእነ ታማኝ ጋር በዚህ ድርጅት ውስጥ እሰራለሁ። የቦርድ አባል ነኝ። ኢትዮጵያን ዲያሎግ ፎረም የሚባል የውይይትና የመፍትሄ አፈላላጊ ድርጅት ውስጥም የህዝብ ግንኙነት ሆኜ እየሰራሁ ነው። በጣም የታወቁ ምሁራኖችን በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ከህዝብ ጋር በማወያየት መፍትሄ የመሻት ዓላማ ያለው ነው። በተለይ ኢትዮጵያ ላይ ያተኮረ ነው።
በቴክኖሎጂም፣ኒኩሌር ፊዚክስ፣በኪነ ጥበብ፣በባህል፣በፖለቲካና ኢኮኖሚ ጉዳዮች ኢትዮጵያን አስመልክቶ ርዕሰ ጉዳዮችን እየመረጥን በዚህ ዙሪያ ባለሙያ የሆኑ ኢትዮጵያውያንን ጋብዘን በችግሩና በመፍትሄው ዙሪያ ያተኩረ ጹሁፍ እንዲያቀርቡ እናደርጋለን። እኛ ከፖለቲካ ፓርቲ ድርጅት ጋር ግንኙነት የለንም። ነገር ግን የምንሰራቸው ሥራች ህዝቡ በቂ እውቀትና መረጃ እንዲኖረው እናደርጋለን። መንግሥትም የሚጠቀምባቸው ከሆነ ለመስጠትና ለማማከር ፈቃደኞች ነን።
አዲስ ዘመን፡- ብርሃኑ ዘሪሁንና ጳውሎስ ኞኞ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ለሚጽፏቸው ርዕሰ ጉዳዮች እርስዎ ካርቱን ይሰሩ ነበር። ምን ምን ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ናቸው?
ፕሮፌሰር አቻምየለህ፡-የአርት ስኩል ተማሪ እያለሁ የእኔ ጓደኛ ዮሐንስ ገዳሙ ለኢትዮጵያ ሬዲዮ ማስታወቂያ ይሰራ ነበር። እኔ ደግሞ ለጋዜጠኞች ካርቱን እሰራ ነበር። ለምሳሌ ከጋሽ ጳውሎስ ጋር ዚያድባሪን በተመለከተ ለሚጽፈው ጽሁፍ ዚያድባሪን ኢትዮጵያን ለመውረር ባሰፈሰፈ ጊዜ ዚያድባሪን በተለያየ መልክ በካርቶን እየሰራን እናወጣ ነበር ። ፖለቲካና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይም እንዲሁ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ የተለያዩ የካርቶን ሥራዎችን ሰርቻለሁ።
ከጋሽ ብርሃኑ ለሚጽፋቸው ጽሑፎች ካርቶን እሰራለት ነበር። በአዲስ ዘመን፣በኢትዮጵያ ድምጽ፤በሰንደቅ ዓላማችን በሚባሉ ጋዜጦች የካርቶን ሥራዎችን ሰርቻለሁ። ለምሳሌ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ የማስታውሰው ዱዱ የሚባል ገጸ ባህሪ ነበር። በሳምንት ቅዳሜ እትም የሚወጣ ነው። ዱዱ የሚባለው ልጅ አስቸጋሪ ባህሪ ያለው ገጸ ባህሪ ነው።
ለምሳሌ ሲኒማ ቤት ለመግባት መኪናቸውን በር ላይ የሚያቆሙ ሰዎችን ልጠብቅላችሁ ብሎ ሲያባብላቸው እነሱም ዞር በል ወስላታ ብለውት ከሄዱ የመኪናውን ጎማ በመርፊና በሚስማር ያስተነፍሳል። ይህ ድርጊት ተገቢ አይደለም ብሎ ለማስተማር የሚጻፍ ጽሁፍ አለ። ለእንደእነዚህ አይነት ጽሁፎች ካርቶን እሰራ ነበር።
የስዕልና ኪነ ጥበብ የመጀመሪያውን መጽሄት ጀምሬ ነበር። በዚህ መጽሄት ገብረክርስቶስ ደስታ፣ሰለሞን ደሬሳ፣እኔም ግጥምና ጽሁፍ እጽፍ ነበር። ሥራዎቻችን ለማሳየት ታታሪ ነበርን። በዚህም ኪነ ጥበብን ለህዝብ ለማስተዋወቅ ጥረት አድርገናል። ገንዘብ ስላልነበረን በየድርጅቶች በር እየሄድን ለምን ድርጅታችሁን አናስተዋውቅላችሁም በሚል ክፍያ እንጠይቃቸው ነበር። በዚህ መልኩ መጽሄቷን አዘጋጅተን ብርሃንና ሰላም እናሳትም ነበር።
አዲስ ዘመን፡-እሳቸውም ማስታወቂያ ይሰሩ ነበር ብለውኛል። እስኪ እሳቸው ከሰሯቸው ማስታወቂያዎች አንዱን ይነገሩኝ?
ፕሮፌሰር አቻምየለህ፡-አቶ ሀብተስላሴ ብዙ ነገር ነው የሚሰራው። አንድ እሳቸው የነገሩኝን የማስታወቂያ ሥራ ብነግረህ በጣም ትገረማለህ። በጣም ፈጣን ሰው ስለሆኑ በወቅቱ ቀዥቃዣ ሚኒስትር ይሏቸው ነበር። ከተለያዩ የዓለም አገሮች የኢንዱስትሪ ድርጅት ተወካዮች ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ። በዚህ ጊዜ እሳቸው ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመነጋገር ከእዮቤልዩ ቤተ መንግሥት አስፈቅደው ሞላ ተብሎ የሚጠራውን አንበሳ አየር መንገድ ድረስ ወስደው እንግዶቹ ከአውሮፕላን ከወረዱ በኋላ አንበሳውን ወደ ጎብኚዎቹ ይዘውት ሲሄዱ እንግዶቹ ተመልሰው ወደ አውሮፕላኑ መሯሯጥ ጀመሩ።
አትጨነቁ ተብለው አንበሳውን እየዳሰሱ ሰው እንደማይጎዳ በተግባር አሳዩአቸው። የውጭ አገራት ዜጎቹም በእሳቸው ድርጊት በጣም ተገርመው ከእሳቸውና ከአንበሳው ጋር እየሆኑ ፎቶ ተነሱ። ይህ ክስተትም በመጽሄት እየታተመ በውጭ አገራት ተሰራጭቷል። በዚህ መልክ ስለ ኢትዮጵያን ድራማዊ በሆነ መልኩ ማስታወቂያ ሰርተዋል። ይህ ማስታወቂያ ከተሰራ ከስድስት ዓመት በኋላ ነው እኔ ቱሪስት ድርጅት የተቀጠርኩት። ቱሪስት ድርጅት በተቋቋመ በስድስተኛ ዓመቱ ነው እኔ የተቀጠርኩት።
አዲስ ዘመን፡- በኪነ ጥበብ (በስዕል) ሥራዎች ኢትዮጵያን በተገቢው መልኩ አስተዋውቄያለሁ የሚል እምነት አልዎት?
ፕሮፌሰር አቻምየለህ፡- ምስክር የሚሆነኝ አፍሪካን ተመልክቶ ስለ ኪነ ጥበብ በተጻፉ መጽሐፎች ላይ ስለእኔም የተጻፈ ብዙ አለ። እኔም የኢትዮጵያን ኪነ ጥበብ (አርት)በሚመለከት በተለያዩ ጊዜያቶች የጻፍኳቸው መጽሐፎች አሉ። በጋዜጣና በመጽሄቶች ሙያዊ ጽሑፎችን ጸፊያለሁ። ለምሳሌ እኤእ በ1996 እንግሊዝ አገር ትልቅ የስዕል ኤግዚቢሽን ላይ የኢትዮጵያን አርት አስመልክቶ ከአንድ ሱዳናዊ ጋር ሆነን አንድ ጽሑፍ አውጥተናል። የኢትዮጵያ አርቲስቶችንም ለማስተዋወቅ ሞክሪያለሁ። እኤእ በ2007 23 ታዋቂ ኢትዮጵያውያን አርቲስቶች የተሳተፉበት የስዕል ኤግዚቢሽን አቅርቢያለሁ።
የኢትዮጵያን ዘመናዊ ኪነ ጥበብ (ኮንቴንፖራሪ አርት) አንድ መጽሐፍ ጽፊያለሁ። እነ ዓለም ፈለገሰላም፣አገኘሁ እንግዳ፣ ስክንድር በጎሲያን፣ገብረክርስቶስ ደስታ፣ፓዮኒል ያሉ እውቅ ሰዓሊያን ለዘመናዊ የኢትዮጵያ የስዕል ሥራዎች ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረጉትን ታሪካቸውንና የስዕላቸውን አይነት አጠር ባለ መልኩ የማስተዋወቅ ሥራ ሰርቻለሁ። ከሙያ አጋሮቼ ጋር በመሆንም በአሜሪካም አገር የስዕል ኤግዚቢሽን አሳይተናል። ኢትዮጵያውያን በረሀብ ብቻ ሳይሆን በኪነ ጥበብ ዕድገትም የጎላ ድርሻ እንዳለን ስዕሎችን አሳይተናል። ለምሳሌ የአቶ አገኘሁን ጉርድ ስዕልን በአንድ ሚሊዮን ዶላር ወጪ አድርገን ወደ አሜሪካ ወስደን ማሳየት ችለናል ። እኔ አርትና የሙዚየም ሙያ አጥንቻለሁ። ባለኝ ሙያና አቅም ኢትዮጵያን ለማስተዋወቅ ሞክሬያለሁ።
አዲስ ዘመን፡- በዓለምና በሙያዬ እንድታወቅ አድርጎኛል የሚሉት የስዕል ሥራዎች የትኛው ነው?
ፕሮፌሰር አቻምየለህ፡- ከሥራዎች መርጨ ይህኛው ይበልጥ አስተዋውቆኛል ማለት ይከብዳል። ምክንያቱም ሁሉም የስዕል ሥራዎቼ ሀሳቡ ከመጣና ንድፍ ደረጃ ከደረሱ በኋላ ጊዜ ወስደህ የሰራኋቸው ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ አንዱን ልምረጥ ብትል አስቸጋሪ ነው። በየጊዜውና በየወቅቱ አዳዲስ ሀሳቦች ይፈልቃሉና። ልክ በወቅቱ ሁኔታ ተመስጠህና ስሜትህ ገፋፍቶህ ከምጽፋቸው ግጥሞች ውስጥ አንዱን መርጠህ ይህኛው ይሻላል ማለት አስቸጋሪ ነው። አራት ልጆች ቢኖሩህ የትኛውን ይበልጥ ትወዳለህ እንደማለት ስለሆነ መምረጥ ከባድ ነው።
ሆኖም ከህዝብ ጋር ያስተዋወቁኝ ስዓሎች አሉኝ። ለምሳሌ ሶንግ ፎር አፍሪካ የሚባለው ስዕሌ በተለያዩ የውጭ አገራት ሙዚየሞች ይገኛል። የአድዋ አንበሳ (ዘላይን ኦፍ አድዋ) የሚል ስዕልም አለኝ ። ይህ ስዕል ዳግማዊ ሚኒልክንና አንበሳውን ጎን ለጎን አድርጊ የሳልኩት ስዕል ነው ። ይህን ስዓል ኢትዮጵያ ድረስ አምጥቼ ኤግዚቢሽን አሳይቻለሁ። ታዋቂ ስዓል ነው ‹‹በፖስተርም›› ደረጃም ከ500 በላይ ታትሞ ለብዙ ሰው እንዲደርስ ተደርጓል።
ለምሳሌ አሜሪካን ውስጥ ታማኝና እኔ ሆነን የአድዋ አንበሳ የሚለውን ስዕል ለጨረታ አውጥተን 10ሺ ዶላር ተሸጧል። በተለያዩ ቦታዎች ይህን ስዕል በጨረታ እየገዙ የወሰዱ ሰዎች አሉ። ሙዚየሞችም እንዲሁ። ዓለም አቀፍ ሙዚየም ውስጥም ይኸው ስዕሌ አለ። በኢትዮጵያ ዘመናዊ ኪነ ጥበብ ዕድገት ላይ የበኩሌን ድርሻ ለማበርከት ጥረት አድርጊያለሁ።
አዲስ ዘመን፡-በኢትዮጵያ ውስጥ ዘመናዊ ኪነ ጥበብ ዕድገት ከፍ እንዲልና ዓለም አቀፍ ተጽእኖ እንዲፈጥር ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
ፕሮፌሰር አቻምየለህ፡-በሥነ ጥበብ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤቶች እየሄዱ የስዕል ሥራቸውን ቢሰሩ በተማሪዎች ዘንድ መነሳሳትን ስለሚፈጥር እምቅ ችሎታ ያላቸውን ሰዎች ማውጣት ይቻላል። ቴአትርም፣ሙዚቃም እንዲሁ ቢሰራ ተማሪዎቹ ብቃታቸውን ያሳድጉበታል፣በተማሪዎች ገና ከልጅነታቸው መክሊታቸውን እንዲፈልጉ ይረዳቸዋል ። ስርዓት ተዘርግቶለትና የጊዜ ሰሌዳ ወጥቶለት ተግባራዊ ቢደረግ የተሻሉና ተጽእኖ ፈጣሪ ባለሙያዎችን ማፍራት ይቻላል የሚል እምነት አለኝ። መንግሥትም ለሙያው ትኩረት ሰጥቶ መስራት አለበት እላለሁ። ምክንያቱም የኪነ ጥበብ ሥራ አገርን ማስተዋወቅና የገቢ ምንጭ ማድረግ ይቻላል። ለልማትና ለዴሞክራሲ ዕድገትም ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል።
አዲስ ዘመን፡-በስዕል ሥራዎት ምን የተለየ ገጠመኝ ይኖርዎት ይሆን?
ፕሮፌሰር አቻምየለህ፡-የስዕል ሥራዎችን ለማሳየት እንግሊዝ አገር በተዘጋጀው የስዕል ኤግዚቢሽን ተሳትፌ ነበር። በዚህ ጊዜ በኤግዚቢሽኑ ውስጥ ተመስጬ ስዕል እየሳልኩ ስለነበር ኤግዚቢሽኑ ሲጠናቀቅ አንዱን ስዕሌን ረስቼው ሄዱኩ። ከአራት ዓመት በኋላ ኤግዜቢሽን ለመሳተፍ ወደ እንግሊዝ አገር ስመጣ ኤግዚቢሽኑ ድረስ በመምጣት የጠፋብኝን ስዕሌን አንድ ግለሰብ አምጥቶ ሰጠኝ። ይህ ብቻ ሳይሆን ቀደም ሲል ስያቸው በሽያጭም ሆነ በሌላ መልኩ በእኔ እጅ ያልነበሩ ሰባት የስዕል ሥራዎቼ ከተለያዩ ግለሰቦችና ተቋማት በጥቆማ ተገኝተው በኤግዚቢሽኑ ላይ ለዕይታ ቀርበው መገኘታቸው ለእኔ ትልቅና ያልጠበኩት ነገር ነው።
አዲስ ዘመን፡-በስዕል ስራዎችዎ ለአገር ባበረከቱት አስተዋጽኦ ሽልማት ተበርክቶሎዎት ይሆን?
ፕሮፌሰር አቻምየለህ፡- ልክ እንደ የአጼ ኃይለስላሴ ሽልማት ድርጅት በአሜሪካ ውስጥ አስተዋጽኦ ያደረጉ ኢትዮጵያውያንን በማፈላልግ በየዓመቱ ዕውቅና የሚሰጥ ድርጅት አለ። በ1990 ሽልማት ከተሰጣቸው ሰዎች አንዱ እኔ ነኝ። በአገር ደረጃ በኪነ ጥበብ ለአገር አስተዋጽኦ አድርገሀል በሚል ሽልማት ተበርክቶልኛል። የራስህ ወገን ዕውቅና ሲሰጥህ ትልቅ ነገር ነው።
አዲስ ዘመን ፡- በፖለቲካ ዙሪያ ላይ ያለዎት አመለካከት ምንድነው ?
ፕሮፌሰር አቻምየለህ ፡- ፖለቲካ የህብረተሰብን ወገናዊነት በጠበቀ መልኩ እስከ ተሰራበት ድረስ ጥሩ መድረክ ነው
የሚል ሃሳብ አለኝ። ሆኖም በእኛ አገር ህዝብ ለፖለቲካ ያለው አመለካከት እንዲበላሽ የተደረገበት ሁኔታ አለ። መጥፎ አድርጎ እንዲሳል ያደረገው ፖለቲካን ሲጫወት የነበረውና የሥርዓቱ ተዋናይ የሆነው አካል ነው። እነዚህ ሰዎች ህዝቡ ፖለቲካን እንዲጠላና በጥርጣሬ መልክ እንዲመለከት አድርገውታል። እንጂ በምንም መልኩ ፖለቲካና ፖለቲከኛ መኮንን የለበትም። ይህ በተቻለ መጠን ሊታረም የሚችለው የፖለቲካ ተዋንያኑ ለህዝብ የገቡትን ቃላቸው ሲያከብሩና ለህዝብ ወገናዊነታቸውን አሳይተው መስራት ሲችሉ ነው።
አዲስ ዘመን፡-እርስዎስ የፖለቲካ ተሳትፎዎት ምን ይመስላል?
ፕሮፌሰር አቻምየለህ፡ -እኔ በፖለቲካ ተሳትፎ አለኝ። በደረግ ጊዜ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በነበሩት ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ በመሰረቱት የመድህን ድርጅት አባል ነኝ። በዚህ የፖለቲካ ድርጅት ቢያንስ 500 የሚሆኑ ምሁራን ሰዎችን በአባልነት ያካተተ ነው። ድርጅቱ በደርግም ሆነ በኢህአዴግ የሚወደድ ድርጅት አይደለም።
አዲስ ዘመን፡-ድርጅቱ አሁን በህይወት አለ?እርስዎስ አሁንም አባል ነዎት?
ፕሮፌሰር አቻምየለህ፡-አዎ በህይወት አለ። እኔም አሁንም አባልና አመራር ነኝ።
አዲስ ዘመን፡-ወደ አገር ውስጥ መጥታችሁ በመጪው ምርጫ መወዳደር ሀሳብ የላችሁም?
ፕሮፌሰር አቻምየለህ፡-በአሁኑ ወቅት በምርጫ ለመወዳደር ሀሳቡ የለንም። በተቻለ መጠን በአገሪቱ 138 ፓርቲዎች አሉ ስለተባለ ምርጫው በተሳካ መልኩ እንዲካሄድ እንደግፋለን። በምርጫው ጥሩ ውጤት እንዲመጣ እንመኛለን።
አዲስ ዘመን፡-ውጭ አገር የነበሩ አብዛኛዎቹ ፓርቲዎች ወደ አገር ውስጥ በሰላማዊ መልኩ ለመታገል ወደ አገር ውስጥ ገብተዋል። እናንተስ በአገር ውስጥ ገብታችሁ ለመታገል እቅድ አላችሁ?
ፕሮፌሰር አቻምየለህ፡-ሀሳቡ አለን ። ወደ አገር ውስጥ ለመግባት እየሰራን ነው።
አዲስ ዘመን፡-የተወሰኑ ፓርቲዎች አመራሮች የውጭ አገር ዜግነት ስላላቸው ህገ መንግስቱ መምረጥ እንዳይችሉ ይገድባቸዋል። እናንተ በመጪው ምርጫ የማትሳተፉት በዚህ ምክንያት ነው ወይ?
ፕሮፌሰር አቻምየለህ፡-አይደለም። አስበንበት መምጣት ከፈለግን ዜግነቱን ጥለን መምጣት እንችላለን። እኔ አሜሪካን አገር ብኖርም ልቤ አገሬ ነው ያለው። እኔነቴን ያወኩበት ማንነቴን የተገነዘብኩበት አገሬ ስለሆነች ውጭ አገር ብዙ ዕድልና ምቹ ሁኔታ ባገኝም እስካሁን ድረስ ትልቅነቴም ሆነ ትንሽነቴ የሚገለጸው በኢትዮጵያዊነቴ ነው። ኢትዮጵያዊ ማንነት በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያለው፣ ትልቅ ውጤት ያመጣና ያስመዘገበ ስለሆነ ያንን ለመቀጠል ምንም ወደኋላ የምንልበት ምክንያት የለም።
አዲስ ዘመን፡-በአገሪቱ ለውጥ ዙሪያ ምን አስተያየት አለዎት ?
ፕሮፌሰር አቻምየለህ፡- ልክ እንደ ሌላው ኢትዮጵያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ በመጀመሪያዎቹ ወራት የስልጣን ዘመናቸው እንደገለጹት ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ እንዳሉት መሰረት የሚጓዙ ከሆነ የምንደግፈው ነው፣አብሮ ለመስራትም ኃላፊነትም ያለብን መሆኑን እንገነዘባለን። የጎሳ ፖለቲካ ግን የትም አያደርሰንም። ኢትዮጵያውያን ብዙ የአንድነት ገመዶች አሉን። የጎሳን ፖለቲካ ማቀንቀን ማለት ያ ለዘመናት አንድ አድርጎ የገመደን እሴት መካድ ይሆናል።
ምክንያቱም ኦሮሞም፣አማራም፣ጉራጌም ይሁን ባለው አካባቢ ያፈራው የአንድነት እሴት አለ። ያ እሴት ያደገው ለብቻው ሳይሆን ከሌሎች ጋር በነበረው የጋራ መተሳሰብና መስተጋብር፣ ነው። ይህ መስተጋብር የለም ማለት ነብር ላይ ዥጉርጉር ቀለማት የለበትም ብሎ እንደ መካድ ይቆጠራል። ይህን መሰረት አድርገን ከሰራን ብልጽግናንና ዴሞክራሲን እንጎናጸፋለን።
አዲስ ዘመን፡-የብሄር ፖለቲካን ይቃወማሉ ማለት ነው?
ፕሮፌሰር አቻምየለህ፡-አዎ በጣም እቃወማለሁ። የምወላውልበት ጉዳይ አይደለም። ኢትዮጵያዊ ነኝ። የኦሮሞ፣የአማራ፣የትግሬ ደም አለብኝ። እንደእኔ ከተለያዩ ብሄሮች የተቀለመ ሰው ኢትዮጵያዊነት በላይ የሚገልጸው ነገር አይኖርም።
አዲስ ዘመን፡- ውስን ጊዜዎትን መስዋዕት አድርገው ለቃለ መጠይቁ ስለተባበሩን አመሰግናለሁ።
ፕሮፌሰር አቻምየለህ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ነሐሴ 18 ቀን 2011
ጌትነት ምህረቴ