አዲስ አበባ፡- በ2012 ዓ.ም በገጠር ለሚፈጠረው የ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ እድል ስድስት ቢሊዮን ብር በጀት ይዞ አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቁን በግብርና ሚኒስቴር የገጠር ሥራ ዕድል ፈጠራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አስታወቁ። ገንዘቡ ህጋዊ መንገድን ተከትሎ እና አሰልቺ አሰራሮችን በማስቀረት በተዘዋዋሪ የብድር ፈንድ በኩል ተግባራዊ እንደሚደረግም ተገልጿል።
ዳይሬክተሩ አቶ ስለሺ በቀለ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፣ መንግሥት በዓመት ሦስት ሚሊዮን ዜጎችን ወደ ሥራ ለማስገባት ባቀደው መሰረት በ2012 ዓ.ም በገጠር ሥራ ዕድል ፈጠራ የግብርና ዘርፍ ሰፊ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር የሚያስችል ትልቅ አቅም አለው። ከግብርና ዘርፉ ውጭም ሌሎች ሴክተሮችንም በሥራ ዕድል ፈጠራ መርሐ ግብር አካቶ እያስተባበረ እንዳለ አስታውቀዋል።
መርሐ ግብሩን በሚመለከት ከክልሎች ጋር በዕቅዱ ላይ ተናቦ ለመስራት አንዲቻል ምን ዓይነት ግብዓቶች እንደሚያስፈልጉ ፣ ከአመራሮችና ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እንደተደረገበት ያስረዱት ዳይሬክተሩ፣ ለእያንዳንዱ ሥራ የጊዜ ሰሌዳ እንደተቀመጠም ጠቁመዋል። በፌዴራልና በክልል ደረጃ መሠራት ያለባቸው ሥራዎችም ተለይተው በየክልሉ የነበሩ መልካም ተሞክሮዎችን ማስፋት እንደሚያስፈልግና የጋራ ግንዛቤ መያዙን አስታውቀዋል።
ለሥራ እድል ፈጠራው ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች ውስጥ ግብርናው የአንበሳውን ድርሻ እንደሚይዝ ያመለከቱት ዳይሬክተሩ ከዚህም ውስጥ የእጽዋትና የእንስሳት ዘርፍ 60 በመቶ ሽፋን እንደተሰጣቸው ተናግረዋል።ከግብርናው በመቀጠል የማኑፈክቸሪንግ ፣ የማዕድን ፣የንግድ ፣ የኮንስትራክሽን ፣የአገልግሎት ዘርፎችም እንደየ አካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ በሥራ ዕድል ፈጠራው የተለዩ ዘርፎች መሆናቸው ታውቋል።
ከ2008 አስከ 2010 ዓ.ም የሥራ ዕድል ፈጠራው ምን ይመስላል? ዘርፉ ምን ዓይነት ችግሮች ነበሩበት? አፈጻጸሙስ ምን ይመስል ነበር? በሚል ተቋሙ ያስጠናውን ጥናት ዋቢ አድርገው እንዳመለከቱት፣ ከጥናቱ ለቀጣይ ሥራ የሚጠቅሙ አዎንታዊ ግብዓቶች ተወስደዋል። በዚህም መሰረት በግብርናው ዘርፍ የዶሮ እርባታ ፣ የወተት ልማት ፣ መስኖን የመሳሰሉት በከፍተኛ ደረጃ ሊሰራባቸው እንደሚገባ ተለይተዋል።
የቱሪዝም ዘርፍ መንግሥት ትኩረት የሰጠው የሥራ ዘርፍ እንደሆነ የገለጹት ዳይሬክተሩ በገጠሩ ነባራዊ ሁኔታም አንድ የሥራ መስክ ተደርጎ እንደተቀመጠና በአገልግሎት ዘርፍ ሥር እንደተካተተም አስታውሰዋል። ቱሪዝም በባህሪው የመሰረተ ልማት መሟላትን የሚጠይቅ ሲሆን የዘርፉ ጸጋዎችን ጥቅም ላይ ለማዋል እንደታቀደ እና ከክልል አመራሮችና ከባለ ድርሻ አካላት ጋር መግባባት ላይ ተደርሷል ብለዋል።
ዕቅዱን ለመተግበር እንደተግዳሮት የሚታዩ ጉዳዮችም የተለዩ ሲሆን የመፍትሄ አቅጣጫዎችም ተቀምጠውላቸዋል። እነዚህም የማስፈጸም አቅም ውስንነት ፣ የክህሎት ማነስ ፣ ከቀበሌ እስከ ከፍተኛው መዋቅር ድረስ ተናቦ ያለመሥራት ፣ በየደረጃው ያሉ አካላት መረጃዎችን በአግባቡ ያለመያዝ እና ሙሉ ጊዜን ሥራ ላይ ያለማዋል ችግሮች ተጠቃሽ ናቸው። ሥራው በአንድ አካል ብቻ የሚፈጸም ባለመሆኑ ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ተናቦና ተቀናጅቶ በመሥራት የተጠቀሱትን ችግሮች በማረም እቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በመምከር ዝግጅት መደረጉን አስረድተዋል።
አዲስ ዘመን ነሐሴ 16/2011
ኢያሱ መሰለ