አዲስ አበባ፡- መለስ ፋውንዴሽን ከመላው ሀገሪቱ የተውጣጡ በሒሳብና በፊዚክስ ትምህርቶች የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ 170 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የቴክኖሎጂ ሥልጠና ሰጠ።
በፋውንዴሽኑ የኢኮሎጂ ኃላፊ ወይዘሮ ሰምሀር ሲሳይ ፋውንዴሽኑ ለሁለተኛ ጊዜ ባዘጋጀው የስልጠና መድረክ ላይ ተገኝተው እንደገለጹት፣ የቴክኖሎጂ ሥልጠናው በኢኖቪሽንና ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰጥ ነው። ተማሪዎቹ ከልጅነታቸው ጀምሮ የቴክኖሎጂ ፍላጎቱ እንዲያድርባቸው ከማድረጉም በላይ ወደ ዩኒቨርሲቲዎች በሚገቡበት ወቅት ሳይንሱን መርጠው ወደ አዳዲስ ነገሮች ፈጠራ እንዲያዘነብሉ ይረዳቸዋል ብለዋል።
ወጣት ተማሪዎቹን ከቴክኖሎጂዎች ጋር የማስተዋወቁና ፍላጎቱን የማስረጽ ሥልጠናው እየተሰጠ የሚገኘው ዘንድሮ ለሁለተኛ ዙር ሲሆን እስከ አራተኛ ዙር በየክረምቱ የሚቀጥልም ሆኖ ለአንድ ወር ያህል ጊዜ የሚወስድ ነው ብለዋል።
ተማሪዎች ስለ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ከዚያም በተጨማሪ ሳይንስ፣ሒሳብ እና ኢንጂነሪንግ ዘርፎች ላይ ትኩረት እንዲሰጡ ታስቦ የሚሰጥ ሥልጠና መሆኑን የተናገሩት ወይዘሮ ሰምሀር፣ በሥልጠናው መጨረሻም ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታዎቻቸው አዳዲስ ሐሳቦች አፍልቀው በተግባር ወደ ውጤት የሚቀይሩበት እድልና አሰራር እንደሚመቻችላቸው ጠቁመዋል።
ከኦሮሚያ ልዩ ዞን ለገጣፎ የመጣው ተማሪ ምህረትአብ ሳምሶን እንደተናገረው፣ ሥልጠናው የኮምፒዩተር ሳይንስ ሲሆን በቀጣዮቹ ጊዜያት የቴክኖሎጂ ፍላጎት እንዲያድርብን የሚያደርግ ነው ብሏል። ዓለም የምትመራው በቴክኖሎጂ ስለሆነ በየትኛውም ዘርፍ የዚህ እውቀት ባለቤት ሆኖ መገኘት አስፈላጊና ተመራጭ ሊያደርግ እንደሚችል ጠቅሶ የተማሪዎችን የቴክኖሎጂ እይታም የሚያሳፋ እንደሆነ ተናግሯል።
የኮምፒዩተር ፕሮግራም ሥልጠናው ሀገሪቱን የሚረከቧት ወጣቶች የቴክኖሎጂ እውቀቱ ያላቸው እንዲሆኑ በር ይከፍታል የምትለው የመቐለዋ ተማሪ ሊዲያ ጸጋነህ በቀጣይ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቴን በሕክምናው ዘርፍ የመማር እቅድና ፍላጎት ቢኖረኝም የቴክኖሎጂ እውቀቴን ማጎልበቴ ለሀገሬ በሙያዬ አዲስ ነገር ማበርከት እንድችል ያደርገኛል ብላለች።
ከጎንደር የመጣችው ተማሪ ቃልኪዳን ኃይሉ በበኩሏ የኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ ሥልጠናው ለማንኛውም ሰው በዚህ ዘመን ያለው ፋይዳ አያጠያይቅም። ለተማሪዎች ሲሆን ደግሞ ጥቅሙ እጥፍ ድርብ ይሆናል፣ምክንያቱም ከዓለም ጋር በቅርበት በመተዋወቅ ለሀገራችን አዳዲስ ፈጠራዎች ማበርከትና ትውልዱን ለማስተማር ሰፊ እድል ባለቤቶች ነን ስትል ተናግራለች።
አዲስ ዘመን ነሐሴ 16/2011
ሙሐመድ ሁሴን