አዲስ አበባ፡- የመደመር ስድስት ምሰሶዎችን የሰነቀ “ጳጉሜን በመደመር” አገር አቀፍ መርሐ ግብር ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት አስታወቀ፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መግለጫ፣ ኢትዮጵያን በመደመር እሳቤ አንድነቷንና ብልጽግናዋን እውን ለማድረግ በጀመረችው አዲስ ምዕራፍ መሰረት “ጳጉሜን በመደመር” አገር አቀፍ መርሐ ግብር ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውቋል፡፡ በዚህም ከጳጉሜ 1 እስከ 6 ያሉት ቀናት የየራሳቸው ስያሜ የተሰጣቸው ሲሆን ጳጉሜ 1 ብልጽግና፣ ጳጉሜ 2 ሰላም፣ ጳጉሜ 3 አገራዊ ኩራት፣ ጳጉሜ 4 ዴሞክራሲ፣ ጳጉሜ 5 ፍትህና ጳጉሜ 6 የብሔራዊ አንድነት ቀን የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸዋል፡፡
የተለያዩ የመንግሥት አካላትም የየዕለት እንቅስቃሴዎቹን ለማቀድ፣ ለማስተባበር፣ ለመምራትና ለማስፈጸም ኃላፊነት መውሰዳቸውንና አካሄዱን በተመለከተም በተለያዩ መንገዶች ለህዝብ የሚያሳውቁ መሆናቸውን ጽህፈት ቤቱ ገልጿል። በዚህ መሰረት ጳጉሜ 1 የብልጽግና ቀንን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት፣ ጳጉሜ 2 የሰላም ቀንን የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል፣ ጳጉሜ 3 የአገራዊ ኩራት ቀንን የአዲስ አበባ ከንቲባ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ፣ ጳጉሜ 4 የዴሞክራሲ ቀንን የትራንስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ፣ ጳጉሜ 5 የፍትህ ቀንን የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቢ ህግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ፣ ጳጉሜ 6 የብሔራዊ አንድነት ቀንን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ለማስተባበር ኃላፊነት ወስደዋል።
ህብረተሰቡም በመርሐ ግብሮቹ ላይ በመሳተፍ አገራዊ ብልጽግናን፣ ሰላምን፣ አገራዊ ኩራትን፣ ዴሞክራሲን፣ ፍትህንና ብሔራዊ አንድነትን በማሳደግና በማበልጸግ ወደ መጭው አዲስ ዓመት ተስፋ ሰንቆ እንዲሰራ ጥሪ ቀርቧል።
አዲስ ዘመን ነሐሴ 16/2011
ይበል ካሳ