ሶለላዬ ሶለላዬ ሶለላው፣
አንተን አይደለም ወይ የማነሳሳው፣
ቀና ብለህ እየኝ የሰው ጡር አለው፤… በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች በተለይም ልጃገረዶችና ሴቶች በተዋበው አልባሳቸው በቡድን በቡድን ሆነው ጣዕመ ዜማ ያለው ባህላዊ ጨዋታ እያሰሙ በኢንተር ኮንትኔንታል ሆቴል የተገኙ ታዳሚዎችን ያዝናናሉ፤ ባህሉንም ያስተዋውቃሉ፡፡
የአማራ ሴቶች ማሕበር ያዘጋጀው ይህ መርሐ ግብር በየዓመቱ በወርሐ ነሐሴ በተለይም ከ16 እስከ 21 የሚከበረውን የአሸንድዬ ፣ ሻደይና ሶለላ ባህላዊ የልጃገረዶች ጨዋታ ምክንያት በማድረግ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ የተዘጋጀ ነው፡፡ ከነሐሴ 1 ቀን ጀምሮ በክፍለ ከተማና በወረዳ ደረጃ በተለያዩ ዝግጅቶች ሲከበር የቆየው ይህ በዓል በትናንትናው ዕለትም የበዓሉን ዋዜማ በማስመልከት በፓናል ውይይቶችና በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል፡፡ በበዓሉ ላይ የተለያዩ የፌዴራልና የክልል ባለስልጣናት ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪና የንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር እንዳወቅ አብጤ እንደገለጹት፣ የአማራ ህዝቦች ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፉ የቆዩ የበርካታ ታሪካዊ ፣ ሃይማኖታዊ፣ ትውፊታዊና ባህላዊ እሴቶች ባለቤት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ልጃገረዶች እንዲህ በህብረ ቀለማት ባሸበረቁ አልባሳቶችና ጌጣጌጦች ደምቀው የሚያከብሩት የአሸንድዬ፣ሻደይና ሶለል ጨዋታ
የአማራ ህዝብ ካሉት በርካታ መገለጫዎች መካከል አንዱ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ይህ በዓል በአዲስ አበባ በእንዲህ መልክ መከበር መጀመሩም በህዝቦች ትግል የመጣው ለውጥ ውጤት መሆኑ መታወስ እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡
አሸንዳ ከሚባል የሣር ዓይነት ስያሜውን ያገኘው ይህ በዓል ለልጃገረዶች የነጻነት ማብሰሪያ፣ የውበት መግለጫ ፣ የመተጫጫ፣ የመሪነትና የተመሪነት ጥበብ መቅሰሚያ፣ የአብሮነትና የደግነት እሴት መገለጫ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ ባህል በዋናነት የማንነት መገለጫ ቢሆንም አንድነትን ፣መተሳሰብን ፣
መተጋገዝንና ፍቅርን ያጎለብታልም ብለዋል።
የአማራ ሴቶች ማሕበር የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ሰብሳቢ ክብርት ወይዘሮ ጸዳለ መኮንን በበኩላቸው የአማራ ህዝብ ተዘርዝሮ የማያልቁ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት መሆኑን በመግለጽ እነዚህን ውብና ድንቅ ባሕሎች በተገቢው መንገድ በመንከባከብ፣ በማሳደግ፣ በመጠበቅና በማስተዋወቅ ከትውልድ ወደ ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ ተናግረዋል። የአማራ ሴቶች ማሕበር አዲስ አበባ ቅርንጫፍም በህዝቦች መካከል መቀራረብ ለመፍጠር፣ አብሮነትን ለማሳደግና ለኢትዮጵያ ህዝቦች ለማስተዋወቅ በማሰብ በዓሉ በመዲናዋ እንዲከበር መድረጉን ገልጸዋል። በዓሉን በእውቀት ላይ ተመስርቶ ለማሳደግም እንዲህ አይነት መሰል የፓናል ውይይቶች አስፈላጊ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በፓናል ውይይቱ ይህ ሃይማኖታዊና ባህላዊ መነሻ ያለው የልጃገረዶች ጨዋታ በተለያዩ የአማራ አካባቢዎች የተለያየ ስያሜ እንዳለውና ማህበራዊ ፋይዳውም የጎላ እንደሆነ ተነስቷል። በውይይቱ ከተሳታፊዎች ከተነሱ ጥያቄዎች ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች ለተመሳሳይ ተግባር የተሰጡ ሶስት ስያሜዎች በአንድ ስያሜ የሚጠቃለሉ? በበዓሉ ላይ ልጃገረዶቹን በተለያየ ድርጊት የሚያጅቡ ወጣቶችም በመኖራቸው በዓሉ እነሱንም እንዲያካትት ቢደረግ? የሚሉ ጥያቄዎች ተነስተው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።
በዓሉ ከዛሬ ጀምሮ ለስድስት ተከታታይ ቀናት በልጃገረዶች ጨዋታ ሲከበር ቆይቶ እሁድ ነሐሴ 19 ቀን ሚሊኒየም አዳራሽ በሚደረግ ደማቅ ዝግጅት ይጠናቀቃል።
አዲስ ዘመን ነሐሴ 16/2011
ኢያሱ መሰለ