ዲያቆን አይሸሹም
ተካ በደቡብ ሱዳን በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡ ደብብ ሱዳን በእርስ በርስ ጦርነት ስትታመስ፣ በርካታ ሰዎች
ሲሞቱና ሲፈናቀሉ ተመልክተዋል፡፡ ይህ ምልከታቸው ታዲያ በሀገራችን እያንዣበበ ያለው የሰላም መደፍረስና አለመረጋጋት ወደ መጥፎ
ሁኔታ እንዳይሄድና ያ በደቡብ ሱዳን የተመለከቱት ሰቆቃ በሀገራቸው እንዳይከሰት በመስጋት ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን መስዋዕት አድርገው
ስለሀገራቸው ሰላም፣ ይቅርታና አንድነት እንዲሰሩ አስገድዷቸዋል፡፡
ዲያቆን አይሸሹም ዜጎች ወደ መጪው ዘመን ለመሻገር ይቅርታን አንድነትንና ሰላምን በልባቸው ይዘው መሻገር እንዳለባቸው ይማጸናሉ፤ በእርቀሰላም መንገድ፡፡ እያንዳንዱ ዜጋ ሀገሪቱ ላይ የተጋረጠውን አደጋ በማጤን እራሱን የሰላም ልማትና ዕድገት ሊጠቀምበት እንደሚገባ ተማፅነዋል።
እንደ ዲያቆን አይሸሹም ሀሳብ ሰላም ከምንተነፍስው አየር እና ከምንመገበው ምግብ ተለይቶ አይታይም። ዲያቆን አይሸሹም እና አጋሮቻቸው መንግሥትም ሆነ የሚመለከታቸው አካላት ሀገርን የማስጠበቅ አደራቸውን እንዲወጡ ይጠይቃሉ። መንግሥት የህዝቡን ሰላም እና ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን በመወጣት ታማኝነቱንና ተቀባይነቱን እንዲያረጋግጥ፣ፖለቲካ ፓርቲዎችም ከየትኛውም አጀንዳ በፊት በሕይወት የመኖር ተፈጥሯዊ ዋስትና ዕውን እንዲሆን ህዝብን ማዕከል እንዲያደርጉ፣ የሃይማኖት አባቶችም በጾምና በጸሎት እንዲተጉ፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የዕድሜ ባለጸጎችም ልጆችን በመምከርና በመገሰጽ ክቡር ግዴታቸውን እንዲወጡ በተጨማሪም መምህራንና ተማሪዎች፣ የሚዲያ ተቋማትና አክቲቪስቶች የስፖርት ተቋማትና ደጋፊዎች እያንዳንዱ ዜጋ መጪውን አዲስ ዓመት በይቅርታ መንፈስ እንዲሻገር የሠላም ጥሪ አቅርበዋል።
ወይዘሮ ገነት አሰፋ የሐረር ከተማ ነዋሪ እና የሰላም አምባሳደር በመሆን እናቶችን ያስተባበሩና የመሩም ናቸው። ሌሎች ጓደኞቻቸውን በማነሳሳትና ከሚመለከተው አካል ድጋፍ በመጠየቅ ከአንድ ወር በላይ የቤተሰባቸውን ጉዳይ ወደጎን ብለው በዘጠኙም ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች በመዟዟር ተንበርክከው እያለቀሱ የሠላም ጥሪ አቅርበዋል።
ከአጋሮቻቸው ጋር በመሆን የኢትዮጵያ እናቶችን የልብ ትርታ አስደምጠዋል። አንጻራዊ ሰላም ማየታቸው ድካማቸው መና እንዳልቀረ በመግለጽም ዛሬም ቢሆን የሰላም አምባሳደር እናቶችን በመወከል የተለመደ ጥሪያቸውን ያሰማሉ፤ ወይዘሮ ገነት። አሁንም በተለያዩ አጋጣሚዎች በራሳቸው ተነሳሽነት ስለሀገራቸው ሰላምና ደህንነት ጥሪ እያቀረቡ ላሉ ቅን ልቦችም በጎ ምላሽ መስጠት እንደሚያስፈልግ ይመክራሉ።
በርከት ያሉ ወላጅ አልባ ህጻናትን በማሳደግ የበጎ አድራጎት ሥራ የሚሰሩት እኚህ እናት በሠላም መደፍረስ የመጀመሪያዎቹ ተጠቂዎች አቅመ ደካሞች ፣ እናቶችና ህጻናት በመሆናቸው የትኛውም አካል እነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች በማሰብ ለእርቀ ሰላሙ ጥሪ ተባባሪ መሆን ይገባዋል ይላሉ። ሁሉም ኢትዮጵያዊ መጪውን አዲስ ዓመት በፍቅር በይቅርታና በአንድነት እንዲሻገር የቀረበለትን የሰላም ጥሪ መቀበል እንዳለበት የእናትነት ምክራቸውን ሰጥተዋል። በእያንዳንዱ ሃይማኖት ውስጥ ሰላምና ፍቅር መሰበኩም ፈጣሪ የሚወደውና ለነፍስም ለስጋም የሚበጅ ቀና መንገድ መሆኑን መገንዘብ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
ሌላዋ የሰላም አምባሳደር እናት ደግሞ ከወደ ሀዋሳ የተገኙ ናቸው። ወይዘሮ አብነት አዳነ ከማንም በላይ የሰላም ተጠቃሚም ተጎጂም የሚሆኑት እናቶችና ህጻናት መሆናቸውን በመግለጽ የወይዘሮ ገነትን ሀሳብ ያጠናክራሉ። በሀገራችን ሰላም እንዲሰፍን ቀደም ሲል ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች መልዕክት ማስተላለፋቸው ሀገራዊ ግዴታቸው እንደነበር አስታውሰዋል። በሀገራችን እያየን ያለነው ጉዳይ አስከፊ በመሆኑ ከወዲሁ ሰዎች ቆም ብለው እንዲያስቡ ለማድረግ የሰላምን አዋጅ ይዘው እንደወጡም ይናገራሉ። አሁንም በቅን ልቦናና ሀገራዊ ኃላፊነት ተነሳስተው የሰላም፣ የይቅርታና የአንድነት መንፈስን ይዘን መጪውን ዓመት እንድንሻገር ድምጻቸውን ከሚያሰሙ ወገኖቻችን ጎን መቆም እንደሚገባ አስታውቀዋል።
የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ዋና ሰብሳቢ ካርዲናል ብርሐነ ኢየሱስ ሱራፌል እርቀ ሰላም ዛሬ በሀገራችን የተጀመረ አዲስ ጉዳይ አለመሆኑን በመግለጽ ኢትዮጵያ ፈጣሪውን የሚፈራ ህዝብ ያለባት፣ የእርቅና የሰላምን መንገድ የምታውቅ፣ ህዝቦቿም ለረጅም ዓመታት በአብሮነት ሲኖሩ ችግሮቻቸውን በዛፍ ጥላ ሥር ቁጭ ብለው በአባቶች ሽምግልና የመፍታት ባህልና ወግ ያላቸው መሆኑን ያስረዳሉ። ቂምና በቀል ፈጣሪ ከሚጠየፋቸው ጉዳዮች ዋነኞቹ መሆናቸውን የተናገሩት ካርዲናሉ የቂምና የጥላቻ አረሞች ከህዝቡ መሐል ተነቅለው በሀገራችን የፍቅርና የሰላም አየር እንዲነፍስ የቀረበውን የእርቀ ሰላም ጥሪ በመቀበል ሁሉም ድጋፍ እንዲያደርግ ተማጽነዋል።
ቂምና ጥላቻን ከትውልድ ወደ ትውልድ ማስተላለፍ የለብንም ያሉት ካርዲናሉ ህዝብ ስለሀገሩ ሰላምና ስለፈጣሪው ቃል ሲል ይህን እየተወራረሰ የመጣውን ቁርሾ በመተው ለቀረበለት ጥሪ የይቅርታ ልቡን እንዲሰጥ አባታዊ ምክራቸውን ለግሰዋል። ኢትዮጵያ በፈጣሪ እርዳታና በህዝቦቿ ቀና አስተሳሰብ ወደ ሚያኮራው አንድነቷ፣ ሰላሟና ፍቅሯ እንደምትመለስም ምልዑ ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።
አሁን በእርቅ ላይ የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን ቁጥራቸው እየተበራከተ መምጣቱን የተናገሩት ካርዲናል ብርሐነ ኢየሱስ በመንግሥት የተመዘገቡና በግል ተነሳሽነት የሚንቀሳቀሱ የሰላም መልዕክተኞች መበራከታቸው ለሀገሪቱ ሰላም ተስፋ ሰጪ እንደሆነ አስረድተዋል። ሁሉም በአንድ ላይ ቆመው በሀገራችን እርቀ ሰላም እንዲወርድና አዲሱን ዓመት በይቅርታ እንድንሻገር ትብብራቸውን ማሳደግ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
በተለይ በዚህ አስከፊ ሰዓት ሚዲያ ህዝብን የማቀራረብና በጎ በጎ ነገሮችን የማስተላለፍ ሚና እንደሚጠበቅበት የገለጹት ካርዲናሉ ሀገርን ከጥፋት ለመታደግ የሚደረገውን የእርቅና የሰላም ጥሪ ማገዝ እንደሚገባው ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ከድህነት ወጥታ በልማት በልጽጋ ህዝቦቿን በሰላምና በፍቅር አቅፋ መሄድ እንድትችል ሚዲያዎች ገንቢ አስተሳሰቦችን በማቅረብ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ እንደሚገባ ባቀረቡት አባታዊ ምክራቸው በማንሳት እኛም የእርቀ ሰላም የተመቸ ልብ ይኑረን መልዕክታችን ነው።
አዲስ ዘመን ነሐሴ 16/2011
ኢያሱ መሰለ