አዲስ አበባ ፦ የተወሰኑ የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከግሎቹ ባልተናነሰ ሁኔታ በህገ ወጥ የመማር ማስተማር ስራ ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አንዷለም አድማሴ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት አብዛኞቹ በተለይም ክልል ላይ የሚገኙት የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ባልተፈቀደላቸው የትምህርት መስክ ላይ ስልጠና እየሰጡ እንደሚገኙ ገልጸዋል::
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ አዲስ አበባ ከተማ ላይ በአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከክልል የመጡ ዩኒቨርሲቲዎች የማታ እናስተምራለን ብለው ተማሪዎችን በመመዝገብ ያስተምራሉ:: ይህ በኤጀንሲው እውቅና ያልተሰጠው አሰራር መሆኑን አብራርተዋል::
የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ በዚህ መልኩ በሚያስተምሩበት ጊዜ ቤተ መጻህፍትም ሆነ ቤተ ሙከራ አያሟሉም፣ መምህራኖቻቸውም በቅርብ አይገኙም፣ ይህ ሁኔታ ደግሞ የመማር ማስተማር ሂደቱን የሚጎዳ ከመሆኑም በላይ ኤጀንሲው በዚህ መልኩ ለሚያስተምሩ ተቋማት እውቅና አለመስጠቱን ጠቁመዋል::
በሌላ በኩልም ከግል ኮሌጆች ጋር በጥምረት እናስተምራለን ብለው የቀን ተማሪ መዝግበው ያስተምራሉ ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ፣በዚህ መልኩ አስተምረው የሚሰጡት ዲግሪ በኤጀንሲው ዘንድ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ተናግረዋል::
ለህብረተሰቡም አሰራሩ ህጋዊ እንዳልሆነ የተለያዩ መገናኛ ብዙሀንን በመጠቀም ተናግረናል፤እያንዳንዱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ፕሬዚዳንትም በዚህ ስራው ተጠያቂ ይሆናል ብለዋል::
አሁን ላይም በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሯ አማካይነት ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በዚህ መልክ ማስተማር እንደማይችሉ ደብዳቤ ተጽፎላቸዋል:: እስከ አሁን ያስተማሯቸውንና በማስተማር ላይ ያሉትን የተማሪዎች መረጃም በጽሁፍ በዝርዝር እንዲያቀርቡ ተጠይቀዋል:: ይህንን መሰረት አድርጎም መንግስት የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወስድ ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል::
አዲስ ዘመን ነሀሴ 15/2011
እፀገነት አክሊሉ