አዲስ አበባ፡- የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ‹‹ ጅማ ዩኒቨርሲቲና ኤቢኤች (ጥምረት ለተሻለ ጤና) ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል አማካሪ በአዲስ አበባ እየሰጡ ያለው ትምህርት ሕጋዊ አይደለም›› በማለት የወሰደውን እርምጃ ዩኒቨርሲቲውና አማካሪው ተቋም ‹‹ድርጊቱ ተፅዕኖ የሚያሳድር በመሆኑ ኤጀንሲው ማረሚያ እንዲያወጣና ስማችንን እንዲያድስልን እንፈልጋለን›› ሲሉ ጠይቀዋል ፡፡ ኤጀንሲው በበኩሉ ‹‹ሁለቱ ተቋማት አደብ መግዛት አለባቸው›› ብሏል፡፡
የዩኒቨርሲቲው የሕዝብ ግንኙነት አቶ መዘምር ሰይፉ፤ የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ በአዲስ አበባ ቅርንጫፍ የሚሰጠው ትምህርት ሕጋዊ ባለመሆኑ ተቀባይነት የለውም የሚል መግለጫ አውጥቷል፡፡ ለ2012 የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባ ማካሄዱም ሕገወጥ ነው:: በፌስ ቡክ ገፁም ዜጎችን የማሳሳት ሥራ እየተሠራ ነው ብሏል፡፡ ለሕዝብ እንዲደርስ የተደረገው ይህ መረጃ በዩኒቨርሲቲው ስም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖን የሚያሳድር ስለሆነም ኤጀንሲው ማረሚያ በማውጣት ያጠፋውን የተቋሙን ስም መመለስ እንደሚገባው ጠይቀዋል፡፡
የኤቢኤች (ጥምረት ለተሻለ ጤና) ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል አማካሪ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ማርቆስ ፈለቀ፤ ኤጀንሲው ዩኒቨርሲቲው ከጅማ ከተማ ወጥቶ መስራትም ሆነ ከሌሎች አካላት ጋር በትብብር መሥራት እንደማይችልና የትምህርት መርሐ ግብሩን እንደማያውቀው መግለፁ ስህተት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲውን ለማቋቋም በወጣው አዋጅ ዩኒቨርሲቲው ዋናው ግቢ ከሚገኝበት ጅማ ከተማ ውጪ በሌሎች ቦታዎች የትምህርት ክፍሎች፣ የምርምርና የማሕበረሰብ አገልግሎት ማዕከሎችን ሊያቋቁም እንደሚችል ያስቀምጣል፡፡ በዚህም በሕግ ያልተከለከለን ሥልጣን ኤጀንሲው መከልከሉ ተገቢነት እንደሌለው ነው የገለጹት፡፡ አያይዘውም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አዋጅ መሠረት ዩኒቨርሲቲዎች ተልዕኳቸውን ለማሟላት ከማንኛውም ድጋፍ ሊሰጣቸው ከሚችል ተቋም ጋር መሥራት እንደሚችሉ እንደሚደነግግና ኤጀንሲው ግን አዋጁን በሚፃረር መልኩ በደብዳቤ ማገዱ የሕግ አግባብነት እንደሌለው ዶክተር ማርቆስ ተናግረዋል፡፡
ዶክተር ማርቆስ፤ እ.አ.አ. 2013 በተደረገ የመግባቢያ ስምምነት ኃላፊነቶቹ ተዘርዝረው ዩኒቨርሲቲው የትምህርት ሥራውን አማካሪ ተቋሙ ደግሞ አስተዳደራዊ ድጋፍ ሊሰጥ ተስማምተው ስራቸውን በጋራ መጀመራቸውን አስታውሰው፤ ለትምህርቱ የሚያስፈልገውን ሙሉ ግብዓትም መንግስት ምንም ዓይነት ወጪ ሳያወጣ አማካሪ ተቋሙ እንዲያቀርብ በመስማማት ስራውን በጋራ መጀመራቸውን አስረድተዋል፡፡
ከመርሐ ግብሩ ከሚገኘው ገቢ የትርፍ ድርሻ ስምምነት መሠረት ሥራ ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ ይህንንም የማሳወቅ ግዴታ ባይኖርባቸውም ለትምህርት ሚኒስቴር አሳውቀዋል፡፡ በወቅቱ የነበሩት የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ በቦታው ተገኝተው መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብተው እንዳስጀመሩትም ዶክተር ማርቆስ አስታውሰዋል፡፡
ይህንኑ ስምምነት ለኤጀንሲውም በጽሁፍ ቢያሳቁም በአሁኑ ወቅት ግን ምንም እንደማያውቅ አድርጎ ማቅረቡ ትክክል አለመሆኑን ዶክተር ማርቆስ ገልፀው፤ ከስድስት ወር በፊት የሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሁለት ሚኒስትር ዴኤታዎች በቦታው በመገኘት በጉብኝታቸው ተደስተውና ሌሎች ተቋማትም ተሞክሮ መውሰድ እንዳለባቸው ተገልፆላቸው እንደነበር ነው ዋና ሥራ አስኪያጁ የገለጹት፤ ለዚህም የጥራታቸው ማረጋገጫ የሚሆኑ የተለያዩ የሰነድ ማስረጃዎች እንዳሏቸውም አስረድተዋል፡፡
የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተሰጧቸውን ሦስት ተልዕኮዎች እንዲወጡና በተለይ በአሁኑ ወቅት ለሚተገበረው አዲስ የፍኖተ ካርታ ከውጤት ለማድረስ የግሉ ዘርፍ ሚናው የላቀ መሆኑን በመግለጽ፤ ይህን መሠረት በማድረግ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ከኤቢኤች ኃላፊነቱ ከተወሰነ የግል ማህበር አማካሪ ድርጅት ጋር ስምምነት ተፈራርሞ ላለፉት ሰባት ዓመታት በአዲስ አበባ ከተማ በስምንት የድህረ ምረቃ መርሐ ግብሮችና በሕክምና የዶክትሬት ዲግሪ አገልግሎቶችን በመስጠት ሕብረተሰቡን መጥቀሙ ያለውን ፋይዳም ሚኒስቴሩ መግለጹን ጠቅሰው፤ ይህን ብሎ የመሰከረ አካል መቃወሙ እንዳስገረማቸው ተናግረዋል፡፡
ዶክተር ማርቆስ፤ አማካሪ ተቋሙ ሥራው የማማከር እንጂ የትምህርት ተቋም አለመሆኑን ጠቅሰው፤ ኤጀንሲው 2006 ዓ.ም በደብዳቤ እንዳሳወቀ ቢገልጽም እስከዛሬ ስህተት ፈፅመው ከነበረ ይህንን ያህል ዓመት እርምጃ አለመውሰዱ ተገቢ እንዳልነበር ተናግረዋል፡፡
ኤጀንሲው በፌስቡክ ገጹ የለቀቀው መረጃ ሕብረተሰቡን ያደናገረ በመሆኑ ለፈፀመው ጥፋት ሕዝብን፣ መንግስትን፣ ተማሪዎችንና ሁሉንም በማያሻማ ቋንቋ ይቅርታ መጠየቅ እንዳለበት ፣ ይህን ድርጊት የፈፀሙ አካላት አስተዳደራዊ ቅጣት እንዲጣልባቸው በመጠየቅ፤ በድርጅቱና በዩኒቨርሲቲው ሥም ላይ ለደረሰው በደል ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ በሕግ መብታቸውን እንደሚያስከብሩ አስታውቀዋል፡፡
ተቋሙ ግን ከዩኒቨርሲቲው ጋር ያለውን ሥራ እንደሚቀጥልና ለቀጣይ የትምህርት ዘመንም አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገና በዚህ መልኩ ተማሪዎችም ሆኑ የተማሪ ወላጆች ስጋት እንዳይገባቸውና መርሀ ግብሩም እንደማይቆም ዶክተር ማርቆስ አረጋግጠዋል፡፡
የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቁጥር 650/2001 በአንቀጽ 93 ንዑስ አንቀጽ አንድ ላይ አገልግሎት በሌሎች ወገኖች እንዲሰጥ ስለማድረግ ይደነግጋል፡፡ በዚህም ማንኛውም የመንግስት ተቋም ተገቢና ተግባራዊ ሊደረግ የሚችል ሆኖ ሲያገኘው የድጋፍ ሰጪ አገልግሎቶችን በሌሎች አገልግሎት አቅራቢዎች እንዲሰጥ ሊያደርግ እንደሚችል አስቀምጧል፡፡ በተመሳሳይ የጅማ ዩኒቨርሲቲ እንደገና ማቋቋሚያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 240/2003 በአንቀጽ ሦስት መሠረት የዩኒቨርሲቲው ዋናው ግቢ ጅማ ከተማ ሆኖ በሌሎች ቦታዎች የትምህርት ክፍሎችና የምርምርና የሕብረተሰብ አገልግሎት ማዕከሎችን ሊያቋቁም እንደሚችል አስቀምጧል፡፡
የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ታምራት ሞታ በበኩላቸው፤ የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር የትብብር ሥልጠና እንደሚሰጡና ይህ ደግሞ የተከለከለ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በ2006 ዓ.ም በዚህ መልኩ ሥልጠና እንዳይሰጥ በሚል ደብዳቤ ተበትኖ ሕጉን ያከበሩት ወዲያው ከችግራቸው ሲወጡ ሌሎቹ ግን በችግራቸው መቀጠላቸውን፣ ከእነዚህ ተቋማት አንዱ የጅማ ዩኒቨርሲቲ እንደሆነም የተናገሩት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ በኤጀንሲው ፍቃድ አግኝተው የሚሠሩ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ ደብዳቤ በመጻፍ እርምጃ መውሰዱን አስረድተዋል፡፡
‹‹ሚኒስቴሩ ዩኒቨርሲቲዎች የትብብር ሥልጠና መስጠታቸው ትክክል ባለመሆኑ እንዲያቆሙ ደብዳቤ ጽፏል፡፡ ማቆም ብቻ ሳይሆን በትምህርት ላይ የሚገኙና ከዚህ ቀደም ከተቋማቱ የተመረቁ ተማሪዎችንም ዝርዝር እንዲልኩ ጠይቋል፡፡ ሆኖም ግን አሁንም ከድርጊቱ ሳይወጡ አንዳንድ ተቋማት ማስታወቂያ እያስነገሩ ለ2012 ምዝገባ እያካሄዱ ይገኛሉ፡፡ ይህን ተከትሎም ኤጀንሲው የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ነው›› ብለዋል፡፡
እንደ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ከኤቢኤች አማካሪ ድርጅት ጋር እየሠራ ሲሆን፤ ዩኒቨርሲቲው ካምፓስ መክፈት አይችልም፡፡ ካምፓስ የሚከፈተው በራሱ በዩኒቨርሲቲው ታምኖበት በቦርድ ፀድቆ ጥያቄው ለሚኒስቴሩ ቀርቦ ሲፈቀድ ብቻ ነው፡፡ ለዚህም የተቀመጠ ግልጽ አሠራር አለ፡፡ ካምፓስ ማለት ሕንፃ መገንባት፣ የሠው ኃይል ቀጥሮ መሥራትን የሚጠይቅ በመሆኑ በጀት ያስፈልገዋል፡፡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ተፈቅዶ የሚከናወን በመሆኑ ካምፓስ ሊከፍት አይችልም፤ ፈቃድም አላገኘም፡፡
ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ‹‹ዩኒቨርሲቲው የሕክምና ተማሪዎችን በአዲስ አበባ ላይ እየተቀበለ ያለው በየዓመቱ መንግስት የሚያወጣውን የመግቢያ መስፈርት ወደጎን በማለት ከተፈቀደው መግቢያ ነጥብ በታች ያላቸውን ተማሪዎች ነው፡፡ የመንግስትን መስፈርት ለማምለጫነትም ኤቢኤች የተባለውን ተቋም እንደ መሸሸጊያ ይጠቀማል፡፡አማካሪ ተቋሙ የማማከር ሥራ እንጂ የከፍተኛ ትምህርት መስጠት አይችልም፡፡በመሆኑም በአሁኑ ወቅት እያደረጉ ካሉት እንቅስቃሴ መታቀብ አለባቸው ›› ብለዋል፡፡
በተጨባጭ መረጃ እርምጃ የተወሰደባቸው ሦስት የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፤እንዲሁም ጅማ ዩኒቨርሲቲ፣ ደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ፣ ባህርዳርና ሐረማያ ዩኒቨርሲቲዎች ናቸው፡፡ ተጠያቂነቱም ቀጣይነት ያለው ሲሆን፤ ሕብረተሰቡም ዕውቅና ኖሮት ሀብት ንብረቱን እንዳያባክን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በተቋማቱ ከዚህ ቀደም ተምረው የትምህርት ቆይታቸውን አጠናቀው የተመረቁና በአሁኑ ወቅት ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የሚገኙ ተማሪዎች ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ገና አልተወሰነም፡፡ ሥም ዝርዝራቸውን እንዲልኩ ግን ተቋማቱ ተጠይቀዋል፡፡ ይህም ውይይት ተደርጎበት ውሳኔ ይተላለፋል፡፡ ይህን ተከትሎ የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መረጃውን እየሠጡ ባለመሆናቸው በሚኒስቴሩ በኩል ጫና እየተደረገ መሆኑን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል ፡፡
አቶ ታምራት የመንግስት ተቋማት በመሆናቸው መንግስት ፈቅዶ በጀት መድቦ ነው ሊያሰራ የሚችለው:: ዩኒቨርሲቲው የሚሰጠው መርሐ ግብር አስፈላጊነትና አዋጪነት ተጠንቶ በሚኒስቴሩ ፈቃድ ሊያገኝ ይገባል፡፡ በወቅቱ በሚኒስትር ዴኤታ የመንግስትን ፖሊሲ ቃኝቶና ፍላጎትን ተመልክቶ መደረግ ያለበትንና የሌለበትን ሊወስን ይችላል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከሚኒስቴሩ በላይ ሊሆን አይችልም፡፡ ደብዳቤውም ከአዋጁ ጋር የሚቃረን አይደለም ብለው አስተባብለዋል፡፡
አቶ ታምራት፤ በትብብር መሥራት አይቻልም አልተባለም፤ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ከአማካሪ ድርጅቱ ጋር በሚሠራው ሥራ ከአንድ ተማሪ በአንድ መንፈቀ ዓመት(አንድ ተርም) ከአንድ ተማሪ 75 ሺህ ብር ይቀበላል፡፡ ይህም በዓመት 225 ሺህ ብር ሲሆን፤ ለአብነት ከአንድ የህክምና ተማሪ የሰባት ዓመት ቆይታ አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊየን ብር ይሰበስባል፡፡ ከዚህ ውስጥ 48 በመቶውን ጅማ ዩኒቨርሲቲ የሚወስድ ሲሆን፤ 52 በመቶ የሚሆነውን ኤቢኤች ይወስዳል፡፡ ምን ስለሠራ ይህን ሁሉ ገንዘብ፣ ለምንስ ይቀበላል? የትስ ነው የሚገባው? የሚለው አጠያያቂ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
እንደ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ወላጆች ቤታቸውን ሸጠው ልጆቻቸውን ያስተምራሉ፡፡ ለመንግስት ግን የዩኒቨርሲቲው ገቢ ተብሎ የሚታወቅ ባለመሆኑ መጣራት ያለበት በርካታ ጉዳይ አለ፡፡ በዚህም ያሉትን የሕግ ክፍተቶችን በመጠቀም ተጠቃሚ ለመሆን የሚጥር አካል እንዳለም አመላካች ነው፡፡ የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ በተወካዮች ምክር ቤት የተቀየረ በመሆኑ አዲሱ ሲመጣ የአፈፃፀም መመሪያዎችን የማውጣትና መሰል ችግሮች እንዳይፈጠሩ፣ የትኛው መርሐ ግብር በትብብር ይሰጥ ማን ከማን ጋር በትብብር ይሥራ የሚለው ተጠንቶ በውይይት የሚመለስ ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን ነሀሴ 15/2011
ፍዮሪ ተወልደ