አዲስ አበባ፡- የስኳር ኮርፖሬሽን ከ13 እስከ 14 ወራት ለምርት የሚደርሱ፣ በሽታና ተባዮችን መቋቋምም የሚችሉ አራት አገር በቀል የሸንኮራ አገዳ ዝርያዎችን በምርምር ማግኘቱን አስታወቀ።
በኮርፖሬሽኑ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጋሻው አይችሉህም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፣ የሸንኮራ አገዳ ዝርያዎቹ በኮርፖሬሽኑ የምርምርና ልማት ዋና ማዕከል ተመራማሪ በሆኑት በዶክተር ኢሳያስ ጠና የተገኙ ሲሆን፣ ከ13 እስከ 14 ወራት ለምርት የሚደርሱ፣ በሽታዎችና ተባዮችን እንዲሁም አካባቢ ተኮር የሆኑ የጨዋማነት፣ የድርቅና የውሃ ተፋሰስ ችግር ያለባቸውን ቦታዎች መቋቋምም የሚችሉ ናቸው።
አቶ ጋሻው ‹‹በምርምር የተገኙት ዝርያዎች ለተለያዩ ሸንኮራ አገዳ አብቃይ ስነ ምህዳሮች ተስማሚ ናቸው። ከፍተኛ የአገዳ ምርት የሚሰጡና የበለጠ የስኳር ይዘት ያላቸው ሲሆኑ፤ ምርት ለመስጠት ከ18 እስከ 22 ወራት ከሚወስድባቸው ከነባሮቹ የሸንኮራ አገዳ ዝርያዎች ከ20 እስከ 30 በመቶ የበለጠ የስኳር ምርት መስጠት ይችላሉ›› ብለዋል።
በምርምር የተገኙት አራት አገር በቀል የሸንኮራ አገዳ ዝርያዎች በስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወዮ ሮባና በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የሰላም ሚኒስትር አማካሪና የስኳር ኮርፖሬሽን የሥራ አመራር ቦርድ አባል አቶ ካይዳኪ ገዛኸኝ ግንቦት 30 ቀን 2011 ዓ.ም መመረቃቸውንም የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚው ተናግረዋል።
ዝርያዎቹ በአገሪቱ የስኳር ኢንዱስትሪ ታሪክ የመጀመሪያ ሲሆኑ፤ በብሔራዊ የዝርያ አጽዳቂ ኮሚቴ ግንቦት 23 ቀን 2011 ዓ.ም እውቅና አግኝተው መመዝገባቸውንም አቶ ጋሻው ጠቁመዋል ።
አዲስ ዘመን ነሀሴ 15/2011
አጎናፍር ገዛኽኝ