አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት፤ በ2011 በጀት ዓመት 18ነጥብ751 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን አስታወቀ።
የድርጅቱ የኮርፖሬት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ዳይሬክተር አቶ አሸብር ኖታ፤ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት ድርጅቱ በበጀት ዓመቱ የኦፕሬሽንና አስተዳደራዊ ወጪዎቹን ሸፍኖ ከታክስ በፊት አንድ ነጥብ 713 ቢሊዮን ብር ትርፍ አገኝቷል።
እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ድርጅቱ ገቢውን የሰበሰበው ከመርከብ አገልግሎት፣ ከወደብና ተርሚናል አገልግሎት፣ ከባቦጋያ ማሪታይምና ሎጂስቲክ አካዳሚ እንዲሁም ከኮርፖሬት አገልግሎቶች ነው።
ዳይሬክተሩ ድርጅቱ በመርከብ አገልግሎት 4ሚሊዮን 338ሺ 437 ቶን የገቢ ጭነት ማመላለሱን፣ በጭነት የማስተላለፍ አገልግሎትም 181ሺ49 ኮንቴይነሮችና 4ሺ377 ተሽከርካሪዎችን በመልቲ ሞዳል ስርዓት ወደ አገር ውስጥ ወደቦችና የጉምሩክ ፍቃድ ያላቸው መጋዘኖች ማድረሱን ገልፀዋል።
ድርጅቱ የወደብ ተርሚናል አገልግሎትና የዝግ መጋዘን አገልግሎትም መስጠቱን፣ 2ነጥብ615 ሚሊዮን ቶን የገቢ ጭነት እና 279ሺ836 የወጭ ጭነት በዩኒሞዳል የትራንስፖርት ስርዓት ማስተላለፍ መቻሉን፣ ከባቦጋያ ማሪታይምና ሎጂስቲክ አካዳሚ የውጭና የድርጅቱን 721 ሰልጣኞችን ተቀብሎ በማሰልጠን የባህረኞችን ክህሎት ማዳበሩን፣ ለውጭ ሰልጣኞች ለሰጠው አገልግሎትም የ3ነጥብ429 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
የአገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት ከመደገፍና አትራፊነቱን ጠብቆ ከማስቀጠል በተጨማሪ የውጪ ንግዱን ለመደገፍ የተለያዩ ማበረታቻዎችን ማድረጉን ያነሱት ዳይሬክተሩ፤ በማኑፋክቸሪንግ እና በወጪ ንግድ ስራ ለተሰማሩና ለተፈቀደላቸው ባለሃብቶች ማበረታቻዎችን ማድረጉን፣ባለሃብቶቹ ለምርት ግብዓት ለሚያስገቧቸው ጥሬ ዕቃዎች፣ የግንባታ መሳሪያዎች፣ ማሽነሪዎችና ወደ ውጪ ለሚልኳቸው ምርቶች በየብስ 25 በመቶ፣ እንዲሁም በባህር ትራንስፖርት የአምስት በመቶ የዋጋ ቅናሽ እንደተደረገላቸው አስረድተዋል። በየብስና በባህር ትራንስፖርት አገልግሎቶቹ በተደረገላቸው ቅናሽም ድርጅቶቹ 39 ነጥብ 029 ሚሊዮን ብር መደጎማቸውን ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ነሀሴ 15/2011
አጎናፍር ገዛኽኝ