አዲስ አበባ፡- በአዲስ ዘመን ጋዜጣ በፍረዱኝ ዓምድ ሐምሌ 10 ቀን 2011 ዓ.ም ‹‹ማህደሩን ማን ወሰደው?›› በሚል ርዕስ በተስተናገደው ፅሁፍ መነሻነት የቤት ቁጥር 280 እናት ማህደር መገኘቱን የየካ ክፍለ ከተማ የወረዳ አምስት አስተዳደር አስታወቀ፡፡
የወረዳው ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ኣብርሃም ኪዳነማርያም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በአጎታቸው ሥም ተመዝግቦ የቤተሠብ አባላት ይኖሩበት የነበረው ቤት ሥም ዝውውር ወደ ቀድሞ አጎታቸው ሚስት በመዛወሩ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ለችግር ተጋልጠው ነበር፡፡በመሐል አዲስ አበባ ከተማ መገናኛ እየኖሩ የማዕድ ቤት፣ መፀዳጃ ቤት፣ ብሎም ውሃና መብራት አገልግሎት ተነፍጓቸዋል፡፡ አስተዳደሩም ቅሬታቸው አግባብ መሆኑን ቢያምንም መፍትሔ እንዳይሰጥ ግን ቤቱን የተመለከተው እናት ማህደር በመጥፋቱ ምላሽ እንዳይሰጥ አድርጎት ቆይቷል፡፡
ዋና ሥራ አስፈፃሚው ‹‹ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ለበርካታ ዓመታት ከኖሩበት ቤት ሲፈናቀሉ ማየት አሳዛኝ በመሆኑ በወረዳው የነበረውን የማህደር አቀማመጥ ክፍተት ለማረም ባከናወነው ቁርጠኛ ተግባር ሰነዶችን ዳግም በማደራጀት ማህደሩ ሊገኝ ችሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት የጠፋው ማህደር የተገኘ ቢሆንም በ1996 ዓ.ም እንዴትና ምክንያቱ ምን እንደሆነ ባልታወቀ ሁኔታ የተደረገው ሥም ዝውውር ጥያቄ ግን ምላሽ አላገኘም:: በተገኘው ሰነድም እነ ዳንኤል ደምሴ በአጎታቸው አቶ ገብሩ ንስራነ ሥም ከተመዘገቡ ነዋሪዎች መካከል እንደነበሩ ማረጋገጥ ተችሏል›› ብለዋል፡፡
እንደ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ማብራሪያ፤ የቀበሌ ቤቱን ይኖርበት የነበረው ግለሰብ ሕይወት ሳያልፍ ሥም ማዞር የማይቻል እንደሆነ ቢታወቅም በተገኘው እናት ማህደር ውስጥ ባሉት 246 የሰነድ ማስረጃዎች ውስጥ ግን አቶ ገብሩ በሕይወት እያሉ ወደ ቀድሞ ባለቤታቸው ቤቱ እንዴት ሊተላለፍ እንደቻለ የሚያሳይ ምንም ማስረጃ አልተገኘም፡፡ ግለሠቡም በሕይወት ስላሉ ከቤቱ እንዴት እንደወጡ ሲጠየቁ ተገደው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ሥም ዝውውሩ እንዴት እንደተከናወነ ማስረጃ ቢገኝ ድርጊቱ ሕገወጥ መሆኑ ተረጋግጦ አስተዳደሩም እርምጃ መውሰድ ያስችለው ነበር፡፡ ሆኖም ግን በአሁኑ ወቅት ጉዳዩ በሕግ በመያዙ የተገኘውን ማህደር አስተዳደሩ ለፍርድ ቤት አስረክቧል:: በዚህም በተቻለ መጠን ፍርድ እንዳይዛባና ፍትሕ መጓደል እንዳያጋጥም ወረዳው የተቻለውን እያረገ ይገኛል፡፡
አዲስ ዘመን ነሀሴ 15/2011
ፍዮሪ ተወልደ