አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ በአገር አቀፍ ደረጃ በስፋት እየተሰራ ያለውን የአረንጓዴ አሻራ ስራን እንደሚያደንቁ የመለስ ዜናዊ ፋውንዴሽን የቦርድ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ አዜብ መስፍን ገለጹ፡፡
የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ሰባተኛ የሙት ዓመት መታሰቢያ በጉለሌ መለስ ዜናዊ መታሰቢያ ፓርክ ትናንት ሲከበር ወይዘሮ አዜብ እንዳሉት፤ አሁን በሀገሪቱ በስፋት እየተሰራ ያለውን የአረንጓዴ አሻራ ስራ የሚደነቅ ነው፡፡ አቶ መለስ በህይወት በነበሩበት ወቅት ለአረንጓዴ ልማት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውንና በርካታ ስራዎች መስራታቸውንም ተናግረዋል፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃም ዕቅድ ተይዞበት መሰራቱንና በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችም መተከላቸውን አስታውሰዋል፡፡
ባለፉት ሰባት አመታት መለስ ፋውንዴሽን በርካታ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል ያሉት ወይዘሮ አዜብ፤ ከወዳጅ ሀገራት፣ ከሀገር ውስጥና ከተለያዩ ክልሎች በተውጣጣ ገንዘብ በአቶ መለስ ስም የህዝብ መናፈሻ ፓርክ እየተሰራ እንዳለ ጠቁመዋል፡፡ ተጠናቅቆ ወደ ስራ ሲገባም ለሀገርና ለወገን እንደሚጠቅም አስረድተዋል፡፡
በፓርኩ እየተሰሩ ያሉ የተለያዩ የግንባታ ዲዛይኖች ከባድና ያልተለመዱ በመሆናቸው በጣም ረዥም ጊዜን እንደፈጁም ወይዘሮ አዜብ ተናግረዋል፡፡ ግብአቶቹም ከሁሉም ክልሎች የመጡ መሆናቸውንም ገልፀዋል፡፡
እንደ ወይዘሮ አዜብ ገለፃ፤ በፓርኩ ውስጥ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች የአቶ መለስ ስራዎች ማንፀባረቂያ ሊሆኑ የሚችሉ ናቸው፡፡አሁን የፓርኩ ማጠቃለያ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመው፤ በ2012 ዓ.ም አጋማሽ ለህዝብ ክፍት እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
ባለፉት ሰባት አመታት አቶ መለስ በህይወት እያሉ ያጠኗቸው፣ የፃፏቸው ፅሁፎች፣ በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ መድረኮች ላይ ያደረጓቸው ንግግሮች እና ማስታወሻዎችን በማሰባሰብና ለመጪው ትውልድ በሚጠቅም መልኩ ዲጂታላይዝድ በማድረግ ወደ መለስ ፋውንዴሽን የማስገባት ስራም መሰራቱን ወይዘሮ አዜብ ተናግረዋል፡፡
በመታሰቢያ መርሃ ግብሩ በፓርኩ ውስጥ እየተሰሩ ያሉ የግንባታ ስራዎች የተጎበኙ ሲሆን፤ ከመላው ሀገሪቱ የተውጣጡ በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ በፋውንዴሽኑ ድጋፍ ለአንድ ወር የክረምት ወቅት ስልጠና ሊወስዱ የመጡ ተማሪዎች እና የአቶ መለስ የቀድሞ የስራ ባልደረቦች የተሳተፉበት የችግኝ ተከላ መርሀ ግብርም በፓርኩ ቅጥር ግቢ ተካሂዷል፡፡
አዲስ ዘመን ነሀሴ 15/2011
ሐይማኖት ከበደ