አሶሳ፡- የኦሮሚያና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ትብብር በጸጥታና ልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እያገዛቸው መሆኑን የክልሎቹ የጋራ የሰላምና የልማት ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
ላለፉት ሁለት ቀናት በአሶሳ ሲካሄድ በሰነበተው የምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መድረክ የኦሮሚያና የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የጋራ የልማትና የሰላም ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ያከናወናቸውን ተግባራት የተመለከተ ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
የማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ተሾመ ደሳለኝ እንደተናገሩት ጽህፈት ቤቱ ተቋቁሞ ስራ ከጀመረበት ከ2009 ዓ.ም. ወዲህ ሁለቱ ክልሎች በሰላምና ልማት ዙሪያ ተቀራርበው መስራት በመቻላቸው በአካባቢው ይከሰቱ የነበሩ ግጭቶችን አስወግደው በርካታ የሰላምና የልማት ውጤቶችን ማስመዝገብ ችለዋል፡፡ ክልሎቹን የሚያስተሳስሩ አዳዲስ የመንገድ ግንባታዎችም በመከናወን ላይ ናቸው፡፡
ምስራቅ ወለጋንና ካማሽ ዞኖችን የሚያገናኘው የ19 ኪሎ ሜትር መንገድ ግንባታ 50 በመቶ የተጠናቀቀ ሲሆን ዞኖቹን በሌላ አቅጣጫ የሚያስተሳስር 46 ኪሎ ሜትር መንገድ ለመገንባት 390 ሚሊየን ብር ተመድቦ ጨረታ ወጥቶ ስራ ተጀምሯል፡፡ የውሃ ፕሮጀክቶች ግንባታም እየተካሄደ ይገኛል፡፡
እንደ አቶ ተሾመ ገለጻ የክልሎቹን ግንኙነት ለማጠናከር በተለያዩ መንገዶች ተዘግተው የነበሩ መንገዶችን ማስከፈት ተችሏል፡፡ ሊከሰቱ የሚችሉ የጸጥታ ችግሮችን ለመከላከልም ለ 23 ወረዳዎች 26 ሞተር ሳይክሎች ቀርበዋል፡፡ ከሁለቱ ክልሎች የተፈናቀሉ ከ 250 ሺህ በላይ ዜጎች ወደቀያቸው ተመልሰው መተማመን ለመፍጠር የሚያስችሉ የሰላምና እርቅ ኮንፈረንሶች ተካሂደዋል፡፡ የወንጀል ተጠርጣሪዎችም ለህግ እንዲቀርቡ ተደርጓል፡፡
የሰላም ጉዳይ በውስን ተቋማት ጥረት ብቻ የሚሳካ ባለመሆኑ ሁሉም መስሪያ ቤቶች ሰላምን ጉዳያቸው አድርገው እንዲሰሩ ተደርጓል ያሉት አቶ ተሾመ፤ በ13 የልማትና የጸጥታ መስሪያ ቤቶች በሰላም ዙሪያ የሚሰራ ወኪል እንዲኖር ተደርጓል ፤ ግጭቶችን ቀድሞ መከላከል እንዲቻልም ከቀበሌ እስከ ክልል ያሉ የመንግስት ተቋማት በየጊዜው የሚገናኙበት ሁኔታም ተፈጥሯል ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ትልቅሰው ይታያል ኦሮሚያና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በሰላምና በልማት ዙሪያ እያከናወኑ ያሉት ተግባራት ለሌሎች አርዓያ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ነሀሴ 15/2011
መላኩ ኤሮሴ