ጅማ፡- የኅብረት ሥራ ማህበራት አገሪቱ ችግር ውስጥ በነበረችባቸው ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ፖለቲካውን ለማረጋጋት ትልቅ ድርሻ እንደነበራቸው የፌዴራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ገለፀ፡፡
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡስማን ሱሩር ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፣ ማኅበራቱ በተለይ ባለፉት ሦስት ዓመታት አምራቹን በቀጥታ ከሸማቹ ጋር በማገናኘትና የዋጋ ንረትን በማረጋጋት በከተሞች ውስጥ እየተፈጠረ ያለውን ያልተገባ የኑሮ ውድነት እንዲስተካከል በማድረግ ሃገሪቱ የገጠማትን ቀውስ ለማርገብ ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡ ይህም ፖለቲካዊ ቀውሱ በኢኮኖሚያዊ ቀውስ ታጅቦ እንዳይባባስና ችግሩ ወደ ከፋ ደረጃ እንዳይደርስ ከፍተኛ እገዛ አድርጓል፡፡
ስለሆነም ማኅበራቱ ግብርናውን ለማዘመንና ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን ኢኮኖሚያዊ ሽግግር ለማፋጠን ባላቸው ጉልህ ድርሻ በኢኮኖሚው ዘርፍ እየተጫወቱ ካሉት ወሳኝ ሚና ባሻገር ፖለቲካውን በማረጋጋት ረገድም ትልቅ ድርሻ ነበራቸው፡፡ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ዜጎችን በስፋት በማደራጀት፣ የሃገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት በሆነው የግብርናው ዘርፍ ላይ በንቃት በማሳተፍና ግብርናውን በማዘመን ለሃገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙም አቶ ዑስማን ገልፀዋል፡፡
የጅማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱልሐኪም ሙሉ የህብረት ሥራ ማህበራት የአገሪቱን ዕድገት ለማፋጠን ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ አቶ አብዱልከሪም እንዳሉት፣ ዕውቀትን፣ ክህሎትንና ሀብትን አስተባብሮ የተሻለ አገራዊ ዕድገትን በማስመዝገብ ረገድ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ዓይነተኛ አማራጭ ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ እስካሁን ባለው ሂደትም በዞኑና በክልሉ ተስፋ ሰጭ ሆነ ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡ የኅብረት ሥራ ማኅበራቱ የሃገርን ልማት በማፋጠን ረገድ እያበረከቱት ካለው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ባሻገር በሀገሪቱ ሕዝቦች መካከል አብሮነትና አንድነት እንዲጠነክር ድልድይ ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡
ሰላምና ዲሞክራሲን ለማስፈንና ፖለቲካዊ መረጋጋትን ለማምጣት የማኅበራቱ ሚና ከፍተኛ መሆኑን በማመላከት፣ በኢኮኖሚው ዘርፍ ብቻ ሳይሆን አለመግባባቶች እንዲረግቡና የሃገሪቱ ፖለቲካ ከባቢ አየር ሰላማዊ እንዲሆን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ዋና አስተዳዳሪው ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ህብረት ሥራ ማህበራቱ ካላቸው ሁለንተናዊ ፋይዳ አንጻር በዞኑና በክልሉ መንግስትም ሆነ እንደ ሃገር እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠል የሚገባው መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በዞኑ ጎማ ወረዳ በሆነችው በሻሻና በቀዳ መሳ ቀበሌዎች የሚገኙት የድሮሚናና ሁንዳኦሊ መሰረታዊ የህብረት ሥራ ማህበራት በዘርፉ እየተመዘገበ ላለው ውጤት ተጨባጭ ማሳያዎች መሆናቸውን በመግለጽ በርካታ አርሶ አደሮችን በአባልነት በመያዝና ገቢያቸውን በማሳደግ ኑሯቸውን እየለወጡ ከመሆኑም ባሻገር ሦስት ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብር በማውጣት የከፍተኛ ትምህርት መሰናዶ ትምህርት ቤት በመገንባት ለአካባቢው ነዋሪዎች አስረክበዋል፡፡
የፌዴራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ከነሐሴ 9 እስከ 11 ቀን 2011 ዓ.ም በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በጅማ ከተማ ባዘጋጀው የምክክር መድረክ የሴክተሩን የ2011 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ገምግሟል፤ የ2012 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይም ከክልል ኃላፊዎችና ባለድርሻ ካላት ጋር ተወያቶ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
አዲስ ዘመን ነሀሴ 15/2011
ይበል ካሳ