አዲስ አበባ፡- “እሬቻ” ፍቅርና ስምምነት የሚበረታበት ፣ የተጣሉ የሚታረቁበት ፣ለመጪው አመት ብሩህ ተስፋ የሚሰንቁበት መሆኑን የቱለማ አባገዳ፣የኦሮሞ ህብረት ፀሀፊ እንዲሁም የበአሉ የኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጎበና ኦላሬሶ ገለፁ፡፡
ትናንት በኦሮሚያ ባህል ማእከል አዳራሽ የእሬቻ በዓል (የማመስገኛ ቀን)ን በተመለከተ በተሰጠው መግለጫ፤ አቶ ጎበና እንደተናገሩት፤የፍቅርና የሰላም ተምሳሌት የሆነውን እሬቻ በዓል በአዲስ አበባ ለማክበር ዝግጅት ተጠናቅቋል፡፡
የአባገዳዎቹ አማካሪ የሆኑት ቀሲስ በላይ መኮንን በበኩላቸው፤ ለሆራ እሬቻ በአል የእንኳን አደረሳችሁ ጥሪያቸውን አስተላልፈው የምስጋና መስጫ የእሬቻ በአልን ለማክበር የሚያስችሉት ቅድመ ሁኔታዎች በመጠናቀቃቸው መላው ኢትዮጵያውያን በጋራ ደምቀው የሚታዩበት እንደሚሆን እምነታቸውን ተናግረዋል፡፡
እሬቻ ሰላም ፍቅር አንድነት መመሰጋገኛ እንዲሁም በህብረተሰቡ ዘንድ መልካም ግንኙነት የሚበረታበት መሆኑን በመጠቆም፤ ከሀገር ውስጥና ከባህር ማዶ የሚመጡ ከአምስት እስከ ስምንት ሚሊዮን የሚገመቱ እንግዶች ይታደሙበታል ተብሎ በተገመተው በዚህ ፕሮግራም ላይ ፍፁም ሰላማዊ የሆነ አቀባበል ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ቀሲስ በላይ ተናግረዋል፡፡
በዓሉ በቢሾፍቱ መስከረም 24 እንዲሁም በአዲስ አበባ መስከረም 25 እንደሚከበርና ቀኑም እንደ አስፈላጊነቱ ሊቀየር እንደሚችል፤ ያንንም ለህዝብ እንደሚያሳውቁ ከአባገዳ ህብረቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
አዲስ ዘመን ነሀሴ 15/2011
ዳግማዊት ግርማ