አዲስ አበባ፤ የክረምት ወቅት የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የጤናውን ዘርፍ በመደገፍ ረገድ ያለው አስተዋፅኦ የጎላ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሰሃርላ አብዱላሂ በጥቁር አንበሳ እና በዘውዲቱ ሆስፒታሎች ውስጥ እየተካሄደ ያለውን የክረምት ወቅት የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ትናንት በጎበኙበት ወቅት እደገለፁት፤ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ በተለያየ መልኩ ለጤናው ዘርፍ ጉልህ አስተዋፅኦ ያበረክታል፡፡
እንደ ሚኒስትር ዴኤታዋ ገለፃ ከፍተኛ የታካሚዎች ፍሰት በሚታይበት በጥቁር አንበሳ አጠቃላይ ሆስፒታል ወጣቶቹ ህሙማንን የመንከባከብ፣ በሆስፒታሉ የሚገኙ ልዩ ልዩ የስራ ክፍሎችን የማገዝና መሰል የበጎ ፍቃድ ስራዎችን ሲያከናውኑ ቆይተዋል፡፡ ተግባሩም ህሙማን ሳይንገላቱ የህክምና አገልግሎቱን እንዲያገኙ በማስቻሉ ለጤናው ዘርፍ ከፍተኛ አስታዋፅኦ አበርክቷል፡፡
‹‹ህሙማን በሆስፒታሎች ውስጥ ከሚማረሩባቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የህክምና ካርድ መጥፋትና ሌሎችም ምክንያቶች ናቸው›› ያሉት ሚኒስትር ደኤታዋ፤ በወጣቶቹ እየተደረገላቸው ያለው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የጤናውን ዘርፍ በመደገፍ ረገድ ያለው ሚናም ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በተመሳሳይም በዘውዲቱ ሆስፒታል ወጣቶቹ በተለይ ከአስር አመት በላይ የሆኑ የህክምና ካርዶችንና ፋይሎችን የማይፈለጉት እንዲወገዱ፣ የሚፈለጉት ደግሞ ተስተካክለው እዲቀመጡ ማድረጋቸውም የበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ በጤናው ዘርፍ ያበረከተው ሌላኛው አስተዋፅኦ መሆኑንም ሚኒስትር ደኤታዋ ጠቅሰዋል፡፡
የላብራቶሪ አገልግሎት ፈልገው ወደ ሆስፒታሎች የሚመጡ ታካሚዎች አገልግሎቱን እንዲያገኙ ወጣቶቹ ያከናወኗቸው ቅደም ተከተል የማስያዝ፣ የማደራጀትና አቅመ ደካሞችን የማገዝ ስራዎች ለታካሚዎችም ሆነ ለህክምና ባለሙያዎች ትልቅ እፎይታ መስጠቱንም አስታውቀዋል፡፡
በቀጣይ በጤናው ዘርፍ የሚደረገው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተሰማርተው ላሉ ወጣቶች በዋናነትም በህክምና ትምህርት ዘርፍ ላይ ላሉት የህክምና ሙያን እንዲያውቁ ኮትኩቶ የማሳደግና ስልጠናዎችን የመስጠት ስራዎች እንደሚከናወኑም ሚኒስትር ደኤታዋ አያይዘው ገልፀዋል፡፡ የጤና ሚኒስቴርም ለበጎ ፍቃድ ወጣቶች የተለያዩ መርሀ ግብሮችን በመቅረፅ የህክምና ዘርፉን እንዲያውቁ እንደሚያደርግም ጠቁመዋል፡፡
በዘንድሮ የክረምት ወቅት ‹‹በጎነት በሆስፒታል›› በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ 12 የመንግስት ሆስፒታሎች እየተካሄደ ባለው የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከ1 ሺ በላይ የሚሆኑ ወጣቶች የተሳተፉ ሲሆን፤ በጎ ፈቃደኞቹ ህሙማንን የመንከባከብ፣ የካርድ ክፍሎችን የማገዝ፣ የፅዳትና ሌሎችንም ስራዎች እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡
አዲስ ዘመን ነሀሴ 15/2011
አስናቀ ፀጋዬ