ወጣት ፀሐይ መካሻ ከሶስት ዓመታት በፊት በአንድ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ውስጥ ተቀጥራ ትሰራ እንደነበር ታስታውሳለች። በወቅቱም ደመወዝ አነስተኛ ነበር የሚከፈላት። ብዙም ሳትቆይ ስራውን በመልቀቅ ሌላ ስራ ማፈላለግ ትጀምራለች። ከብዙ ልፋት በኋላም ላይላክ በተሰኘው የሴቶችና ህፃናት ንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ አምራች ፋብሪካ ውስጥ ትቀጠራለች።
አሁን በፋብሪካው የምርት ቁጥር ዘርፍ ላይ እየሰራች የምትገኘው ወጣት ፀሐይ፣ የተሻለ የወር ደመወዝ ተከፋይ መሆኗን ትገልጻለች። በፋብሪካው ስራዎች በጥንቃቄ እንደሚከናወኑ ጠቅሳ፣ ለሰራተኞች ደህንነት ቅድሚያ መሰጠቱንም ነው የምትገልጸው። ይህም ስራውን ይበልጥ እንድተወደው አድርጓታል፡፡
ፋብሪካው በአንድ ወቅት ማምረት አቁሞ እንደነበር የምታስታውሰው ወጣቷ፣ ማምረት ባቆመባቸው ወራትም አንድም ሰራተኛ አለመቀነሱንና ደመወዝም አለመከልከሉን ትናገራለች። ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት የገጠመው ችግር በመንግስት በኩል ቢፈታ ምርቱን በማሳደግ ለሌሎችም ዜጎች ተጨማሪ የስራ እድል መፍጠር እና በስራ ላይ ለሚገኙት ሰራተኞችም የደመወዝ ማሻሻያ ሊያደርግ እንደሚችል ታብራራለች።
ወጣት ዳንኤል በጋሻው በ2008 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ በኤሌክትሮ ሜካኒካል ኢንጂነሪንግ በመጀመሪያ ዲግሪ ቢመረቅም ስራ ለማግኘት ተቸግሮ ቆይቶ ነበር። በ2009 ዓ.ም መጨረሻ ላይላክ የተሰኘው የሴቶችና ህፃናት የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ማምረቻ ፋብሪካ ሲከፈት በፕሮዳክሽን ማናጀርነት ተቀጥሮ የመስራት እድል ተፈጥሮለታል። በአሁኑ ወቅት ጥሩ ደመወዝ ከሚከፈላቸው የድርጅቱ ሰራተኞች ውስጥ አንዱ የሆነው ወጣት ዳንኤል፣ ፋብሪካው ሲስፋፋና በገበያው ውስጥ ዘልቆ ሲገባ የተሻለ ደመወዝ ሊያገኝ እንደሚችል እምነቱ አለው።
ከመጀመሩ በፊት ከውጪ በመጡ ባለሞያዎች የሰባት ወራት ስልጠና ተከታትሎ ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ እንደቻለም ወጣቱ ያስረዳል። የሰራተኞችን ደህንነት ለማረጋገጥ ሰፊ ጥረቶች መደረጋቸውን ጠቅሶ ፣ ከንፅህና ጀምሮ ለሰራተኞች የአፍ ማስክ፣ ገዋን፣ ጓንትና ሌሎችም አስፈላጊ የደህንነት ቁሳቁስ መሟላታቸውን ያስረዳል።
ፋብሪካው በመንግስት ቢሮክራሲና በውጪ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት ጥሬ እቃዎችን ከውጪ ማስገባት ባለመቻሉ ለአስር ወራት ያህል ተዘግቶ እንደነበር ወጣት ዳንኤል ያስታውሳል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ፋብሪካው ለሰራተኞች ሙሉ ደመወዝ ሲከፍል መቆየቱንና ይህም የሰራተኞችን መብት የሚያከብር መሆኑን እንደሚያመለክት ይገልፃል። የውጪ ምንዛሬ እንደልብ ቢኖርና ጥሬ እቃዎችም ቢሟሉ ፋብሪካው ተጨማሪ ሰራተኞችን ቀጥሮ ማሰራትና የስራ እድል መፍጠር እንደሚችልም ወጣት ዳንኤልም ያመለክታል።
የፋብሪካው ቢዝነስ ልማት አማካሪ አቶ ሞኢዝ አባስ እንደሚገልፁት የህፃናትና ሴቶች ንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ በከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ተገዝተው ወደ ሃገር ውስጥ ይገባሉ። ይህንኑ የውጪ ምንዛሬ ብክነት በሃገር በቀል ድርጅት ምርቶች ለመቀነስና የሃገሪቷን የውጭ ምንዛሬ ችግር በተወሰነ መልኩ ለመፍታት ነው ፋብሪካው የተቋቋመው። ይሁን እንጂ ፕሮጀክቱ ከተጠነሰሰበት ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ ጥናት፣ የቅድመ ዝግጅት፣ ግንባታ፣ የማሽን ተከላና በአሁኑ ወቅት ደግሞ የማምረት ስራውን በሚያካሂድበት ወቅት ፋብሪካው በርካታ መሰናክሎች አጋጥመውታል።
እንደ አማካሪው ገለፃ፤ የውጪ ምንዛሬ እጥረትና ለዘርፉ የሚሰጠው ምዘናና ስርጭት አጥጋቢ አለመሆንና በተለይ የፋይናንስ ተቋማት በወቅቱ ምላሽ አለመስጠት ፋብሪካውን ካጋጠሙት ችግሮች መካከል ዋና ዋናዎቹ ናቸው። በተለያዩ የመንግስት አካላት በተለይም የአመራር ፖሊሲ አውጪና አካሎቻቸው መካከል ያለው አሰራር የኢንፎርሜሽን ክፍተቶች ያሉበት መሆኑና ለውጪ ባለሃብቶችና ለሃገር ውስጥ አምራቾች የሚደረገው ድጋፍ ልዩነት ለፋብሪካው እድገት ተጨማሪ እንቅፋቶች ሆነዋል።
‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ምርቱ ስለተመረተ ብቻ ጥራት የለውም ማለት አይቻልም›› የሚሉት አማካሪው፣ ‹‹የፋብሪካው ምርቶች ጥራታቸውን የጠበቁና የሸማቹን አቅም ያገናዘቡ ቢሆንም ለሃገር ውስጥ ባለሃብቶች በመንግስት በኩል የሚሰጠው ድጋፍና አናሳ በመሆኑ በሚፈለገው ልክ ምርቱን አስተዋውቆ ለገበያ ማቅረብ አልቻለም ›› ሲሉ ያብራራሉ።
በመሰረታዊና አላቂ እቃዎች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለሃያ ዓመታት የሰሩትና በአሁኑ ወቅት የፋብሪካው ዋና አማካሪ በመሆን የሚሰሩት አቶ ሰልሃዲን መሃመድ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ መሰረታዊና አላቂ እቃዎች ህብረተሰቡ በቀን ተቀን እንቅስቃሴው ውስጥ በመሰረታዊነት ያስፈልጉታል። ከነዚህ ምርቶች አንደኛው የህፃናትና ሴቶች ንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ነው።
ከሃያ ዓመታት በፊት ሀገሪቷ ከውጭ ሃገር የምታስገባው የሴቶችና የህፃናት የንፅህና መጠበቂያ ቁስ ከሁለት ኮንቲነር የሚበልጥ አልነበረም የሚሉት አማካሪው፣ በዋጋውም በተደራሽነቱም ዝቅተኛ እንደነበር ይጠቅሳሉ።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ህፃናት ንፅህና መጠበቂያ ቁስ ፍላጎት እየጨመረ ቢሄድም፣ ቁሱን በሃገር ውስጥ የሚያመርት ፋብሪካ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አልነበረም። ከዛሬ ሶስት ዓመት በፊት የተቋቋመው ላይላክ የህፃናትና ሴቶች ንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ማምረቻ ፋብሪካ በኢትዮጵያ ቀዳሚው ፋብሪካ ለመሆን በቅቷል። ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት ለስምንት ሰዓታት የሚያመርት ሲሆን፣ በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር የሃገሪቷን ፍላጎት በተወሰነ መልኩ ማሟላት ይችላል።
ባለው የውጪ ምንዛሬ እጥረትና የጥሬ እቃዎች አቅርቦት ችግር ምክንያት ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ሊያመርት እንዳልቻለ አቶ ሳልሃዲን፣ የፋብሪካው ምርቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚመረቱት ጋር ተወዳዳሪ መሆናቸውን ይገልጻሉ። በዋጋ ደረጃም ተመጣጣኝ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባትና የሃገር ውስጥ ባለሃብቶችን ለማበረታታት በወጣው ፖሊሲ መሰረት ከመንግስት በኩል አስፈላጊውን ድጋፍና ማበረታቻ ሊደረግለት እንደሚገባም ነው ያመለከቱት።
የፋብሪካው መስራችና ባለቤት አቶ መሃመድ የሱፍ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ፋብሪካው ጥሬ እቃዎችን ከአሜሪካ፣ ጃፓን፣ ቻይናና ሆንግኮንግ ያስመጣል። ይሁንና በውጪ ምንዛሬ እጥረት ሳቢያ ጥሬ እቃዎችን ወደሃገር ውስጥ እንደልብ ማስገባት አልተቻለም። በዚህም ምክንያት ለአስር ወራት ፋብሪካው ተዘግቶም ነበር፡፡
ፋብሪካው ወደውጪ ሃገራትም ጭምር በተለይ ወደ ጎረቤት ሃገራት ምርቱን የመላክ ፍላጎትም አቅሙም እንዳለው ጠቅሰው፣ በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት ጥሬ እቃዎችን እንደልብ ወደሃገር ውስጥ ማስገባት እንዳልቻለ በመጥቀስ የአማካሪዎቹን ሀሳብ ያጠናክራሉ ። በዚህ የተነሳም በሙሉ አቅሙ አምርቶ በተለይ ለሃገር ውስጥ ተጠቃሚዎች ማቅረብ እንዳልቻለም ያመለክታሉ።
በጅቡቲና ደቡብ ሱዳን ምርቶቹን የመጠቀም ፍላጎት እንዳለ የሚናገሩት አቶ መሃመድ፤ በአሜሪካም ገበያ የማፈላለግ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ይጠቁማሉ። በብዛት አምርቶ ለእነዚህ ገበያዎች ለማቅረብ እንዲችል ፋብሪካው የገጠመው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ሊፈታላት ይገባል ይላሉ።
ፋብሪካ በ100 ሚሊዮን ብር ካፒታል ተቋቁሞ በ2009 ዓ.ም መጨረሻ ነው ማምረት የጀመረው። ከሃምሳ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የስራ እድል ፈጥሯል። በአሁኑ ወቅት በስራ ላይ የሚገኙት የፋብሪካው ማሽኖችም በዓመት 74 ሚሊዮን የህፃናት ዳይፐርና 86 ሚሊዮን የሴቶች ንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ የማምረት አቅም እንዳለው ከፋብሪካው የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።
በመንግስት ጥናት ተደገፎ በቅርቡ ይፋ በሆነ መረጃ መሰረት በኢትዮጵያ አንድ ቢሊዮን የሴቶች እንዲሁም የዚህን ያህል እጥፍ የህፃናት ንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ፍላጎት እንዳለ የሚታወቅ ሲሆን፣ 85 ከመቶ የሚሆነው ይኽው ቁስ በከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ ከውጭ ሀገር እንደሚገባ ታውቋል።
ከኃላፊዎቹ መረዳት እንደተቻለው ፤ የውጭ ምንዛሬ እጥረቱ ካልተፈታና ጥሬ እቃዎች እንደ ልብ ካልገቡ ፋብሪካው አሁንም የመቆም አደጋ ሊያገጥመው ይችላል። በመሆኑም የገጠመው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ሊፈታለት ይገባል። ፋብሪካውም የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም ችግሩን ለመፍታት ጥረት ማድረግ ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን ነሀሴ 14/2011
አስናቀ ፀጋዬ
የኒውክሌር የጦር መሳሪያ ታጣቂዎቹ የ‹‹ትገባኛለች››ፍጥጫ
ታምራት ተስ ፋዬ
ሕንድ እና ፓኪስታን እኤአ 1947 ከታላቋ ብሪታኒያ ቅኝ ግዛት ነፃ ወጥተው ከአንድ ወደ ሁለት አገርነት ከተለወጡ ማግስት አንስቶ ላለፉት ሰባት አስርት ዓመታት አንድም ቀን ሰላም ሆነው አያውቁም። የካሽሚር ግዛት ‹‹ትገባኛለች››ን ዋነኛ ምክንያት የሚያደርገው የኢስላማባድና የኒውዴህሊ ፍጥጫም ሁለቱን ሀገሮች ለሁለት ጊዜያት ያህል ጦር አማዟል፡፡
በእርግጥ ሁለቱ የኒውክሌር የጦር መሳሪያ ታጣቂ ባላንጦች እአአ በ2003 የተኩስ አቁም ስምምነት አድርገዋል፡፡ በስምምነቱም ጃሙና ካሽሚር በተባለ ስፍራ ላይ የተወሰነውን ወታደራዊ የድንበር መስመር በመቀበል ከጠብ ለመራቅ ተስማምተዋል፡፡ ይሁንና ዛሬም ድረስ የካሽሚር ውዝግባቸው ያልተዘጋ አጀንዳቸው ሆኖ ዘልቋል፡፡
ሀገሮቹ በካሽሚር ጉዳይ ሁሌም ስሜተ ስሱ ናቸው፡፡ አንዷ ሌላኛዋን በጭራሽ አታምናትም። አትቀበላትም። በቀጠናው የሁለቱም አገሮች ወታደሮች ሁሌም በተጠንቀቅ ላይ ናቸው። ፍጥጫቸው ረገብ በሚልበት ወቅት እንኳን ውጥረትና መፈራራት ጠፍቶ አያውቅም። የእርስ በርስ መወነጃጀላቸውም የተለመደ ነው፡፡
ባሳለፍነው አመት ኢምራን ከሃን የሚመራው የፓኪስታን ፓርቲ ምርጫውን በማሸነፍ ከ220 ሚሊየን በላይ ህዝብ ያላትና የኒውክሌር ባለቤት የሆነችውን አገር ለመምራት ስልጣን ሲረከቡ፣የሁለቱ አገራት ቁርሾ ፈር ሊያገኝ አንደሚችል በርካቶች ተስፋ ነበራቸው፡፡
ቀደም ሲል የፓኪስታን ብርቱ የክሪኬት ስፖርት ተጫዋች የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ከሃን፣ በምጣኔ ሐብት ድቀት፤ በድንበር ውዝግብ እንዲሁም በፅንፈኞች ሽብር ክፉኛ የቆሰለችውን፣ በጦርነት ዳሽቃ፣ሰላምና ዜጓቿን የተነጠቀችውን አገር ገፅታ ከመለወጥ በተጓዳኝ ለአመታት እልባት ለናፈቀው የጎረቤታሞቹ ጉዳይ መፍትሄ ለመስጠት እንደሚሰሩም ማረጋገጫም ቃላቸውን ሰጥተው ነበር፡፡
‹‹በክሪኬት ስፖርት ምክንያት ከማንኛውም ፓኪስታናዊ በላይ ህንድን ጠንቅቄ አውቃታለሁ› የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ከሃን፤ በዘመነ ስልጣናቸው ከኒውዴሊህ መንግስት ጋር መልካም ወዳጅነት ለመመስረት ፍላጎታቸው ስለመሆኑም በአደባባይ አስታውቀዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሁለቱ ጎረቤት አገራት መካከል ሰላም እንዲወርድ እንደሚተጉ ቢገልፁም፤ የመሪነቱን ወንበር ከተቆናጠጡ በኋላ ግን ይህን ቃላቸውን ወደ ተግባር የመለወጥ ቁርጠኝነታቸው እዚህ ግባ የሚባል አልሆነም፡፡
በስልጣን ተዋረድ አንዱ መሪ መጥቶ በሌላው ቢተካም ከፍቅር ይልቅ ጠብ የማያጣው የሁለቱ የኒውክሌር የጦር መሳሪያ ታጣቂ ባላንጦች ፍጥጫ፣ በተለይ በኢምራን ከሃን የስልጣን ዘመን ይባስ ብሎ እየጦዘ የመጣ ይመስላል፡፡ ባሳለፍነው ጥር ወር በካሽሚር ግዛት ከ40 በላይ የሕንድ ወታደሮች መገደላቸውም በርቀት በተጠንቀቅ ይጠባበቁ የነበሩትን የሁለቱ አገራት ወታደሮች ይበልጥ እንዲፋጠጡ አድርጓቸውም ታይቷል፡፡
በክስተቱ ምክንያት የሁለቱ አገራት ግንኙነት ከአንገት በላይ መሆን ከጀመረ ብዙም ሳይቆይ ሕንድ ከቀናት በፊት በሕገ-መንግስቷ በአንቀጽ የሰፈረውን ካሽሚር የነበራትን ልዩ መብትና አስተዳደራዊ ስልጣን መሻሯ በጎረቤታሞቹ አገራት መካከል እየተቀጣጠለ በነበረው እሳት ላይ ቤንዚን አርከፍክፎበታል፡፡
የሕንድ የአገር ውስጥ ሚኒስትሩ አሚት ሻህ፤ መንግስታቸው ለካሽሚር ልዩ መብት የሚሰጠውን የህገመንግሥቱን አንቀፅ 370 መሻሩንና የካሽሚር ግዛት ከአገሪቱ ጋር አንድ አድርጎ ለማስተዳደር ማቀዱን መግለጻቸውም ነገሩን ከድጡ ወደ ማጡ አሸጋግሮታል፡፡
አንቀጹ ካሽሚር የራሷን አዋጆች የማዘጋጀትና ሌሎችንም ውሳኔዎችን የማሳለፍ ልዩ አስተዳደራዊ ሥልጣንና መብቶች የሚሰጥ ነበር፤ ከመከላከያ፣ የውጭ ግንኙነት፣ ፋይናንስና ኮሚዩንኬሽን ውጪ ጉዳዮች ውጪ ግዛቲቱ የራሷን ሕግጋት የማውጣት ስልጣን የሚያጎናጽፍ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ መንግስት ይህን አንቀፅ በአብላጫ ድምፅ በመሻር ከእንግዲህ ‹‹አስተዳድረዋለሁ›› ባለው የካሽሚር ግዛት በርካታ ወታደሮችን ማሰማራቱና በግዛቲቱም የሰዓት እላፊ ገደብ መጣሉም በአገሪቱ ሕዝብ ዘንድ አድናቆትን አትርፎበታል፤ እርምጃው የሞዲ ጥንካሬ ማሳያ ተደርጎም ተወስዷል፡፡
የካሽሚር ግዛት ነዋሪዎች በአንፃሩ ውሳኔውን በብርቱ አውግዘውታል፡፡ ስሜታዊነት የታከለበት ጠንካራ ተቃውሞንም አስከትሏል፡፡ በተለይ በካሽሚር ግዛት የሚገኘው በጃሙ አካባቢ ላይ ለረዥም ጊዜ የይገባኛል ጥያቄ ስታቀርብ የቆየችውን የፓኪስታን መንግስት በእጅጉ አስቆጥቶታል፡፡
የኢስላማባዱ መንግስት ይሕ ስሜቱን በሚያንፀባርቅ መልኩም አፍታም ሳይቆይ ከሕንድ ጋር ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በመቀነስ የንግድ አጋርነቱን ማቋረጡን አስታውቋል። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በጉዳዩ ላይ ጣልቃ እንዲገባ እስከ መጠየቅም ደርሷል፡፡ ጉዳዩን ወደ ተመድ ጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤትም ወስዶታል፡፡
የአገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሻሕ መሐመድ ቁረይሽ ››በዚህ ጉዳይ አንደራደርም›› ብለዋል፡፡ በፓኪስታን የነፃነት ቀን ክብረ በአል ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ከሀንም የጎረቤታቸውን ውሳኔ በማብጠልጠል አገራቸው አስፈላጊ ከሆነ ለወታደራዊ ፍልሚያ ዝግጁ ስለመሆኗ ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡ ይህም ጡዘቱን ይበልጥ አስፈሪ አድርጎታል፡፡
በህንድ 73ኛ አመት የነፃነት ቀን ክብረ በአል ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በበኩላቸው ውሳኔውን ድንቅ አፈፃፀም በሚል በማሞካሸት አገሪቱን አንድ በማድረግ እድገት ለማምጣት በእጅጉ እንደሚያግዝ አስገንዝበዋል። የመንግሥታቸውን ውሳኔ የነቀፉትን ሁሉ ወደ ጎን በመተው የካሽሚር ጣጣ የአገራቸው የውስጥ ጉዳይ እንደሆነ ተናግረዋል።
በርካታ መገናኛ ብዙሃንና የፖለቲካ ጉዳይ ተንታኞችም የኒውክሌር የጦር መሳሪያ ታጣቂ አገራቱ ፍጥጫ የሚያስከትለውን አስከፊ ጥፋት ከወዲሁ ከማስገንዘብ ባለፈ የጎረቤታሞቹ ፍልሚያ ሌሎች ሀይሎችን ጭምር ሊያፋልም እንደሚችል ስጋታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡
አለማችንን የሚዘውሩ አገራት የሁለቱን አገራት ፍጥጫ ተከትሎ ከማን ጎን ሊቆሙ ይችላሉ የሚለውም ወሳኝ ጥያቄ ሆኗል፡፡ የዋሽንግተን ፖስቱ ባርክሃ ዱት የብላድሚር ፑቲንዋ ሩሲያ ከኒውዴህሊ ጎን መቆሟን አሳውቃለች፣ ከህንድ ጋር በድንበር የምትወዛገበው ቻይና በበኩሏ የኢሳላማባድን መንግስት መደገፍ መርጣለች›› ሲል አስነብቧል፡፡
በእርግጥም ቻይና የካሽሚርን ጉዳይ ወደ ጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት አድርሳዋለች፡፡ ምክር ቤቱም እእአ ከ1964 በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ የሁለቱን አገራት የካሽሚር ጉዳይ በዝግ ስብሰባ ለመመልከት ተገዷል፡ ፡ በስብሰባው ሕንድም ሆነች ፓኪስታን ጉዳዩን ከማባባስ እንዲቆጠቡ በመጠየቅ «የጃሙ እና ካሽሚር እጣ-ፈንታ በሰላማዊ መንገድ ሊወሰን ይገባል» የሚል አቋሙን አሳይቷል፡፡
ሞስኮና ቤጂንግ የየቅል ምርጫቸውን ካደረጉ ዋሽንግተን ‹‹ለማን ትወግናለች›› ተብሎ መጠየቁም አይቀር ነው፡፡ የአሜሪካና የፓኪስታን ግንኙነት ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ጥብቅና አንዳቸው ለሌላቸው የሚያስፈልጉበት ቢሆንም፣ ከዶናልድ ትራምፕ መምጣት በኋላ ግን ይህ ግንኙነት በእጅጉ ተቀዛቅዟል።
ለወትሮ አንዳቸው ለሌላቸው አስፈላጊ የነበሩት አገራትም አይንሽን ለአፈር ተባብለዋል። በተለይ የትራምፕ አስተዳደር በቢሊየን ዶላር የሚተመነውን የደህነንት ድጋፍ መሰረዙ ሽብርተኝነትን በመከላከል ረገድ በኢስላማበድ ላይ የነበረውን ጥገኝነቱን ስለ ማቋረጧ በቂ ምልክት ተደርጓል።
በእርግጥ ዶናልድ ትራምፕ ለሕንድ እጃቸውን በመዘርጋት በፓኪስታን መንግስት ላይ መኮሳተራቸው ለኒውደህሊ መልካም አጋጣሚን ፈጥሮ ነበር፡፡ ይህም ግንኙነት ከአመት በኋላ መልኩን የቀየረ እየመሰለ ሲሆን፣የዋሽንግተንና ኢስላማባድ ግንኙቱነት ግን መልካም በሚባል እርምጃ ላይ ይገኛል፡፡
ይህ እስከሆነ ደግሞ የነጩ ቤተ መንግስት አስተዳደር በሁለቱ አገራት ፍጥጫ ላይ የሚያሳድረው ጫና መመጣጠኑ የግድ ነው፡፡ የዋሽንግተኑን መንግስት ወደ ፓኪስታን እንዲያደላ የሚያስገድዱ አጀንዳዎች ሰለመኖራቸውም የፖለቲካ ምሁራን ይጠቁማሉ፡፡
ኢስላማባድ በአፋጋኒስታን ድንበር በካሽሚር አዋሳኝ በርካታ ወታደሮችን ለማሰማራት አስባለች መባሉ ወደ መጨረሻ ምእራፍ ተሸጋግሯል በተባለው የአሜሪካና ታሊባን የሰላም ድርድር ላይ አሉታዊ ተጽእኖ መፍጠሩ ተጠቁሟል፡፡ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ለህንድ ፍቅር ቢኖራቸውም፣የሁለቱ አገራት ፍጥጫ ኢስላማባድን እንዲያስቀድሙ ሊያስገድዳቸው ይችላል የሚል ግምት አሳድሯል፡፡
ከኒውርክ ታይምስ ጋር ቆይታ ያደረጉት በዩናይትድ ስቴትስ የፓኪስታን አምባሳደር አሳድ ማጂድ ከሃን በበኩላቸው፣ የካሽሚርና አፍጋኒስታን አጀንዳ ፈፅሞ ግንኙነት እንደማይኖረው ጠቅሰው፣ፓኪስታንም ለታሊባን ሰላም ድርድር ስኬታማነት የማትከፍለው መስዋዕትነት እንደሌለ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
ከባላንጣዎቹ ጎን የሚሰለፉት አገራት እያደር በተለዩበት በዚህ ወቅት በሁለቱ ሀገሮች ድንበር ላይ ወታደሮች መታኮሳቸውና አምስት የሚሆኑት ሕይወታቸውን ማጣታቸው በበርካቶች ዘንድ የኒውክሌር ታጣቂዎቹ ራሳቸውን ለጦርነት እያሟሟቁ ስለመሆኑ እንዲታመን ፍንጭ ሰጥቷል፡፡ የቀድሞው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምክትል ጸሐፊ ሎርድ ብራውን ከቢቢሲ ሬዲዮ 4 ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉትም ሁለቱ አገራት ጡንቻ ለመፈታተሸ በእጅጉ ተቃርበዋል፡፡
የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ጡንቻ ለመፈታተሽ የተዘጋጁ መስለዋል