
በተጠናቀቀው ሳምንት በእግር ኳስ ስፖርት በርካታ የአገር ውስጥ ዜና ዎችን ተመልክተናል። እነዚህ ወሬዎች ከተጫዋቾች ዝውውር አንስቶ ውዝግብ እስካስተናገደው የተጫዋቾች ደመወዝ በቀጥታ ተያያዥነት ያላቸው ነበሩ። በተለይ የተጫዋቾች ደመወዝን አስመልክቶ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከሰሞኑ ያሰማው ዜና እና ያወጣው መመሪያ ብዙሃኑን በሁለት ጎራ ከፍሎ እያጨቃ ጨቀ ይገኛል።
የአዲስ ዘመን የእሁድ ገፅ የስፖርት ዝግጅት ክፍላችን ለዛሬ በዚህ ሳምንት የተከሰቱ የእግር ኳስ ዜናዎችን ሊያስታውሳችሁ ወዷል። ለዜናዎቹ ዋቢም የሶከር ኢትዮጵያ ድረ ገፅን በዋናነት ተጠቅሟል። በቀዳሚነትም የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ቀዳሚ ተሰላፊ የሆነችውን የሎዛ አበራን ጉዳይ እ ነሆ ይላል።
ሎዛ አበራ
በሳምንቱ ከተሰሙ ጆሮ ገብ ዜናዎች መካከል በዋናነት ጉዳይ ሆኖ የሰነበተው የሎዛ አበራ ለማልታው ክለብ ‹‹ቢርኪርካራ›› ፊርማዋን ለማኖር ትናንት እረፋዱ ላይ መብረሯን የሚገልፀው ዜና ነበር።
ሶከር ኢትዮጵያ እንደዘገበው ባለፈው የውድድር ዓመት አጋማሽ ከሲዊድኑ ከንግስባካ ክለብ ጋር ረዘም ያለ የሙከራ ጊዜ አሳልፋ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰችው ሎዛ አበራ ፊርማዋን ለአዳማ ከተማ በማስፈር በውድድር ላይ ቆይታለች። ዳግም ከኢትዮጵያ ውጭ የመጫወት እድል ያገኘችው ተጫዋቿ ነገ ምሳ ሰዓት ወደ ማልታ በማቅናት ለቢርኪርካራ የሁለት ዓመት ኮንትራት እንደምትፈርም ወኪሏ ሳምሶን ናስሮ ለድረገፁ መግለፁን አስነብቧል።
ተጫዋቿ ወደ ማልታ ስታመራ ያለምንም የሙከራ ጊዜ እንደሆነም ተዘግቧል። ብቃቷን እንድትጠብቅ ለተከታታይ ቀናት በትንሿ የአዲስ አበባ ስታዲየም ከባለሙያ ጋር ልምምድ ስትሠራ እንደቆየች ታውቋል። የተጫዋቿ የጉዞ እና ሆቴል ወጪ በክለቡ እንደሚሸፈንም ተገልጿል። በ1999 ዓ.ም የተመሰረተው ቢርኪርካራ የአገሪቱን የሴቶች ሊግ ላለፉት ተከታታይ ሦስት ዓመታት ማንሳቱ ይታወቃል።
የደመወዝ ጣርያውን ተቃውሞ
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በሳምንቱ ውስጥ የማንኛውም የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ተጫዋች ደመወዝ ከ50 ሺ ብር መብለጥ የለበትም ብሎ ያሳለፈው ውሳኔ ከወዲሁ ውዝግብ እያስነሳ ነው። በዚህም የኢትዮጵያ ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋቾች ማህበር ውሳኔውን በቀዳሚነት ተቃውሟል። የተለያዩ መገናኛ ብዙሃንም ይህን ጉዳይ በስፋት ዘግበውታል።
አሶሴሽኑ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በፃፈው እና ለባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ለወጣቶች እና ስፖርት ኮሚሽን፣ ለበጎ አድራጎት እና ማህበራት ኤጀንሲ ፣ ለሠራተኛ እና አሰሪ ኤጀንሲ እንዲሁም ለመገናኛ ብዙሃን ግልባጭ ባደረገው ደብዳቤ የደመወዝ ጣሪያ ውሳኔውን ተቃውሟል።
በቅርቡ ህጋዊነቱን በማረጋገጥ የተቋቋመባቸውን ዓላማዎች ወደ ማስፈፀም ሥራ የገባው የኢትዮጵያ ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋቾች ማህበር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተጨዋቾችን ደመወዝ ጣሪያ ሃምሳ ሺ ብር እንዲሆን ያሳለፈውን ውሳኔ በፕሬዚዳንቱ ዮሃንስ ሳህሌ ፊርማ በወጣ ደብዳቤ በመቃውም እንደማህበር የመጀመሪያ ፈተናውን ጀምሯል። ደብዳቤው የፌዴሬሽኑን የመጨረሻ ውሳኔ ከመቃወም ባለፈ ለውሳኔው የተጠራው ስብሰባ የነበረበትን የአካሄድ ግድፈትም አንቀፆችን በመጥቀስ ተቃውሟል።
በዚህም ደብዳቤው እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ እየተጠቀመበት ባለው ደንብ መሰረት አሶሴሽኑ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ሙያተኞች ማህበር አባል መሆኑን በመጥቀስ በውሳኔው ወቅት ፌዴሬሽኑ ስላቀረበው ጥናት እንደ ሙያተኞች አባል ስለጉዳዩ ቅድመ ዝግጅት እንዳያደርግ ምንም አይነት ማስረጃ እንዳልተሰጠው ያትታል። በተጨማሪም ማህበሩ በሥሩ ያሉትን ሙያተኞች ወክሎ ስምምነቶችን ለማድረግ ምንም አይነት አማራጭ ያልተሰጠው መሆኑን በመግለፅ የቢሾፍቱው ስብስባ ላይ በተሳተፉ እና ውሳኔው በደረሷቸው ክለቦች አግባብነት ላይም ጥያቄ ያነሳል። በመጨረሻው የደብዳቤው ክፍልም ፌዴሬሽኑ የሄደበት መንገድ የፊፋን የስፖርት ችሎት ደንብ የጣሰ በመሆኑ ማህበሩ ህጋዊ መስመሮችን በመከተል በጉዳዩ እንደሚገፋበት አስታውቋል።
ወላይታ ድቻ
አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራን የቀጠረው ወላይታ ድቻ ሁለት የአማካይ ስፍራ ተጫዋቾችን ወደ ክለቡ ማቀላቀሉን በድጋሚ የሶከር ኢትዮጵያ ድረ ገፅ አስነብቧል። አስቀድሞ አማካዩን ዘላለም ኢሳያስን የመጀመሪያ ፈራሚ ያደረጉ ሲሆን አሁን ደግሞ ሰለሞን ወዴሳ እና ነጋሽ ታደሰን በሁለት ዓመት ስምምነት ወደ ክለቡ አምጥቷል።
የተከላካይ አማካዩ ሰለሞን ወዴሳ በሀዋሳ ከተማ ወጣት ቡድን ከ17 እና 20 ዓመት ቡድን የተገኘ ተጫዋች ሲሆን በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ሀዋሳን ከለቀቀ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ መድን አምርቶ በክለቡ ጥሩ የውድድር ጊዜን አሳልፏል።
ሌላው የክለቡ አዲስ ፈራሚ ነጋሽ ታደሰ እንደ ሰለሞን ሁሉ በሀዋሳ ወጣት ቡድን የእግር ኳስ ህይወቱን ጅማሮ ያደረገ ሲሆን በሀዋሳ ዋናው ቡድን ውስጥም በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ካደገ በኃላ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴን ያደረገ ተጫዋች ነው።
እስከ አሁን ሦስት አዳዲስ ተጫዋችን ያስፈረሙት የጦና ንቦቹ የነባር ተጫዋቾችን ውል ለማራዘምም በእንቅስቃሴ ላይ የሚገኙ ሲሆን በአዳማ እየተደረገ ያለውን ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ እየተመለከቱ የሚገኙት አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ በርከት ያሉ ወጣቶችን ለማሳደግ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ከሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል።
ሴካፋ ከ15 ዓመት በታች
በሳምንቱ ተነግረው ጆሮ ገብ ከሆኑ ዜናዎች መካከል አንዱ የሆነው ከ15 ዓመት በታች የሴካፋ ውድድር ነው። በዚህም በኤርትራ አዘጋጅነት በሚካሄደው ውድድር ላይ ተሳታፊ የሚሆነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን አስመልክቶ መግለጫ ተሰጥቶ ነበር።
የፌደሬሽኑ የቴክኒክ እና ልማት ክፍል ኃላፊ አቶ መኮንን ኩሩ ስለ ውድድሩ ገለፃ ባደረጉበት ወቅት እንደተናገሩት፤ ከዚህ ቀደም ከ11 ዓመት በታች ቡድን ወደ ቻይና ተልኮ ጥሩ እንቅስቃሴ አሳይቷል። አሁን ደግሞ በአገሪቷ ለመጀመሪያ ጊዜ ተብሎ በሚታሰበው የእድሜ እርከን ቡድን ተዋቅሮ ወደ ኤርትራ ተልኳል። ብሔራዊ ቡድኑ በመጀመሪያ ከሴካፋ ጥሪ የደረሰው በሰኔ ወር መጨረሻ አካባቢ ነው። ይህም የተጣበበ ጊዜ እንዲፈጠር የሆነው ደግሞ የውድድሩ አዘጋጅ ኤርትራ ውድድሩን ለማከናወን ቶሎ ፈቅዳ ምላሽ ስላልሰጠች ነበር። ቢሆንም ግን ቡድኑ ዝግጅቱን ቀደም ብሎ በሐምሌ ወር መጀመሪያ ማድረግ ጀምሯል።
እንደ አቶ መኮንን ገለፃ፤ በኢትዮጵያ በዚህ የእድሜ እርከን የሚወዳደር ሊግ የለም። እንደ አማራጭ የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌደሬሽን ሲያወዳድር ቢቆይም ሙሉ ለሙሉ ከዛ ውድድር ብቻ የተውጣጣ ብሔራዊ ቡድን መገንባት አስፈላጊ ሆኖ አልተገኘም። በዚህ ምክንያት ሁለት አማራጮች መመልከት አስፈላጊ ሆኗል። የመጀመሪያው የነበረው የኮፓ ኮካኮላ ውድድር ነበር።
‹‹በዚህ ውድድር ጥሩ ነገር እናገኛለን ብለን አስበን ነበረ›› ያሉት አቶ መኮንን ነገር ግን ሰዎችን አሰማርተው በየውድድር ስፍራው የተመለከቱት ነገር አጥጋቢ እንዳልነበር ገልፀዋል። ምክንያቱ ደግሞ በየውድድሮቹ የነበረው የክልሎች የእድሜ ጉዳይ ችግር ስለነበረበት ነው። እንደ ሁለተኛ አማራጭም በየክልሉ ያሉ ተጨዋቾችን በመሰብሰብ ምልመላ ለማድረግ ተሞክሯል። በዚህም ከ400 በላይ ተጨዋቾችን ከየክልሎቹ ተሰብስበው በምልመላው ውስጥ ተሳታፊ ሆነዋል። በዚህም 92 ተጫዋቾችን ወደ አዲስ አበባ ተጠርተው ወደ ሁለተኛ ዙር መረጣ ተገብቷል። ምልመላውም በወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ ለሦስት ቀናት ተደርጎ 20 ተጨዋቾች ተለይተዋል።
አዲስ ዘመን ነሃሴ 12/2011
ዳግም ከበደ