ምንም እንኳን ሁለተኛ ትውልድ ከሚባሉት መካከል ቢሆንም፣ ከመማር ማስተማር ስራው በተጓዳኝ፣ ያለበትን አካባቢ ህብረተሰብ ችግር ማቃለል ያለመታከት እየሰራ ስለመሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ፤ በአሁኑ ወቅት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን እንደ ማዕበል እየናጣቸው የሚገኘውን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የጎራ ግጭት ታሪክ አድርጎ የሰላም ተምሳሌት ለመሆንም እየተጋ ይገኛል፤ ለ2012 የትምህርት ዘመንም 3ሺ612 አዲስ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ተዘጋጅቷል፤ ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ።
እኛም ለዛሬው እትማችን ዩኒቨርሲቲው ለ2012 የትምህርት ዘመን በስኬት መካሄድ ምን ዝግጅት እያደረገ ነው፤ ካለበት መልክዓ ምድራዊና ማህበራዊ አውድ አኳያ ማህበረሰቡን ያማከለ ምን ተግባር አከናውኗል፤ በቀጣይስ ምን ለመስራት አስቧል፤ በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶክተር አብዲ አህመድ ሀሰን ጋር ያደረግነውን ቆይታ በሚከተለው መልኩ ይዘን ቀርበናል፡፡
በ2011 ትምህርት ዘመን
ዶክተር አብዲ፣ 2011 የትምህርት ዘመን ለጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ አመራርና መምህራን በጥቅሉ እንደ ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ሰራተኞች፤ ብዙ ችግር ያሳለፍንበት ፈታኝ ወቅት ነበር ይላሉ፡፡ ምንም እንኳን ዓመቱ ፈታኝ ቢሆንም የጎላ ችግር ሳይደርስ የመማር ማስተማር፣ የጥናትና ምርምር እንዲሁም የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎቱን እያከናወነ ማጠናቀቁን ይገልጻሉ፡፡ የ2011 ትምህርት ዘመንን ሲጀምሩም በዋናነት ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ እንዴት ነው በሰላማዊ ሁኔታ ቀጥሎ ተማሪዎችን ማስተማር የሚችለው? የሚለው ላይ በማተኮር ሲሆን፤ በተለይም ሐምሌ 2010 በከተማው ተከስቶ የነበረው ችግር የፈጠረውን ስጋት መቀነስ ያስቻሉ ተግባራትን በማከናወን ወደስራ መግባት መቻሉን አብራርተዋል፡፡
እንደ ዶክተር አብዲ ገለጻ፤ በዚህ መልኩ የተጀመረው የመማር ማስተማር ሂደትም በሂደቱ መሰናክሎች ያጋጠሙት ቢሆንም የጎላ ችግር ግን አልነበረም፡፡ ለምሳሌ፣ ምክንያት በመፈለግ ሁለት ጊዜ ብሔር ለበስ ግጭት ተከስቶ ነበር፡፡ ሆኖም የአንድም ሰው ህይወት ሳያልፍ፤ ወዲያውኑ ችግሩን መግታት ተችሏል፡፡ ይህ ደግሞ የዩኒቨርሲቲው አመራር ከመላው ሰራተኛ ብሎም ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጀምሮ ከከተማው አመራርና ህብረሰተብ ጋር በጋር የመሰራቱ ውጤት ነው፡፡
በዚህ መልኩ ያለፈውን የ2011 የትምህርት ዘመን ችግሮች ታሳቢ በማድረግም በ2012 የትምህርት ዘመን ሰላማዊ የመማር ማስተማር ጊዜ ለማሳለፍ የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ስራ እየተከናወነ ሲሆን፤ በዚህም የትምህርት ዘመኑ በጥሩ ሁኔታና በጥሩ መንፈስ እንዲጠናቀቅ ከከተማው፣ ከክልሉና ከፌዴራል የመንግስትና የዘርፉ አመራሮች ጋር መስራት ታቅዷል፡፡
ህዝብ ተኮር ሥራ እና ጥናት ምርምር
እንደ ዶክተር አብዲ ማብራሪያ፤ ማንኛውም ዩኒቨርሲቲ በአንድ ክልል ወይም ከተማ ውስጥ ሲቋቋም ከመማር ማስተማር በዘለለ የአካባቢውን ህብረተሰብ ችግር ተገንዝቦ ለመፍትሄው የመስራት ዓላማ ይዞ ነው፡፡ የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲም ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል (ሴንተር ኦፍ ኤክሰለንሲ ይሆናል) ተብሎ የታሰበው የአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደሩን ችግር ለመፍታት የሚያስችሉ ጥናትና ምርምሮችን መስራትና መፍትሄ ማስገኘት ላይ ነው፡፡ በሶማሌ ክልል ደግሞ ከ85 በመቶ በላይ ያለው የህብረተሰብ ክፍል አርብቶ አደር እንደመሆኑ፤ ለአርብቶ አደሩ ጥቅም የሚሰጡ አገልግሎቶችን ለማድረስ ብዙ ሰርቷል፡፡
አርብቶ አደር ሲባል ህይወቱ ከእንስሳቱ ጋር የተቆራኘ በመሆኑ አንድ ቦታ ሰፍሮ የሚቀመጥ ሳይሆን ለእንስሳቱ ውሃን ፍለጋ ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀስ ነው፡ ፡ በክልሉ ደግሞ በብዛት ውሃ ስለሌለ የአርብቶ አደሮችን ውሃ ወዳለበት የመንቀሳቀስ ሂደት ያጎላዋል። በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው እነዚህ አርብቶ አደሮች በምን መልኩ ውሃን ማግኘት ይችላሉ በሚል የዩኒቨርሲቲው መምህራን ባከናወኑት ጥናት አበረታች ውጤት ተገኝቷል፡፡
አርብቶ አደሩ የተረጋጋ ኑሮ እንዲመራና የእርሻ ስራ እንዲያከናውን ከማድረግ አኳያም በአንድ መምህር በተደረገ ጥናት ውሃን ቆፍሮ ከማውጣት ይልቅ እስከ ስምንት ሜትር የሚረዝም ቱቦ በመሬት ውስጥ በማስገባት ውሃን የማውጣት ተግባር ተከናውኗል፡፡ ይሄም በተለይ ፋፈን አካባቢ አርብቶ አደሩ ተረጋግቶ ከመኖሩም ባለፈ ወደከፊል አርሶ አደርነት እንዲሸጋገር አግዟል፡፡
ከዚህ በተጓዳኝ ከ12ኛ ክፍል በዘለለ ትምህርት ማግኘት ያልቻሉ አርብቶ አደሮችን በምን መልኩ መደበኛ ትምህርት እንዲያገኙ ማድረግ ይቻላል በሚል ዩኒቨርሲቲው አርብቶ አደሩን ማስተማር አንዱ ዓላማው አድርጎ ሰባት ማዕከላትን ከፍቷል፡፡ አንደኛው ማዕከል ጅግጅጋ ከተማ ውስጥ ሲሆን፤ ተማሪዎች በማታ፣ በሳምንት መጨረሻ (ቅዳሜና እሁድ) ይማራሉ፡፡
በተመሳሳይ ጎዴ አካባቢ ባለው ማዕከልም የከተማውም ሆነ በአካባቢው ያሉ አርብቶ አደሮች እየተማሩበት ነው፡፡ ቀብሪደሀር፣ ሽንሌና ደገሀቡርም ተጨማሪ ማዕከላት ያሉ ሲሆን፤ በቶጎጫሌ ማዕከልም በተለይ ድንበር ላይ ያለች ከተማ እንደመሆኗ ከክልሉ አርብቶ አደሮች ባለፈም ድንበር ተሻግረው የሚማሩም አሉ፡፡
በተመሳሳይ ክልሉ ሰፊ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በአርብቶ አደሩ በሚደረገው እንቅስቃሴ በሽታዎች ሊከሰቱ፤ አካባቢዎችም ሊጎዱ ይችላሉ፡፡ በዚህም የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ከአጋር ድርጅት ጋር በመሆን የችግሩ ተጋላጭ አካባቢዎችን በመለየት በየሩብ ዓመቱ መድሃኒትና ክትባት የመስጠት ተግባር እያከናወነ ይገኛል፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን እየተከናወነ ያለው ተግባር አራት ዓመት የሆነውና የትግበራው ሁለተኛ ምዕራፍ ላይ የደረሰው ከስዊዘርላንድ መንግስት ጋር በመሆን የተጀመረ ፕሮጀክት ሲሆን፤ ሰው፣ እንስሳቱና ተፈጥሮ አንዱ አንዱን ሳይጎዳ ተደጋግፈው መቀጠል የሚችሉበትን እድል መፍጠር ላይ ያተኮረ ፕሮጀክት ነው፡፡
ይሄን ፕሮጀክት በመተግበር ሂደት ባለሙያዎችን ስዊዘርላንድ በማሰልጠን እነዚህን ሶስት አካላት አቀናጅተው ማገዝ የሚችሉበትን አቅም ፈጥሮ የማሰራት ተግባር የተከናወነበት ነው፡፡ በዚህ ረገድ በተለይ ጎዴ አካባቢ ለሰውም ሆነ ለእንስሳት ክትባት ከመስጠት ጀምሮ ችግኝ በመትከል ጭምር የአካባቢውን የተፈጥሮ ስነምህዳር እስከመጠበቅ የሚደርስ የሚበረታታ ተግባር ተከናውኗል። በሽታ ዎችን ለመለየት ወይም ለመመርመር የሚያስፈልግ የላቦራቶሪ አገልግሎትም ዩኒቨርሲቲው ያመቻቻል፡፡ በጥቅሉ ዩኒቨርሲቲው አርብቶ አደሩን ለማገዝ እነዚህንና ሌሎች በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡
የጥናት ስራዎች ከሼልፍ እንዳይቀሩ
ዩኒቨርሲቲው ጥናቶች እንዲከናወኑ ከማድረግ ባለፈ የተጠኑት በሼልፍ እንዳይቀሩና አርብቶ አደሩ ጋ ደርሰው ሊተገበሩና ወደ ውጤት ሊቀየሩ በሚችሉበት ሂደት ላይም እየሰራ ይገኛል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ጥናቶች በቀላሉ የሚከናወኑ ሳይሆን በብዙ ውጣውረድ ውስጥ ታልፎ ከዳር የሚደርሱ፤ አንዳንዶቹም በተለያዩ መሰናክሎች ምክንያት በመካከል ተቋርጠው የሚቀሩ ናቸው፡፡ ለምሳሌ፣ ዓምና በገጠመው ችግር ዩኒቨርሲቲውንም ሆነ ከተማውን ለቅቀው በወጡ መምህራን ምክንያት የትላልቅ ፕሮጀክቶች ጥናቶች ተቋርጠዋል፡፡ አንዳንዶችም ከሼልፍ ሳይወርዱ ቀርተዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲውም ይሄን ከግምት በማስገባት እስካሁን የተከናወኑ ጥናቶችንና አሁንም እየተሰሩ ያሉ ጥናቶችን የገመገመበት መድረክ አዘጋጅቶ ነበር። በዚህ መድረክም እነዚህን ጥናቶች በምን መልኩ ህዝቡጋ ደርሰው ሊተገበሩ ይችላሉ፤ በሚለው ላይ ያተኮረ ውይይት የተደረገበት ሲሆን፤ ጥናት ከማድረግ፣ ችግሮችን ከመለየት፣ መፍትሄ ከማስቀመጥና ከመ ተግበር ብሎም ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ከማድረግ አኳያ እንዴት መስራት እንደሚገባ አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ ይገኛል፡፡
ይሄን ስራ ለውጤት እንዲበቃ ለማስቻልም የምርምር ዘርፉ በራሱ ምክትል ፕሬዚዳንት እንዲመራ የሚያስችል የአደረጃጀት ለውጥ በማድረግ የጥናትና ምርምር ዘርፉን የማጠናከር አሰራር ተዘርግቷል፡፡ ይህ ዘርፍም ጥናቶች ከተከናወኑ በኋላ በምን መልኩ ህብረተሰቡ ውስጥ ገብቶ ይተገበራል በሚለው ላይ ከአጋሮች ጋር የህብረተሰቡ ችግሮች ተለይተው መፍትሄ የሚያገኙበት እና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነታቸው የሚረጋገጥበት አግባብ ላይ ይሰራል፡፡
ለ2012 ትምህርት ዘመን
ዩኒቨርሲቲው፣ ለ2012 በጀት ዓመት በመማር ማስተማሩ፣ በጥናትና ምርምሩ እንዲሁም በማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎቱ ከእስካሁኑ የተሻለ ተግባርን ለማከናወን ዝግጅቱን እያጠነቀቀቀ ይገኛል፡፡ በዚህም አዳዲስ የትምህርት ክፍሎችንና ፕሮግራሞችን ከመጀመር አንስቶ ለዚህ እውን መሆን ጉልህ ሚና ያለው የሰላማዊ የመማር ማስተማር ድባብን ለመፍጠር የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ ነው፡፡
ለምሳሌ፣ ዩኒቨርሲቲው የምስራቅ አፍሪካ ሕጻናት እድገት ምርምር ተቋም ነው፡፡ ይሄን ታሳቢ ያደረገ ስራ ለመስራት እንቅስቃሴ የተጀመረና በሚተገበርበት ሂደት ዙሪያም አሜሪካ ከሚገኘው ቴክሳስ ዩኒቨርሲቲ ጋር የመግባቢያ ሰነድ የተፈራረመ ቢሆንም፤ ስራውን ለመጀመር የሚያስችል የባለሙያዎች ስልጠና ከመስጠትና ካሪኩለም ከመቅረጽ የዘለለ ስራ አልተከናወነበትም፡፡ በ2012 ግን እንደ ክልል ሞዴል የሚሆን ትምህርት ቤት ለማቋቋምና ለመክፈት እቅድ የተያዘ ሲሆን፤ ቀጥሎ እንደ አገር በኋላም እንደ ምስራቅ አፍሪካ የሚሰራ ይሆናል፡፡
በተመሳሳይ እአአ በ2025 በምስራቅ አፍሪካ የአርብቶ አደርና ከፊል አርሶ አደር የልህቀት ማዕከል ለመሆን ግብ አስቀምጧል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታም ምንም እንኳን አርብቶ አደሩን መሰረት ያደረጉ ስራዎች ቢከናወኑም ያን ግብ ግን ለማሳካት ሊከብድ ይችላል፡ ፡ ሆኖም 2012 በዚህ ላይ የራሳቸውን አሻራ ሊያሳርፉ የሚችሉ ተግባራት የሚከናወኑበት ይሆናል፡፡
ይህ ሁሉ እውን የሚሆነው ግን የዩኒቨርሲቲው ሰላም ሲረጋገጥ እንደመሆኑ፤ ለ2012 ትምህርት ዘመን ሰላማዊ ጉዞም በ2011 ከነበረው ሂደት ልምድ ተወስዶና ችግሮች ተለይተው ትኩረት ተሰጥቶ ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ባለፈ ከፌዴራል፣ ከክልል፣ ከከተማ አስተዳደሩ አመራር አካላት፤ ከዘርፉ ባለድርሻዎችና ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል፡፡
አዲስ ዘመን ነሐሴ 13/2011
ወንድወሰን ሽመልስ