
. የሠራተኛ ማህበሩ ክፍያ «ለሁሉ» ን ተጠያቂ አድርጓል
. የተቋሙ ለውጥ ሀገርና ህዝብ በሚፈልገው ደረጃ አይደለም
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ለተጠቃሚዎች ከሚያቀርበው የኤሌክትሪክ ፍጆታ በ2011 በጀት ዓመት የሰበሰበው ገቢ 35 በመቶ ብቻ መሆኑን መሰረታዊ የሠራተኞች ማህበር አስታወቀ። ገንዘቡ ላለመሰብሰቡ ክፍያ ፋይናንሻል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት “ ለሁሉ” የተባለውን ተቋም ተጠያቂ አድርጓል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መሰረታዊ የሠራ ተኞች ማህበር ሊቀመንበር አቶ አድማሱ ወንድምአገኘሁ በተለይ ለአዲስ
ዘመን እንዳስታወቁት፤ በበጀት ዓመቱ ዝቅተኛ ገቢ ለመሰብሰቡ ዋነኛ ምክንያት የተቋሙን የአገልግሎት ክፍያ ገቢ ለመሰብሰብ ኃላፊነት የወሰደው
የክፍያ ፋይናንሻል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ‹‹ለሁሉ›› የአፈፃፀም ጉድለት ነው። ድርጅቱ ሥራውን ከተቋሙ ወስዶ መሥራት
ከመጀመሩ አስቀድሞ ዓመታዊ ገቢው እስከ 90 በመቶ ድረስ ይሰበሰብ እንደነበር ገልጸው
የ2011 በጀት ዓመት አፈፃፀም ግን 35 በመቶ መሆኑን ተናግረዋል።
65 በመቶ መሰብሰብ የነበረበት የተቋሙ የፍጆታ ገቢ አለመሰብሰቡን የሚያመለክተው ሪፖርት ለማኔጅመንት ቀርቦ መገምገሙን ጠቅሰዋል።
‹‹ቀደም ሲል ተቋሙ ራሱ በሚያስተዳድራቸው ገንዘብ ሰብሳቢዎች አማካይነት ነበር የአገልግሎት ክፍያ የሚሰበስበው›› ያሉት ሊቀመንበሩ የክፍያ ፋይናንሻል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት (ለሁሉ) ኃላፊነቱን ወስዶ ክፍያ ከህብረተሰቡ መቀበል ከጀመረ አንስቶ የገንዘብ አሰባሰቡ ሲያጨቃጭቅ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
‹‹የተሰበሰበው ገንዘብ በውሉ መሰረት እየገባ ነው? ወይስ አይደለም?›› የሚለው ጉዳይ ማህበሩን እና የማኔጅመንት አካላትን ያወዛግብ እንደነበርም ገልጸዋል፡፡ ገንዘቡ በተፈለገው ጊዜ እና የገንዘብ ልክ ለተቋሙ የማይደርስበት አጋጣሚ እንደነበርም አንስተው ቢሰበሰብ እንኳን ምን ያህል እንደነበር የማይታወቅበት አግባብ እንደነበር ይፋ አድርገዋል፡፡
የተቋሙ ሠራተኞች የኤሌክትሪክ ዝርጋታውን ሠርተው ሲያበቁ የአገልግሎት ክፍያውን እንዲሰበስብ ለሌላ አካል መሰጠቱ ተገቢ አለመሆኑንና ይሄንንም መቃወማቸውን ተናግረዋል። ከዚህ ጋር የተያያዘ ጥያቄ እንዳያነሱም ጫና ይደረግባቸው እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡
እንደ ማህበሩ ሊቀመንበር ገለጻ፤ ‹‹ለሁሉ›› የክፍያ ጣቢያ የሰበሰበውን ገንዘብ በምን አግባብ ገቢ ማድረግ እንዳለበት እንዲሁም ክትትል እና ቁጥጥሩን የሚያሳይ ተጨባጭ ውል አልነበረም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የአገልግሎት ክፍያ መሰብሰብ ሥራው ወደ ለሁሉ ሲተላለፍ በምን መንገድ እንደተሰጠ የሚያሳይ ግልጽ ሰነድ በተገቢው መንገድ ማግኘት አልተቻለም፡፡
የሠራተኛ ማህበሩ ሊቀመንበር የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አዲሱ ቦርድ በዚህ እና መሰል ጉዳዮች ላይ ከሠራተኛ ማህበሩ ጋር ተነጋግሮ መግባባት ላይ መድረሱን ተናግረው፤ በውስጥ አቅም ገቢን ለመሰብሰብ እየተዘረጋ ያለው ዘመናዊ አሠራር የተፈጠረውን ችግር ይፈታል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል፡፡ የተቋሙ ለውጥ አገሪቷ እና ህዝቡ በሚፈልጉት ፍጥነት እየሄደ አይደለም የሚል እምነት እንዳላቸው የተናገሩት አቶ አድማሱ ተቋሙን ሪፎርም የማድረግ ሥራ እየተሠራ ቢሆንም የቁጥጥር እና ክትትል መላላት አሁንም ድረስ ይታያል ብለዋል፡፡ ድርጅቱ ከቀን ወደ ቀን አቅሙ ወርዷል ብለው እንደሚያምኑ አልሸሸጉም፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮሙ ዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ ጉዳዩን አስመልክቶ ማብራሪያ እንዲሰጡን በዝግጅት ክፍላችን በኩል ሙከራ ያደረግን ቢሆንም በቅርቡ መገናኛ ብዙሃንን በጋራ ጠርተው ጋዜጣዊ መግለጫ እንሰጣለን በሚል ምክንያት መረጃ ሳይሰጡን ቀርተዋል፡፡ የገቢ አሰባሰቡ 35 በመቶ እንደሆነ በቅርቡ ተሰብስቦ ሪፖርት መቅረቡን ከሠራተኛ ማህበሩ ሊቀመንበር ማረጋገጥ ብንችልም እርሳቸው ግን ሪፖርቱ በማ ኔጅመንት እንጂ በቦርድ አለመጽደቁን ነግረውናል፡፡
የ2011 የኤሌክትሪክ ፍጆታ ገቢ አሰባሰብ ዝቅተኛ ለመሆኑ ዋናው ተጠያቂ ነው ወደተባለ የክፍያ ፋይናንሻል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ”ለሁሉ” ዋና መስሪያቤት በመሄድ ጉዳዩ ከሚመለከተው አካል ምላሽ ለማግኘት ብንሞክርም ኃላፊው ዕረፍት ላይ ናቸው ፤ተወካይም ሆነ ምክትል የለም በሚል ልናገኛቸው አልቻልንም፤ይግኙበታል ተብሎ ከቢሯቸው የተሰጠን የእጅ ስልክም የማይሠራ ሆኖ አግኝተነዋል፤ በዚህም ምክንያት አስተያየታቸውን ልናካትት አልቻልንም።
ጥቅምት 2011 በአዳማ ከተማ ለጋዜጠኞች በተዘጋጀ መ ድረክ ላይ እንደተገለጸው አጠቃላይ የደንበኞች ብዛት 2.9 ሚ ሊየን ሲሆን ከእነዚህ መ ካከል 83 በመ ቶ የመ ኖሪያ ቤት ደንበኞች ናቸው። አጠቃላይ ሽፋኑ 58 በመቶ ሲሆን ኤሌክትሪክ ያገኙ ከተሞች ብዛት 6 ሺ 905 ነው። ዓመታዊ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ በ2010 ዓ.ም 5 ቢሊየን 91 ሚሊየን ብር ነበር ፤ ከታኅሣሥ 2011 ጀምሮ ደግሞ የታሪፉ ዋጋ አራት እጥፍ መሻሻሉ የሚታወስ ነው።
አዲስ ዘመን ነሀሴ 12/2011
ዳግም ከበደ