
• ተቃዋሚዎችና ወታደራዊ ኃይሉ ስልጣን ለመጋራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሱዳን ተቃዋሚዎች ስብስብ ከሆነው የነፃነትና የለውጥ ኃይል አባላት ጋር ትናንት ባደረጉት ውይይት የነፃነትና የለውጥ ኃይል አባላት በሱዳን የይቅርታ እና የአንድነት ባህልን እንዲያዳብሩ መክረዋል፡፡ የሱዳን ተቃዋሚዎችና ወታደራዊ ኃይል ስልጣን መጋራት የሚያስችላቸውን የመጨረሻ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
“ውጤታማ ስምምነት ወሳኝ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ዋናው ፈታኝ ጉዳይ ግን ስምምነቱን ማስቀጠል እና ተግባራዊ ማድረግ ላይ መሆኑን አሳስበዋል፡፡ አባላቱ በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ኢትዮጵያን በመወከል የሱዳን የፖለቲካ ኃይሎች ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ለነበራቸው ሚና ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የነፃነትና የለውጥ ኃይል አባላቱ የተደረሱት ህገ መንግሥታዊ እና ፖለቲካዊ ስምምነቶች ቀጣይነት ላለው ዴሞክራሲ እና ልማት መሰረት ናቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በተያያዘ ዜናም የሱዳን ተቃዋሚዎችና ወታደራዊ ኃይል በመሰረቱት የሽግግር መንግሥት ዙሪያ ስልጣን ለመጋራት የሚያስችላቸውን የመጨረሻ የስምምነት ስነ ስርዓት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና የሌሎች
ሀገራት መሪዎች በተገኙበት ተካሂዷል፡፡
በዚህ ስምምነት መሰረት የሱዳን ተቃዋሚዎችና ወታደራዊ ኃይል ስልጣን እንደሚጋሩ ነው የሚጠበቀው፡፡
ይህም በሀገሪቱ ለበርካታ ወራቶች የቆየውን የፀጥታ እና ህዝባዊ ተቃውሞ ፍፃሜ ያስገኛል ተብሎ እምነት ተጥሎበታል፡፡
በስምምነቱ መሰረት የልዑላዊ ምክር ቤት የሚቋቋም ሲሆን ምክር ቤቱ ስድስት የሲቪል እና አምስት ወታደራዊ አመራሮችን በአባልነት ያካትታል፡፡
የልዑላዊ ምክር ቤቱን ሁለቱ ወገኖች በየሦስት ዓመት እየተፈራረቁ የሚመሩት ሲሆን በዚህ መሰረት ለቀጣይ ሦስት ዓመታት የነፃነትና የለውጥ ኃይል ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሚሾም መሆኑን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በዘገባው አስነብቧል፡፡
አዲስ ዘመን ነሀሴ 12/2011