
አዲስ አበባ፡- የንግድና ባዛር ፌስቲቫሎች ህዝቡ የጋራ መስተጋብር እንዲፈጥር በማድረግ የእርስ በእርስ ትስስርን የሚያጠናክር መሆኑን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው ትናንት በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል የኢዮሀ ኤክስፖ መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት ባዛርና ፌስቲቫሎች የህዝቦች ባህል ጎልቶ ወደ አደባባይ እንዲወጣ በማድረግ በህዝቦች መካከል ከፍተኛ የሆነ መስተጋብር ለመፍጠር ይረዳል፡፡ ፌስቲቫሎች አንዱ የሌላውን ባህል ለማወቅ እንዲሁም የገበያ ትስስርን በማሳለጥ ጉልህ የሆነ ምጣኔ ሀብታዊ ፋይዳ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡
እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፤ ህብረተሰቡ የሚፈልገውን እየሸመተ በሌሎች ባህላዊ ቁሶች እየተደሰተ አባቶቻችን ያወረሱንን የመቻቻልና የአብሮነት እሴቶቻችንን የሚያስቀጥልበት ዋነኛ መንገድ ነው፡፡ እንዲሁም የህዝቦች ባህል እንዲሰፋ፣ ታሪክ እንዲጠነክርና ወንድማማችነትና እህትማማችነት እንዲጎለብት በማድረግ የጋራ ዕሴቶቻችንን ያዳብራል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የማህበራዊ ጉዳዮች አስተባባሪ፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር እንዳወቅ አብጤ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ባዛርና ፌስቲቫሎች አገልግሎት ሰጪዎች ከሸማቹ ማህበረሰብ ጋር ትውውቅ የሚፈጥሩበትና የሸማቹን ፍላጎት የሚያረኩበት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ጤናማና ፍትሐዊ የንግድ ውድድር በማድረግ ያልተገባ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ይረዳል፡፡ እንዲሁም አንድነታችንን አጠናክረን የምንቀጥልበት መንገድ ነው፡፡ መስተዳድሩም እንዲህ ዓይነት ዝግጅቶችን ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢዮሃ አዲስ ኢንተርቴይመንት እና ኤቨንት ባለቤት አቶ ሲራክ ዋሲሁን በዚሁ ወቅት አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለመንግሥት ተማሪዎች ላሰበው ፕሮግራም የሚሆን አስራ ሁለት ሺ ደብተርና ሁለት ሺ እስኪርቢቶ አበርክተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ነሀሴ 12/2011
ሞገስ ፀጋዬ