የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅርቦት ታሪካዊ መነሻ የአጼ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት መገባደጃ ወቅት እንደነበር መዛግብት ያመላክታሉ፡፡ በተለይ 1887 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ጅቡቲ ባቡር መስመር ዝርጋታ ጋር ተያይዞ በወቅቱ ለነበሩት በቁጥር አነስተኛ ተሽከርካሪዎች ፍጆታ የሚሆን ነዳጅ አጂፕ፣ ሼልና ካልቴክስ በሚባሉ የውጭ ነዳጅ አቅራቢ ኩባንያዎች አማካኝነት ነዳጅ በጅቡቲ ወደብ በኩል በሎኮሞቲቭ ተጭኖ ወደ አገር ውስጥ ይገባ የነበረበት ጊዜ ተጠቃሽ ነው፡፡
ይህ ወቅት የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅርቦት ታሪካዊ መነሻ ይሁን እንጂ በተነጻጻሪነት በርካታ መጠን ያለው ነዳጅ ከ1928- 1933 ዓ.ም ፋሽሽት ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት ግዛቷን ለመስፋፋት ያመቻት ዘንድ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን በተለይ ደግሞ መንገዶችን እየገነባች ታንቀሳቅሳቸው ለነበሩ ተሽከርካሪዎች ፍጆታ የሚሆን ነዳጅ በአሰብና ምጽዋ በኩል ታስገባ ነበር፡፡
ከነፃነት በኋላ ደግሞ አዲስ አበባ በማዘጋጃ ምክር ቤት ተደራጅታ ዘመናዊ ቅርጽ ስትይዝና በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ከተሞች ዘመናዊ ቅርጽ እየያዙ ሲመጡ ተሽከርካሪዎች ወደ አገር ውስጥ መግባት ጀመሩ፡፡ ይህንን ተከትሎ የነዳጅ አቅርቦት በዘመናዊና በተደራጀ መልኩ ማስገባት የጊዜው ቁልፍ ጥያቄ ሆኖ ነበር፡፡ በመሆኑም በ1954 ዓ.ም ለአገሪቱ የሚፈለገውን የነዳጅ መጠን ማቅረብ እንዲቻል በአሰብ የነዳጅ ፋብሪካ እንዲገነባ በኢትዮጵያ መንግሥት ውሳኔ ላይ መደረሱን ከኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የተገኙ ታሪካዊ ሰነዶች ያመላክታሉ፡፡
ወደ መንግሥታዊና ተቋማዊ ቅርፅ መሸጋገር
በኢትዮጵያ ነዳጅ የመጠቀምና የማቅረብ ሥራ ከአጼ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት መጨረሻ ጀምሮ የረጅም ጊዜ ታሪክ ያለው ቢሆንም፤ ነዳጅ ለሀገራችን የሚኖረው ጠቀሜታና አስፈላጊነት ደረጃ በደረጃ እየጎላ መጥቶ የነዳጅ አቅርቦት በመንግሥት ተቋም ደረጃ ባለቤት ኖሮት የማከናወኑ ሂደት የተጀመረው በ1956 ዓ.ም ነው፡፡ በዚህ ወቅት በሀገሪቱ የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ ግንባታ ተጀምሮ የፕሮጀክቱ ሥራ ሚያዝያ 30 ቀን 1959 ዓ.ም የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካው በይፋ ተመርቆ ሥራ እንደጀመረና በወቅቱም የነዳጅ ድፍድፍ ከውጭ ሀገር በግዢ በማስገባት ነዳጅ አጣርቶ ለህብረተሰቡ የማቅረብ ሥራ እንደተጀመረ የድርጅቱ የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡
በ1959 ዓ.ም «የኢትዮጵያ ነዳጅ ማጣሪያ አክሲዮን ማኅበር» በሚል ስያሜ ድፍድፍ ነዳጅን በማጣራት የተጀመረው የኢትዮጵያ የነዳጅ አቅርቦት ሥራ በ1969 ዓ.ም «የኢትዮጵያ ነዳጅ ድርጅት» ከዚያም በኢህአዴግ መንግሥት በ1989 «የብሔራዊ መጠባበቂያ ነዳጅ ዴፖዎች አስተዳደር» በሚል ስያሜ በተቋቋሙ ድርጅቶች ሥራውን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ በኋላም የኢትዮጵያ ነዳጅ ድርጅትና የብሔራዊ መጠባበቂያ ነዳጅ ዴፖዎች አስተዳደር አንድ ላይ ተዋህደው በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 265/2004 አማካኝነት የአሁኑን የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ፈጥረዋል፡፡
አቅርቦት
በ2004 ዓ.ም ድርጅቱ እንደ አዲስ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮም የነዳጅ አቅርቦት ሥራውም ድፍድፍ ነዳጅን ወደ አገር ውስጥ አስገብቶ ከማጣራት ሙሉ በሙሉ የተጣራ ነዳጅ ወደ ማስመጣት ብቻ እንዲሸጋገር ተደረገ፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ድርጅቱ የተጣሩ የነዳጅ ምርቶችን በዋነኛነት በጅቡቲ በኩል እንዲሁም የቤንዚን ምርትን ከሱዳን በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡት የተለያዩ የነዳጅ ምርቶች ቤንዚን፣ ነጭ ናፍጣ፣ የአውሮፕላን ነዳጅ፣ ኬሮሲን፣ ቀላልና ከባድ ጥቁር ናፍጣ ሲሆኑ መጠናቸው በየዓመቱ በአማካይ 10 ፐርሰንት እያደገ መጥቶ በአሁኑ ሰዓት የአገሪቱ የነዳጅ ፍላጎት ከ3.5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ ደርሷል፡፡ ይህ ደግሞ በየዓመቱ ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የሚጠይቅ ሆኗል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም የአገሪቱ የነዳጅ አቅርቦት ሥራ መደበኛ ሂደቱን ጠብቆ እየተከናወነ መሆኑንና አቅርቦቱም በበቂ ደረጃ ላይ የሚገኝ መሆኑን የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የንግድ አቅርቦትና ሽያጭ ሥራ አስኪያጅ አቶ አባይነው ሃሰን ይናገራሉ፡፡
የበቂ አቅርቦት-እጥረት እንቆቅልሽ
በቂ የነዳጅ አቅርቦት አለ ይባል እንጅ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዲስ አበባን ጨምሮ በሌሎችም የአገሪቱ ከተሞች የነዳጅ እጥረት ተደጋግሞ ሲከሰት ይስተዋላል፡፡ እጥረቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መጥቶ ሰሞኑን አዲስ አበባን ጨምሮ በክልል ከተሞች የነዳጅ በተለይም የቤንዚን እጥረት ተከስቶ ዋነኛ መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ ለመሆኑ እየቀረበ ያለው የነዳጅ አቅርቦት በቂ ከሆነ እጥረቱ ከየት መጣ?
የድርጅቱ የንግድ አቅርቦትና ሽያጭ ሥራ አስኪያጅ አቶ አባይነው ሃሰን እንደሚሉት የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋናው ኃላፊነቱ ለሀገሪቱ የሚያስፈልገውን የነዳጅ ምርት ፍላጎት ማጥናትና መጠኑንና ጥራቱን ጠብቆ ማቅረብ ነው፡፡ «በዚህ በጀት ዓመትም አቅርቦቱ በትክክል እየተከናወነ ነው፤ አቅርቦት ላይ ምንም አይነት ክፍተት እንደሌለ አይተናል» የሚሉት አቶ አባይነው በዚህ መሰረትም በ2011 በጀት ዓመት ለማቅረብ የታቀደው አራት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ነዳጅ መሆኑን ጠቁመው፣ ከዚህ ውስጥ 489ሺ 534 ሜትሪክ ቶኑ ቤንዚን ነው፡፡ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር አጠቃላይ የነዳጅ አቅርቦቱ የአስራ አንድ በመቶ የቤንዚን ደግሞ አስራ አምስት በመቶ ዕድገት አሳይቷል ይላሉ፡፡
ሽያጭን በተመለከተም ከሐምሌ 2010 እስከ መስከረም 2011 ባሉት ሦስት ወራት በሩብ ዓመቱ በጥቅሉ 957 ሺ17 ሜትሪክ ቶን ተጣራ ነዳጅ ለመሸጥ ታቅዶ909 ሺ 788 ሜትሪክ ቶን ነዳጅ ተሽጧል፡፡ የሽያጭና አቅርቦት ሥራ አስኪያጁ የተሸጠው ነዳጅ የዕቅዱ 95 በመቶ መሆኑንና አፈጻጸሙም ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የስድስት በመቶ ጭማሪ ማሳየቱንና አቅርቦቱም ከዓመት ዓመት እያደገ መምጣቱን ጠቁመው፤ «አቅርቦቱ በበቂ ሁኔታ እየተከናወነ ነው፤ ችግሩ ያለው ስርጭት ላይ ነው» ይላሉ፡፡
ከስርጭቱ ጀርባስ?
አቶ አባይነው እንደሚሉት የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የነዳጅ ምርቶችን ከውጭ ገዝቶ ለነዳጅ ኩባንያዎች የማቅረብና የማከፋፈል እንጅ የተወሰነ በመሆኑ ነዳጅን ከነዳጅ ድርጅት ገዝቶ ለማደያዎች የማሰራጨት ሥልጣን ስለሌለው የስርጭት ሥራው ሙሉ በሙሉ የሚከናወነው አስራ ሦስት በሚሆኑ የነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎች አማካኝነት ነው፡፡ ነዳጅ ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚና ማህበራዊ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው ቢሆንም በሰው ሰራሽ ችግርም ሆነ በሌሎች ምክንያቶች የሚከሰት እጥረት የሚያስከትለው ጉዳት አደገኛ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያዞ በስርጭት ችግር ምክንያት በየጊዜው የሚስተዋለው የነዳጅ እጥረት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከፍተኛ ሁኔታ እየተባባሰ መጥቶ ህብረተሰቡ ለአላስፈላጊ እንግልት እየዳረገውና ከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እያስከተለ መሆኑን ከሰሞኑ በስፋት ተስተውሏል፡፡
ከዚህ የስርጭት ችግር ጀርባ ያለው አካል ማን እንደሆነ የተጠየቁት የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የሽያጭና አቅርቦት ሥራ አስኪያጅ፤ «ድርጅቱ ባደረገው ዳሰሳ ጥናት መሰረት በየቦታው፣ በየሱቁ ቤንዚን በህገ ወጥ መንገድ ሲሸጥ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል» ይላሉ፡፡ በተጨማሪም ሌሎች በአካባቢው ከሚገኙ የምስራቅ አፍሪካ አገራት አንጻር ሲታይ ኢትዮጵያ ነዳጅ የምትሸጥበት ዋጋ በጣም ርካሽ የሚባል በመሆኑ ወደ ጎረቤት አገራት ነዳጅ እየወሰዱ የሚሸጡ አካላት እንዳሉ የሚያሳዩ ግምቶች መኖራቸውን ይገልጻሉ፡፡ እነዚህ ሁለት ችግሮችም በነዳጅ ላይ ለተከሰተው እጥረት ዋነኛ መንስኤዎች ይሆናሉ በሚል ግምት ውስጥ ገብቶ የእጥረቱን ምክንያት ለማወቅ ዝርዝር ጥናት እየተካሄደ መሆኑም ታውቋል፡፡ ለዚህም ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት በተገኙበት ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡ ከጥናቱ ውጤት በኋላም ከስርጭት ጋር ተያያዞ የሚፈጠረው የነዳጅ እጥረት ምንጩ ምን እንደሆነ በትክክል ተለይቶ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚሠራ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 8.2011
ይበል ካሳ