ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ
አንድ የሚጠላ አንድ የሚወደድ።
እንዳለው ደራሲው በመንደሩ በምትገ ኘው መንገድ አላፊ አግዳሚው በዝቷል። በጣም ጠባብ በሆነው መተላለፊያ ወከባ በመሆኑ ቀኑን ሙሉ አያሌ ሰዎች ላይ ታች ሲመላለሱ ይታያሉ። አንዳንዱ ቆሞ ያፋሽካል፤ ሌላው ወዲህ ወዲያ ውር ውር! እያለ የዕለት ጉርሱን ለመፈለግ ይኳትናል። በእርግጥ ቆም ብሎ ሰፈሩን ለመቃኘት የሚሞክር ሰው ካለ የአካባቢውን ገጽታ በሚገባ ይረዳል።
በአካባቢ የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ከመንገዱ ጥበት የተነሳ አንዱ በአንዱ ላይ እየተላተመ መሄድ፤ ከተሽከርካሪ ጋር መጋፋት ብዙም ላያስገርም ይችላል። ምንም እንኳ ይህ ገጽታ የአብዛኞቹ አዲስ አበቤዎች መደበኛ ሕይወት ቢሆንም፤ በዚህ መንደር ግን ለየት የሚያደርገው ተመሳሳይ የኑሮ ገጽታን የተላበሱ ሰዎች መናኸሪያ መሆኑ ነው።
አብዛኞቹ ቤቶች እርጅና የተጫጫናቸው ከመሆኑ የተነሳ የቆርቆሮ ጣሪያዎቻቸው መልክ ወይቦ ሌላ ገጽታ ተላብሰዋል። አንዱ ቤት ዘሞ አጠገቡ ያለው ሌላኛው ዛኒጋባ ቤት ላይ ተደግፏል። እርጅና የከበዳቸው ሳይሆን በፍቅር የተቃቀፉ ይመስላሉ። አንዱ የሚደፋው ቆሻሻ መሬት ለመሬት ተንከባሎ ወደ ሌላኛው ቤት ሰተት ብሎ ይገባል። የሌላኛው ቤት ቆሻሻ ከአንዱ ቤት ይርሳል። አንዱ ቤት ያለው ጫጫታ አሊያም ደስታ ከሚቀጥለው ጎረቤት በሚገባ ይሰማል። የአንዱ ቤት ሚስጥር ከሚቀጥለው በር ላለመድረሱ ማረጋገጫ የለም። የቤቶቹ በእጅጉን ተጠጋግቶ መገንባት ለእነዚህ ነገሮች ምቹ ሁኔታ የፈጠረ ይመስላል። በአካባቢው በአብዛኛው የቀበሌ ቤቶች ይበዛሉ።
በአዲስ አበባ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ሩፋኤል ከሚባለው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በሰሜናዊ አቅጣጫ በ500 ሜትር ርቀት ላይ እነዚህ ሁሉ ገጽታዎች ይታያሉ። የአካባቢው ነዋሪዎች መደበኛ ህይወቱ ጋር አቆራኝቶ ስለሚኖር እምብዛም ስሜት ላይሰጠው ይችላል። ነገር ግን ከሌላ ሰፈር ለሚሄድ ሰው በብዙ መንገድ አግራሞትን የሚፈጥሩ፤ ወይ ኑሮ ጉራማይሌ የሚያስብሉ ክንውኖችን ሊመለከት ይችላል።
የዝግጅት ክፍላችን ከእዚህ መንደር ውስጥ ከአስፋልት ዳር በአነስተኛ የችርቻሮ ንግድ ላይ የተሰማሩ ‹‹ጉሊት›› ንግድ በሚባለው ላይ ኑሯቸውን የሚመሩ ሰዎችን ይቃኛል።
ወይዘሮ በቀለች ኢሶ በመንደሩ በጉሊት ሥራ ላይ ተሰማርተዋል። የትዳር አጋራቸው ይሳካል ብለው በተደጋጋሚ ጊዜ ለሥራ ቅጥር ሞክረው ነበር። ባለቤታቸው ግን ትንሽ ከሰሩ በኋላ ሥራውን ያቋርጣሉ። የጤና እክል ከቤት እንዲውሉ አስገድዷቸዋል። «በቧህ ላይ ቆረቆር» እንዲሉ ነውና በሥራ አጥነቱ ላይ የኑሮ ጫና ተጨምሮ ሶስት ልጆች ላሏቸው ወላጆች በችግር ላይ ችግር ደራርቦባቸዋል።
የመጀመሪያ ልጃቸው 10ኛ ክፍል አርቋጦ ቤተሰቡን ሊረዳ ያገኘውን እየሰራ ይታትራል። ሁለተኛ ልጃቸው ደግሞ 10 ክፍል ተፈትኖ ውጤት አልመጣለትም። ሦስተኛ ልጃቸው ገና 11 ዓመቱ ነው እናም የወላጆቹን እንክብካቤ ይፈልጋል። በአንድም ይሁን በሌላ እነዚህ ሦስት ልጆች በቤተሰብ ላይ የተንጠለጠሉ ናቸው።
አምስት ቤተሰብ አባላት ታዲያ ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ኑሮ እየገፉ በአንዲት ጠባብ ቤት ውስጥ ተከራይተው ይኖራሉ። የቤቷ ኪራይ ደግሞ በየወሩ 2000 ብር ነው። ለእነርሱ ውሎ ማደር ብቻ በቂ ነው። ከዚህ በተረፈ ግን የተንደላቀቀ ሕይወት የሚመኙበት አሊያም ደግሞ የተሻለ ነገር ለማድረግ የሚንጠራሩበት አቅምም ሆነ ፍላጎት የላቸውም፤ ምክንያቱም ኑሮ ጫናዋን አበርትታባቸው ፈተና ውስጥ ናቸውና።
ወይዘሮ በቀለች በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 09 አካባቢ ከ24 ዓመት በላይ ኖረዋል። በስብሰባውም ሆነ ሌሎች ማህበራዊ ህይወት ላይ በንቃት የሚሳተፉና ከሰዎች ባላቸው ግንኙነት ተግባቢ የሚባሉ ሰው እንደሆኑ ስለራሳቸው ይመሰክራሉ። በተለይ ደግሞ 01 በሚባለው አካባቢ ለዓመታት ኖረዋልና፤ ከበርካታ ሰዎችም ጋር ትውውቃቸው የጠነከረ ሆኗል።
በአሁኑ ወቅትም በወረዳ ዘጠኝ ሩፋኤል ቤተክርስቲያን አካባቢ የሚኖሩ ሲሆን፤ ኑሮን ለማሸነፍ ያልሞከሩት ሥራ፤ ያልፈነቀሉት ድንጋይ እንደሌለ በእራሳቸው አንደበት ይናገራሉ። በ1995 ዓ.ም በብሎኬት ምርት ለማምረት በሚል ከ20 ሰዎች ጋር ተደራጅተው ከመንግስትም 20ሺ ብር ተበድረው ሥራ ጀምረው ነበር። በጀሞ ኮንደሚኒየም ሳይት ግን የጀመሩት ስራ እንዳሰቡት አልሄደም። “የማህበሩ ገንዘብ ያዥ አባት፣ ገንዘብ ተቀባይ ደግሞ ልጅ ስለነበሩ ትርፍ ከየት ይምጣ፤ በስተመጨረሻም ትርፉ የት እንገደባ ሳይታወቅ እንዳልሆነ ሆነ። ማህበሩም ተበተነ፤ ለዕዳም ተዳረግን”ይላሉ።
ከዚያም በመቀጠል ኑሯቸውን ለመደጎም ሲሉ ብሩክሊን በሚባል ሆቴል የፅዳት ሠራተኛ ሆነው ተቀጠሩ። ምንም እንኳ ገቢው ጥሩ ቢሆንም ብዙ ዓመታት ከሠሩ በኋላ አቅም አጡ፤ ጉልበት እየከዳቸው ሲመጣ ሥራውን ለማቋረጥም ተገደዱ። የኑሮ ውጣ ውረድን ለመቋቋም ሲሉም ሌላ የሥራ ዘርፍ መረጡ። ጉሊት የሚሰሩ ሰዎችን ተጠግተው ትንሽ እውቀት ከቀሰሙ በኋላ የመንገድ ዳር ንግድ ጀመሩ። ለዕለት የቤት ፍጆታ የሚውሉ እንደ ቃሪያ፣ ጎመን፣ ካሮት፣ ቲማቲም፣ ሽኩርትና የመሳሰሉ አትክልቶችን ይነግዱ ጀመር። በዚህ ሁኔታ እንደምንም ብለው ኑሮን ሲታገሉ፤ የዕለት ጉርሳቸውንም ለመሸፈን ሲታትሩ ይውላሉ።
ባለቤታቸው በተለያዩ ተቋማት የጥበቃ ሥራ ለመቀጠር ሞክረው ነበር፤ ግን አልተሳካላቸውም። ሥራውን ሲጀምሩ ወዲውኑ ይታመማሉ አሊያም በሥራ ቦታ ላይ እንዳሉ ይወድቃሉ። ይህ በመሆኑ ቀጣሪዎች ደስተኛ አልሆኑምና ሥራ አጥ ሆነው ከቤት ከዋሉ ዓመታትን አስቆጥረዋል። ታዲያ ወይዘሮ በቀለች በጉሊት ሆነው ብዙ ነገር በአዕምሯቸው ይመላለሳል። ባለቤታቸው በወቅቱ ምግብ ያስፈልጋቸዋልና፤ ልጆቻቸውም እንዲሁ። የ11 ዓመት ልጃቸው ደግሞ ደብተር፣ እስክቢርቶና ሌላ ወጪ ያሳስባቸዋል። የሁለቱ ልጆቻቸውም የወደፊት እጣ ፋንታ ያስጨንቃቸዋል።
ወይዘሮዋ ጭንቀታቸው በዚህ ብቻ አያበቃም። በአሁኑ ወቅት ሰማይ የነካው የኑሮ ውድነት “ናላዬን እያዞረ ነው” ይላሉ። በወር ለአምስት ቤተሰብ 20 ኪሎ ጤፍ ለመሸመት እጅግ ፈተና ውስጥ ይገባሉ። በአሁኑ ወቅት መንግስት በየወረዳው የሸማቾች ማህበር አቋቁሞ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ለማገዝ ጥረት እያደረገ ቢሆንም፤ በተዘዋዋሪ መንገድ ሃብታሞች የሚጠቀሙበት አሠራር እየተበራከተ መሆ ኑም የኑሮ ጫናዋውን በተፈለገው መጠን ማቃለል እንዳልቻለ አምርረው ይናገራሉ።
በአሁኑ ወቅት የቤት ኪራይ ለመክፈል የሚያዩትን መከራ ቢያውቁትም የእርሳቸው ገቢ ሳይጨምር ግን የቤት ኪራይ ሁሌም መጨመሩ ሌላው አሳሳቢ ጉዳያቸው ሆኗል። በዚህ ሁኔታ ከቤተሰቤ ጋር ጎዳና እንዳልወጣ ሲሉ ፈጣሪያቸውን ይማፀናሉ። ኮንደሚኒየም አገኛለሁ ብለው ከ10 ዓመት በፊት ተመዝግበው ነበር፤ ግን አልሆላቸውም። እስካሁን የቆጠቡትም 10ሺ ብር ብቻ ነው። አቅም ስላጡ ቁጠባውን አቋርጠዋል፤ ግን አንድ ቀን ቤት እንደሚደርሳቸው ተስፋ ያደርጋሉ።
ለዓመታት የቀበሌ ቤት እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፤ ግን አልተሳካላቸውም። በአሁኑ ወቅት በሚኖሩት ኑሮ ፈጣሪን ማማረር አይፈልጉም። ለመንግስትም ለፈጣሪም የም ለምነው ነገር ቢኖር ይህን የኑሮ ውድነት ዝቅ አድርግልን ብዬ ነው ሲሉ ትካዜ እና ፈገግታ በተሞላው ገጽታቸው ታጅበው የውስጣቸውን ስሜት ያስተጋባሉ።
ሌላኛዋ የአካባቢው ነዋሪ ወይዘሮ ፀሐይ ሞላ ደግሞ በቁጥር ከ20 የማያንሱ የጭሳጭስ ዓይነቶችን ይዘዋል። ቀበርቾ ለውጋት ፣ ጡንጅት ለማዕጥንት፣ ዕጣን ለበረከት፣ አደስ ለደስደስ ፣ ከሴ ለቅቤ ማንጠሪያ፣ ቀረፋ ለሻይና ቡና ማጣፈጫ ብሎም ምግብ መሰልቀጫ እያሉ ከዘረዘሩ በኋላ ምርቶቹን ለገበያ አቅርበው እንደሚሸጡ አስረዱኝ። ከዚህም ውጭ እርድ፣ ጥቁር እና ነጭ ዕጣን በርካታ ጭሳጭሶችን ይዘዋል።
ከዓመታት በፊት እንጀራ ጋግረው ነበር ኑሯቸውን የሚደጉሙት። አሁን ግን ዕድሜያቸው ስለገፋ የእሳቱን ኃይል መቋቋም አልተቻላቸውም። ምንም እንኳን ሥራው አዋጭ ቢሆንም ጉልበት ላነሰው ነጋዴ በየቀኑ እንጀራ ጋግሮ መሸጥ ፈተና እንደሆነ ነው የሚናገሩት። እናም ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑኗቸውን በሌላ ዘዴ ለመደጎም አስበው ነበር፤ ከሁለት ዓመት በፊት ጭሳጭስ መነገድ የጀመሩት።
ወይዘሮ ፀሐይ በአሁኑ ወቅት እየሰሩ ባሉት ሥራ ብዙም ደስተኛ አይደሉም። የኑሮ መወደድና የዕለት ገቢያቸው አለመ መጣጠኑ ያሳስባቸዋል። ቤት ተከራይተው፣ ቀለብ ሸምተውና ማህበራዊ ሕይወትን የሚጠይቋቸውን መዋጮዎች በዚሁ ስራ ብቻ አሟልተው ኑሮን መደለል ከብ ዷቸዋል።
“ኑሯችን የቁጥ ቁጥ” ናት የሚሉት ወይዘሮዋ፤ “በእነዚህ ዓይነት ዝቅተኛ ደረጃ ለይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚደጎሙበት አሊያም ደግሞ በቋሚነት የሚረዱበት አሠራር እስከሌለ ድረስ አገሪቱ የድሆች መናኸሪያ ትሆናለች” ይላሉ። መንግስትም ለመሰል ዜጎች የሚሰጠው ድጋፍ እምብዛም እንዳልሆነ ነው የሚናገሩት።
ወይዘሮ ፀሐይ ልክ እንደ ወይዘሮ በቀለች በተደጋጋሚ የቀበሌ ቤት እንዲሰጣቸው ወረዳ 09 ሄደው አመልክተዋል፤ አልፎ ተርፎም ተማፅነዋል፤ በየወቅቱ ሰሚ እንጂ አዳማጭ ጆሮ አላገኙም። ይልቅስ ከእነርሱ ኋላ የሚያመለክቱ ግን ደግሞ በገቢያቸው የተሻለ ደረጃ ላይ ያሉ ለዚያውም ጥሩ ደመወዝ ለሚያገኙ ሰዎች የቀበሌ ቤት ሲሰጣቸው በአይናቸው እየተመለከቱ ብዙ ታዝበዋል። ፍርድ ሲጓደል፣ ድሃ ሲበደል አቤት የሚል ሰው እየጠፋ ነው ሲሉም የኑሮ ውጣ ውረድን፤ የሰዎች አስተውሎት መዛባትን ይኮንናሉ፤ ዋ! ኑሮ፣ ወይ ሰው ሆይ! እያሉ።
አዲስ ዘመን ነሀሴ 11/2011
ክፍለዮሐንስ አንበርብር