ህይወት በብዙ ውስጣዊና ውጫዊ ክሮች ግማድ የተሰራች ጥበብ ናት ። ጥበብን የሚያከብራት፣ በጥሩ አያያዝ ሲኖርባት ያላስተዋለ ደግሞ እንዲሁ ያልፍባታል። ህይወትን በማስተዋል ለመምራት ታዲያ ከጭፍንና ስሜታዊ አካሄድ ራስን በማውጣት፣ የተከደኑ ውስጣዊ ዓይኖቻችንን ለመክፈት መቻል አለብን።
ታዋቂዋ ደራሲ ማያ አንጄሎ፣ “የተከፈቱ ዓይኖች ያሉት ሰው ዛሬን በትናንት ዓይን አያያትም፤ ይልቅስ ዛሬ ላይ ቆሞ ነገውን ማየት የሚችል ነው፤” ትላለች። ዓይኖቻችን ሲከፈቱ ከምናየው የብርሃን ነጸብራቅ እይታ በላይ የማይታየውን ማየት እንችላለን ማለት ነው።
ከሐምሌ ወር መጀመሪያ እስከ ነሐሴ አጋማሽ በሃዋሳ “መልካም ወጣት ለኢትዮጵያ አንድነት” ፣ በሚል መሪ ቃል በምናካሂደው የወጣቶች ስልጠና ላይ አንድ ወጣት ለአምስት የስልጠና ቀናት የሚቆይበት ሥራ እየሰራን ነው። በእነዚህ አጭር የቆይታ ቀናት፣ ውስጥ ወጣቶቹ ከያዙት ይልቅ የለቀቁትን ፣ ከጨመሩት ይልቅ ያጡትን የሚታዘቡበት ዓውድ በመፍጠር ብዙዎቹ ራሳቸውን የሚያዩበት እድል ተፈጥሮላቸዋል።
የተፈጠረው ዕድል እኔን እንደ አዘጋጅ ያሳየኝ ፣ እውነት ቢኖር ሰው ራሱን የሚያይበትና የቆመበትን ሁኔታ የሚገልጽለት አቧራውን፣ በጥቂቱ የሚያራግፍለት ካገኘ ራሱን ማየት የሚችል፣ የሚማር፣ የሚያስተውል፣ የሚታረምና ደስተኛ የሆነ ልዩ ፍጥረት መሆኑን ታዝቤያለሁ። ማንም ሰው በትሁት መልኩ ያለበትን ቦታ ለማየት የተከደነውን ዓይን መክፈት ብቻ በቂው መሆኑን ማየት ይቻላል። እስቲ ጥቂት ምሳሌዎችን ለማንሳት ይፈቀድልኝ።
ወጣቱ፣ በኢትዮጵያ ምእራብ የአስተዳደር ክልል ውስጥ ኗሪ ነው። እንዲህ ሲል ይጀምራል… ጸጸት እያንገላታኝ ነው፤ የመጣሁት። ስለይቅርታ ከተማርኩ በኋላ ይቅርታ ልጠይቅ በማልችልበት ሁኔታ ውስጥ በመውደቄ ቁጭት አንገብግቦኛል። ታሪኩን ከረዥሙ በአጭሩ ሳቀርበው፣ ወጣቱ አንድ ማለዳ ላይ ከአባቱ ጋር ክፉኛ ይጣላል። ከቤት ከወጣ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ሲመለስ ፣ አባቱን ራሱን ሰቅሎ ያገኛል። በድንጋጤ ውስጥ ሆኖ ታናሽ ወንድሙን ይጠራና ከተሰቀለበት ጣራ ላይ ያወርዱትና ያስተኙታል።
ለእናታቸውም ሄደው ጉልት ንግዷ ላይ ሳለች ይነግሯታል ። ስትሮጥ መጥታ እውነቱን ታያለች ። ለእርሷ የነገሯት ግን አባታቸውን በድንገት ቤቱ ውስጥ ወድቆ ማግኘታቸውን ነው፤ ከሰፈር ሰው ጋር ተጯጩሃ ባሏን ትቀብራለች። ትንሽ እህቱ ግን አሁንም አሁንም፣ ደጋግማ ወንድሟን፣ አባቴ ካንተ ጋር ጠዋት ከመጣላቱ ውጭ ያየሁበት የሰውነት ድካምም ህመምም አልነበረም እኮ፤ እንዴት ሊሞት ቻለ? እያለች ትነዘንዘዋለች። በጠየቀችውም ቁጥር ጥያቄዋንም ጸጸቱንም ለመርሳት እየወጣ ይጠጣል፤ ይጠጣል…ትምህርት ቤት ለስሙ ይሄዳል እንጂ፤ አይማርም ፤ ቤተክርስቲያን ለስሙ ይገባል እንጂ፤ አያመልክም ። ወደቤት የመመለስ ሃሳብ ሲመጣበት የአባቱን ፎቶና የእህቱን ጥያቄ ሽሽት ደጅ ለደጅ ሲጠጣ ቆይቶ በውድቅት ሌሊት ይገባል።
ይህ በዚህ እንዳለ፣ በማርሲል ቴሌቪዥን የመልካም ወጣቶችን ምስክርነት ከሰማ በኋላ ግን ቀልቡ መለስ እያለለት፣ ተገኝቼ ብመጣ ይሻለኝ ይሆናል፤ ብሎ ስላሰበ መጥቶ ነው፤ ይህንን የተናገረው።
ጸጸትን ፣ በመጠጥ፣ ንዴትን በመጠጥ፣ ቁጭትን በመጠጥ፣ ጥፋትን በመጠጥ የሚያጠፉ ይመስል ብሶታቸውን በመጠጥ ፈረስ ፣ ጭነው ለማባረር የሚፈልጉ ሰዎች ብዙ ናቸው። ከላይ የጠቀስኩላችሁን ዓይነት ሰዎች በዘመድ መካከል፣ በጎረቤት፣ በትምህርት ቤት፣ በመስሪያ ቤት ውስጥ ሊገጥሟችሁ እንደሚችሉ አያጠራጥርም።
ይህ ወጣት ታዲያ ፣ ለእናቱና ለእህቱ የደበቀውን ምስጢርና በውስጡ የሚገነፍለውን እውነት ለአደባባይ ከማብቃቱም ሌላ ይቅርታ ጠይቋቸዋል። አሁን ለእርሱ ምንም ቢመጣበት እረፍት ነው፤ ለእነርሱ ጥቂት የሚያልፍ ሃዘን መፍጠሩ የማይካድ እውነት ቢሆንም ለጠረጠረ ልብ፣ ማወቅን የመሰለ ብርቱ መድሃኒት ደግሞ የለም፤ በተለይ በጥርጣሬ ትነፍር ለነበረችው እህቱ ትልቅ ግልግል ነው።
ወጣቱ ዓይኖቹን ሊገልጽ ወደቻለበት ስፍራ መጥቶ ይህንን መናገሩ በእጅጉ እንደረዳው አያጠራጥርም። ትንሽ በጎ ቃል በብርቱ ሃዘን ውስጥ የነበረን ልብ መፈወሱ ደግሞ እውነት ነው።
ሌላኛዋ ምሳሌያችን የሆነችው ወጣት ደግሞ፣ ልጅነቷ ውበት ሆኖ ልቧን እፍን ሲያደርጋት የልጅ እግርነት ባሏን በማይረባ ምክንያት ከስሳ ፍርድ ቤት ካቆመችውና ከተፋታች በኋላ ያደነቋት ሁሉ ጥለዋት ሄደው አውላላ ሜዳ ላይ መቅረቷን አውግታናለች።
ራሳችንን ተፈላጊና ተወዳጅ ሌላውን ደግሞ የማይፈለግና ምናምንቴ አድርገን የምናይበትን መነጽር ካላወለቅን በስሜት ጭፍና የምንነዳ ሰዎች እንሆናለን። ይህች ዙሪያ ገባዋን ማጤን ያልቻለች ወጣት ወደቀደመ ቤቷ ባትመለስም ልቧ በመመለሱ ትልቅ እፎይታ ያገኘች ናት ። ማንኛችንም ውስጣዊ ዓይኖቻችንን መክፈት ካልቻልንና ካላስተዋልን ፣ ከእውነት ይልቅ ስሜት ዳኛችን ይሆናል።
አንዳንድ ሰዎች ሃዘናቸው ውስጥ ሲቆዩ ትናንትናቸውን ዛሬ እየኖሩ መሆናቸውን አያውቁም፤ በዚያ ላይ ዛሬያቸውንም እያባከኑ ነው፤ ስለዚህ የትናንት ጸጸትህን በይቅርታና በምህረት ልብ አጥቦ ለነገ ኑሮ ዛሬ መዘጋጀት ምንኛ መታደል ነው። የዚያን ጊዜም የተዘጉ ዓይኖች ወለል ብለው ተከፈቱ፤ ማለት ነው።
ሰው የትናንት ስሜቱን እያስታመመና እሽሩሩ እያለ ሲቆይ የሚረባው ትናንትናውን ለነጠቁት ሁኔታዎችና በነጠቁት ሰዎች ጭንቅላት ውስጥም እየኖረ ነው፤ ያለው ማለት ነው። የልቡና ዓይኖቹ የተዘጉበት ሰው፣ ችግሩን ማስታመም ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ከንፈር መጠጣን የሚናፍቅ ጭምር ነው። ከንፈር መጣጮቹ ሁሉ ግን፣ ያዘኑለት ብቻ ሳይሆኑ ያዘኑበትም ሊሆኑ እንደሚችሉ አያጤንም። ምናልባትም በወደቀበት ሥፍራ በማየታቸው የሚደሰቱም ሊሆኑ ይችላሉ።
ጀርመኖች፣ “ጠላትህን ወንዝ ሲወስደው ስታይ ምራቅህን ጢቅ በልበት” የሚል አባባል አላቸው ይባላል፤ (የድሮዎቹ ይሆኑ ያሁኖቹ አይታወቅም ፤ እንጃ) ምራቅህ ጎርፉን እንዲያብስበት ይሁን የጥላቻውን ደረጃ ከፍ ለማድረግ አይታወቅም፤ ብቻ ይሉታል። ጠላትን ግን መቼም ቢሆን ምራቅህ ጎርፍ ሆኖ አያፍነውም፤ ግን ለማዳን አለማገዙ እውነት ነው። ጥላቻ ለከት ሲያጣ ግን የጎርፍ ላይ ምራቅ መሆኑ አይጠረጠርም፤ ጎርፉን አያበዛውም ፤ በጠላውም ሰው ላይ ክብርን አያመጣም ፤ አንድ ነገር ግን ግልጽ ነው፤ ይህ ሰው ዓይኖቹ ያልተገለጡለት የጥላቻው እስረኛ ነው።
በጥላቻ የታሰረ ሰው፤ ጥላቻውን እየተንከባከበና እሽሩሩ እያለ፣ በውጤቱም ራሱን እያጨሰና እየጨሰ በግለቱ የሚቃጠል ልበ-ዝግ ምስኪን ሰው ነው። ዓይኖቹ ያልተከፈቱለት ሰው፣ ሌላውን በጥርጣሬ ለማየት ቅርብ በመሆኑ ከንግግሩ ውስጥም “ያልጠረጠረ ተመነጠረ” የሚል ሐረግ የማያጣ ነው።
የሥራ ባልደረቦቹ ያነሱትን ሐሳብ ለማጣጣል ምክንያት የሚፈልግ፣ አይቻልም ለማለት ትንታኔና ዝርዝር ሀሳብ ማዘጋጀት ግን የሚችል ፤ ይወድቃል፤ አይሳካም፤ አይሆንም ለማለት የሚፈጥን ሰው ነው፤ ሳይጀምር ይጨርሳል። እንዲህ ዓይነት ሃሳብ የሚያመክኑ ሰዎች ዓይኖቻቸው ካለመከፈታቸው ብዛት በጨለማው ላይ መተከዝ የሚቀናቸው ናቸው። ተጀምሮ ሲደናቀፍ ሲያዩ “አላልኩም ነበር?” ለማለት የሚቻኮሉ ናቸው። ከመጀመር ይልቅ ባይጀመር፤ ከመሞከር ይልቅ ባይሞከር ማለት የሚቀናቸው ናቸውና።
እንዲህ ዓይነት ሰብዕና ያላቸው ሰዎች ፤ ከታች ቆመው ላይ የወጣውን ሰው ከወደቅክ አጥንትህ አይተርፍም ብለው ያስፈራራሉ። ራሳቸው አይወጡም፤ የወጣውንም ሰው እንዲቆይ አይመክሩም፤ ያሳንፋሉ፤ ያስፈራራሉ፣ ያዳክማሉ እንጂ።
እነዚህን ዓይነት ሰዎች፣ ከዓለም ረዥሙና ትልቁን የኤቨረስት ተራራን የሚወጣ ሰው ቢያዩ ቀበጥና በሞቱ የቆረጠ ሥራ-ፈት እንደሆነ ከመናገር ወደኋላ አይሉም። የማይሞከር ነገርን መሞከር የሰውን ልጅ ብቃትና ክህሎት ከፍ እንደሚያደርግና እንደሚያጸና ጉዳይ ሳይሆን የቀበጦች ድርጊያ እንደሆነ ሳያፍሩ ይናገራሉ። ተጨፍነዋልና ሌላው ያየው አይታያቸውም።
ዓይኖቹ የተከፈቱለት ሰው ግን የወጣውን ማበረታታት ብቻ አይደለም፤ የወደቀን ያስነሳሉ፤ ወድቀውም ቢሆን ይነሳሉ፣ የመስራት ብቃትን ያሳያሉ። የህያውነት እንጂ የሞት ምስክር አይደሉም። አያስፈራሩም፤ አያዳክሙም፤ አያሳንፉም፤ ይገፋፋሉ፤ ይገፋሉ፤ አብረውም ይቆማሉ ።
ህይወት በትኩስና ጣፋጭ ኬኮች የተሞላ ሳህን አይደለም፤ በህይወት ማዕድ ላይ መራራና ጎምዛዛ፣ የማይጥምና ስኳር አልባ ቂጣዎች፣ እንዲሁም ትዕግስትን የሚፈታተኑ የማይታኘኩ አንጓ ያላቸውና ጠጣር ነገሮች ያጋጥማሉ። ይህም ማለት ከልደት እስከሞት በምንጓዝባቸው መንገዶች ላይ ከወተት እስከ አጥንት የምንመገባቸው ነገሮች ተዘጋጅተው አይጠብቁንም። ከመጀመሪያዎቹ የህይወት መንገዶች ቀጥሎ ባሉት ሂደቶች ላይ፣ ብዙውን ጊዜ የኑሮ መንገዶቻችንን የመምረጥ እዳው በእኛ ላይ ይወድቃል፤ ስለዚህ ቀጥተኛውን ከጠመዝማዛው፤ ሻካራውን ከለስላሳው ለይተን መምረጥ ሊገባን ይችላል። ያኔም በምናደርገው ምርጫ መልካም ወይም ክፉ አጋጣሚ በህይወታችን ይፈራረቃል።
ባልተከፈቱ ዓይኖች መንገድን ስንመርጥ ፍጻሜያችን አሳዛኝ አንዳንዴም፣ እንጦርጦስ ይሆናል። ይህ እውነት ፣ ብዙ ጊዜ ተፈጽሞ አይተናል። አሳዛኙን አጋጣሚ ወደ አስደሳች ሁነት መለወጥ ሲቻል እንጦርጦሱ ግን የህይወት ዋጋ ስለሚያስከፍል መመለስ አንችልበትም።
ድሮ ከገጠር ወጥታ ከተማ የገባች የሰፈር ልጃገረድ ጫማና ሻሽ ለውጣ ወደባላገር (ገጠር) ስትመጣ ከተማ ውስጥ መንጋ ብር ከመንገድ ዳር የሚታፈስ መስሏቸው ይወጡና የከተማው ህይወት አንጋዶ ሲጥላቸው ለአይናለም የሆነ ቀሚስ እኔን ጠልፎ ጣለኝ ብለው የሚቆጩ የገጠር ባሎቻቸው ኑሮ ማረኝ ብለው የሚመለሱ ብዙዎች ነበሩ።
ዛሬ ደግሞ ከሃገር ቤት ወደባህር ማዶ ስደት የሚሄዱ ሰዎች ሞት ባህር ላይ ብዙ ሰልፍ ይዞ ሲጠብቃቸው ሞትን ንቀውና የሚመኙትን እና የማያውቁትን ህይወት አስበልጠው መጓዝ መቀጠላቸውን ስናስብ ግራ ያጋባናል፤ ግን ይህም ካልተከፈተ ዓይን የሚመነጭ ውሳኔ የሚያስከትለው ጦስ መሆኑ የታመነ ነው።
ወደሳውዲ አረቢያ በስደት ገብተው ወደሃገር ቤት ተጠርዘው (መጠረዝ ማለት ከጠረፍ ውጭ በአየርም ይሁን በምድር ከሃገር አውጥቶ መጣል ነው) ከተመለሱ ኢትዮጵያውያን መካከል አንዷ ስትናገር፣ በአረብ ሃገር የምናየውን ስቃይ ሳስብ መፈጠርህን ነው፤ የሚያስጠላህ ትላለች። ለቀጠሩህ ሰዎች ከማለዳ እስከ እራት ሰዓት ከሰራህ በኋላ እንደ እቃ ዘመዳቸው ቤት ከእራት መልስ ትላክና እስከ ውድቅት ትሰራለህ። እንቅልፍ እንኳን ቢያንጎላጅህ የሚያዝንልህ የለም፤ ዱላና የንቀት ስድብ ነው፤ የሚጠብቅህ ትላለች።
ያ፣ ብቻ እንዳይመስልህ ጥሩ አሰሪ ካላጋጠመህ ለወሲብ ባርነት ሁሉ ትጋለጣለህ ስትል አበሳዋን ታወራለች። እና ይህን እየሰሙ የሚሄዱትን ሰዎች “ምን መልእክት ታስተላልፊላቸዋለሽ” ስላት፣ አይናችሁን ክፈቱና አውጥታችሁ አውርዳችሁ፣ ወስኑ፤ ካለበለዚያ ራስን ማጥፋት ሁሉ ሊያስከተል ይችላል ስትል ነው፤ ያሳሰበችው።
የሚገርመው ነገር ይህንን መሰል ችግር እንዳለ በውል ቢሰሙም በቁጥር ጥቂት የማይባሉ ሰዎች፣ ጨክነው ወደማያስፈልግ ውሳኔ ውስጥ ሲገቡ እናያለን።
አንዳንድ አሳዛኝ ፍጻሜዎችን በስሜት ተመርተን የምናደርጋቸው ናቸውና ውስጣዊ ዓይኖቻችንን ከፍተን ስሜታችንን በመቆጣጠር፣ ራሳችንን መግዛት ስንጀምር እናልፋቸዋለን።
የተከደኑ ዓይኖች ሲገለጡ ደካማው ይበረታል፤ ያዘነው ይጽናናል፤ የተለየው ይሰበሰባል፤ ያኮረፈው ይፍታታል፤ የጠላ ይወድዳል፤ የተጣላ ይታረቃል፤ ያፈረሰ ይገነባል፤ የፈለሰ ይመለሳል፤ ህይወትም ከባዱን ቀለል አድርጋ ታሳየናለች።
በነገራችን ላይ እያንዳንዱ የሰውነት ክፍላችን በምክንያት የተፈጠረ ነው። በተለይ ዓይኖቻችን የማስተዋል ምሳሌዎቻችን ናቸው፤ የሚያዩ ሁሉ አያስተውሉም ይሁንናም፣ በእነዚህ ዓይኖቻችን ያየናቸውን ማናቸውንም ነገሮች በአዎንታዊና በጎ መልክ ለውጠን ለመተርጎም የሚያግዙ ውስጣዊ ዓይኖቻችንን ለመክፈት እንድንችል ተደርገናል። ያንን የሚቆጣጠረው አእምሯችን ነገሮቻችንን በጥበብ እንድናደርግና በሞገስ እንድናከናውን ያሳስበናል። ሁለቱ ሲናበቡ ሥራችን ያማረና ትርጉም ያለው ይሆናል።
ስለአካላት ካነሳን ዘንዳ ጥቂት ላክልላችሁና እንሰነባበት፤ ልክ እንደዓይኖቻችን ሁሉ፣ እጆቻችን የተፈጠሩት በመልካም ሥራ ለመገለጥና ሌሎችን ለማገዝ ና ለመርዳት እንጂ ለመቅጣት፤ ለማሰቃየትና እና ለመዝረፍ አይደለም።
ጆሮዎቻችንም የተሰጡን የሰማነውን ክፉ ለማጋነንና ለክስ ለማቅረብ፣ ያልሰማነውንም እንደሰማን ለመምሰልና ለውሸት ወሬ ስርጭት መፈብረኪያነት ሳይሆን እውነትንና ጠቃሚ የሆነውን ወደውስጣችን በማስገባት ገንቢ ነገሮችን ለማስተናገድ ነው።
እግሮቻችንም ራሳችንን ወደሞት ለማፍ ጠንና ሌሎችን ለማስገባት ሌላውንም ለመርገጥ ሳይሆን የመሻሻልና የእድገት ምልክት የጉዞ አቅጣጫ መጠቆሚያም እንዲሆኑ ነው፤ የተ ፈጠሩት።
አንደበት የተሰጠንም እንዲሁ መልካም፣ ገንቢ፣ የሚያደረጁና የሚያፋቅሩ የሚያስ ተባብሩና የሚያመሰግኑ ሃሳቦችን ለማስተላለፍ እንጂ ለእርግማን፣ ለጸብ፣ ለክፋት፣ ለግጭትና ለማፈናቀል የሚዳርጉ ሃሳቦችን ለመናገር አይደለም ።
የተከደኑ ዓይኖቻችንን በመግለጥና በማስ ተዋል በርካታ መልካምነቶችን ለሰው ልጆች ሁሉ በማድረስ ጊዜውንና ሁኔታዎችን በመልካም ተግባርና ንግግር ጭምር እንድታሳልፉ ተመኘ ሁላችሁ። “ደግ ተመኝ፤ ደግ ይሆንልሃል” ተብሏልና እናንተም ውድ የሃገሬ ልጆች፣ ደግ ያሰማችሁ፣ ደግ ያናግራችሁ፤ ደግ አድራጊ ሆናችሁም፣ በደግ ተገለፁ!!
ህይወት በትኩስና
ጣፋጭ ኬኮች የተሞላ ሳህን አይደለም፤ በህይወት ማዕድ ላይ መራራና ጎምዛዛ፣ የማይጥምና ስኳር አልባ ቂጣዎች፣ እንዲሁም ትዕግስትን የሚፈታተኑ የማይታኘኩ አንጓ ያላቸውና ጠጣር ነገሮች ያጋጥማሉ
አዲስ ዘመን ነሀሴ 11/2011
ከአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ