ዛሬ በተማሪዎች መካከል የእግር ኳስ ጨዋታ ይካሄዳል።ሁሌም ቢሆን በዚህ ሜዳ ላይ የሚኖረው ቆይታ ደማቅ እንደሚሆን ብዙዎች ያውቃሉ።ጨዋታው ባለ ጊዜ በርካቶች ከያሉበት ተገኝተው ቡድኖቻቸውን ይደግፋሉ፤ ተጫዋቾቹን ለማበርታትና የአቅማቸውን ለማድረግም የሚያህላቸው የለም።
ሜዳው በዕድሜ አነስተኞቹን ከታላላቆቻቸው በአንድ ለማዋል ሰበብ ነው።ሁሉም በተገናኙ ቁጥር ደግሞ ቋንቋቸው አንድ ይሆናል።እኩል እየጮሁ እኩል ይደሰታሉ።ስሜትና ሃሳባቸው በአንድ ተጣምሮም ከኳሷ ጋር ወድቀው ይነሳሉ።
አንዳንዴ ቡድኖቹ መሃል የሚኖረው ጨዋታ በጠብና ድብድብ ሊቋጭ ይችላል።በተለይ ደግሞ ውጤቱ ባልታሰበ መንገድ ሲጠናቀቅ ይህ ዓይነቱ አጋጣሚ አይቀሬ ይሆናል።እንዲህ በሆነ ጊዜ አንዳንዶች የመጡበትን ዓላማ ይዘነጋሉ።የፍቅር ቆይታቸውን ቀይረውም በጠብና ድብድብ ማልያ ይታያሉ።
በዚህ ሰዓት ማንም ከመሀል ገብቶ ማረጋጋት ይቸግረዋል።ስድብና መበሻሸቁን ከድንጋይ ውርወራው ተቋቁሞ ራሱን የሚሰጥ ጥቂት ነው።ድንገት ግን ‹‹ፖሊሰ! ፖሊስ!›› የሚለው ቃል ሲሰማ ሁሉም በየመጣበት አቅጣጫ ይበተናል።
አንዳንዴ ደግሞ ድብድቡ ከቡድንም አልፎ በተናጠል ይሆናል።ጥቂት ትዕግስት አልባ ተማሪዎች ጉዳዩን የግል አድርገው ከጨዋታ መልስ ለጠብና ድብድብ ይፈላለጋሉ።ብዙ ጊዜ ይህ ዓይነቱ ግጭት ዕድሜ ኖሮት አያውቅም።ምክንያትና መነሻውን የሚለዩ ገላጋዮች ከመሀል ገብተው ጉዳዩን በአንዴ ይቋጩታል።ጥቂቶች ግን እንዲህ መሆኑን አይፈልጉትም።እንዳሻቸው ተደባድበው ቢወጣላችው ምርጫቸው ነው።
ድሪባ ገመቹ ተወልዶ ባደገበት የሙገር አካባቢ እምብዛም አልቆየም።ወላጆቹ አዲስ አበባ ሲገቡ የእሱም ዕጣ ፈንታ አብሯቸው ሊኖር አስገደደው።ድሪባ የከተማን ህይወት ተላምዶ ከእኩዮቹ ለመግባባት አልገዘገየም።ፈጥኖ አካባቢውን አወቀ።ከትምህርት ቤቱና ከሰፈር ጓደኞቹ ተቀራርቦም ዘመደ ብዙ ሆነ።
ድሪባ፣ ባልንጀሮቹ ሲበዙ ከሁሉም በጎና አጉል ባህሪን ቀሰመ።መልካም ከሚባሉት ጥሩ ምግባርና የትምህርት ትኩረት እንደሚገኝ ገባው።ከሌሎቹ ደግሞ ተቃራኒ ድርጊት ስለመኖሩ አወቀ።እርሱ ግን ከሁለቱም ጎን አልራቀም።ትምህርቱን እያጠና ዓይኖቹ ሌላውንም ቃረሙ።
በእይታው እንደዋዛ ቃኝቶ አልተመለሰም። በዘመነኞቹ ወጣቶች ውሎና አለባበስ ተማረከ።እነሱን ለመምሰል ደረትና ክንዱን ተነቀሰ።በእጆቹ የጎማ ጌጦች ደርድሮም ጸጉሩን አንጨባረረ።አረማመዱ ሲቀየር እንደባልንጀሮቹ መሆኑ ደስ አሰኘው።ኑሮውን ከሽማግሌ አባቱ አድርጎም ትምህርቱን መማር ቀጠለ።
ድሪባ፣ አንዳንዴ ወደ ኳስ ሜዳው ይዘልቃል። ዕድሉን ባገኘ ጊዜም ከቡድን አቻዎቹ ጋር ሆኖ ኳስ ያንከባልላል።የእርሱ ቡደን ሲያሸንፍ ደስ ሲለው፤ ቡድኑ ሲረታበት ይከፋል።ያም ሆኖ ግን በሌሎች ቀናት ተመልሶ ሜዳ ለመግባት ተስፋ አይቆርጥም።
ሁሌም በኳስ ሜዳ ውሎው ጨዋታና ፍቅር ብቻ አያተርፍም።አንዳንዴን ከተቃራኒ ቡድን ተጫዋቾች ጋር ሊጋጭ ይችላል።አጋጣሚው ጉዳዩን ቀላል ካደረገው በይቅርታና በይሁንታ ማለፍ ተለምዷል።ባስ ሲል ደግሞ ተዛዝቶና ለጠብ ተቃጥሮ ቂምን ማሻገሩ ይኖራል።
አንድ ቀን ድሪባ ከቡድን አቻዎቹ ጋር ሆኖ ኳስ ሊጫወት ሜዳ ገባ።የዛንለታው ጨዋታ ከወትሮው ደመቅ ያለ ነበር።ብዙዎቹ ለራሳቸው ቡድን እየጮሁ ድጋፍ ይሰጣሉ።አንዳንዶች ደግሞ ከዳር ቆመው በተመስጦ ያስተውላሉ።ጨዋታው ተጋግሎ ውጥረቱ ሲያይል ሁለቱ ቡድኖች ላለመሸናነፍ የሚያደርጉት ፉክክር ቀጠለ።
ኳሷ መሀል ሜዳ ደርሳ ከጎል ጫፍ ስትቃረብ ከመንገዷ ለመመለስ የሚደረገው ትግል ፈታኝ ሆነ።ሩጫና ርግጫው በወድቆ መነሳት ታጅቦም የተመልካቹን ቀልብ ሳበ።
አሁን ሁለቱ ቡድኖች ለፍጻሜ ተቃርበዋል። ላለመሸናነፍ የሚደርጉት ትግልም ከእልህ ጥግ አድርሷቸዋል።ድሪባ ቡድኑ መልካም ውጤት ይኖረው ዘንድ ጥረቱን ቀጥሏል።በሩጫው መሀል ከፊቱ እየተደቀነ አላላውስ ያለውን ወጣትም ለመቋቋም እየሞከረ ነው።ወጣቱ የተቃራኒ ቡድን ተጫዋች በመሆኑ በልጦ ለማለፍ የማያደርገው የለም።
ድሪባ፣ ተጫዋቹ በስም ‹‹ተረፈ›› እንደሚባል ያውቃል።ከዚህ ቀድሞም በተመሳሳይ ጨዋታዎች ላይ በእኩል ተሰልፈዋል።ተረፈ ዛሬን ብቻ ሳይሆን የዛኔም በጨዋታ መሀል ሲፈታተነው ነበር።ከፊቱ እየቀደመ ጠልፎ ሊጥለው ሞክሯል።መንገዱን እየዘጋና አላግባብ እየጋረደም ጥፋተኛ ሊያስብለው እንደነበር ያስታውሳል።
ተረፈ፣ በዛሬው ጨዋታ ከወትሮው ብሶበታል።የድሪባን እግር ተከትሎ ጠልፎ ለመጣል የሚያደርገውን ሙከራ አልተወም።በእጆቹ እየጎሸመና በትከሻው እየገፋ መፈታተኑን ቀጥሏል።ድሪባ የልጁ ባህርይ ከጨዋታው በላይ ሆኖበት ወስጡ እየተፈተነ ነው።ተደጋጋሚ ትንኮሳውም አለምክንያት ያለመሆኑን ጠርጥሯል።
አሁን የዕለቱ የጨዋታ ጊዜ መጠናቀቁን ዳኛው በፊሽካቸው አረጋግጠዋል።ይህ እንደታወቀ ተጫዋቾቹና ደጋፊዎቻቸው ሜዳውን ትተው ለመበታተን አፍታ አልቆዩም።ተረፈ ግን ይህ መሆኑ ብቻ የበቃው አይመስልም።ዓይኖቹን ከወዲያ ወዲህ እያንከራተተ አንድ ሰው ፈለገ – ድሪባን።
ድሪባን እንዳገኘው ተንደርደሮ አጠገቡ ቆመ።ሁኔታው ለጠብ መሆኑን የጠረጠሩ ልጆች ተሯሩጠው መሀላቸው ገቡ።ችግሩ በግልግል ከተፈታ በኋላ ተረፈ መዛትና መፎከሩን አልተወም።ጥርሱን እየነከሰና ዓይኑን እያፈጠጠ ደጋግሞ ዛተበት።ዛቻና ማስፈራሪያውን የሰሙ አንዳንዶች ድሪባን ከእሱ አርቀው ወሰዱት።ለጊዜው ጠቡ በርዶ ሁሉም ከስፍራው ተበተነ።
በሌላቀን
ድሪባና ተረፈ ዛሬም በኳስ ሜዳው ተገናኝተዋል። ሁለቱም ያለፈውን ቂም አልረሱትም።ባሻገር እየተያዩ ይገለማመጣሉ።ጠብ የሻታቸው ስለመሆኑ ከሁኔታቸው ያስታውቃል። በግልምጫ እየተያዩ ይዛዛታሉ፤በዛቻው መሀልም ጥላቻቸው በግልጽ ይነበባል።
ድንገት ካሉበት ተነስተው መያያዝ ሲጀምሩ ድብድባቸው ለገላጋይ የሚያመች አልሆነም።ላለመሸነፍ የሚደርጉት ትግል የከበደ ሆኖ ለብዙዎች ከአቅም በላይ ሆነ።ይሄኔ ሁኔታው ያስጨነቃቸው አንዳንዶች ፈጥነው ፖሊሶችን ጠሩ።ፖሊሶቹ ጠበኞቹን ይዘው ወደ ጣቢያ ወሰዷቸው።
በዕለት የግጭት ሁኔታ የተመዘገበው የወጣቶቹ ድርጊት በፖሊስ ዘንድ ትኩረት ተችሮት ቀናትን በፖሊስ ጣቢያ እንዲያሳልፉ ሆነ።ሁለቱም በቂ ዋስ አቅርበው ከእስር አስኪፈቱም ምክርና ተግሳጽ እየተቀበሉ ቆዩ።
ጉዳዩ ከግጭት አልፎ ሁለቱንም እስከ ፖሊስ ጣቢያ ቢያደርስም በተረፈ ላይ ያደረው ቂምና ጥላቻ ከድሪባ የተለየ ሆኖ ሰነበተ።አሁንም ከእሱ ጋር ቢጣላና ጅምር እልሁን ቢወጣበት ደስ ይለዋል።ይህን ሲያስብ ደግሞ የሚተናነቀውን ስሜት ለመቋቋም አቅም ያጣል።
የተረፈ ትውልድና ዕድገት አዲስ አበባ ነው።በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤትም ሲማር ቆይቷል።አስራ አንደኛ ክፍል ሲደርሰ ግን ወደቀጣዩ ክፍል መዛወር አልቻለም።ይህ መሆኑ ትምህርቱን በነበረበት እንዲያቋርጥ ሰበብ ሆነ።ዘንድሮ ባልንጀሮቹ አስራሁለተኛ ክፍል ገብተዋል።እሱ ግን ይህን ዕድል ማግኘት አልቻለም።
አንዳንዴ ተረፈ የወጣትነቱን መባከን ሲያስብ ከልቡ ይቆጫል።በተለይ እኩዮቹን ባየ ጊዜ የእነሱ ከትምህርት መዋል ያብከነክነዋል።ይህን ስሜቱን ለመርሳትና ዳግም ላለማሰብ ሲፈልግም ራሱን በመጠጥ እያዝናና በአረቄ መለኪያ ራሱን ሸሽጎ ይውላል።
ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ ደግሞ ተረፈ ከጎኑ ስል ጩቤን አይለይም።በሚገባበት ጠላ ቤትና በሌሎች ስፍራዎች ሁሉ የያዘውን እየነካካ ትኩረት መሳብ ደስ ይለዋል።አንዳንዴ የቀድሞ ትምህርት ቤቱ ብቅ እያለ የቅርብ ጓደኞቹን ያገኛል።ከኳስ ሜዳው ዘልቆም የፍላጎቱን አድርሶ ይመለሳል።
‹‹የማዘር ቤት›› ውሎ
የማዘር ቤት ከዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት በቅርብ ርቀት ላይ ይገኛል።በርከት የሚሉ ተማሪዎችም ባሻቸው ጊዜ ብቅ እያሉ ይጎበኙታል።በዚህ ስፍራ ጠላን ጨምሮ አረቄና ሲጋራ ይሸጥበታል።በተማሪዎች ደንበኝነት ተጨናንቆ የሚውለው ይህ ቤት መዝናናትን አማራጭ ያደረጉ አቻዎች ያዘወትሩታል።ጥንድ እየሆኑ ወደ ጠላው ቤት ጎራ የሚሉት ደግሞ ሳይረግጡት መዋል አይሆንላቸውም።
የማዘር ቤትን ተማሪዎች ከነደንብልብሳቸው ሲገቡበት ማየት ብርቅ አይደለም።ጠላ እየጠጡ አረቄ መጎንጨትና ሲጋራ እያጤሱ ጫት መቃምም የተለመደ ነው።ይህን የሚያውቁ አንዳንድ ሰዎች ድርጊቱን በእጅጉ ይኮንኑታል።ማናቸውም ግን ተማሪዎቹን ወደዚህ ስፍራ እንዳይመጡ የማድረግ አቅማቸውን ማሳየት አልቻሉም።ይህ ቤት አምናና ካቻምና እንደነበረው ሁሉ ዘንድሮም በተማሪ ደንበኞቹ ታጅቦ ዕድሜውን መቁጠር ጀምሯል።
ተረፈ የማዘር ቤትን ከሚያዘወትሩት ደንበኞች መሀል አንዱ ነው።ከሚኖርበት የፈረንሳይ ለጋሲዮን ሰፈር ይልቅ ይህ ጠላ ቤትና የአራት ኪሎ አካባቢ ትርጉም ይሰጡታል።ሁሌም ቢሆን ሲጋራውን እያቦነነ በዚህ ስፍራ መዋልን ምርጫው እንዳደረገ ነው።
ድሪባም ቢሆን የማዘር ቤትን መጎበኘት ደስ ይለዋል።ለእሱ ይህ ቦታ እንደ መዝናኛው ነው።ጠላ ባመረው ጊዜ ከጓደኞቹ ተጋብዞ የሚጋብዝበት ጭምር በመሆኑ ሹልክ ብሎ መምጣቱን ይወደዋል።
ህዳር 25 ቀን 2008 ዓ.ም
ወቅቱ ዓመታዊው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን የሚከበርበት ሰሞን ነው።ጥቂት ቀናት ብቻ የቀሩትን አገራዊ በዓል በድምቀት ለማክበር ተማሪዎቹ ዝግጅቱን የጀመሩት ገና ከወዲሁ ነው።በተለያዩ አልባሳት የተዋቡና ለበዓሉ ልዩ ድምቀት የሰጡ ተማሪዎች የመንገዱን ጫፍ ይዘው ከወዲያ ወዲህ ይላሉ።
በማዘር ቤት የታደሙ ጥቂት ተማሪዎች ደግሞ የተቀዳላቸውን ጠላ እየተጎነጩ ጨዋታና ሳቅ ይዘዋል።አንዳንዶቹ ገና በጠዋቱ በመምጣታቸው ከፊታቸው ሞቅታ ይነበባል።ተረፈ ዛሬም እንደትወሮው ሁሉ ከስፍራው የደረሰው አስቀድሞ ነው።ከተለመደው ቦታ ተቀምጦ ጠላውን እየተጎነጨ ቢያረፍድም በቀላሉ ‹‹በቃኝ›› የሚል አይመስልም።ሲጋራውን በላይ በላዩ እያጤሰ ጠላውን ደጋግሞ ያስቀዳል።
ተረፈ፣ የትምህርት ቤት ጓደኞቹ ስለተቀላቀሉት ፊቱ በፈገግታ ተሞልቷል።የቀድሞውን ከዘንድሮው እያወጋም ከብዙዎቹ ጋር ይሳሳቃል።ጥቂት ቆይቶ ግን ይህን ደስታውን የሚያጠፋ አጋጣሚ ተከሰተ።ድሪባን ከጓደኞቹ ጋር ወደ ማዘር ቤት ሲገባ ተመለከተው።
አሁን ተረፈ ገጽታው እየተለወጠ ነው።ከድሪባ ጋር የነበረውን ሁሉ እያስታወሰ መቁነጥነጥ ጀምሯል። ሁኔታውን ያስተዋለ አንድ ጓደኛው መለዋወጡን አጢኖ ምክንያቱን ጠየቀው።ድሪባን ድንገት በማየቱ ተናዶ እንደሆነ ገለጸለት።ይህ ብቻ አልበቃውም።የእስር ቤቱን ጉዳይ አስታውሶ ይዝትበት እንደነበር ጨምሮ ነገረው።
ጥቂት ቆይቶ ሁለቱ ባላንጣዎች ፊት ለፊት ተያዩ።አፍታ ሳይቆይ ድሪባ የጠጣበትን ሂሳብ ከፍሎ ከማዘር ቤት ወጣ።ተረፈም የያዘውን በቁሙ ጨልጦ ከጀርባው ተከተለው።ድሪባ ወደትምህርት ቤቱ አቅጣጫ እያመራ ነው። ፊትና ኋላ መሄዳቸው እንደቀጠለ ተረፈ በፍጥነት ሮጦ ደረሰበት።
ድሪባ ኮቴውን ሰምቶ ዞር ከማለቱ ተረፈ ከጎኑ የሻጠውን ጩቤ አውጥቶ ግንባሩ ላይ ወጋው።ይህን ያዩ ተማሪዎችና ጥቂት መንገደኞች በድንጋጤ ተጯጩኸው ከመንገዱ ራቁ።ተረፈ ደም ለብሶ መሬት የተዘረረውን ድሪባን በቦክስ እያጣደፈ ዳግም ስል ጩቤውን ሰነዘረ።ትከሻውን ወግቶ ወደ ደረቱ እግርና እጆቹን አልፎም ወደ ብልቱ አለፈ።ስለቱ ከድሪባ አካል ያስተረፈው አልነበረም።
አካባቢው በግርግር እንደተሞላ ‹‹እግሬ እውጪኝ›› ያለው ተረፈ ከስፍራው በፍጥነት ሮጦ ተሰወረ።የሆነውን ሁሉ ያዩ ተማሪዎችና እግረኞች በደም ተነከሮ የወደቀውን ድሪባ ተጠግተው አስተዋሉ።ድሪባ በትንሹ ይተነፍሳል።ተስፋ አልቆረጡም።መኪና ለምነው ወደ የካቲት 12 ሆስፒታል አደረሱት።ተጎጂው የሆሰፒታሉን ደጃፍ እንደረገጠ ህይወቱ አለፈ።
የፖሊስ ምርመራ
ከቀኑ 8 ሰዓት ላይ በስፍራው የደረሰው ፖሊስ በአካባቢው ነበሩ የተባሉትን የተረፈ ጓደኞች ለምስክርነት ወሰደ። በዕለቱ ስለተፈጸመው ወንጀልና ተጠርጣሪውን ለመያዝ የሚስችሉትን ማስረጃዎች አሰባስቦም አሰሳውን ቀጠለ። ተረፈን ከአካባቢው ሳይርቅ በቁጥጥር ስር ለማዋል ጊዜ አልፈጀበትም።
ተረፈ ከፖሊስ ዘንድ ቀርቦ የዕምነት ክህደት ቃሉን ሰጠ።በፖሊስ መዝገብ ቁጥር 519/08 በተከፈተው ፋይልም ወንጀል መርማሪው ምክትል ሳጂን መንግስቱ ታደሰ የሚናገረውን ሁሉ እያሰፈረ ጥያቄዎቹን አቀረበ።ተጠርጣሪው ወንጀሉን የፈጸመው ብቻውን ስለመሆኑ ጠቀሰ።በአባሪ ተባባሪነት በቁጥጥር ስር የዋሉት ባልንጀሮቹም እንዲለቀቁለት ጠየቀ።
ፖሊስ የሰዎችን ምስክርነት ከተከሳሹ ቃል ጋር በማቀናጀት አስረጂ የሚሆኑ ማሳያዎችን ከህክምና ማረጋገጫዎች ጋር አዛምዶ ለዓቃቤህግ አቀረበ።ክሱን በጥልቀት የመረመረው ዓቃቤህግ በተጠርጣሪው ላይ የቀረቡትን ማረጋገጫዎች ከህጉ ጋር አገናዝቦ ለብያኔ ይበቃ ዘንድ በፍርድቤት ክስ እንዲመሰረት አደረገ።
ውሳኔ
ሐምሌ 30 ቀን 2010 ዓ.ም
በዚህ ቀን የተሰየመው የአራዳ ምድብ ችሎት በከባድ ሰው መግደል ወንጀል የተከሰሰውን የተረፈ መኮንን ጉዳይ መርምሮ ጥፋተኝነቱን አረጋግጧል።ተከሳሹም እንዲከላ ከል በተሰጠው ዕድል በድጋሚ ድርጊቱን አምኖ ቃሉን ሰጥቷል።ፍርድቤቱ የተቀመጠውን ሕግ በአግባቡ መርምሮም ተከሳሽን ያስተምራል ያለውን የአስራሰድስት ዓመት ከስድስት ወር እስራት በይኖበታል።
አዲስ ዘመን ነሀሴ 11/2011
መልካምስራ አፈወርቅ