
የዘንድሮው ክረምት ከበድ ባለ ብርድ ታጅቦ የሀገሪቱን ጫፍ እስከ ጫፍ በዝናብ ያጠግባት ይዟል! እሰየው ነው አሁን ባለንበት ደረጃ ዝናብ ማለት ህይወት ነውና። ሰበብ ሳይኖር እንኳ ዋጋው ዕለት ከዕለት እየጨመረ ዜጎቻችንን እያማረረ ያለው ኑሯችን ድርቅ ቢጨመርበት ደግሞ ምን ሊያደርገን ይችላል የሚለውን ማሰብ በራሱ ይዘገንናል።
ወቅቱ ነውና በተለይ ወርሐ ነሐሴ ሰማይ ምድሩ ጨልሟል። ይናፍቀን የነበረው ጉምም አለፍ አለፍ ብሎ እየታየ ነው። የጀመርነውን የአረንጓዴ ልማት አጠናክረን ከቀጠልን ደግሞ ከዚህም በላይ ጉም ከዚህም በላይ ደመናና ዝናብ እንደምንበሸበሽ አያጠራጠርም። በርትተን አሻራችን ማሳረፉ ላይ እንበርታ!
ጨለማው ነሐሴ ጳጉሜን አስከትሎ ሲያልፍ ደግሞ ብርሃናማው መስከረም ብዙ ሀገራዊ ተስፋዎችን ይዞ ብቅ ይላል። የዚህ አዲስ ዓመት መቀበያ ዋና አጀንዳ ደግሞ እርቅና ይቅርታ መሆኑ እየተሰማ ነውና በጣም ደስ ይላል።
የሰላምና አብሮነት መሰረት ነውና ከእርቅ በላይ የሚናፈቅ ምን አጀንዳስ ይኖራል? ለዚህም ነው በርዕሳችን ጨለማ የሆኑትን ቂም በቀልንና ጥላቻን ከነሐሴ ጋር ወደ ኋላ ጥለን የአዲሱን ዓመት መባቻ መስከረምን በእርቅ ልንቀበል እንደርደር ማለታችን!
እርቅ የትናንትን ጠባሳ ሽሮ ነገን ብሩህ ማድረጊያ ፍቱን መድሃኒት ነው። እርቅ የአብሮ የመኖር ሚስጥርና የጀግኖች ተግባር ነው። የክርስትና፣ እስልምናና ዋቄ ፈታም ሆነ ሌሎች እምነቶች ጉልህ ሥፍራ ከሚሰጧቸው ነገሮች ቀዳሚው እርቅ እንደሆነም ከማናችንም የተሰወረ አይደለም።
ዛሬያችንን መልካም አድርገን ለቀጣይ ትውልድ የተሻለች ሀገር ማስረከብ የምንችለውም በረባ ባልረባው እየተነታረክንና ቂም እየቋጠርን ሳይሆን ይቅር እያልንና እርቅ እየፈጠርን መጓዝ ስንችል ብቻ መሆኑም የአደባባይ ሀቅ ነው።
እውነት ነው እንኳን እንደ ሀገር 100 ሚሊዮን ሆነን ይቅርና በየቤታችንና በየተቋማችን ባለን ማህበራዊ መስተጋብር በየቀኑ የሚያጋጩንና የሚያጣሉን ነገሮች ብዙዎች ናቸው። በሌላ አነጋገር ግጭትና የሰው ልጆች ህይወት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው። ስለሆነም እርቅን የህይወት መመሪያ ማድረጉ ቤተሰብን፣ ተቋምንና ሀገርን ለማስቀጠል ቁልፍ ሚና አለው ማለት ነው።
ለዘመናት የዘለቅንበት ፖለቲካችን ደግሞ ከእርቅ ይልቅ ጥላቻን፤ ነገሮችን ተነጋግሮ ከመፍታት ይልቅ ተቧድኖና ነፍጥ መዞ መጠቃቃትን ያስተማረን ነው። የመንግሥትነት ሥልጣን እየተያዘ የመጣውም አንዱ አሸናፊ አንዱ ተሸናፊ በሆኑበት መንገድ ነው። ከዚህም ጋር ተያይዞ ሳንወድ የተጣቡን በርካታ ቁርሾዎችና ግጭቶች ነበሩ፤ አሁንም አሉ።
ይሁንና በተለይም በኢትዮጵያ ከነፈሰው መልካም የለውጥ አየር ጋር ተያይዞ በዶ/ር አብይ የሚመራው መንግሥት ለዘመናት የዘለቅንበትን የቂምና የጥላቻ እርሾ የሚሻር አዲስ መንገድ አስተዋውቆናል። ፍቅር፣ ይቅርታና መደመር የሚል! በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን
ዶክተር አብይ አህመድ የተለያዩ ንግግሮች ውስጥም ይቅር እንባባል፣ እንፋቀር፣ እንደመር ኢትዮጵያን ወደ ቀድሞ ክብሯ እንመልሳት የሚሉ ሐሳቦች ተደጋግመው የሚሰሙትም መጪው ዘመን ብሩህና ተስፋ ሰጪ የሚሆነው ይቅርታ ተደራርገንና ቂምን ሽረን በእርቅ ስንዘልቅ በመሆኑ ነው።
ስለ እርቅ ሲወራ ሊተኮርበት የሚገባው ጉዳይ እርቅ ጽናትን የሚጠይቅና ጀግኖች ብቻ ሊከውኑት የሚችል ቅዱስ ተግባርን መሆኑን ነው። በእርቅ ሂደት ካልነኩኝ አልነካም የሚል ብሂል ቦታ የለውም። ከዚህ ይልቅ ተነክቼም ሆነ ተጎድቼም ይቅር እላለሁ የሚል ጽናትን መላበስን ይጠይቃል።
ስለሆነም ዳመናማውና ጭጋጋማውን ክረምት ሸኝተን ብርሃናማውን መስከረምና መጪውን የ2012 አዲስ ዓመት ለመቀበል ስንንደረደር በጓደኛ፣ በቤተሰብ በተቋምና በአገር ደረጃ ይቅር መባባልን የየዕለት ተግባራችን አድርገን ሊሆን ይገባል እንላለን!
አዲስ ዘመን ነሃሴ 11/2011