ኢትዮጵያ ያላትን የደን ሀብት ጥቅም ላይ በማዋል ሂደት ብዙም ያልተጓዘች ሀገር ናት፡፡ ያለንን የደን ሀብት በወጉ መገልገል አለመቻላችን ደግሞ አንድም ከደን ምርት ማግኘት የሚገባንን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ሲያሳጣን፤ በሌላ በኩል ደግሞ የደን ሽፋናችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ እንዲሄድ ምክንያት ሆኗል፡፡ ደንን በወጉ በማልማትና በመገልገል ኢኮኖሚያቸውን መደገፍ የቻሉ ሀገራትን ተሞክሮ በመውሰድ መተግበር እንደ ሀገር ሊታሰብበት የሚገባ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡
የደን ሀብታችንን በሚገባው መልኩ አልምቶ መጠቀም አለመቻላችን የማያሻማ ሀቅ ነው። ለዚህ ደግሞ የደን ሀብት አጠቃቀም እቅድ አዘጋጅቶ መተግበር ያለመቻሉ እንደ ዋንኛ ምክንያት ይነሳል። ዛሬ በዘርፉ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለማሳደግና ሀገራዊ ገቢን ለማሳደግ በመንግስት በኩል እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል፡፡ ቶሎ ለምርት የሚደርሱትንና በቀላሉ ሊለሙ የሚችሉትን የደን ሀብቶች በመለየት፤ በማልማትና የአጠቃቀም መመሪያዎች በማዘጋጀት ለኢኮኖሚያዊ እድገቱ የሚኖራቸውን ሚና የማሳደግ ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡
በተለይም የቀርከሀ ምርት በአለም ገበያ ተፈላጊነቱ እያገ መሆኑና ጠቀሜታው እያየለ በመምጣቱ እንደ ሀገር ከምርቱ ተጠቃሚ ለመሆን እየተሰራበት ይገኛል፡፡ የቀርከሀን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንደ እድል በመጠቀምና በአለም ገበያ ያለው ከፍተኛ ተፈላጊነት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት አሰጥቶታል፡፡ ምርቱን በማሳደግና ከዚያ የሚገኘው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ማሳደግ ተገቢነቱም አያጠያይቅም፡፡
በአፍሪካ ደረጃ ቀዳሚና ሰፊ የቀርከሀ ሽፋን ያላት ኢትዮጵያ ከምርቱ ተጠቃሚ ሳትሆን ቆይታለች። በሌሎች ሀገራት ከፍተኛ ጥቅም በመስጠት ላይ የሚገኘው የቀርከሀ ምርት ጥቅሙን ለማሰደግ እየተሰራ መሆኑን የአካባቢ የደንና የአየር ለውጥ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡ኮምሽኑ በሀገር ደረጃ ያለውን የቀርከሀ ተክል ሽፋን ለማሳደግና ከምርቱ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ማሳደግ የሚያስችል እቅድ መያዙ ተጠቅሷል፡፡
ሀገሪቱ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2030 ከቀርከሀ ምርት ከሁለት ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የማግኘት እቅድ ያላት ሲሆን በአሁኑ ከአለም ገበያ ያላት ድርሻ 0.2 በመቶ የዘለለ እንዳልሆነ ከኮሚሽኑ የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡ የኮሚሽኑ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ከበደ ይልማ ከዘርፉ የሚገኘው ጥቅም አነስተኛ እንዲሆን ያደረገውን ምክንያት ሲጠቅሱ፤ “የቀርከሀና የሌሎች ደኖች አጠቃቀም እቅድ አዘጋጅቶ መተግበር አለመቻሉ ነው፡፡” ይላሉ።
ምክትል ዳይሬክተሩ፤ የቀርከሀን ተክል ከፍተኛ ጥቅም በመረዳት በመንግስት በኩል ትኩረት ተሰጥቶበት ሊሰራበት የታቀደ መሆኑን ገልፀው፤ በዘርፉ ለሚሰማሩ ባለሀብቶችም ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ አመላክተዋል፡፡ ቀርከሀ ከሚሰጠው ጥቅም አንፃር ‘አረንጓዴ ወርቅ’ በመባል የሚታወቅ መሆኑን የሚናሩት ምክትል ዳይሬክተሩ አቶ ከበደ ይልማ፤ ይህንን አረንጓዴ ወርቅ በማልማት የሀገርን ገቢ ማሳደግ እንደሚቻል ያስረዳሉ፡፡
በሀገር ደረጃ እስከ ሶስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ማልማት የሚቻል መሆኑን የሚገልፁት ምክትል ዳይሬክተሩ፤ አሁን ላይ ማምረት ከሚቻለው እጅግ ያነሰ ምርትና ከሚገባው በታች ጥቅም በመስጠት ላይ የሚገኝ መሆኑን ማሳያዎችን በመጥቀስ ይዘረዝራሉ፡፡
የቀርከሀ ምርት ልማት ስትራቴጂና መርሀ ግብር ረቂቅ ሰነድ ተዘጋጅቶ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት የተደረገበት በመሆኑ በዘርፉ ለመስራት የታቀደው ሰፊ ስራ በተሻለ መልኩ ለመፈፀም ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑ ተገልፃል፡፡ ለዚህ አረንጓዴ ወርቅ ትልቅ ትኩረት መስጠት ለሀገር ኢኮኖሚያዊ ግንባታ የሚኖረው ሚና የላቀ መሆኑም ተጠቁሟል።
መንግስት በቀርከሀ ዘርፍ ምርታማነትን ለማሳደግ ከሚያደርጋቸው ጥረቶች ባሻገር፤ የግል ባለሀብቶች በዘርፉ ለመሰማራትና የተለያዩ የቀርከሀ ምርቶችን ወደውጪ በመላክ እንቅስቃሴ መጀመራቸው መልካም ጅምር ነው፡፡ ባለሀብቶቹ በአለም ገበያ ላይ ለቀርከሀ ምርት ያለውን የፍላጎት ከፍ ማለት ተገንዝበው ወደ ምርቱ መግባታቸው የራሳቸውንና የሀገራቸውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የሚያሳድግላቸው መሆኑን ይናገራል፡፡
በቀርከሀ ተክል ምርት ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች ምርቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተቀባይነቱ እንዳደገና ትርፋማነቱም እያጨመረ መምጣቱን ይናገራሉ። አቶ አዲሱ ሀይሉ ኢሴ የተባለ የቀርከሀ ስራ ማህበር መስራች ናቸው፡፡ በታጠቅ ኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ የሚገኘው የቀርከሀ ምርቶችን በማምረት ላይ የሚገኘው ፋብሪካቸው በዘርፉ ተሰማርቶ ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን ይናገራሉ፡፡
ከዛሬ ስምንት ዓመት በፊት እስቲኪኒና ከሰል ከቀርከሀ ተክል ማምረት መጀመራቸውን ይገልፃሉ። አሁን ላይ በዘርፉ ትርፋማ የሆነው ድርጅታቸው ከቀርከሀ ተክል የተለያዩ ምርቶችን በማምረት ለውጪና ለሀገር ውስጥ ገበያ እንደሚያቀርብ ይገልፃሉ፡፡ ከቀርከሀ ላምኔትድ ቦርድ፣ መጋረጃ፣ ሰንደል፣ ስሊንክ፣ ሰንደልና… የተለያዩ ምርቶችን በማምረት ሂደት ላይ መሆናቸውንም ይገልፃሉ፡፡
በቀርከሀ ምርት ስራ ላይ በመሰማራት ለሀገር ከሚያስገኙት ገቢ በተጨማሪ በፋብሪካው ውስጥ ወጣቶች የስራ እድል እንዲፈጠርላቸውና የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ኑሮ መደጎም እንዳስቻላቸው አቶ አዲሱ ይገልፃሉ፡፡ ከ300 በላይ የስራ እድል የፈጠረው ፋብሪካቸው ለወደፊት የምርት ብዛቱንና ዓይነቱን አስፍቶ ለመስራትና ወደ ውጪ የሚላኩ የቀርከሀ ምርቶች ላይ ትኩረት ለማድረግ እቅድ እንዳለው ያስረዳሉ፡፡
በዘርፉ ሰፊ እድል እንዳለ የሚናገሩት አቶ አዲሱ የቀርከሀ ምርት እያደገ መሄድና አቅርቦቱ ከፍ ማለት ይበልጥ ውጤታማ እንደሚያደርግ፤ ለዚህ ደግሞ በመንግስት እየተሰራ ያለው ስራ አበረታች መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ እንደ ሀገር ቀርከሀ የሚሰጠው ጥቅም ታውቆ መሰራት ይኖርበታል የሚሉት ባለ ሀብቱ፤ ሀገሪቱ ከዚህ ምርት ማግኘት የሚገባትን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለማስፋት አሁን እየተደረገ ያለው ትኩረት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡
በአሁን ወቅት ለቀርከሀ ምርት የተሰጠው ትኩረት ጥሩ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ አዲሱ በተለይም የቀርከሀ ምርቱ ተጠንቶ በምርት ሂደቱ ላይ መሻሻል እንዲኖርና ምርታማነቱን ለመጨመር በእቅድ ደረጃ መዘጋጀቱ የተሻለ ውጤት ያስገኛል የሚል እምነት አሳድሮባቸዋል፡ ፡ ድርጅታቸው ይህንን እድል በመጠቀም የተለያዩ ምርቶችን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ በስፋት እንደሚያቀርብ የገለፁት አቶ አዲሱ በዘርፉ መነቃቃት መፈጠሩን ይገልፃሉ፡፡
አሁን በታጠቅ ኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ ካለው ፋብሪካቸው በተጨማሪ በሀዋሳና በጥቁር እንጪኒ ከተሞች የቀርከሀ ምርት ውስን ስራዎች እንደሚሰሩና ወደፊትም በእነዚህ ከተሞች ፋብሪካዎችን በመትከል የምርት ሂደቱን ማስፋትና በዘርፉ ወደተሻለ ውጤት ላይ ለመድረስ እየሰሩ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
አሁን የአለም ገበያ ለኢትዮጵያ ትልቅ ተስፋ ይዞ መጥቷል የሚሉት አቶ አዲሱ፤ እድሉን ለመጠቀምና በሰፊው አምርቶ ለገበያ ለማቅረብ ማቀዳቸውን ይገልፃሉ፡፡ ለዚህም ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ቀርከሀ በመትከልና ሲደርስ ወደ ምርት ለማምጣት የሚያስችል ስራ ለመስራት አርሲ ዞን ውስጥ ቦታ መጠየቃቸውንና ይህም በሂደት ላይ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ በተጨማሪም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የቀርከሀ ፓርክ ለመመስረትም እቅድ ይዘው እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
እንደ አቶ አዲሱ ሁሉ በቀርከሀ ምርት ተሰማርተው ገቢያቸውን ያሳደጉና የስራ እድል የፈጠሩ ፋብሪካዎች ተበራክተዋል፡፡ ይህ ደግሞ በመስኩ ተሰማርተው ወደ ምርት የገቡ ፋብሪካዎች በቀርከሀ ምርት ላይ ትርፋማ ስለመሆናቸው አመላካች ይመስላል፡፡ ለዚህ ነው በቀርከሀ ምርት ላይ የሚሰሩ ስራዎች ለውጥ በማስመዝገብ ላይ ያሉት፤
በቀርከሀ ምርት አሁን ያለውን ሰፊ የገበያ እድል መጠቀም ሀገራዊ የውጪ ምንዛሬ ከመጨመሩም ባሻገር፤ በዘርፉ ከፍተኛ የስራ እድል መፍጠር የሚያስችልና ለአርሶ አደሩ የገቢ ምንጭ መሆን የሚችል ነው፡፡ በመንግስትና በግል ባለሀብቶች ትኩረት ተሰጥቶበት እየተሰራበት ያለው የቀርከሀ ምርት ለሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገት የራሱ የሆነ ጉልህ ሚና ማበርከት የሚችል በመሆኑ ሊበረታታ የሚገባው ተግባር መሆኑ መጠቆም እንወዳለን፡፡
አዲስ ዘመን ነሀሴ 10/2011
ተገኝ ብሩ (ሻሚል)