ኢትዮጵያ ከዓለም ቡና በማምረት አምስተኛ ስትሆን የአረቢካ ቡና መገኛ ናት፡፡ በዓለም ገበያ የኢትዮጰያ ቡና ተወዳጅ እንደሆነም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ኢትዮጵያ የቡና መገኛነቷን ብቻ ሳይሆን ተያያዥ እሴቶች ባለቤት ብትሆንም ከቡና ምርቷ ተገቢውን ገቢ እያገኘች አይደለም፡፡ ቡና አምራቹና ላኪው በተቀናጀ መንገድ ባለመስራታቸው ከቡና መገኘት ያለበት ገቢም በየጊዜው እያሽቆለቆለ ይገኛል፡፡
ሰሞኑን የቡና ላኪዎች ማህበር ከኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣንና ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ጋር ቡና ወደ ውጭ በሚላክበት አሰራር ላይ ተወያይቷል፡፡
በውይይቱ ከአምራቾች የቡና ላኪዎች ቁጥር መብዛት፣ ከአርሷደሩ ጀምሮ እስከ ላኪው ድረስ ትስስር አለመኖር፣ መንግስት ለአምራቾችና እሴት ጨምረው ለሚልኩ ድርጅቶች በቂ የሆነ ድጋፍ አለማድረግ፣ ቡና ተጭኖ ከአርሷደሩ ሲመጣ መንገዶች ላይ ዘረፋ መስፋፋቱ እንዲሁም የሰው ሀይል እጥረት በተለይ በቡና ለቀማ ወቅት ሰራተኛ አለመገኘት እንደ ችግር ተነስተዋል፡፡
የቡና አምራች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ሁሴን አግራው፤ ከጥራት ጋር በተገናኘ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ኤክስፖርተሩ የሚገዛውን ቡና በሚፈለገው የጥራት ደረጃ ማግኘት አለመቻልና የመኪና ሽያጭ ተብሎ የተጀመረው አሰራር ችግር መፍጠሩን ይጠቅሳሉ፡፡ አብዛኛው መኪና ወደ መጋዘን ከገባ በኋላ ቡና ላኪው መኪናዎቹን ፈልጎ የመላክ አሰራር መስተካከል እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡
በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ልማትና ግብይት ባለስልጣን በኩል ደግሞ የወጣውን ደንብና መመሪያ ማስፈፀም በተለይ ክልል ላይ የብቃት ማነስ እንዳለ ይናገራሉ፡፡ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ላኪዎች የሚገዛበት ዋጋና የዓለም አቀፍ ዋጋ የተለያየ ነው የሚሉት አቶ ሁሴን፤ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ወደ ስራ ከገባ በኋላ ከፍተኛ ችግር እየሆነ መምጣቱን ያስታውሳሉ፡፡ ከቅርብ ጊዜ በኋላ ግን ከዓለም ገበያው ጋር የተናበቡ አሰራሮች እየተዘረጉ እንደሚገኙም ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንድማገኝ ነገራ እንደሚሉት፤ አሁን ያለው ስርዓት የቡና ናሙና ተወስዶ ደረጃ የሚወጣበት አሰራርን የተከተለ ነው፡፡ የወጣው ደረጃ ላይ ቅሬታ ካለ ቀርቦ የሚታይበት ሁኔታም አለ፡፡ አብዛኛው ላኪ ግዥ የሚፈፅመው በመጋዘን ደረሰኝ ላይ መሰረት አድርጎ በመሆኑ የጥራት ችግሮች ይስተዋሉበታል፡፡ አሁን ግን ላኪዎች የመጋዘን ደረሰኝ ብቻ ሳይሆን የሚገዙትን ቡና ናሙና እያዩ እንዳስፈላጊነቱም እየቀመሱ የሚገዙበት ስርዓት ለመፍጠር ታስቧል፡፡
እንደ አቶ ወንድማገኝ ገለፃ፤ አርሷደሩ የሚያመርተው ምርት ምን ያህል እያደገ እንደሆነ መታየት አለበት፡፡ ምክንያቱም የቡና ምርት በየጊዜው ከማደግ ይልቅ ባለበት እየቀጠለ ነው፡፡ ሌሎች አገራት በሚያመርቱት ቡና ላይ ይመራመራሉ፤ በተለይ በሽታ የሚቋቋሙ ምርጥ ዘር የማምጣትና ከአካባቢው ጋር የሚላመድ ዘር የመፍጠር ስራ ይሰራሉ፡፡ የአገር ውስጥ የቡና ሽያጭ ዋጋም አንዳንዴ ኤክስፖርት ከሚደረገው ዋጋ ብልጫ ያሳያል፤ ምክንያቱም የአቅርቦት ሁኔታው ችግር ስላለበት ነው፡፡ ከሚመረተው 450 ሺ ቶን ቡና ውስጥ ወደ 50 በመቶ ለአገር ውስጥ ፍላጎት ይውላል፡፡
የቡና አምራቹ ወደ ማጠቢያ ጣቢያ ቡና ሲወስድ እና አቅራቢዎች ደግሞ ከማጠቢያው ማዕከል ሲወስዱ አንዳንዴ የሚዛን መዛባት እንዳለ የጠቀሱት አቶ ወንድማገኝ፤ ማጠቢያ ጣቢያዎች አካባቢ ያለው ስራ ዘላቂ እንዲሆንና አርሶ አደሩ ቡና ለማምጣት የሚነሳሳው ትክክለኛ መስተንግዶ ሲኖር መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በቀጣይ ሚዛኑን ሁሉም ሰው ሊያምንበት የሚችል አሰራር በማድረግ ሁለትና ከዚያ በላይ የመመዘኛ ማሽኖች እንዲኖሩ ማድረግና ምርት ሲያስረክቡና ሲቀበሉ በቴክኖሎጂ በተደገፈ መንገድ እንዲሆን እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ይጠቅሳሉ፡፡
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ልማትና ግብይት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ በበኩላቸው፤ በ2010 ዓ.ም 238 ሺ ቶን ወደ ውጭ የተላከ ቢሆንም ብዛት ያለው ምርት አሁንም መጋዘን እንዳለ ይናገራሉ፡፡ አብዛኛው የቡና ምርት የጥራት ችግር ያለበት በመሆኑ በቀጣይ ናሙና ታይቶ የማስገባት እቅድ እንዳለ ይጠቅሳሉ፡፡
በመጋዘኖች ውስጥ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ የተከማቸ የቡና ምርት እንደሚገኝ የጠቀሱት ዶክተር አዱኛ፤ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁኑ ዓመት ድረስ ያሉትን ክምችቶች ለመላክ ዝግጅት መደረጉን ይናገራሉ፡፡ የአለም የቡና ገበያ በመቀነሱ ምክንያት ወደ ውጭ የተላኩ ቡናዎች የተፈለገውን ያክል የውጭ ምንዛሬ አለማምጣታቸውንም ይጠቁማሉ፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት በሶስት ወር ውስጥ 68 ሺ ቶን ቡና ለመላክ እቅድ ተይዞ 59 ሺ ቶን ቡና መላኩን በመጥቀስ፤ የተቀረው ቡና በመጋዘን ውስጥ እንደሚገኝ ይናገራሉ፡፡ በቀጣይ ባለስልጣኑ ህገወጥ የቡና ንግድን ለመከላከል፣ በአለም ገበያ ያለው የቡና ዋጋና በአገር ውስጥ ላኪዎች የሚገዙበት ዋጋ ተመጣጣኝ እንዲሆን ማድረግና ያሉ የአሰራር ክፍተቶችን ለመለየት ዝግጅት መደረጉንም ያስረዳሉ፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 8/2011
በመርድ ክፍሉ