በአገሪቱ ንፁህ የመጠጥ ውሃን ለማዳረስ በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡ ነገር ግን አሁንም ቢሆን የንፁህ የመጠጥ ውሃ እጥረት በተለያዩ አገሪቱ ክፍሎች ይታያል፡፡
በመንግሥትም ይሁን በግብረ ሰናይ ድርጅቶች የተሰሩት የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ምን አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ፣ ለምን ያክል ሰው አገልግሎት እንደሚሰጡና ምን ችግሮች እንዳሉባቸው አይታወቅም፡፡ በዚህም የተነሳ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሰሞኑን ከክልል የውሃና ኢነርጂ ቢሮዎች ጋር በመሆን ዘመናዊ በሆነ መንገድ በአገሪቱ ላይ የሚገኙ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ተቋማትን ለመቁጠር እቅድ ይዟል፡፡ ቆጠራው የንጹህ ውሃ ተደራሽነት ምን ያክል እንደሆነ ለማወቅ እንደሚያግዝም ይገመታል፡፡
የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፤ ከስምንት ዓመት በፊት የተሰራው የውሃ ተቋማት የቆጠራ ስርዓት ኋላቀር ስለነበር የተፈለገው መረጃ አለመገኘቱን ያስታውሳሉ፡፡ በመጠጥ ውሃና ሳንቴሽንም አገራዊ መረጃ ለመሰብሰብ እንዲቻል ዘመናዊ የሆነ መረጃ አሰባሰብ ዘዴ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት መደረጉንም ይጠቅሳሉ፡፡ በዘመናዊ መንገድ የተገኘው መረጃ ላይ በመመርኮዝ አገራዊ የመጠጥ ውሃ ተደራሽነት ምን ደረጃ ላይ እንዳለና ወደፊት የሚሰሩት እቅዶች እውነተኛ መረጃ ላይ የተመረኮዙ እንዲሆኑ እገዛ እንዳለው ሚኒስትሩ ይናገራሉ፡፡
እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ፤ ቀደም ባለው ጊዜ መረጃዎች በበቂ ሁኔታ ባለመምጣታቸው በአገር ደረጃ የመጠጥ ውሃና ሳንቴሽን መሰረተ ልማቶች በግምት ወደ 600ሺ ይደርሳሉ ተብሎ እንዲቀመጥ አድርጓል፡፡ አስፈላጊ መረጃዎች በትክክል ባለመታወቃቸው በየአካባቢው ያለው የውሃው መጠን፣ ውሃው ለስንት ሰው ይዳረሳል፣ ጥራቱ ምን ያክል ነው እና የውሃ መሰረተ ልማቱ ምን ደረጃ ላይ እንዳለ አይታወቅም፡፡
በአሁን ጊዜ በሁሉም አካባቢዎች የሚገኙ የውሃ ተቋማት ብልሽት በሚገጥማቸው ጊዜ በወቅቱ ስለማይታወቅ በፍጥነት ጥገና ማካሄድ አይቻልም የሚሉት ሚኒስትሩ በዚህ የተነሳም የየአካባቢዎቹ ነዋሪዎች በውሃው እጥረት ችግር ለረጅም ጊዜ እንደሚቆዩ ያስረዳሉ፡፡ ዘመናዊ የመረጃ ስርዓት ከሌለ ጉድለቱን ማወቅ እንደማይቻልና የአገሪቱ የውሃ አቅርቦት የት ደርሷል የሚለውን ለማየት ዘመናዊ የመረጃ አሰባሰብ ዘዴ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡
በአገሪቱ ዘመናዊ በሆነ መንገድ የውሃ ተቋማት ቆጠራ ለማካሄድ ሦስት ሺ 924 ታብሌቶችን መገዛቱን በመጥቀስ፤ በቅርቡ ወደ ክልሎች እንደሚሰራጩም ይጠቁማሉ፡፡ የተገኘው መረጃው በትክክል ተመዘግቦ ወደ አንድ ቋት እንዲገባ በማድረግ ያሉትን መልካም ስራዎችና እጥረቶችን ለመለየት እንደሚያስችል ይናገራሉ፡፡ በምሳሌነትም በገጠር አካባቢ የሚገኝ የጉድጓድ ውሃ ከተቆጠረ በኋላ ከጉድጓድ ውሃው ምን ያክል ሰው ተጠቃሚ እየሆነ እንዳለና ያሉበትን እጥረቶች ለይቶ ለማወቅ መረጃው አስፈላጊ መሆኑን ያብራራሉ፡፡
እንደ ሚኒስትሩ አባባል፤ ለሙከራ በድሬዳዋና በሐረር ከተሞች ቆጠራው የተሰራ ሲሆን በከተሞቹ ያሉ መረጃዎች የተሰበሰቡት በአጭር ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ በሌሎች አካባቢዎች ቆጠራውን ለማስጀመር በተያዘው ሳምንት የአሰልጣኞች ስልጠና ይሰጣል፡፡ ስልጠና የወሰዱት አሰልጣኞች በክልሎች ውስጥ ቆጣሪዎችን በማሰልጠን ከታህሳስ 22 ቀን እስከ ጥር 6 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ አጠቃላይ ቆጠራ ይደረጋል፡፡ ለአጠቃላይ ስራው 100 ሚሊዮን ብር ተመድቧል፡፡
የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ደኤታ ዶክተር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ እንደሚሉት፤ ቆጠራው በሚካሄድበት ወቅት በአንዳንድ አካባቢዎች የፀጥታ ችግርና የሀይል መቆራረጦች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ የፀጥታ ችግር ያለበት አካባቢ እንደ አማራጭ የተያዘው ለጊዜው ከቆጠራ ውጭ ማድረግና አካባቢው ወደ መረጋጋት ሲመጣ ቆጠራ ማካሄድ ነው፡፡ የፀጥታ ችግር የሌለባቸው አካባቢዎች ላይ ቆጠራው እንዲሰራ ይደረጋል፡፡ ቀለል ያለ የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ደግሞ የክልል አስተዳደሮች ጸጥታውን እንዲያስጠብቁ ኃላፊነት የሚሰጥ ሲሆን የቆጠራ ባለሙያዎችና የፀጥታ አካላት አብረው የሚሰሩበትን ሁኔታ ለመፍጠር ውይይት ይደረጋል፡፡
በሶማሌ ክልል የውሃ መሀንዲስ አቶ መሀመድ አህመድ እንደሚናገሩት፤ ለመጀመሪያ ጊዜ በቴክኖሎጂ የታገዘ የውሃ፣ የትምህርትና የጤና ተቋማት ቆጠራ የተደረገው በሶማሌ ክልል ነው፡፡ ክልሉ ከፍተኛ የቆዳ ስፋት ቢኖረውም የመንገዶች አለመመቻቸትና የኤሌክትሪክ ሀይል በየወረዳዎቹ አለመኖር ችግር ፈጥሮ የነበረ ሲሆን ችግሩን ለመፍታትም መኪናዎችን በኪራይ በማዘጋጀትና ሁለት የሞባይል ባትሪ በመስጠት ቆጠራው ተከናውኗል ብለዋል፡፡ ከተገኘው መረጃ የታየው የውሃ ተደራሽ ችግር፣ የውሃ ጄኔሬተሮች እጥረትና የውሃ ማስተላለፊያዎች ባለመኖራቸው በክልሉ የውሃ ተደራሽነት ዝቅተኛ መሆኑን ያሳያል ብለዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 8/2011
መርድ ክፍሉ