አቶ ዮናስ ካሳሁን ይባላሉ፤ አዲስ አበባ ተወልደው ቢያድጉም፤ ረዥሙን ጊዜያቸውን በጀርመን አገር ኖረዋል፡፡ በጀርመን አገር ያፈሩትን ጥሪትም ቋጥረው ወደኢትዮጵያ በመምጣት በተለያዩ ኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡
ሆኖም በዚህ ወቅት ግን ኢትዮጵያ እንጂ የተወለዱባትን አዲስ አበባን ወይም የዘር ግንዳቸውን ቆጥረው ኦሮሚያ ላይ ነው ኢንቨስት የማደርገው አላሉም፡፡ ምርጫቸው ራሳቸውንም ሆነ አገርና ህዝብ ሊጠቀም የሚያስችላቸው የኢንቨስትመንትና ስፋራ ነበር፡፡
በዚህም አንደኛ፣ በአገሪቱ የመሰረተ ልማት ግንባታ ውስጥ ያለውን ክፍተት ለመሙላት የድርሻቸውን መወጣት የሚያስችላቸው የኮንስትራክሽን ድርጅት ለማቋቋም፤ ሁለተኛም፣ በኢትዮጵያ ያለውን እምቅ ሀብት ለመመልከት በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚንቀሳቀሱ የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ጎብኚዎች ማረፊያ የሚሆኑ የሪዞርትና ሆቴሎች ዘርፍ ተሰማርቶ ለመስራት ይወስናሉ፡፡
አስበውም አልቀሩ “ፍሪዳ” የተሰኘው የኮንስትራክሽን ድርጅት አቋቁመው የኮንስትራክሽን ስራቸውን ጀመሩ፡፡ ለሆቴልና ሎጅ ኢንቨስትመንታቸውም የቱሪዝም ሀብቱና ፍሰቱ ኖሮ ይሄን ጎብኚ ማስተናገድ የሚችሉ ሆቴሎችና ሎጆች የሌሉባቸውን አካባቢዎች ለዩ፡፡
በዚህ ሂደት በሎጅ ደረጃ ወንጪን፤ በሆቴል ደረጃ ደግሞ ጅግጅጋን ይመርጣሉ፡፡ በወንጪ ለሚያስገነቡት የ700ሚሊዬን ብር የሪዞርት ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ይጀምራሉ፤ በጅግጅጋም ተግባራዊ ሊያደርጉ ያሰቡትን የመነሻ ግምታዊ የኢንቨስትመንት ወጪው 193 ሚሊዬን ብር የሆነን ባለአምስት ኮከብ ሆቴልን ለመገንባት ቦታ ተረክበው ከሁለት ዓመት በፊት ወደግንባታ ይገባሉ፡፡
አቶ ዮናስ እንደሚሉት፤ ብዙ ሰው ወደ ጅግጅጋ ሲባል ይፈራል፡፡ ይህ ደግሞ አካባቢውን ቀርቦ ካለማየት የመነጨ ሲሆን፤ ቀርቦ ላየው ግን አገሩም ለኢንቨስትመንት አዋጪ፤ ህዝቡም ሰው አፍቃሪና ወዳድ፣ ሰላማዊና እንግዳ ተቀባይ ነው፡፡ እርሳቸውም በሆቴል ዘርፉ ጅግጅጋ ኢንቨስት ለማድረግ ሲወስኑ ከርቀት ሆኖ የሚባለውን ከመስማት ይልቅ ቀርቦ ማየትን፤ አካባቢን ወይም የትውልድ ቦታን በማልማት ስሜት ሳይሆን የራስን፣ የህዝብና የአገርን ተጠቃሚነት ሊያረጋግጥ በሚችል አዋጪ ስፍራ ሀብትን ፈሰስ ማድረግን መርጠው ነው፡፡
በዚህ መልኩ ወስነው ወደ ግንባታ በመግባት ስራውን በማፋጠን ላይ እያሉ ግን ያልጠበቁት ክስተት ተፈጠረ፡፡ ይሄም አምና በዚህ ወቅት በጅግጅጋ ብሎም በሶማሌ ክልል ተፈጥሮ በነበረው የጸጥታ ችግር ነበር፡፡
ይህ ወቅት ለእሳቸውም ሆነ በአካባቢው ላለው ህብረተሰብ አስቸጋሪ ሆኖ ያለፈ ሲሆን፤ በዚህ ምክንያትም የሆቴል ግንባታ ስራቸው ከአንድም ሁለት ጊዜ ለመቋረጥ በቃ፡፡ ይሁን እንጂ በክልሉ በተወሰደው የማረጋጋት እርምጃ ሁኔታዎች ወደነበሩበት ሲመለሱ ዳግም ግንባታውን መቀጠል ችለዋል፡፡
ሰላም ሳይኖር ሲቀር በኢንቨስትመንት ሂደት ብዙ ነገር እንደሚናጋ የሚናገሩት አቶ ዮናስ፤ ሲጀምሩ በ193 ሚሊዬን የኢንቨስትመንት ወጪ ይጠናቀቃል ብለው ያሰቡት የሆቴል ግንባታ በተፈጠው ችግርና ከዚህ ጋር ተያይዞ በታየው መጓተት ምክንያት በተፈጠሩ የግንባታ ወጪዎች መናር ለመጠናቀቅ እስከ 300 ሚሊዬን ብር ሊፈጅ እንደሚችል ለአብነት ያነሳሉ፡፡
ሆኖም እንዲህ አይነት ችግር ሲፈጠር ፈርቶ ማፈግፈግ ወይም ሌላ ነገር ማድረግ ሳይሆን፤ የህዝቦችን ትስስርና ግንኙነት የሚያጠናክሩ እንዲህ አይነት የኢንቨስትመንትና ንግድ ስራዎችን አስፋፍቶ መስራት ተገቢ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ምክንያቱም በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች መሳተፍ ሲቻል በተለያየ አግባብ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ማጠናከር፤ የጋራ ልማትና ተጠቃሚነትንም ማሳደግ ይቻላል፡፡
ይሄን አምነው በመንቀሳቀሳቸውም ሲጠናቀቅ ለ300 ሰው የስራ እድል ይፈጥራል የተባለለትን እና 94 የተለያየ ደረጃ ያላቸው አልጋዎችን፣ ስድስት ያክል የስብሰባ አዳራሾችን፣ ባዝና ስቲምን ጨምሮ የተለያዩ አገልግሎት የሚሰጡ ክፍሎች የያዘው የሆቴል ግንባታን ቀን ከሌት በመስራት በቀጣይ አስር ወራት አጠናቅቆ ለአገልግሎት ለማብቃት እየተጉ ነው፡፡ ይህ ሆቴል ሲጠናቀቅ ለጅግጅጋ ከተማ የሆቴል ዘርፍ ትልቅ አቅም እንደሚሆን በመጠቆምም፤ እርሳቸው አገርና ህዝብን እንጂ ብሔርን ወይም የትውልድ ቦታን አስበው እንዳልሰሩ ሁሉ ሌሎች ባለሃብቶችም በዛው ልክ እንዲሰሩ መክረዋል፡፡
በክልሉ ልማት መፋጠን ውስጥ የህዝብ ሀብት የሆነውን የባህል እሴት የማልማት ስራ እየተከናወነ ቢሆንም ይህ ብቻውን ግን ባህሉ እንዲለማም ሆነ ኢኮኖሚው ውጤት እንዲያስገኝ እንደማይችል የሚናገሩት ደግሞ፣ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ሃላፊ ወይዘሮ ሂቦ አህመድ ናቸው፡፡
እርሳቸው እንደሚሉት፤ የባህል ልማት ብቻውን ውጤት አይደለም፡፡ የለማ ባህል ሊጎበኝና ገቢ ሊያስገኝ የሚችለው በባህሉ አካባቢ የቱሪስት ማረፊያ ሲኖር ነው፡፡ ጅግጅጋ ደግሞ ምንም እንኳን በፍጥነት እያደገች ያለች ከተማ ብትሆንና ሆቴሎችም እያደጉ ቢሆንም፤ ያለ በቂ ግንዛቤ ሆቴሎችን ከመስራት ያለፈ በሆቴሎቹ ጥሩ አገልግሎት ከመስጠት አኳያ ችግሮች አሉ፡፡
እነዚህ ሆቴሎች የኮከብ ደረጃ እንኳን የሌላቸው ሲሆን፤ ይሄን ችግር ለመፍታትም የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠት የመደገፍ ስራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ በዚህ ዓመትም አንድ ሆቴል እንዲገመገም የተደረገ ሲሆን፤ በቀጣይም ሌሎች ሆቴሎች በዚህ መልኩ እንዲሄዱ ይደረጋል፡፡ የክልሉን የቱሪዝም ፍሰት ከማሳደግ አኳያ በእነዚህ ሆቴሎች አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ድክመት መኖሩ ደግሞ ለሚገለገልባቸው ጎብኚ የቆይታ ጊዜ ላይ ተጽዕኖ ስለሚፈጥር ድጋፍና ክትትሉ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
በዚህም በዚህ ዓመት ስራ አስኪያጆችን፣ አስተናጋጆችንና ምግብ አብሳዮችን ጨምሮ 220 የሚሆኑ ባለሙያዎችን ለማሰልጠንና ለ11 ሆቴሎች ለማከፋፈል ታቅዷል፡፡ ይህ ተግባርም በቀጣይም ባለሃብቶች ገንዘባቸውን ከማውጣትና ሆቴሎችን ከመገንባት ባለፈ ምን አይነት አገልግሎት መስጠት እንደሚገባቸውና ለራሳቸውም እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው አውቀው እንዲሰሩ የሚያደርግ ሲሆን፤ የሆቴል ዘርፉን ለማሳደግ ባለሃብቱ በተለይም ኢትዮጵያዊያን የድርሻቸውን ሊያበረክቱ ይገባል::
በክልሉ የኢንቨስትመንት ኤጀንሲ የፕሮሞሽን ኬዝ ቲም መሪ አቶ ሁሴን አብዲ፣ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ከ2003 ዓ.ም በፊት በክልሉ የነበረው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ አነስተኛ ቢሆንም በኋላ ግን መነቃቃት አሳይቷል፡፡ ሆኖም በሚፈለገው ልክ ያልሄደ ይልቁንም በአመዛኙ በኢንቨስትመንት ስም የተወሰዱ መሬቶች ታጥረው የተቀመጡበት ወቅት ነበር፡፡ በመጠኑም ቢሆን የክልሉ ተወላጆች የሚያከናውኑት ኢንቨስትመንት የተሻለ እንቅስቃሴ የነበረው ሲሆን፤ የውጭ ባለሃብቶች በአንጻሩ ያን ያክል ውጤታማ ተግባር ያላከናወኑበትም ነበር፡፡
በሂደት ግን የክልሉን የሰላም ሁኔታ፣ የኢንቨስትመንት አመቺነትና በመንግስት በሚደረገው ድጋፍ ዙሪያ የማስተዋወቅ ስራ በመከናወኑ የክልሉ ተወላጆችም ተሳትፎ እያደገ፤ የውጪ ባለሃብቱም እየገባ ሄደ፡፡ በተለይ ባለፈው በጀት ዓመት በርካታ የውጭም የአገር ውስጥም ባለሃብቶች ወደክልሉ ገብተው በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ተሰማርተዋል፡፡በውሃ፣ በፓስታና በመኮረኒ፣ በዱቄት፣ በዳቦ፣ በፋይበር ግላስና ሌሎችም ፋብሪካዎችን የማቋቋም፤ የዋቤ ሸበሌና ሌሎችም ወንዞችን ተከትሎ የግብርና ኢንቨስትመንትን የመቀላቀል አዝማሚያዎች አድገዋል፡፡
ከዚህ ባለፈ ክልሉ ሰፊ የባህል ሀብት ያለውና የንግድ ማዕከልም እንደመሆኑ በርካታ ሰዎችና ቱሪስቶች የሚመጡበት እድል ሰፊ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የሆቴል ኢንቨስትመንቱ ሊጠናከር ይገባዋል፡፡ እስካሁን ግን በአመዛኙ ሆቴሎች ያሉት ጅግጅጋ ላይ እነርሱም አብዛኞቹ በክልሉ ተወላጆች ሲሆን፤ ከእነዚህም በዳያስፖራው የተሰራውም ከሶስትና አራት አይበልጥም፡፡የሌላ ክልል ተወላጆችም ቢሆኑ ከእርሻው ኢንቨስትመንት ያለፈ ብዙም ተሳትፎ የላቸውም::
የውጪ ባለሃብቱም ያን ያክል የሚታይ ስራ ሲያከናውኑ አይታይም፡፡ ሆኖም የሆቴል ዘርፉም ሆነ ሌላው ኢንቨስትመንት ከአሁኑ የላቀ የሁሉንም ዜጎች ተሳትፎ ይፈልጋል:: አሁን ደግሞ በክልሉ ሰላም፣ ምቹ ሁኔታና እምቅ የኢንቨስትመንት አቅም አለ፡፡ በመሆኑም የክልሉ መንግስት ለሁሉም ኢትዮጵያውያን፣ ዳያስፖራውና የውጭ ባለሃብቱ ገብቶ እንዲያለማ ጥሪ ያቀርባል፡፡
የክልሉ የኢንቨስትመንት ኤጀንሲ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ አብዲአሲስ መሀመድ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ አሁን ላይ በክልሉ የተፈጠው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ከቀደሙት ዓመታት ከነበረው አንጻር ፍሰቱ ጥሩ መሆኑን የ2011 በጀት ዓመት ማጠቃለያ ሪፖርት ያሳያል፡፡ በዚህም በ2011 በጀት ዓመት በክልሉ 1ቢሊዬን 126ሚሊዬን 191ሺ 967 ብር የኢንቨስትመንት ካፒታል ያስመዘገቡ 472 የሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ዲያስፖራ አባላትን ጨምሮ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ኢንቨስት አድርገዋል፡፡
ክልሉም የመጣውን ለውጥ በመጠቀም የተለያዩ የሪፎርም ስራዎችን በመስራት ለክልሉ ህዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት፤ ብሎም ልማቱ ቀጣይነት ባለው መንገድ እንዲሄድ ለማስቻል በትኩረት እየሰራበት ይገኛል፡፡ ይሄም ከለውጡ ጋር ተዳምሮ ባለሃብቶች ያላቸውን ሃብትና ንብረት ያለምንም ስጋት በመተማመን ኢንቨስት ለማድረግ እንዲደፍሩ እያደረጋቸው ነው፡፡
እንደ አቶ አብዲአሲስ ገለጻ፤ የክልሉ መንግስትም ከሚያደርገው ድጋፍ በተጓዳኝ፣ የክትትልና እርምት ተግባራትን የሚያከናውን ሲሆን፤ ይሄም በተለይ በኢንቨስትመንት ስም ታጥረው ያሉ የልማት ቦታዎችን ለመለየትና እርምት ለመውሰድ፣ ተገቢውን የድጋፍ ስራ ለማከናወን፣ ብሎም ከባለሀብቱ ጋር ተቀናጅቶና ተወያይቶ ለተሻለ ውጤት ለመስራት ያግዛል:: በመሆኑም ባለሃብቶች በክልሉ ያለውን እምቅ አቅምና ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጭ ተጠቅመው በመስራት ለራሳቸውም ለክልሉም የሚሆን ስራን ማከናወን ይጠበቅባቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን ነሃሴ 6/2011
ወንድወሰን ሽመልስ
The incisive analyses woven throughout your piece are truly remarkable.