
ገንዘብ በአንድ አገር ወይም ማህበረሰብ ውስጥ ለሸቀጥ (አስፈላጊ እቃ) ና አገልግሎት መግዢያ እንዲሁም እዳ መክፈያ የሚያገለግል መሳሪያ እንደሆነ ይታወቃል። የጥንቱ ገንዘብ ዋጋ ይመነጭ የነበረው ከራሱ ከተሰራበት እቃ ዋጋ ነበር (ለምሳሌ፡ ከወርቅ የተሰራ ሳንቲምን መጥቀስ ይቻላል። በኢትዮጵም የገንዘብ አገልግሎት ከተጀመረ ብዙ ዓመታት ተቆጥረዋል። ነገር ግን የገንዘብ ኖት አያያዝ ችግር በመኖሩ ምክንያት ለተደጋጋሚ ህትመት ብዙ ገንዘብ እንዲወጣ አድርጓል። አብዛኛው ሰው የገንዘብ ኖት የሚይዘው ከቦርሳ ውጭ በመሆኑ የገንዘብ ኖቶቹ የመጨማደድና መቀደድ ማገልገል ከሚገባቸው ጊዜ በታች እንዲቆዩ በማድረጉ አገሪቱ ላይ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እያደረሰ እንደሚገኝ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ ተስፋዬ መላኩ እንደሚናገሩት፤ የገንዘብ ኖት አያያዝ በህብረተሰቡ ዘንድ በጣም ደካማ ነው። በተማረውም ይሁን ባልተማረው ህብረተሰብ ተመሳሳይ የሆነ አያያዝ ነው ያለው። ሁሉም ሰው ገንዘብ ሲይዝ አጣጥፎ ወደ ኪስ የመክተት ሁኔታዎች ይበዛሉ። ይህ ድርጊት ደግሞ በመላ የአገሪቱ ህዝብ ላይ በተለይ በአርሷደሩ አካባቢ ይበልጥ ይስተዋላል።
የገንዘብ አያያዝ ችግሩ ኢኮኖሚው ላይም የራሱ የሆነ ጫና አለው የሚሉት አቶ ተስፋዬ፤ መንግሥት ገንዘብ በብዛት የሚያሳትመው ውጪ በመሆኑ በተደጋጋሚ ሲያሳትም ብዙ ወጪ እንደሚያወጣ ይናገራሉ። ገንዘቦች በአግባቡ ተይዘው የሚገባውን ያክል እንዲያገለግሉ ቢደረግ ኖሮ በየዓመቱ የሚወጣውን በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ማዳን ይቻል እንደነበር ይጠቅሳሉ። ነገር ግን ገንዘቦቹ የሚገባቸውን ልክ ሳያገለግሉ ከአገልግሎት ውጭ ሲሆኑ ብዙ ገንዘብ ስለሚባክን የአገሪቱንም ኢኮኖሚ እንደሚጎዳ ያስረዳሉ።
እንደ አቶ ተስፋዬ ገለፃ፤ የአንድ ብር ኖት በነበረበት ወቅት የአንድ ብር አገልግሎት ውስን ነበር። ለዚህ ደግሞ የአያያዝ ችግሮች ከፍተኛውን ደረጃ ይይዛሉ። ወደ ሳንቲም ደረጃ ከተቀየረ በኋላ የአንድ ብር አገልግሎት ሰፊ እየሆነ ይገኛል። የሳንቲሙ አንድ ብር እንዲያገለግል ለተቀመጠበት ጊዜ መቆየት ይችላል። ለዚህ ደግሞ የማተሚያ ወጪ ቀንሷል። ወጪው በቀነሰ ቁጥር ይወጣ የነበረው ገንዘብ ለሌላ ልማት ማዋል ያስችላል።
በርግጥ በአሁኑ ዘመን የኤሌክትሮኒክስ ገንዘብ አጠቃቀም ሲስተም እንዲኖር የሚበረታታ ነገር ነው። ይሄ ለተጠቃሚውም ለመንግሥትም ትልቅ ጥቅም አለው። ብዙ ገንዘብ ተሸክሞ እንቅስቃሴ በተደረገ ቁጥር ለአደጋ የመጋለጥ እድሉ የሰፋ ነው። የገንዘብ ኖት ይዞ በስጋት ከመዘዋወር በኤሌክትሮኒክስ ገንዘብ ማንቀሳቀስ በጣም አስፈላጊ ነው።
ነገር ግን በአገራችን ደረጃ ሲታይ የኤሌክትሮኒክስ ገንዘብ ማንቀሳቀሻ መሳሪያዎች እጥረት አለባቸው። ለምሳሌ የኤቲ ኤም ማሽኖች ሲታዩ ቴክኖሎጂያቸው የተሻሻለ ባለመሆኑ በአግባቡ እየሰሩ አለመሆኑን ይገልፃሉ። ማሽኖቹ አገልግሎት ከሚሰጡበት የማይሰጡበት ጊዜ ስለሚበልጥ ማሽኖቹ ብቁ ሆነው በቴክኖሎጂ ገንዘብ የማስተላለፋቸው ነገር መታየት እንዳለበት ይናገራሉ። በማንኛውም ሰዓት የኤሌክትሮኒክስ ማሽኖች አገልግሎት የሚሰጡ ከሆነ የገንዘብ አጠቃቀምና አያያዝ ላይ ለውጥ እንዲመጣ ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች አጠቃቀም ግንዛቤ መስጠት እንደሚገባ ያመለክታሉ።
በሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ ፍሬዘር ጥላሁን እንደሚናገሩት፤ ገንዘብ የግል ሳይሆን የአገር ሀብት ነው። በአንድ አገር ውስጥ መንግሥት ገንዘብ አሳትሞ ወደ ኢኮኖሚው ሲጨምር ሰዎች ለገንዘብ ኖቱ እንክብካቤ ማድረግ አለባቸው። በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ከፍተኛ ገንዘብ በእጅ የሚያዝበት ሁኔታ ይበዛል። ከገንዘብ መያዣ ቦርሳ ውጭ ወይም በተለያየ ሁኔታ ገንዘብ እየተያዘ ለብክነት ይዳረጋል። ገንዘቡ ሲቀደድ ወይም ሲባክን ከኢኮኖሚው እንዲወጣ ይደረጋል።
እንደ አቶ ፍሬዘር ገለፃ፤ ገንዘቡ ከኢኮኖሚው ሲወጣ ድጋሚ ገንዘቡን ለማሳተም ከፍተኛ የሆነ ወጪ ይወጣል። በሌላ በኩል ገንዘቡ ከገበያ በመውጣቱ ኢኮኖሚው ውስጥ የሚኖር ቀውስ አለ። በዚህም የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ዘገምተኛ ይሆናል። በሰው እጅ ገንዘብ እንዲበዛ የሆነው የግብይት ስርዓቱ በገንዘብ መሆኑ በተለይ የኤቲ ኤም፣ የኦን ላይን ግብይትና የኤሌክትሮኒክስ የገንዘብ ማስተላለፊያዎች በአብዛኛው አለመኖር ናቸው። ሰዎች ገንዘብ የሚይዙት አንደኛው ለግብይት የተለያዩ አስፈላጊ ነገሮችን ለመግዛት ነው። ሁለተኛው የባንክ ወለድ መጠን ዝቅተኛ ሲሆን ባንክ ማስቀመጥ ያቆማሉ፤ በዛም በእጃቸው ብዙ ገንዘብ ይኖራል። ሶስተኛው ደግሞ ሰው ገንዘብ በእጁ የሚያስቀምጠው ለድንገተኛ ነገሮች ነው።
‹‹ ገንዘብ በሰዎች እጅ እንዳይቆይ ለማድረግ የባንክ ወለድ መጨመርና የኤሌክትሮኒክስ መገበያያ ማሳደግ ይገባል›› የሚሉት አቶ ፍሬዘር፤ በአብዛኛው ሰዎች የሚገለገሉበት የአምስትና የአስር ብር የገንዘብ ኖት ወደ ሳንቲም እንዲለወጡ መደረግ እንዳለበት ያመለክታሉ። በሌሎች አገራት ሞባይል ባንኪንግና ኦን ላይን ገበያ እያደገ በመምጣቱ በሰው እጅ ገንዘብ እንደማይያዝ በመጥቀስ፤ በኢትዮጵያ ባለው የኢንተርኔት መቆራረጥ፣ የኤቲ ኤም ማሽኖች መበላሸት እና ባንክ አካባቢ ያለው መጉላላት በሰው ኪስ ገንዘቦች እንዲበዙ ማድረጉን ያመለክታሉ።
በጳውሎስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሠራተኛ የሆኑት ዶክተር ፍፁም አበራ እንደሚናገሩት፤ የገንዘብ ሽታ ብዙ ጊዜ በትንሽ ሽታ የሚታመም ሰው እንዳለበት አለርጂክ አይነት ስሜት ይፈጥራል። ነገር ግን ያን ያክል የከፋ ነገር አያመጣም። ብዙ ጊዜ በእጅ የምንጠቀማቸው ነገሮች መርዛማ አይሆኑም። ገንዘብ የሚታተምበት ቀለም ውስጥ ያለው ኬሚካል አስምና ሳይንስ ያለበትን ሰው ህመም ይቀሰቅሳሉ። ሆኖም ከገንዘብ ጋር በተያያዘ ብዙ ሰው የመታመም እድል የለውም። በጉዳቱ ዙሪያም ጥናቶች እስካሁን አልተሰሩም። ገንዘቡ አዲስ ሲሆን የራሱ የሆነ ሽታ አለው። የአዲስ ብር ሽታ የአስምና የሳይንስ ህመምን የሚያባብስ እንጂ በራሱ በሽታ አምጪ አይደለም።
እንደ ዶክተር ፍፁም ገለፃ፤ ገንዘብ ላይ የሚሰሩ ሰዎች ጤንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን ማስክ እንዲያደርጉ ይመከራል። በተለይ የአስምና የሳይንስ ተጠቂዎች ከገንዘብ ንክኪ መራቅ ይጠበቅባቸዋል።
አዲስ ዘመን ነሀሴ 6/2011
መርድ ክፍሉ