አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ባለስልጣን ከደረጃ ሐ ግብር ከፋዮች በሐምሌ ወር 3 ነጥብ 84 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ የፌዴራል መንግሥት ደግሞ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ገልጿል፡፡
የባለስልጣኑ የህግ ማስከበር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ታምራት ንጉሴ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ከ209 ሺ 52 የ “ሐ” ግብር ከፋዮች 3 ነጥብ 84 ቢሊዮን ብር ገቢ ተሰብስቧል፣ይህም የእቅዱ 95 ነጥብ 98 በመቶ መሆኑን የተናገሩት አቶ ታምራት ከአምናው ጋር ሲነጻጸር የ378 ነጥብ5 ሚሊዮን ብር ብልጫ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
ወቅቱ ብዙ ችግሮች ያልተነሳበትና ከግብር አወሳሰን ጋር እምብዛም ቅሬታ ያልቀረበበት እንደነበር የገለጹት አቶ ታምራት፤ ከግብር ከፋዮች አመጣጥ አንጻር ግን ችግሮች እንደነበሩ አልሸሸጉም። ግብር ከፋዮች በወሩ መጨረሻ አካባቢ በመምጣታቸው ሠራተኛውም ሆነ ግብር ከፋዩ መንገላታቱን ገልጸዋል።ክሪላንስ አለመውሰዳቸው እና መቶ በመቶ ግብር አለመሰብሰቡም ሌላው ችግር እንደነበር ተናግረዋል።
ባለስልጣኑ ሦስት መሰረታዊ እቅዶችን ይዞ እየሰራ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ በደረጃ “ ሐ” 227 ሺ 692 ግብር ከፋዮች ግብር እንዲከፍሉ ማድረግ፤ 3ነጥብ 99 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ ፣ ለ93 በመቶ ግብር ከፋዮች ነጻ የሚሆኑበትን አገልግሎት መስጠት የሚሉ ናቸው። በዚህም መሰረት የደረጃ ሐ ግብር ከፋዮች መካከል በግብር መክፈያ ጊዜያቸው 209ሺ 52ቱ ግብሩን ከፍለዋል ብለዋል።
በቀጣይ የደረጃ” ሀ” እና “ለ” ግብር ከፋዮች እንግልት እንዳይገጥማቸው ብዙ ነገሮች መመቻቸታቸውን የገለጹት አቶ ታምራት፤ የሁለቱ ግብር ከፋዮች የአከፋፈል ስርዓት ስለሚለያይ የሚያስፈልጋቸውን ከማሟላት አንጻር ዝግጁነቱ ተጠናቋል ብለዋል። በተለይም በሠራተኞች በኩል የሚመጣውን ጫና ለመቀነስ የተለያዩ ሥራዎች መሰራታቸውን ነው የተናገሩት። አሁንም መክፈል የጀመሩ ስላሉ እነርሱን በአግባቡ የማስተናገዱ ሁኔታ ቀጥሏል ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ 37 ነጥብ 65 ቢሊዮን ብር ይሰበሰባል ተብሎ እቅድ ተይዟል ያሉት አቶ ታምራት፤ በመጀመሪያዎቹ አራት የግብር መክፈያ ወራት ውስጥ የዓመቱን እቅድ 50 በመቶ ለመሰብሰብ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
በገቢዎች ሚኒስቴር የመካከለኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ብርቱካን ግርማ እንደተናገሩት፤ እንደ አገር 248 ቢሊዮን ብር ገቢ ይሰበሰባል ተብሎ የታቀደ ሲሆን፤ በመካከለኛ ግብር ከፋዮች ብቻ 14 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የሚሰበሰብ ይሆናል። በዚህም በሐምሌ ወር ብቻ 1ቢሊዮን 15 ሚሊዮን 236 ሺ545 ነጥብ 95 ይሰበሰባል ተብሎ ፤ 1ቢሊዮን 32 ሚሊዮን 469 ሺ 40 ነጥብ 18 መሰብሰብ ተችሏል። ይህም የዕቅዱን 101 ነጥብ 7 በመቶ ነው።
በአገር ደረጃ 4ሺ482 የመካከለኛ ግብር ከፋዮች ያሉ ሲሆን ፤ የግብር ስብሰባው በወራት ተከፋፍሎ ይከናወናል ያሉት ወይዘሮ ብርቱካን፤ እስካሁን ባለው ጊዜ ከእቅድ በላይ ተፈጽሟል። ጥሩ ሥራ መሰራቱም በጠቅላይ ሚኒስትሩ እውቅና እስከመሰጠት አድርሷል። ይህ ደግሞ መነቃቃትን ፈጥሯልና እስከ ጥቅምት ድረስ አምስት ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ይሰበሰባል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ነሀሴ 5/2011
ጽጌረዳ ጫንያለው